የቀዳማዊ ኃይለሥላሤ መንግሥት የኢትዮጵያን የጦር ኃይል ወደ ኮንጎና ኮርያ ልኮ እንደ ነበር ይታወቃል።የደርግ ወታደራዊ መንግሥት በገልፉ ጦርነት ወቅት ኢራቅ ግብጽን ጨምራ እንዳትመታ ግብጽን ለመታደግ ልኮ እንደነበር ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው።የህወሓት ቡድንም ወደ ሩዋንዳ፤ሶማሌና ደቡብ ሱዳን የመከላከያ ሠራዊቱን መስደዱ ግልጽ ነው።የኔ አብይ መነሻ ማናቸውም ይሁኑ በመላኩ ወይም ባለመላኩ ጉዳይ አይደለም።ከበስተጀርባው ምንድን ነገሮችን አስከትሏል የሚለው እንጅ? የግል አስተያየቴን እንደሚከተለው ላቅርበውና ይህን ጹሑፌን የምታነቡ ለዚህ ታሪክ ቅርበት ያላችሁ ወይም ጉዳዩን በውል የተገነዘባችሁ በስፋት ሃሳባችሁን እንደምትሰጡበት ተስፋ አደርጋለሁ።
1/ የአጼ ኃይለሥላሤ ዘውዳዊ መንግሥት ጦሩን ወደ ኮንጎና ኮርያ ሲልክ ጥሩ ዝምድና ለማትረፍ ወይም መልካም ዝና ለማግኘት ይሆናል ብየ አምናለሁ ለዚያም ሊሆን ይችላል ድሮ ኮርያ ዘምተው የነበሩ የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት አባላት በኮርያ መንግሥት የጡረታ ጥቅማ-ጥቅሞችን እንዲያገኙ የተደረገው።በዚህ ጊዜ ኃይለሥላሤ መንግሥት ለጦሩ ይከፍለው የነበረው ክፍያ አነስተኛ ቢሆንም የገንዘቡ አቅም ከፍተኛ ነበር በዚህ ላይ የኢትዮጵያ ገንዘብ ከዶላር ጋር እኩል ክፍያ ይከፈለው ስለነበር በጦሩና በጦሩ አባላት ቤተሰብ ላይ ችግር አልነበረም ማለት ይቻላል።የኑሮ ሁኔታውም እንዲህ ጣራ ላይ የደረሰ ስለአልነበረ የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት ወደ ጎንጎም ሆነ ደቡብ ኮርያ ቢዘምት በቤተሰብ ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ አልነበረውም።ይህን በእውነቱ በበጎ ልናየውና ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ጣልቃ ገብነትን በማይነካ መንገድ እርዳታ መስጠቷ ተገቢ መስሎ ይታየኛል።
2/ በደርግ የወታደራዊ አገዛዝ ዘመን በአፍሪካ ቀንድ የገነነ ሠራዊት ገንብቶ የነበረ ደርግ ሲሆን ወደ ግብጽ የተላኩት የኢትዮጵያ የሠራዊት አባላትም ከሁለት መቶ እስከ ሁለት መቶ እንደማይልቅ አስታውሳለሁ።እዚህ ላይ ደርግ የነበረበት ሁኔታና የኢራቅን የጦር ኃይል ለመመከት ደርግ የላከው ጦር ሁኔታ ሲታይ ደርግ እያሾፈ ነው ወይስ ኃይል ስለሚያጥረው ነው የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተን እንደነበር አስታውሳለሁ።ያም ሆነ ይህ ግን ኢራቅ ግብጽን ሳትዳፈር በመቅረቷ የደርግ ገቨን ተሸፍኖ አልፏል።እንዲያ ይፈራና በግዙፍነቱ ገንኖ ይታወቅ የነበረው የኢትዮጵያ የጦር ኃይል በተገንጣይ ኃይሎች፤ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እናመጣለን ብለው በተነሱ ኃይሎችና በራሱ በደርጉ ርእሰ ብሔር መንግሥቱ ኃይለማርያም እንዲዳከም እንዲበታተንና ለጥቃት ሰለባ እንዲሆን ተደረገ በመጨረሻም አብዛኛው የጎዳና ለማኝ እስከ መሆን ደረሰ ይህን የምልበት ምክንያት የአንድ አገር የጦር ሠራዊት ካለው አገራዊ ተልእኮ አንጻር ሲመዘን የአገርን ዳር ድንበርና ሉአላዊነት ማስከበር በመሆኑ እነዚህ ሳይስተካከሉ በመቅረታቸው አሁን ካለንበት ደረጃ ደርሰን እንገኛለን።
