“ትምህርት ለሁሉም” በሚል መርህ ከ2000 እስከ 2015 እ.ኤ.አ በአለማቀፍ ደረጃ የተያዘውን የትምህርት ተደራሽነት ግብ ኢትዮጵያ በሁሉም መመዘኛዎች ዝቅተኛ ውጤት በማምጣት ማሳካት አለመቻሏን ዩኔስኮ በግሎባል ሞኒቴሪንግ ሪፖርቱ ይፋ አደረገ፡፡ ሃገሪቱ በሁሉም መመዘኛዎች ስኬታማ ባትሆንም በተለይ 7 ሃገራት ብቻ ማሳካት የቻሉትን ጥቅል የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋንን በተሻለ ደረጃ ልታሳካ መቃረቧንና በዚህ ረገድ ያስመዘገበችው ውጤት አመርቂ መሆኑን ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡ አለማቀፉ የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም (UNESCO) ከ15 ዓመት በፊት ታዳጊ ሃገራት የትምህርት ተደራሽነትን ይበልጥ እንዲያስፋፉ በ6 መመዘኛ ነጥቦች የሚገመገሙበት ግቦች ያስቀመጠ ሲሆን ሰሞኑን ይፋ ባደረገው የግምገማ ሪፖርት፤ አብዛኛዎቹ ታዳጊ ሀገራት የገቡትን ቃል አለማሳካታቸውን ጠቁሟል፡፡
“ኢትዮጵያ አያያዟ መልካም ነው፤ እስከ 2030 በሚቆየው የልማት ትልም ጊዜ ውስጥ ግቦቹን ልታሳካ ትችላለች” ብሏል – ሪፖርቱ፡፡
በዚህ ሪፖርት ኢትዮጵያ በሁሉም መመዘኛዎች ከተቀመጡት ግቦች በእጅጉ ወደ ኋላ የቀረ አፈፃፀም ማስመዝገቧ ተጠቁሟል፡፡ በ2015 ሃገሪቱ የጎልማሶች የትምህርት ተደራሽነትን በማስፋፋት በሃገሪቱ ያለውን መሃይምነት ከ50 በመቶ በታች ትቀንሳለች ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ከተቀመጠው ግብ መፈፀም የቻለችው 21 በመቶውን ብቻ ነው፡፡
በሃገሪቱ የ1ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን መከታተል ሲገባቸው ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ህፃናት የእድሉ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ትምህርት ከክፍያ ነፃ በመሆኑ የሴቶች ተሳትፎ መጨመሩን አመልክቷል፡፡
በፊት 61 በመቶ የሚሆኑ ታዳጊዎች የ1ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሳያጠናቅቁ ያቋርጡ እንደነበር የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ በአሁን ወቅት አኀዙ ወደ 37 በመቶ ዝቅ ማለቱን ጠቁሞ ውጤቱ ከተቀመጠው ግብ አንፃር ዝቅተኛ አፈፃፀም ነው ብሎታል፡፡
ኢትዮጵያ እስከ ዘንድሮ የፈረንጆች ዓመት ድረስ የ1ኛ እና የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋንን በማሳደግ ታሳካዋለች የተባለውን ግብ ባለማሳካቷ በሁለተኛው ምዕራፍ እስከ 2030 በሚዘልቀው የ15 ዓመት ግብ ማሳካት ይጠበቅባታል ያለው ሪፖርቱ፤ ለዚህም በየዓመቱ 22 ቢሊዮን ዶላር (ከ440 ቢሊዮን ብር በላይ) በጀት ለዘርፉ መመደብ እንዳለባት ጠቁሟል።
ዩኔስኮ የ15 ዓመት የትምህርት ልማት ግብ ብሎ ያስቀመጣቸው መመዘኛዎች፡- የህፃናት የትምህርት እድል መስፋፋት፣ የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋንን ማሳደግ፣ ለወጣትና ጎልማሶች በእኩል ትምህርትን ማዳረስ፣ መሃይምነትን ከ50 በመቶ በታች መቀነስ፣ የፆታ ተሳትፎ እኩልነትን ማረጋገጥና የትምህርት አጠቃላይ ጥራት ማሳደግ የሚሉት ሲሆኑ ኢትዮጵያ በሁሉም መመዘኛዎች ዝቅተኛ ውጤት ካስመዘገቡት ሃገራት ምድብ ውስጥ ተካታለች። ከስኬት ለመድረስ ብዙ ርቀት መጓዝ ይቀራታል ሲልም ሪፖርቱ አክሏል፡፡
The post ትዮጵያ ሁሉንም የትምህርት ተደራሽነት ግብ መመዘኛዎች አላሳካችም ተባለ appeared first on Zehabesha Amharic.