በፍቅር
ብጥብጥና ኹከት በነገሠባት፣ እንደ አይ ኤስ ላሉ ጽንፈኞች፣ አክራሪ፣ ጨካኝና ነፍሰ ገዳይ ቡድን መናኻሪያ ከኾነችው ከአገረ ሊቢያ ባለፈው ሰሞን ኹላችንንም እጅጉን ያሳቀቀን፣ እንባን ያራጨን፣ እማማ ኢትዮጵያን የኀዘን ከል ያለበሰ ከፉ መርዶን፣ የሚሰቀጥጥ ዜናን ሰምተናል፡፡ እንባችን ገና ከዓይናችን ሳይደርቅና ሳይታበስም ደግሞ ከዛች የሞት ምድር በምንሰማው ወገኖቻችን የእባካችሁ የድረሱልን ጥሪ ግራ ተጋብተን፣ በምናምጥበት፣ እግዚኦ አምላክ ሆይ ድረስልን! እያልን ባለንበት ከፈርዖኖቹ ምድር፣ ከዓባይ ስጦታ ምድር፣ ከወደ ግብጽ ደስ የሚያሰኝ የምሥራችን ሰማን፡፡
ከመሐመድ ጋዳፊ ሞት በኋላ ይኼ ነው የሚባል መሪ በሌላት በአገረ-ሊቢያ በስደት፣ በሞት ፍርሃትና በሥጋት ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን የግብጽ መንግሥት ነጻ አውጥቷቸው በዛች በፈርኦኖች ምድር ወገኖቻችን ደስታቸውን ሲገልጹ ዐየን፡፡ ለእነዚህ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት የኾኑት ጄ/ል አብዱልፈታህ አል ሲሲ በዓለም አቀፉ በካይሮ አየር ማረፊያ ከባለ ሥልጣኖቻቸው ጋር በአካል ተገኝተውም አቀባበል ሲያደርጉላቸው ጭምርም፡፡
ኢትዮጵያውያኑም ስደተኞች ፊታቸው ላይ አንዳንች ልዩ ስሜትና ፈገግታ እየተነበባቸው የግብጽን ባንዲራ እያውለበለቡ ከሞት ሥጋትና ፍርሃት ላታደጓቸው የግብጽ መንግሥትና ለጄ/ል አብዱል ፈታህ አል ሲሲ አድናቆታቸውን፣ ምስጋናቸውን ሲገልጹ የሚያሣዩ ምስሎችንና ቪዲዮዎችንም በርካታ ኢትዮጵያውያን በአድናቆትና እጅግ በመገረም በማኅበራዊ ድረ ገጾች እየተቀባበሉት ይገኛሉ፡፡
በርካታዎችም፡- ‹‹ከናዝሬት መልካም ነገር ይወጣልን?! እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ በታሪካዊ ጠላትነት ከፈረጅናት ከግብጽ ይሄ ዓይነቱ መልካምነት፣ ደግነት እንዴት ኾነ በሚል በመንታ ስሜት ውስጥ ኾነው የግብጽን መንግሥት በእጅጉ እያመሰገኑ ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ ከምስጋናቸው ባሻገር ይህ የጄ/ል አል-ሲሲ ዕርምጃ አንዳች ፖለቲካዊ አጀንዳና ዲፕሎማሲያዊ መልእክት እንዳለው እየተናገሩ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ወደታች ጥቂት ነገሮች አነሣለሁ፡፡ ለነገሩ ይኼ ሁለተኛ ነገር ይመስለኛል፡፡ ትልቁና ዋናው ወገኖቻችን በሕይወት ለአገራቸው ምድር የሚበቁበት መንገድ መመቻቸት መቻሉ ነው፡፡
ዛሬ በሊቢያ በረኻ የወገን፣ የመንግሥት ያለኽ! በሚል ሲጮኹና ሲንከራተቱ የነበሩ እነዚህ ወገኖቻችን ከጭንቀትና ከሥጋት ተገላግለው የሰላም አየር ወደሚተነፍሱበት ወደ ግብጽ ምድር በሰላም መድረሳቸው ሰው የመኾን ክብርን፣ ፍቅርና ሰብአዊ ርኅራኄ ምን እንደኾነ በቅጡ ለምንረዳ ሰው ለኾንን ሰዎች ኹሉ ከፖለቲካውም፣ ከዲፕሎማሲያዊውም አጀንዳ በላይ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ፣ የሚገባኝም!!
