Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ባንኮች የተከፈለ ካፒታላቸው ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ሊሆን ነው

$
0
0

national bank of ethiopiaበኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመግባት የሚያስፈልገው የመነሻ ካፒታል መጠን እንደገና ስለሚከለስ ባንኮችም ለዚህ እንዲዘጋጁ ተነገራቸው፡፡ ምንጮች እንደገለጹት፣ የባንኮች መመሥረቻ ካፒታል መጠን አሁን ካለበት 500 ሚሊዮን ብር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ከፍ በማድረግ ሥራ ላይ ለማዋል ታቅዷል፡፡

የባንኮች መነሻ ካፒታል መጠንን ለማሳደግ መንግሥት ያለውን ዕቅድ በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከባንኮች ሥራ አስፈጻሚዎች ጋር አድርጎት በነበረው የውይይት መድረክ ላይ ማስታወቁን፣ ለዚህም እንዲዘጋጁ ያሳሰበ መሆኑን ምንጮች አስረድተዋል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የፋይናንስ ተቋማት ሊደርሱበት ይገባል የተባለውን ግብ ለማሳካት፣ አንዱ የባንኮችን ካፒታል አቅም ማሳደግ የሚያስፈልግ መሆኑ ስለታመነበት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ ለባንኮቹ ኃላፊዎች ባደረጉት ገለጻ፣ በሥራ ላይ ያሉት የግል ባንኮች ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ያሉዋቸውን ቅርንጫፎች በ25 በመቶ እንዲያሳድጉ ነግረዋቸዋል፡፡ ከተጨማሪዎቹ ቅርንጫፎች ውስጥ ሁለት-ሦስተኛው ከአዲስ አበባ ውጪ መክፈት እንደሚገባቸው ማሳሰባቸው ተሰምቷል፡፡

በብሔራዊ ባንክና በባንኮች ሥራ አስፈጻሚዎች መካከል በነበረው ውይይት ይህንን ሐሳብ ባንኮች እንዲያውቁት መረጃ ከመስጠት ያለፈ ዝርዝር መረጃ ባይቀርብም፣ የባንኮች የመነሻ ካፒታል ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እንዲሆን ፍላጎት ያለ መሆኑን የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ ይህ መጠን አነስተኛው ሊሆን እንደሚችልና ምናልባትም ከዚህ ከፍ ሊል እንደሚችልም ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

የባንኮች ካፒታል መጠን እንደታሰበው አንድ ቢሊዮን ብር እንዲሆን ከተወሰነ፣ አብዛኛዎቹ ባንኮች ችግር ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ የሚል ሥጋት አሳድሯል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ የባንክ የሥራ ኃላፊዎች፣ የባንኮች ማቋቋሚያ ካፒታል መጠንን ለማሳደግ ስለመፈለጉ መረጃው እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ በየትኛውም ደረጃ የመነሻ ካፒታል መጠኑ ቢያድግ ለአብዛኛዎቹ ባንኮች ፈታኝ እንደሚሆንባቸው ተናግረዋል፡፡ በተለይ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የተቋቋሙ ባንኮች ከሦስት ዓመት በፊት የባንኮች መመሥረቻ ካፒታል ከ100 ሚሊዮን ብር ወደ 500 ሚሊዮን ብር እንዲያድግ ሲወሰን፣ ካፒታላቸው 500 ሚሊዮን ብር ያልደረሱ ባንኮች በአምስት ዓመታት ውስጥ ወደዚህ ደረጃ እንዲደርሱ የወጣውን ሕግ ለማሟላት በሚታትሩበት ወቅት፣ ይህ አዲስ ሐሳብ መቅረቡ ሳያሳስባቸው አልቀረም፡፡

ለ500 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል እስካሁን አክሲዮን እየሸጡ ያሉ ባንኮች በመኖራቸውና ይህንንም ለማሟላት አድካሚ የሚባል ጉዞ እየተጓዙ መሆናቸውን የገለጹት አንድ የባንክ ባለሙያ፣ በእርግጥም አዲሱ መመርያ በተግባር ላይ ከዋለ የአብዛኛዎቹ ባንኮች ዕጣ ፈንታ ውህደት እንዲሆን ያደርጋል የሚልም ሥጋት አላቸው፡፡ ጠንካራ ለሚባሉትም ፈታኝ ነው ብለዋል፡፡

