* “ወደ አገራቸው መመለስ ለሚፈልጉት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን” ቴድሮስ አድሃኖም
በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ አፍሪካውያን ላይ የተጀመረው ጥቃት ያስቆጣቸው የናይጄሪያ እንደራሴዎች በደቡብ አፍሪካ የሚገኙት አምባሳደር ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ውሳኔ አስተላለፉ፡፡ የሩዋንዳውን ፕሬዚዳንት በማስተናገድ የተጠመዱት ጠ/ሚ/ር ሃይለማርያም ደሳለኝ በደቡብ አፍሪካ “የተፈጠረው ጊዜያዊ ችግር ነው ብለን እናምናለን” በማለት አስተያየት ሰጡ፡፡ ውጭ ጉዳይ ሚ/ር ቴድሮስ ከየቦታው ሃሳብ እየሰበሰብኩ ነው፤ “ወደ አገራቸው መመለስ ለሚፈልጉ ድጋፍ እናደርጋለን” አሉ፡፡ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ግን የመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡
ሰሞኑን በደቡብ አፍሪካ የተነሳው አሰቃቂ ግድያና ዘረፋ ብዙዎችን እኤአ በ2008 የተከሰተውን እንዲያስታውሱ አድርጓቸዋል፡፡ በወቅቱ ከስድሳ በላይ አፍሪካውያን የተገደሉና የበርካታዎች ንብረት የተዘረፈ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ሰሞኑን በተነሳው ሁከት ሶስት ኢትዮጵያውያን መሞታቸውንና አስከሬናቸውን ወደ ኢትዮጵያ መላኩን ከዚያው የወጡ መረጃዎች ቢጠቁሙም የኢህአዴግ ባለሥልጣናት ግን የሞተው አንድ ብቻ ነው ማለታቸውን ኢቲቪ ዘግቧል፡፡
ከኢትዮጵያውያኑ ሌላ ዜጎቿ እንደሞቱባት የምትጠቀሰው ናይጄሪያ በድርጊቱ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅቶች እያደረገች መሆኑ ተሰምቷል፡፡ የናይጄሪያ እንደራሴዎች በደቡብ አፍሪካ ላይ የከረረ እርምጃ እንዲወሰድ እየሞገቱ ነው፡፡ የናይጄሪያ ተወካዮች ምክርቤት በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ካደረገ በኋላ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙት የናይጄሪያ አምባሳደር ወደ አገራቸው እንዲመጡ አጽድቋል፡፡
sa2sa4በተለያዩ ድረገጾች ላይ የተነበበው ይህ ዜና እንደሚያስረዳው የተከበሩት እንደራሴዎች እጅግ በጋለና አገር ፍቅር ስሜት በወገኖቻቸው እንዲሁም በአፍሪካውያን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት አውግዘዋል፤ ኮንነዋል፡፡ የኤዶ ግዛት እንደራሴ ረቂቅ ሕጉ ላይ የናይጄሪያ መንግሥት ከደቡብ አፍሪካ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲያቋርጥ የማሻሻያ ሃሳብ አቅርበው ነበር፡፡ ሃሳቡን የዴልታው እንደራሴ በአጽንዖት የደገፉ ቢሆንም ውሳኔ ድምጽ ላይ ሲደርስ አምባሳደሩ ወደ አገራቸው በአስቸኳይ እንዲጠሩ የሚለው ሲያልፍ ማሻሻያው ግን በቂ ድምጽ ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ ማሻሻያውን የደገፉ እንደራሴዎች በጉዳዩ ላይ እንደሚሰሩ የተሰማ ቢሆንም አምባሳደሩን ወዳገራቸው ማስመጣቱ በፍጥነት እንዲፈጸም ፕሬዚዳንት ጉድላክ ዮናታን የጉዳዩን አስቸኳይነት ለፕሬዚዳንት ያዕቆብ ዙማ እንዲገልጹ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
