Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ከ መሬት ለባለሀብቱ ጀርባ ? –ኤድመን ተስፋዬ

$
0
0

comment picእ.ኤ.አ በ2007/08 በነዳጅ ሀብቱ እና በሀገሩ ያሉትን እህቶቻችንን እና ወንድሞቻችንን በማሰቃየት የሚታወቀው ሳውዲ አረቢያ መንግስት በንጉሱ ንጉስ አብዱላህ አነሳሽነት የሀገሩን ዜጎች ለመመገብ በሚል አዲስ መርሀ ግብር የነደፈ ሲሆን፣ በንጉሱ የተነደፈው የግብርና መርሀ ግብር አላማው መሬት በሚሸጡ ደሀ ሀገራት መንግስታት ላይ ትኩረት በማድረግ በነዚህ ሀገራት የሚገኙትን ለም መሬቶች በሳውዲ መንግስት ስም በሽያጭ እና ወለድ አግድ የመሬት ይዞታ(ንብረትን በግዥ፣በኮንትራት፣በሊዝ) ባለቤትነት በመያዝ አስፈላጊውን የመዋእለ ነዋይ ፍሰት በማድረግ በነዚህ ሀገራት የሚመረተውን የግብርና ምርት ወደ ሳውዲ በመላክ የሳውዲን ህዝብ መመገብ ነው፡፡ ይህ በአለማችን ላይ የሚገኙትን የዘመናችንን እውቅ ኢኮኖሚስቶች በሳተፈ መልኩ የተጠናው የሳውዲ አረቢያ የግብርና መርሀ ግብር ትኩረት የሚያደርገው በተለያዬ የውጪ ሀገራት ማለትም በኢትዮጲያ፣ሱዳን፣ዩክሬን፣ፊሊፒንስ እና ብራዚል በመሳሰሉት ሀገሮች ላይ ሰፋፊ መሬቶችን በመግዛት አልያም በመኮናተር ምርት አምርቶ ሳውዲ አረቢያን በእህል ምርት እራሷን ማስቻልን ላይ ነው፡፡ ይህንንም የሀገሪቷን አላማ የሳውዲ የንግድ እና ኢንደስትሪ ሚኒስትር በወቅቱ የመጀመሪያ አላማችን በውጪ ሀገራት የመሬት ይዞታ ንብረትን ማግኘት ሲሆን ቀጥሎም ዘመናዊ ግብርና ማስፋፋት በተያያዝም የመዋእለለ ንዋይ ፍሰት በማድረግ የመሠረተ ልማት መዋቅር በማስፋፋት የግብርና ምርቱን ወደ የሳውዲ ዓረቢያ መላክ እንደሆነ ዓላማቸውን በማስረገጥ ገልፀዋል፡፡ ከላይ በጠቀስኩት የሳውዲ መንግሰት አላማ መነሻነት በዋነኛነት የሳውዲ መንግስት ስም በተያዙ ትላልቅ የሀገራችን እርሻ መሬቶች ላይ የተመረተው ሩዝ እ.ኤ.አ ከ 2008 እስከ 2012 ወደ ሳውዲ የተጫነ ሲሆን በተጨማሪም ሀብቱ በሳውዲ ዜጋነት የተመዘገበው የቢሊየነሩ ሼህ መሀመድ አላሙዲን ድርጅት የሆነው የሳውዲ ስታር አግሪካልቸራል ዲቨሎፕመንት እና የህንዱ ካራቱሬ በሀገራችን ሰፋፊ የግብርና መሬቶችን በመውሰድደ የግብርና እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