በእርግጥም እነዚህ ወገኖቻችን ከዛ የሞት መናፍስት ካረበቡበት፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ የሞት አበጋዞችና የክፋት ልጆች ያለ አንዳንች ከልካይ የጥፋት ሰይፋቸውን መዘው ከሚርመሰመሱበት፣ ሞትና ጭካኔ ከነገሠባት ከምድረ ሊቢያ ነጻ ወጥተው በሰላም ወደ ግብጽ ምድር መድረሳቸው እፎይ፣ ተመስገን ፈጣሪ ሆይ የሚያሰኝ ታላቅ ነገር፣ ድንቅ የኾነ የምስራችም ነው፡፡ ሌሎችም በጣርና በጭንቅ ያሉ ወገኖቻችንም የእነርሱ ዕድል እንዲገጥማቸው ነው የምንጸልየው፣ የምንመኝላቸው፡፡
እንደ እውነቱ ከኾነ ኢትዮጵያውያኑ በካይሮ አየር መንገድ የግብጽን ባንዲራ እያውለበለቡ ከመከራ፣ ከጭንቀት፣ ከሞት ለታደጋቸው የግብጽ መንግሥት ደስታቸውን ሲገልጹ ማየት በሥልጣን ላይ ላለው የኢሕአዴግ መንግሥት ትልቅ ኪሣራና ውርደት ነው፡፡ በነጋ ጠባ ልማት፣ ዕድገት እያለ የሚለፍፈው መንግሥት ሕዝቡን ከስደት ለመታደግ አቅቶትና ያለ ምንም እፍረት የወገኖቻችንን እልቂት ለራሱ ፖለቲካዊ አጀንዳ ሲጠቀምበት ታዝበነዋል፡፡ ይህን ውርደት ከማየት የበለጠ እንደ አገር፣ እንደ ሕዝብ ምን የሚያሳፍር፣ ምን የሚጠዘጥዝ ሕመምና ሥቃይ ይኖራል ወገን፡፡
እንደው የጄ/ል አል ሲሲ ምንም የተደበቀ ይባል የተሰወረ ፖለቲካዊ/ዲፖሎማሲያዊ አጀንዳ ይኑራቸው ግና ኢትዮጵያውያኑ ወገኖቻችንን በካይሮ አየር መንገድ ማረፊያ ገኝተው አቀባበል ሲያደርጉላቸው፣ የወገኖቻችንን በግፍ መታረድ ሰምተው ቢያንስ እንኳን ለሕዝቡ መጽናኛ የሚሆን መልእክት ለማስተላለፍ እንኳን ገና እያጣራን ነው በሚል በወገኖቻችን ሞት ላይ ሰብአዊ ርኅራኄ በጎደለው ሁኔታ ርካሽ ፖለቲካቸውን ሲሸቅጡብን፣ ሲነግዱብን አንዳንች እፍረት ብሎ ነገር ያልተሰማቸው ባለ ሥልጣኖቻችን እንደው ይሄን የጄ/ል አል ሲሲን ደግ ተግባር ሲያዩ ምን ተሰምቶአቸው ይኾን?!
ከትልቅ አክብሮትና ትሕትና ጋር፣ ለመሆኑ ክርስቲያን ነን በሚል በአደባባይ ያወጁልን የአገራችን ርዕሰ ብሔርና ጠቅላይ ሚ/ር እነዚህን ወገኖቻችንን የግብጹ ፕ/ት ዓላማቸው ምንም ይሁን ምንም ካይሮ አየር ማረፊያ ድረስ ተገኝተው አቀባባል ሲደርጉላቸው ሲያዩ ምን ተሰምቶአቸው ይሆን?! መቼም ለወገናቸው ልባቸው ውስጥ የቀረች ትንሽ እንጥፍጣፊ የኾነች ፍቅር፣ ክብርና ሰብአዊነት ካላቸው ይህን ውርደትና እፍረት የሚሸከሙበት ጫንቃ፣ ወኔ ይኖራቸውስ ይኾንን?!
