በቅርቡ በሊቢያ የባህር ዳርቻ ፣ በግፍ የተረሸኑትንና የታረዱትን፣ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ፣ በየመን እና በሌሎችም የዓለማችን ክፍሎች በችግርና በስቃይ ውስጥ ያሉትን ወገኖችን ለማሰብ የተዘጋጀ የሻማ ማብራትና የጸሎት ስነ ሥርዓት፣ በአትላንታ ከተማ ተካሄደ።
በዚሁ ከስድስት መቶ የማያንስ የአትላንታ ነዋሪ በተገኘበት ስነ ሥርዓት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ፣ ከፈርስት ሂጂራ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተወካይ፣ ከኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን እና ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አትላንታ አባቶች ተገኝተው በየተራ ጸሎት በማድረግ መርሃ ግብሩን የከፈቱ ሲሆን፣ የኢትዮጵያውያን ጆቫ ዊትነስ ጉባዔ በጊዜ መጣበብ መምጣት አለመቻላቸው ተነግሯል።
በዚሁ የጸሎትና የሻማ ማብራት ስነ ሥርዓት ፣ በሁሉም አባቶች መንፈሳዊ ምክር የተሰጠ ሲሆን፣ በተለይም ሃጂ ሳፊ አላሚን ከፈርስ ሂጂራ ያቀረቡት ግጥም ታዳሚውን በእምባ ያራጨ ነበር። በእምነት አባቶቹ ምክር መካከል በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች ግጥሞችና መጣጥፎች ቀርበዋል።
የወገኖቻችን ሞትና እስራት፣ መከራና ችግር፣ ስቃይና መቃተት የሁላችንም ስሜት እንደሆነ በተነገረበት በዚህ ዝግጅት፣ የዕምነት ተቋማት አንድ መሆንና መቀራረብ ለተቀረው ማህበረሰብ መቀራረብና አንድነት ወሳኝ በመሆኑ በአትላንታ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን የዕምነት ተቋማት የሚያካትትና ቢያንስ በየሶስት ወሩ እየተገናኙ በጋራ በሚያገናኟቸው የማህበረሰብ ጉዳዮች ላይ የሚወያዩበት “በአትላንታ የዕምነት ተቋማት የጋራ ጉባዔ” እንዲመሰረት ሃሳብ ቀርቦ ከእምነት አባቶቹ ተቀባይነትን ሲያገኝ፣ ታዳሚውም በጭብጨባና በዕልልታ ደግፎታል።
በመጨረሻም አርቲስት ቤዛ ታደሰ እጅግ ልብ የሚነካ እንጉርጉሮ ስታቀርብ፣ በቅድሚያ የሃይማኖት አባቶቹ ቀድሞ ከተለኮሱት 28 ሻማዎች ላይ በመለኮስና ለታዳሚው በማቀበል የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት ተካሂዶ፣ 6ፒ ኤም የጀመረው ዝግጅት 9 ተኩል ላይ ተጠናቋል።
The post በአትላንታ ጆርጂያ የሻማ ማብራትና የጸሎት ሥነ ሥርዓት ተካሄደ appeared first on Zehabesha Amharic.