እንደ ዓለም ዓቀፍ የምግብና የእርሻ ድርጅት( Food and Agriculture Organisation (FAO) ጥናት ከሆነ ከኢትዬጵያ 145.6 ሚሊዬን ሄክታር ብዝሃ መሬት ውስጥ 100 ሚሊዬን ሄክታር ለእርሻ የሚሆን መሬት ሲሆን ይህም መሬት የሚታረሰው በአመዛኙ በአነስተኛ መሬት ባላቸው ገበሬዎችና ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ገቢ በሚተዳደሩ ደሃ አርሶ አደሮች ሲሆን በጣም ትልልቅ የንግድ እርሻዎች ድርሻም 400,000 ሽህ ሄክታር መሬት ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 ኦክሰፋም ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው የመካከለኛው ምስራቅና የሩቅ ምስራቅ ኢንቨስተሮች በታዳጊ ሀገራት ኢትዮጲያንም ጨምሮ ለያዙት የግብርና መሬት በሄክታር በአመት አንድ የአሜሪካ ዶላር (በአመት አስራ ዘጠኝ ብር አካባቢ መሆኑ ነው) ብቻ ነው የሚከፍሉት፡፡ በሀገራችንም ሆነ በሌሎች የአለማችን ሀገራት በውጪ ሀገራት መንግስታት ለግብርና ምርት በሚል የተያዘውን መሬት እንደ የአለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሁማን ራይትስ ዎች እና ኦክስፋም ያሉ ተቋማት ከሀገሬው አርሶ አደር የመሬት ባለቤትነት እና መፈናቀል ወዘተ ጋር በተገናኘ ጉዳዩን በሀያ አንደኛው ዘመን የሚደረግ የመሬት መቀራመት መሆኑን በመግለፅ ክፉኛ ቢቃወሙትም የሀገራችንን መንግስት ጨምሮ መሬት ሻጭ የሆኑት መንግስታት መሬት መቸብቸባቸውን ቀጥለውበታል፡፡

የእውቁ ኢኮኖሚስት አዳም እስሚዝ የአለማቀፋዊነት ንድፈ ሀሳብ እንደሚያትተው በሀብት (በሰዋዊም ሆነ በቁሳዊ) ረገድ ሙሉ የሆነ የአለማችን ሀገር ባለመኖሩ ሀገራት በጎደለ ሙላ በሚለው መሰረት አንዱ ባለው ሀብት የሰውን ሀገር ቀዳዳ በመሙላት ቀዳዳውን ከሞላለት ሀገርም ሆነ ከሌሎች ሀገራት በሚያገኘው ሀብት (የገቢ እን የወጪ ንግድ ትርፍ) የራሱን ቀዳዳ በመሙላት የራሱን ሀገር ኢኮኖሚ ከማሻ|ሻል ባለፈ ለአለማቀፋዊ የኢኮኖሚ ትስስር መንስኤ ይሆናል፡፡ የወቅቱን በስግብግቦቹ ካፒታሊስቶች በሳፋ ተቀብሎ በማንኪያ መመለስ በሚል መርህ የሚዘወረውን አለማቀፋዊነት ወደ ጎን ትተን ይህን የአዳም ንድፈ ሀሳብ ከተመለከትነው የሚያመላክተን ፍትሀዊ ሆነ የኢኮኖሚ ሰጥቶ መቀበል መርህ የሚደረግ የሀገራት የኢኮኖሚ ሽርክና ከሀገራት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባለፈ ለአለም ሀገራት የኢኮኖሚ ትስስር መንስኤ የመሆኑን ሁነት ነው፡፡ የውጪ ሀገር መንግስታትም ሆነ ኩባንያዎች በሀገራችን መሬት ላይ ለዛውም የኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት በሆነው ግብርና ላይ መሳተፋቸው በሀገራችን የግብርና ዘርፍ ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ እና አዎንታዊ ተፅእኖ የግብርናው እንቅስቃሴ በሚደረግባት ሀገራችን ያሉትን አርሶ አደሮች እና በሀገራችን የግብርና እንቅስቃሴ የሚያደርጉትን ሀገራት መነሻ በማድረግ ማየቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

በዚህ መነሻነትም የውጪ ባለሀብቶች በሀገራችን መሬት ላይ የሀገራቸውን ህዝብ ለመቀለብ በሚል የሚያከናውኑት የግብርና እንቅስቃሴ በሀገራችን ግብርና ምርት እና አርሶ አደር ላይ ካለው ተፅእኖ አንፃር እና በውጪ ባለሀብቶች እየተከናወነ ያለው የግብርና እንቅስቃሴ በሀገራችን መንግስት ቢከናወን በሀገራችን ከሚያስገኘው ግብርናዊ ጥቅም አንፃር መመዘን ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል የምንገኝበት የሀያ አንደኛው ክፍለ ዘመን በሀገራት መሀል የሚደረግ ኢኮኖሚያዊ ሽርክና በሀገራቱ መሀል ካለው የኢኮኖሚ ሽርክና ባለፈ በሀገራቱ መሀል ባለ የፖለቲካ ሁነት እና ሀገራቱ ከሌላ ሶስተኛ ሀገራት ጋር ካላቸው ጤናማም ሆነ ጤናማ ካልሆነው የፖለቲካል ኢኮኖሚ ግንኙነት ተፅእኖ ስር የወደቀበት ዘመን መሆኑን የውጪ ሀገር መንግስታት በሰው ሀገር እያከናወኑት ያለው የግብርና እንቅስቃሴ ምክንያቱ ለሰው ልጅ የመኖር መንስኤ ለሆነው ምግብ ከመሆኑ ጋር ስንገምደው በሀገራችን የግብርና ምርት እያመረቱ ያሉትን የውጪ ሀገር መንግስታት በተለይ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራትን የወቅቱን የቀጠናውን የፖለቲካ ትኩሳት ማእከል ባደረገ መልኩ ሀገራቱ በሀገራችን የግብርና ምርት በማምረታቸው የተነሳ የወቅቱ የቀጠናው የፖለቲካ ትኩሳት ሀገራችን ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያመጣውን አሉታዊ ተፅእኖ ሀገራቱ በሀገራችን የግብርና ምርት በማምረታቸው የተነሳ ለሀገራችን በቀጠናው ከሚፈጥርላት እና ከፈጠረላት ሀይል አንፃር በመመዘን ማየቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