በኢትዮጵያ ጉብኝት የሚያደርጉትን የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት እያስተናገዱ ያሉት ሃይለማርያም ደሳለኝ በደቡብ አፍሪካ የደረሰውን በተመለከተ በእንግሊዝኛ ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡ ጠ/ሚ/ሩ ታሪክን የዘነጋ በሚመስል ለስላሳ አነጋገር “ደቡብ አፍሪካ ከቅኝ አገዛዝም ሆነ ከአፓርታይድ አገዛዝ ነጻ እንድትወጣ ድጋፍ መስጠታችን ይሰማናል” በማለት አጭሩን ንግግራቸውን አሰምተዋል፡፡ ሲቀጥሉም “አፍሪካውያን በፈለጉበት መኖር” እንደሚችሉ ከገለጹ በኋላ “አሁን የተፈጠረው ጊዜያዊ ክስተት ነው ብለን እናምናለን፤ የደቡብ አፍሪካ መንግሥትና ፓርቲ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድ እንጠብቃለን” በማለት ወደ ግብዣቸው ተመልሰዋል፡፡
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መ/ቤት አራተኛዋ ባለሥልጣን የሆኑትን የበታች ጸሃፊ ዌንዲ ሸርማንን በማስተናገድ የተጠመዱት ቴድሮስ አድሃኖም በፌስቡክ በለቀቁት አጭር መልዕክት “በደቡብ አፍሪቃ ከሚገኙ አንዳንድ ወገኖች” ጋር በስልክ እየተነጋገሩ መሆናቸውን እና ምን መደረግ እንዳለበት ከየቦታው እስካሁን ሃሳብ በመሰብሰብ ሥራ ላይ መጠመዳቸውንsouth-africa-foreigners የሚገልጽ እንደምታ ያለው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ “ወደ አገራቸው መመለስ የሚፈልጉትን” ለመደገፍ መዘጋጀታቸውን በዚሁ መልዕክት ገልጸዋል፡፡
ነዋሪዎችን ከየመኖሪያቸው በማፈናቀል፤ መኖሪያ በማሳጣት እና በግዳጅ ባልፈለጉበት ቦታ በማስፈር የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙ በተለያዩ ዘገባዎች በማስረጃ የሚነገርለት ኢህአዴግ ወደ አገር ለመመለስ ለሚፈልጉ ዝግጅቱ ማድረጉን ቢገልጽም በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ግን ሁኔታው አስፈሪ ቢሆንም ወደ አገራቸው መመለስ እንደማይፈልጉ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ አንዳንዶችም “ከአገራችን የወጣነው የኢኮኖሚ ጥገኝነት አስገድዶን ብቻ አይደለም፤ የመኖር ኅልውናችን አደጋ ላይ በመውደቁም ጭምር ነው” ሲሉ ተሰምተዋል፡፡
ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡ እንዳሉት “ደቡብ አፍሪካውያን ኢትዮጵያዊ ስለተባልን አገር ያለን መስሏቸው ከአገራቸው እንድንወጣ ይነግሩናል፤ በህይወት እያለን ወደ ኢትዮጵያ ሄደን በደኅንነት መኖር ስለማንችል እኮ ነው ስንሞት አስከሬን የምንልከው፤ ይህንን ግን የተረዱት አይመስለኝም” በማለት ሃሳባቸውን ተናግረዋል፡፡
sa9እኤአ በ2000 መጀመሪያዎች አካባቢ በአገራቸው የሚኖሩ ነጭ ሰፋሪዎችን ያባረሩት የዚምባብዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ በዚሁ የደቡብ አፍሪካ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎቿ ደቡብ አፍሪካ እንደሚኖሩ የሚነገርላት ዚምባብዌ የዜጎቿን ጉዳይ ቀዳሚው ስፍራ የሰጠችው መሆኑ ተሰምቷል፡፡ በተለይ ግን ሙጋቤ ጉዳዩን አስመልክቶ በላኩት መልዕክት እንዲህ በማለት በደቡብ አፍሪካውያን ላይ ተሳልቀዋል፤ ዘልፈዋቸውማል፡፡
“ደቡብ አፍሪካውያን አንድ ነጭ በህይወት እያለ በጥፊ ለመምታት ሙከራ እንኳን ስለማያደርጉ (ስለሚፈሩ) ነጭ ሲሞት ሃውልቱን ይደበድባሉ፤ ነገር ግን አንድ ጥቁር የሌላ አገር ዜጋ በመሆኑ ብቻ በድንጋይ ወግረው ይገድላሉ፡፡”
Source: googlgule.com
The post “አምባሳደሩ ወዳገራቸው መመለስ አለባቸው” የናይጄሪያ እንደራሴዎች “አሁን የተፈጠረው ጊዜያዊ ክስተት ነው” ሃይለማርያም appeared first on Zehabesha Amharic.