3/ የህወሃት የመከላከያ ሠራዊት፦በመጀመርያ ደረጃ ከድኻው አርሶ አደር፤ነጋዴና የመንግሥት ሠራተኛ በሚሰበሰብ ግብርና ታክስ ደመወዝ እየተከፈለው የኢትዮጵያ ሠራዊት ሊባል አለመቻሉ ምን ያህል በሕዝብ የተጠላና ሥነምግባር የጎደለው ሠራዊት መሆኑን አስረግጨ ማለፍ እወዳለሁ።በመቀጠል ይህ የህወሃት ሠራዊት ከኢትዮጵያ ህዝብ የተፈጠረና እያንዳንዱ እናት አባት ወዳጅ ዘመድ ያለው እንደሆነ ይታመናል ነገር ግን ዓላማው የኢትዮጵያን ሕዝብ አንገት አስደፍቶ የህወሃትን ሥርዓት እድሜ ማስረዘም በመሆኑ በሕዝብ ዘንድ አመኔታ የተጣለበት አይደለም።ምክንያቱም በደቡብ ኢትዮጵያ፤በኢትዮጵያ ሶማሌ፤በአፋር፤በሰሜን ምእራብ ኢትዮጵያ የፈጸማቸው ተግባሮቹ አጽያፊና ፀረ-ህዝብ ናቸው።ይህ በዚህ እንዳለ ከታች እስከ ላይ ያሉት የሠራዊቱ አለቆች ንብረት በማካበትና በንግድ ሥራ ሲጠመዱ እየተመለከተ የሚለብሰውን ዩኒፎርምና የሚጫማውን ጫማ ከደመወዙ እየተቆረጠ እንዲገዛ ሲደረግ በጋራ ለምን ብሎ ጥያቄ አያነሳም? የተወሰኑት የመብት ጥያቄ አንስተው ሲሞግቱ ከየካምፑ እየተለቀሙ ሲገደሉና ሲታሰሩ ዝምታን መምረጥ አስፈላጊ አልነበረም ይህም አልበቃ ብሎ ወደ ሩዋንዳ ፤ደቡብ ሱዳንና ሶማሌ ሲልኩት ገዥዎቹ ምን ሊያተርፉ እንደሆነ በንቃት የተመለከተው አይመስልም።የተግባር ሥምሪቱን የሚያገኘው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር ሆኖና እንደ አንድ የሚሊታሪ ኃይል ዓለማቀፋዊ ስታንዳርድን አሟልቶ አይደለም። ይህን ሊያሟላ የማይችልበትን ምክንያት ሁላችንም የሚገባን ይመስለኛል።በዚህ ሥርዓት ውስጥ አንድም በብቃቱ ያለበትን ቦታ እንዳልያዘም እናውቃለን በበርሃ አስተሳሰብና በጠመንጃ ኃይል ልግዛ ሲሉ አገርንና ሕዝብን የጎዱ መሆናቸውን የምናውቀው እኛ እንጅ እነሱ አይደሉም ለምን?አገራዊ ወይም ብሄራዊ ሞራል የላቸውም ልባቸው እንዳይራራና ፈሪሃ እግዚአብሄር እንዳይኖራቸው ደግሞ መንፈሳዊ ስሜት የላቸውም የመጡበት ቤተሰብም አገር ሲያጠፋና ህዝብን ሲያደማ የነበረ ነው።እነዚህ ሁሉ ተዳምረው እያጭበረበሩ መኖርን የመረጡ ናቸው ለአብነት፦እኛ የተናገርነው እውነት ነው ይላሉ አንዳንዴ ስብሃት ነጋ የህወሃትን የውሸት ጆንያ ሲከፍተው በጆንያው ውስጥ ያለውን ውሸት ሲነግረን ልብ ብላችሁ ከሆነ(የኤርትራን ጉዳይ አስመልክቶ አንድ ነገር ብሏል)ህወሃት ገና ሲጀመር ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ አንድም እውነትነት ያለው ተግባር ፈጽሞ አያውቅም ራሱ ገድሎ ራሱ ማርዳት እውነት ከሆነ ፍርዱን ለአገር መተው ይሻላል። ህወሃት ነብሰ ገዳይ ዘራፊ ነው ጠባብና ጎጠኛም ነው ይህን ለምን ትነግሩብኛላችሁ ለምንስ አጋለጣችሁኝ ብሎ መግደል በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ማሰር እያሳደዱ ኢትዮጵያውያን አገር ጥለው እንዲጠፉ ማድረግ የህወሃት አይነተኛ መገለጫ ነው።
ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ህወሃት ሠራዊቱን ወደ የተለያዩ አገሮች ሲልክና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመከላከያ ሠራዊቱን ሁለንተናዊ ጉዳዮችን ሲሸፍን ለአንድ የሠራዊት አባል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምን ያህል እንደሚከፍል ማስረጃው ሰነድ በእጀ ባይኖረኝም በግምት ከ5 እስከ 7 ሺ ዶላር ሊከፍል ይችላል የሚለውን ልውሰድና ህወሃት 5.000 ሠራዊት ቢልክ ወይም ቢያከራይ 7000ሲባዛ 5000ሲባዛ በ3አገሮች ምን ያህል ገቢ እንደሚያገኝ አስቡት ይህ ሁሉ ለመከላከያ ሠራዊቱ የሚሰጥ ገንዘብ እንዳይመስላችሁ በቀጥታ ወደ ህወሃት አመራርና የሠራዊቱ ከፍተኛ አዛዦች የግል ባንክ የሚገባና ፎቆች የሚገነቡበት የተለያዩ የንግድ ተቋማት የሚስፋፉበት የአየር-ባየር ንግድ ይሆናል የራሱን ሕዝብ ባነገበው ነፍጥ አንገት አስደፍቶ የሚያስገዛው የህወሃት የመከላከያ ሠራዊት ግን የሚከፈለው ደመወዝ የጫማና የዩኒፎርም ከተቆረጠ በኋላ የሚተርፈውንና በህወሃት ገንዘብ በመደበኛ የወር ገቢው የሚያገኛትን ብቻ ነው።
በአሁኑ ሰአት አገር ጥለው የወጡ በየትኛውም ዓለም የሚገኙ ውድ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ግፍና በደል እየተፈጸመባቸው ይገኛሉ ይገደላሉ፤ይታሰራሉ….ወዘተ ይህን የሚያስፈጽመው ራሱ የህወሃት ሥርዓት እንደሆነ ቅንጣትም ቢሆን መጠራጠር አይኖርብንም።የአገር ሀብት እየተዘረፈ ሦስተኛ ወገን የሆነ አፍ እየተገዛበት ነው።በሰሞኑ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚንስትር ቀደም ሲል በአምባሳደር ሱዛን ሲደረት የነበረውም ሌሎች አሽቃባጮቻቸው የሚሉትም ህወሃት ያለበት ሁኔታ ጠፍቷቸው ሳይሆን ውሻ በበላበት ይጮሃል ነውና በወፍራም ዶላር የተመታ አፍ ከዚህ በላይም ሊያናግር ይችላል ወደፊትም የአገር ሀብት እየተጠረገ ህወሃት አፍ ከመግዛት አይመለስም።እኛ ኢትዮጵያውያንም ከጥቂቶች በስተቀር እጅ እግራችን አጣጥፈን ችግሩ እኛ እስካለንበት እስከሚደርስ እየጠበቅን ነው።ደቡብ አፍሪካ፤የመን፤ሳውዲ የተደረጉት ጥቃቶች ነገ አሜሪካ፤እንግሊዝ፤ፈረንሳይ፤ጀርመን ላይደገሙ ምን ዋስትና አለን?
እነዚህን ምክንያቶች እንድጠቅስ የገፋኝ የህወሃት የመከላከያ ሠራዊት ሥርዓቱን እንዳይገረሰስ የጀርባ አጥንት ሆኖ እያገለገለ ያለ ስለሆነ በዚህ ላይ ምን አይነት ርምጃ ቢወሰድ ውጤት ሊያመጣ ይችላል በሚል ጉዳይ ውስጥ ገብቼ ስለነበር ነው።ይህ ሠራዊት ኢትዮጵያውያን ሲሰደዱ፤ሲታሰሩ፤ሲገደሉ፤በውሸት ክስ ሕገ ወጥ ፍርድ ሲፈረድባቸው፤የህዝብ ሀብት ሲዘረፍ፤የሀገሪቱ ሉዓላዊነት ሲደፈር፤የሀገር ድንበር ሲደፈር ጀሮ ዳባ ልበስ በማለቱ የህወሃት ሠራዊት የሚል ትርጉም እንዲሰጠው ሆኗል ስለዚህ ህዝቡ ትክክለኛውን ትርጓሜ ሰጥቷል።በህዝብ ግብርና ታክስ ደመወዙን እያገኘ ሕዝብ አንገቱን ደፍቶ ለህወሃት እንዲገዛ መሣርያ ከሆነ ከህዝቡ ሊሰጥ የሚገባው ምላሽ ምን ሊሆን ይገባዋል?