በሀገራችን መሬት ምግብ የሚሰራው የሳውዲ መንግስት እና የሀገራችን መንግስት

የሳውዲ መንግስት እንደ መንግስት በሀገራችን መሬት ላይ የራሱን ህዝቡ ለመቀለብ የግብርና ምርት ማምረቱ በራሱ ስህተት ያለው ይመስለኛል፣ እንደ እኔ እምነት ስህተቱ ያለው የሳውዲ መንግስት ይህን ያህል እርቀት ባህር አቋርጦ በሀገራችን መሬት የሚያመርትበት ምክንያት መንግስት ህዝቡን ለመቀለብ ምን ያህል ዋጋ እንደሚከፍል አሳይ መሆኑን እና የአለማችንን የዘመኑን የግብርና አመለካከት ያልተረዳው እና በውጪ ያሉትንም ሆነ የሀገር ውስጥ አቅሙ ያላቸውን ባለሀብቶች በማስተባበር እና ምቹ ሁኔታ በመፍጠር፣ በመንግስታዊ በጀት በሀገራችን የሳውዲ የሚያደርገው አይነት የግብርና እንቅስቃሴ (በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በሰፋፋ እርሻዎች ላይ) በማድግ የግብርና ምርቱን ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ በሀገራችን የሚታየውን የግብርና ምርት የዋጋ ንረት ማስወገድን ያልቻለው የሀገራችን መንግስት ላይ ይመስለኛል፡፡

በአዲስ አበባ ከሚተላለፉ የኤፍ ኤም ፕሮግራሞች በአንዱ ላይ የአየር ሰአት በነበረው የሰይፉ ፋንታሁን ፕሮግራም ላይ ሀብታቸው በሳውዲ ዜግነት የተመዘገበው ቢሊየነሩ ሼህ መሀመድ አላሙዲ ከሰይፉ ፋንታሁን ጋር ባደረጉት አጠር ያለ የስልክ ቃለ ምልልስ ሰይፉ ፋንታሁን እዚህ ብዙ የአርሰናል ደጋፊዎች ስላለን ለምን የአርሰናልን ክለብ አይገዙልንም ብሎ ለጠየቃቸው ጥያቄ ሲመልሱ የአርሰናልን ክለብ መግዛት ይቆየኝና አሁን (በጊዜው) ድርጅታቸው ግብርና ላይ ለመሳተፍ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን በመጥቀስ የግብርና ምርትን በሀገራችን ለማሳደግ እንደሚሰሩ መጥቀሳቸውን አስታውሳለው፡፡ በግብርና ላይ የተሰማራው የሼኩ ኩባንያ ሳውዲ ስታር አግሪከልቸራል ዲቨሎፕመንት በሊዝ ከወሰደው 24700 ሄክታር መሬት ውስጥ 860 ሄክታር መሬት ላይ ሩዝ በመዝራት ያገኘውን ጠቅላላ ምርት በተደጋጋሚ ወደ ሳውዲ መላኩን የኦክስፋም ሪፖርትን እና ዘ ሂንዱ በ ጁን 1/2013 የዘገበውን ዘገባ መነሻ ስናደርግ ሼኩ ቃላቸውን ጠብቀው የሀገራችንን ህዝብ በበቂ ሁኔታ የግብርና ምርት በገበያው እንዲያገኝ ሳይሆን ያደረጉት በሀገራችን መሬት ያመረቱትን ምርት ሀብታቸው ወደ ተመዘገበበት ሀገር ስለ መላካቸው የምንረዳ ይመስለኛል፡፡