ባንኮች አትራፊ መሆናቸው ቢታወቅም የካፒታል መጠናቸውን እንዲያሳድጉ በወጣው አስገዳጅ መመርያ መሠረት፣ 500 ሚሊዮን ብር ካፒታሉን ለማሟላት እያደረጉ ያሉት የአክሲዮን ሽያጭ በተፈለገው ፍጥነት እየተጓዘ ባለመሆኑ፣ እንደገና ካፒታላችሁን አሳድጉ ከተባሉ በአክሲዮን ሽያጭ ለመሙላት የሚቸገሩ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ብቸኛው አማራጭ የሚሆነው አነስተኛ ካፒታል መጠን ያላቸው ባንኮች ወደ ውህደት እንዲገቡ ሊያስገድዳቸው እንደሚችልም እኚሁ ባለሙያ ገልጸዋል፡፡

‹‹የመጨረሻው ውሳኔ ውህደት ቢሆን አሁን በሥራ ላይ ካሉ የባንኮች ባህሪ አንፃር አንዱን ከአንዱ ለማዋሀድ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፤›› የሚልም ሥጋት አላቸው፡፡ የካፒታል ዕድገቱ ለሎች ተፅዕኖዎችም እንዳለው የሚናገሩት እኚሁ ባለሙያ፣ የማቋቋሚያ ካፒታሉ አንድ ቢሊዮን ብር ይሁን ቢባል እንኳን አሁንም አዳዲስ ባንኮች እንዳይፈጠሩ ጋሬጣ ይሆናል ይላሉ፡፡

የመመሥረቻ ካፒታሉ 500 ሚሊዮን ብር ይሁን የሚለው መመርያ ሥራ ላይ ከዋለ ወዲህ እንኳን ይህንን ያህል ካፒታል ለማሰባሰብ አስቸጋሪ ነው ተብሎ በመታመኑ አዲስ ባንክ አለመቋቋሙን አስታውሰዋል፡፡ ባንክ ለማቋቋም አክሲዮን ሲሸጡ የነበሩ ሦስት ባንኮች ሳይቀሩ 500 ሚሊዮን ብሩን መሙላት አንችልም ብለው እንቅስቃሴያቸውን ማቋረጣቸውንም በምሳሌነት አስረድተዋል፡፡

አሁንም የካፒታል መጠኑ ካደገ አዳዲስ ባንኮች እንዳይመሠረቱ በማድረግ፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉት ባንኮች ብቻ እንዲቆዩና ካፒታላቸውን አንድ ቢሊዮን ለመድረስ የሚገደዱትም ቀጣይ ጊዜያቸው ሕጉን ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንዲወጠሩ ያደርጋቸዋል የሚል ግምት አላቸው፡፡ የአዳዲስ ተወዳዳሪ ባንኮች እንዳይፈጠሩ ማድረጉ ደግሞ ሌላው ተፅዕኖ ነው የሚሉት የባንክ ባለሙያዎች፣ እንደ ኬንያ ያሉ አገሮች ከ45 በላይ ባንኮች ያላቸው መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

በሌላ በኩል ለአገሪቱ የባንኮች ዕድገት ከታሰበ የመመሥረቻ ካፒታሉ ማደጉ ይጠቅም ይሆናል እንጂ ጉዳት የለውም የሚሉም አሉ፡፡ የአገሪቱ ባንኮች ከሌሎች ባንኮች ጋር በንፅፅር ሲታዩ ያላቸው ካፒታል እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ፣ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ማድረጉ አግባብ ነው ይላሉ፡፡ ይህንን ካልቻሉ ተጣምረው ጠንካራ ባንክ ካቋቋሙም ጠቃሚ ስለሚሆን ሥጋቱ ተገቢ አይመስላቸውም፡፡ ካፒታሉን የሚያሟሉበት መንገድ የተመቻቸ እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባ፣ አቅማችሁን አሳድጉ የሚለው ሐሳብ ትክክል ነው የሚል እምነት ያላቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት 16 የግል ባንኮች በሥራ ላይ ናቸው፡፡ እስከ 2007 ዓ.ም. የመጀመርያ ስድስት ወራት ድረስ አራት ባንኮች እስካሁን ያሰባሰቡት የካፒታል መጠን ከ500 ሚሊዮን ብር ያነሰ ነው፡፡ ስምንት ያህሉ ደግሞ የተከፈለ ካፒታላቸው ከአንድ ቢሊዮን ብር በታች ነው፡፡ እንደ መንግሥት ዕቅድ አዲስ በሚወጣው መመርያ ተግባራዊ እንዲሆን የሚፈለገው የካፓታል መጠን፣ እስከ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጨረሻ ድረስ ነው፡፡

Source:: Ethiopian Reporter

The post ባንኮች የተከፈለ ካፒታላቸው ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ሊሆን ነው appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>