የህወሃት ከፋፋይና ጎጠኛ ሤራ እንዳለ ሆኖ ማለትም ህዝብን በዘር በጎሳና በሃይማኖት መከፋፈሉ አንዱ ጎሳ ሌላውን ጎሳ በጥርጣሬ እንዲመለከተው ፀንቶ የኖረ በጋራ ተሰስቦና ተከባብሮ በአንድነት የኖረው ዝህብ እንዚያን ሁሉ እሴቶቹን አጥቷል።በሌላ በኩል ደግሞ ህዝቡ በውስጡ ያለውን ብሶት ለማስወገድ ትግሉን እንዳይቀጥል የተቃዋሚ ድርጅቶች ደንቃራና እንቅፋት ሆነውበት ይገኛሉ ዛሬ ድርጅት መመሥረት ፋሽን የሆነበትና ህዝብን ከህወሃት ባልተናነሰ ሁኔታ እየጎዱ እንደሆነ ልብ ሊሉት ይገባል።ህዝብን ነፃ አወጣለሁ ብሎ ሕዝብን አደጋ ውስጥ መክተት ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው ዛሬም ደግሜ እናገረዋለሁ የተቃዋሚ ኃይሎች በየትኛውም የትግልት ገብታችሁ መታገል መብታችሁ ነው።ህዝብን ለአደጋ የሚዳርጉ ተግባሮችን ግን መለየት ያሻል ምክንያቱም ህዝብ አልመረጣችሁም ታገሉልኝ ብሎም አልጠየቃችሁም ያለው ነባራዊ ሁኔታ ወደ ትግሉ እንድተገቡ አድርጓችሁ ከሆነ የትግል ስልታችሁንና ግባችሁን መርምሩ ገና አንድ ጋት ወደ ፊት ሳይኬድ እያለቀ ያለውን ህዝብ ልታስቡት ይገባል።እንደእኔ ትግሉ አግባብ ባለው መንገድ እየሄደ አይደለም።ትግሉ በአግባቡ ቢመራ ኖሮ ህዝብ አንቅሮ የተፋውን ህወሃትን ይቅርና ሌላም ቢሆን ማስወገድ ይቻላል።
የህወሃት የመከላከያ ሠራዊት፦ባሳለፍካቸው ጊዚያቶች የህወሃትን ሥርዓት እድሜ ለማርዘም ሲባል ከህዝብ የሚነጥል ተግባር ፈጽመሃል፤ህወሃት እያከራየ የገቢ መሰብሰቢያ አድርጓሃል፤ህወሃት ያለበት ተጨባጭ ሁኔታ እንደሚያሳየው ግራ የተጋቡ መሪዎቹ ጨልሞባቸው ነው ያለው።እስከ አሁን የፈጸሙት ፀረ-ሕዝብ ተግባራቸው እያባነናቸውና በደም በመጨማለቃቸው በኃይል ሥርአቱን ማቆየት ካልቻሉ የሚጠብቃቸው ምን እንደሚሆን ስለተገነዘቡ ግፉ ከጽዋው ሞልቶ በመፍሰሱ ሁላችንም የሞት የሽረት ትግሉን እንድንገባበት ተገደናል አገሪቱ ይጋራችን ናት ለህወሃት ብቻ መርጦ የሰጠው የለም።ስለዚህ የመከላክያ ሠራዊቱ መሣርያህን እንደያዝክ ህዝቡን በትጥቅ ትግል ላይ የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ድርጅቶችን ተቀላቀል ከህዝብ ጎን ልትቆም ይገባሃል ምክንያቱም የህዝብ ልጅ ነህና ወንድሞችህና እህቶችህ በየአረብ አገሩ አልቀዋል እያለቁም ናቸው አሁን ደግሞ በደቡብ አፍሪቃ በወገኖችህ ላይ እልቂት ጀምሯል ህይወቱንና የሥርአቱን እድሜ ለማራዘም እየተጠቀመብህ ያለው መንግስት ተብየ ችግሩ በየኤባሲዎች እንዲባባስ አደረገ እንጅ ለወገን ደራሽ ሆኖ አልተገኘም እኛም ህወሃት ለኢትዮጵያ ህዝብ ይቆረቆራል ብለን አንጠብቅም።በደርግ ሠራዊት ላይ የተፈፀመው አንተም ላይ ከመፈጸሙ በፊት ጥግህን ልትይዝና የህዝብ ልጅነትን ልታስመሰክር ይገባሃል።በግለጫ እየሰጠሁ ወይም እያስፈራራሁ አይደለም ሠራዊቱን ስለማውቀው አሁን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታም ስለምከታተለው ነገ የሚከሰተውን ነው እየተናገርኩ ያለሁት።
ሕዝባዊ እምብኝተኝነቱ ይቀጥላል!!
ነብሮ ነኝ።
The post ህወሃት የመከላከያ ሠራዊቱን የገቢ ምንጭ በማድረግ ይጠቀምበታል፦ appeared first on Zehabesha Amharic.