የፖለቲካ አመለካከትን እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚወሰድበትን ያልተፃፈ አሰራር ወደ ጎን በመተው በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያሉ አቅሙ ያላቸውን በተለይ በፖለቲካ የተነሳ ያላቸውን ሀብት በሰው ሀገር እያፈሰሱ ያሉትን የሀገራችን ዜጎች የሳውዲ መንግስትን ጨምሮ ሌሎች የውጪ ሀገር መንግስታት በሀገራችን መሬት እያመረቱ እንዳለው የሀገራችንን የግብርና ምርታማነትን በሚያሳድግ እና ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ለሚውል የግብርና እንቅስቃሴ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑበት አሰራር ቢኖር ኖሮ እና ቢዘረጋ በገዛ ሀገራቸው የሚኖሩትን ዜጎች በማፈናቀል እና ደን በመጨፍጨፍ የያዘውን መሬት የግብርና ምርት ሊያመርትበት ባለመቻሉ ለውጪ ሀገር ባለሀብቶች የሚሰጠውን የግብርና መሬት መጠን የሚጠቅሰው ፖሊሲ እንዲከለስ ምክንያት እንደሆነው እና ከሀገራችን ባንኮች የተበደረውን መመለስ እንኳ እንዳቃተው የህንዱ ካራቱሬ አይነት ድርጅቶች በሀገራችን መሬት ባልፈነጩ ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ አዋጭነታቸው እንደሀገር ምንም ባልሆኑ ነገር ግን ለሙስና ካላቸው ተመቻችነት አኩአያ ከፍተኛ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ላይ ልማት በሚል የዳቦ ስም የሀገሪተዋን ሀብት የሚያፈሰው መንግስት የውጪ ሀገራት መንግስታት በሀገራችን ለህዝቦቻቸው ምግብ ዋስትና በሚል እንደሚያደርጉት በገዛ ሀገሩ መሬት ላይ እንደ እነሱ አይነት የግብርና እንቅስቃሴ በመንግስታዊ በጀቱ ለማድረግ አለመንቀሳቀሱ በአንድ በኩል የውጪ ሀገራት መንግስታት በሀገራችን መሬት ላይ የሚያደርጉት የግብርና እንቅስቃሴ ወደፊት ሀገራችን እያመረተች ወደ ውጪ የምትልከውን የግብርና ምርት በሀገራችን መሬት እያመረቱ በአለም ገበያ ተፎካካሪ የመሆናቸው አይቀሬነት ሲታይ በሌላ በኩል የመሬት ፖሊሲው፣የግብርና ግብአት (ማዳበሪያ በዋነኛነት) ብድር የግብርና እንቅስቃሴውን ሲኦል ያደረገበት የሀገሬ አርሶ አደር የራሱን የግብርና እንቅስቃሴ በመተው በውጪ ሀገራት መንግስታት እና ግለሰቦች ባለቤትነት ወደ ተያዙት እርሻዎች ተቀጣሪ ሆኖ የመስራቱ (እየሰራም ይገኛል) እድል ከፍተኛ የመሆኑ ሁነት ኢህአዴግ የስልጣኔ ምንጭም ሆነ የሀገራዊው ፖሊሲዬ ማእከል አርሶ አደሩ ነው ከሚለው ጋር ስንገምደው ኢህአዴግ እንደ መንግስት ግብርናው ላይ የሚከተለው ፖሊሲ ያስገኘውን ውጤት የዜሮ ብዜት የሚያደርገው ይመስለኛል፡፡