ከሊቢያ በረኻ እስከ ደቡብ አፍሪካ፣ ከየመን እስከ ሳውዲና መካከለኛው ምሥራቅ የወገኖቻችን ደም የውሻ ደም ያኽል እንኳን ክብር ተንፍጎት፣ ሕዝባችን ላይ የሞት ሞትና ውርደት ሲታወጅባቸው ኀዘናችን፣ ቁጭታችንን ብሶታችንን ለመካፈል አንድ ቀን እንኳን በቅጡ ድምጻቸው ያልተሰማው ባለ ሥልጣኖቻችን፣ መሪዎቻችን ይህን የአል ሲሲን ሰብአዊነት ሲመለከቱ ምን ተሰምቶአቸው ይኾን?! እናስተዳድረዋለን ለሚሉት ሕዝባቸው ፍቅርና ሰብአዊነት ብሎ ነገር የተራቆቱ እነዚህ ባለ ሥልጣኖቻችን ከበቀልና ከክፋት ወጥተው ቆም ብለው ልባቸውን፣ ራሳቸውን በቅጡ ይፈትሹ፡፡
ጭካኔና በቀል በረበበትና በሚነበብበት ፊታቸው፣ ወዳጃችን ዲ/ን ዳንኤል ክብረት እንደጸፈው ማዘናቸውንም ኾነ መደሰታቸውን በማይገልጽ ድርቅ ያለ ስሜት፣ ከሥልጣን/ከወንበር ጋር ፍቅር በወደቀ ብኩን ልባቸው፣ በስንት ጉትጎታና እግዚኦታ በቴሌቪዥን ቀርበው የሚናገሩት ቃላቸው ሣይቀር እንደ በቆሎ ቂጣ አፋቸው ላይ እየተፈረፈረ ሲወድቅ እየታዘብን፣ ውስጣችን በኀዘን ነዶና ተኮራምቶ ከበገነ፣ ከተቃጠለ በኋላ የማታ ማታ የግዳቸውን የሚያስተላልፉልን እንጨት እንጨት የሚል ማጽናኛቸው እንኳን ከልባችን ከጆሮአችን ለመድረስ አቅም የሌለው መኾኑን ማን በነገራቸው፡፡
ለመሆኑ መንግሥታችን ፍቅርና ሰብአዊነት ምን እንደሆነ ይገባዋል፣ ያውቃልን?! እስቲ ከሰማችሁን ይህችን ዘመን አይሽሬ የኾነች ‹‹ታላቁ ነፍስ›› በሚል በሕዝባቸው የሚሞካሹት፣ የህንድ የነጻነት አባት የኾኑት ማሕተመ ጋንዲ በአንድ ወቅት ተናገሩትን አባባላቸውን ልጥቀስላችሁ፡- ‹‹Power based on Love is a thousand times more effective and permanent than power derived from fear.››
ፍርሃት አምጦ የወለደውን ጭካኔያችሁን እስቲ በፍቅር፣ በሰብአዊነትና በርኅራኄ ዘይት አለስልሱት፡፡ እንዲህ የምታስጨንቁትን ሕዝብ የሚያይ፣ የሚመለከት ፈጣሪ፣ ታዳጊ አምላክ እንዳለም አትዘንጉ፡፡ ያን አፍሪካን ሳይቀር የሚጠብቅ ግዙፍ የኾነ ሰራዊትና መሳሪያ ገንብቻለኹ፣ ማን ወንድ፣ የትኛውስ ጀግና ነው ከፊቴ የሚቆመው ብሎ የተገደረውን ደርግን/ጎልያድን በእናንተ በታናናሾቹ/በዳዊቶቹ ያዋረደው ሕያው አምላክ ዛሬም በዙፋኑ ላይ እንዳለ አትዘንጉት፡፡
እናም መሪዎቻችን ፍቅር ከምንም በላይ ኹሉን ለመግዛት፣ ኹሉን ለማሸነፍ የሚያስችል ታላቅ ኃይልና ብርቱ ጉልበት እንዳለው ቢረዱ እንዴት መልካም በኾነ ነበር፡፡ መሳሪያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ሠራዊታቸውን ተማምነው ሕዝቡን እያስጨነቀ፣ በምስኪን ሕዝቡ ላይ የብረቱን ቀንበር እያጠበቀ ላለው መንግሥታችን ይህ መልእክት ይድርሰው ዘንድ ምኞቴ ነው፡፡
እባካችሁ አምባ ገነኖች የሕዝብን ቁጣና ብሶት በኃይል፣ በመሳሪያ መግታት እንደማይቻልም ከታሪክ ተማሩ፡፡ እኛ ግን እንዲህ እንላለን፣ እንዲህም እንመኛለን፣ መቼም ምኞት አይከለከልምና፡-
ለሕዝብ የአደራ ቃል ታማኝ የኾኑ፣ በሕዝብ ፍቅር የነደዱ፣ በሕዝባቸው ጽኑ ቃል ኪዳን የታሰሩ፣ ራሳቸውን ለመሥዋዕትነት ያዘጋጁ እንደ አይሁዳዊው ሕዝብ ነጻ አውጪ እንደ ሙሴ፡-‹‹ይህን ሕዝብን በምድረ በዳ ከምታጠፋው እኔ ከሕይወት መዝገብ ደምስሰኝ፡፡›› የሚሉ፣ በሕዝባቸው ስለ ሕዝባቸው ፍቅር በነፍሳቸው የቆረጡ፣ ጽኑ፣ ባለ ራእይ የኾኑ፣ ከሥልጣን፣ ከወንበር በፊት ሕዝብ ልብ ውስጥ ትልቅ ስፍራን፣ ክብርን ያገኙ፣ ጀግና መሪዎችን እንመኛለን፤ በእውነት ይህን ማግኘትም ትልቅ መታደል ነው፡፡
እንደ መውጫ ከፍጥረት ታሪክ ማግሥት ጀምሮ የግብጽ ምድር በረከት፣ ሲሳይና ሕይወት በኾነው በዓባይ ውኃ ሺ ዘመናትን ያስቆጠረ ግንኙነት ያላቸው ኢትዮጵያና ግብጽ፣ እስከ ዛሬ ዓይንና ናጫ ከኾኑበት የዓባይ ውኃ ፖለቲካ እስጥ አገባ ለጊዜውም ቢሆን ግብጾቹ አቋማቸውን አለሳልሰው እንዲያ እንዳላልናቁንና እንዳላዋረዱን፣ እንዲህ ወገኖቻችንን ከመታደግ ባለፈ በአደባባይ በርዕሰ ብሔራቸው አማካኝነት ወገኖቻችንን በክብር ለመቀበል የቻሉበት አካኼድ በኢትዮጵያና በግብጽ በኩል ለተጀመረው ዲፕሎማሲያዊ ድርድር አንድ እመርታ፣ አንድ ታላቅ ድል እንደኾነ ነው የሚሰማኝ፡፡
ትንግረተኛ በኾነው በዓባይ ወንዛችን ምክንያት ጠላትነትን ከተርፍንባቸው ከግብጾቹ እንዲህ ዓይነቱ ሰብአዊነትና ርኅራኄ ማየታችን የግብጹን ፕሬዝዳንት እናመስግናቸው ዘንድ ያስገድደናል፡፡ በመንግሥታችን፣ በባለ ስልጣነሞቻችን እያፈርንና እየተሳቀቅንም ቢሆን በሂደት ግብጾቹ አቋማቸውን በማለሳለስ እንዲህ ዓይነቱን ወገኖቻችንን ከሞት የታደጉበትን የወዳጅነት ውለታቸውን፣ ሰብአዊ ርኅራኄያቸውን መቼውንም ቢሆን አገራችንና ሕዝባችን የሚረሳው፣ የሚዘነጋው አይሆንም፡፡
ግብጻውያኑ ከበዛው ተንኮላቸውና መሰሪነታቸው ጋርም ቢሆን ፈረንጆቹ፡- ‹‹A friend in need is a friend in deed!›› እንዲሉ በዚህ የእማማ ኢትዮጵያ ዋይታና የሰቆቃ የቀውጢ ጊዜ ቢያነስ ከጎናችን ቆመው ታማኝነታቸውንና ወዳጅነታቸውን አሳይተውናልና ልናከብራቸቀው፣ ልናወድሳቸው ግድ ይለናል፡፡
በሌላ በኩል ግን ከላይ ለመግለጽ እንደ ሞከርኩት ይህ የግብጽ መንግሥት ዕርምጃ ሕዝቡን ከስደት፣ ከባዕድ ጋር ከሚደርስበት ግፍ፣ መከራ፣ ሥቃይና ሞት ለመታደግ ወኔውም ኾነ አቅሙ ላነሰው፣ ለሚያስተዳድረው ለሕዝቡ ፍቅርና ክብር ለመስጠት ላዳገተው መንግሥታችን ግን ቢያስተውለው ታላቅ ውርደት፣ ኪሳራም ነው!!
የቀሩትም በስደት ላይ ያሉ ወገኖቻችን ወደ አገራቸው በሰላም ይገቡ ዘንድ ጸሎታችን ነው!! ‹‹እግዚአብሔር ትዕግሥትን፣ በጎ ትምህርትንም ይሰጣቸው ዘንድ የድካማቸውንም ፍጹም ዋጋ ይሰጣቸው ዘንድ ስለ ተሰደዱ ሰዎች እንማልዳለን፡፡›› እንድትል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በጸሎተ-ቅዳሴዋ!!
ሻሎም!!
The post የግብጹን መሪ ሰብአዊነት ያዩ ባለ ሥልጣኖቻችን ለሕዝባቸው ምን ምላሽ አላቸው?! appeared first on Zehabesha Amharic.