የሀገራችንን ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ ለማሸጋገር በገዢው ፖርቲ የተነደፈው የአምስት አመቱ የእድገት እና የትራንስፎርሜሽን እቅድ አንድ አመት በቀረበት በያዝነው አመት ኦክስፋም በአለም ላይ ከሚገኙ ሀገራት በቂ የሆነ ምግብ የማይበሉ ህዝቦች ያሉባት ሀገር በሚል ከአለም ሀገራት በሁለተኛ ደረጃ ባስቀመጣት እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ለምግብ እጥረት የተጋለጡ ስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ህዝቦች በዚህ አመት መኖራቸውን በገለጠባት ሀገራችን በግለሰብም ሆነ በመንግስት ደረጃ ሳውዲዎቹ በሀገራችን መሬት የራሳቸውን ህዝብ ለመቀለብ የሚያደርጉትን የግብርና እንቅስቃሴ ከኪራይ ከሚያገኘው አስቂኙ ገቢ በስተቀር በሁለትዮሽ ግንኙነትም ሆነ በተለዋጭ ጥቅም ሀገራችንን ተጠቃሚ ማድረግ ያቃተው እንዲሁም የሳውዲ መንግስት ከግብርናው እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ በሀገራችን ህዝቦች ላይ የሚደርሰውን የሰብአዊ መብት ጥሰት እና መፈናቀል በማስረጃ በማስደገፍ የሚያቀርቡትን አቤቱታ እንደ ለመደው የኒዮ ሊበራሊዝም አስተሳሰብ ውጤቶች በማለት ለሚያልፍው እና ሌላው ቢቀር እንደ መንግስት በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ሙከራ ያላደረገው ኢህአዴግ ለውጪ መንግስታት ለግብርና በሚል የሰጠውን መሬት በተመለከተ የሚከተለው አካሄድ እንደ እኔ እምነት የራሷ አሮባት የሰው ቤት የምታማስለዋን ሴትዮ የሚያስታውስ ይመስለኛል፡:

ሳውዲዎቹ ለሀገራችን የሚያመጡት ትሩፋት ወይስ እዳ ?

ስለ ምድራችን የ ተፈጥሮ ሀብት እና ስነምህዳር የኢኮኖሚክስ አስተምህሮት ንድፈ ሀሳብ እንደ የሚነግረን እንደ የፀሀይ ብርሀን እና ዝናብ የመሳሰሉትን ተፈጥሮአዊ ሀብቶች ገንዘብ ሊገዛቸው አንደማይቻለው ነው፡፡ አሁን ላይ ምድራችን ያጋጠማትን የውሃ እጥረት፣የበረሀ መስፋፋትን ተከትሎ በአለም አቀፍ ደረጃ ያጋጠመው የምግብ እጥረት እና የምግብ ፍጆታዎች የዋጋ መናር መልካምድራዊ በሆኑ ምክንያቶች የተነሳ ለምግብ ፍጆታ የሚሆኑትን የግብርና ምርቶች በሀገሯቸው በበቂ ሁኔታ ለማያመርቱ እና ፍጆታዎቻቸው ከውጪ ሀገር ለሚያስገቡ ሀገራት ሁኔታው አስደንጋጭ ሲሆን፣ ይህ አስደንጋጭ አደጋ ከተጋረጠባቸው ሀገራትም ውስጥ አንዷ በነዳጅ ሀብቷ የምትታወቀው ሳውዲ አንዳ ስትሆን፡፡ ሀገሪቷ ይህን አደጋ ለመወጣት በነደፈችው የግብርና እቅድ መነሻነት እ.ኤ.አ በ2009 በሳውዲ አረቢያ ንጉስ አብዱላህ መሪነት በ መቶ ሚሊዮን ዩኤስ ዶላር የመዋእለ ነዋይ ፍሰት በሀገራችን መሬት የግብርና ምርት ማምረት የጀመረው የሳውዲ መንግስት በጋምቤላ ክልል በስሙ በተያዙ ሰፋፊ መሬቶች ያመረተውን የሩዝ ምርት እ.ኤ.አ ከ 2008 እስከ 2012 ወደ ሳውዲ የጫነ ሲሆን፣ ይህ በሀገራችን የተመረተው የሩዝ ምርት የሀገሪቱን የምግብ ክፍተት ከማጥበቡም በላይ ለሀገሪቱ የምግብ ፍጆታ ዋስትና በሚል በንጉሱ ለተነደፈው እቅድ እንደ ስኬት ተወስዳል፡፡

ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ግብአት ከሆኑት ውስጥ አንዱ የሆነውን የነዳጅ ሀብት የተጎናፀፈችው ሳውዲ በሀገራችን ለምግብ ፍጆታዋ የግብርና ምርት ማምረቷ ከሁለትዮሹ ሀራዊ ግንኙነት አኩአያ ከሚያስገኘው ጥቅም አንፃር ሲታይ በአጭር ጊዜም ይሁን በረዥም ጊዜ ለሀገራችን የነዳጅ ፍጆታ ፍላጎት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ ባይሆን እንኳ ከበፊቱ በተሸለ ሁኔታ ዋስትና እንዲኖራት፣ለሀገራችን ዜጎች ምቹ ያልሆነውን የመሀከላው ምስራቅ ከበፊቱ በተሸለ ሁኔታ ለስራ ወደ አካባቢው በሚሄዱት ዜጎቻችን ላይ በተለይ በእህቶቻችን ላይ የነበረውን መጎሳቆል እንዲቀር መንስኤ ሊሆን በተቻለው ነበር፣ ነገር ግን ከሳውዲ መንግስት ጋር የሀገገራችንን መሬት በተመለከተ ውል የፈፀመውን የኢህአዴግ መንግስት ለትችት በዳረገው በቅርቡ በሳውዲ ሀገር በእህቶቻችን ላይ የተፈፀመው አረመኔአዊ ተግባር ባጎረስኩኝ እጄን ተነከስኩኝ አይነት መሆኑ ውሉ ከሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ያለውን ሀገራዊ ጠቄሜታ ጥያቄ ውስጥ የሚከተው ይመስለኛል፣ በሌላ በኩልም በመሀከለኛወ ምስራቅ ቀጠና አሁን ላይ ለሚታየው የሶሪያ እና የኢራቅ ትኩሳት መንስኤ ለሆነው እና አላማው ቀጠናውን በፅንፈኛ አስተሳሰቡ አንድ አርጎ መምራት ለሆነው አይሲሲ የሎጀስቲክ እና የገንዘብ ምንጭ ነው በማለት በኢራን እና በሶሪያ የሚከሰሰው የ ሳውዲ መንግስት ህዝቡን ለመቀለብ በሀገራችን መሬት ላይ በሚያመርተው ምርት የተነሳ በፅንፈኛው አይሲሲ ሀገራቸው እየተመሰቃቀለ ያሉት ሀገራት እና ጉዳዩ ያሳሰባቸው ከቀጠናው ውጪ ያሉ ሀገራት ሀገራችን ላይ በቀጥታም ይሁን ቀጠተኛ ባልሆነ መንገድ ተፅእኖ ማድረጉ ቢኖር እንኳ በዲፕሎማሳዊውም ሆነ በሌሎች መንገዶች ረገድ እንደ መንግስት ተፅእኖውን ለመቋቋም ያለውን አቅም እና ተነሳሽነት በሳውዲ መንግስት በራሱ ዜጎች ላይ ለተፈፀመው ኢሰበአዊ መከራ ኢህአዴግ መራሹ የሀገራችን መንግስት ያከራየውን መሬት (ከሳውዲ ጋር ያለን የሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ግንኙነት ወደ ሳውዲ ያደላ እና የሳውዲ መንግስት ኢኮኖሚያዊው ድጋፍ ከፈተኛ ቢሆንም አሁን ላይ ካለው የሳውዲ አንገብጋቢ የምግብ ፍጆታ ፍላጎት አኩአያ ያከራየናቸው መሬት ከፍተኛ አቅም ለሀገራችን መፍጠር ይችላል) ለተፅእኖ ያለመጠቀሙን እውነትነት ሲታይ ለሀገራችን አደጋ መፍጠሩ አይቀሬነት ማመላከቻ ይመስለኛል፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአሁን ዘመን በአለማችን እየተስፋፋ ያለውን የሀይማኖት አክራሪነት ባልተለመደ መልኩ እንስሳዊ በሆነ መንገድ ሰይጣናዊ አላማውን ለማሳካት ከሶሪያ እስከ ኢራቅ ከኢራቅ እስከ ሊቢያ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው እና የቀጠናውን ሀገራት በአንድ መንግስት የማስተዳደር አላማ ያለውን አይሲሲ በመርዳት የሚከሰሰው የሳውዲ መንግስት በሀገራችን መሬት በሚያመርተው ምርት የተነሳ የፅንፈኛው ተቃዋሚ የሆኑ ሌሎች አክራሪ ሀይሎችም ይሁን አይሲስ ላይ ጦርነት ያወጁ ሀገራት ሀገራችን ላይ ጥርስ ስለ አለመንከሳቸው መተማመኛ እንዳናገኝ በሀገራችን መሬት የግብርና ምርቶች እያመረተ የሚገኘው የሳውዲ መንግስት መንስኤ የሚሆን ይመስለኛል፡፡

The post ከ መሬት ለባለሀብቱ ጀርባ ? – ኤድመን ተስፋዬ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>