Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

“ያሳደግኹት ውሻ አሳጣኝ መድረሻ” ፥ የአቶ ገብሩ ዐሥራት እና ሊነበብ የሚገባው አነጋጋሪ መጽሐፋቸው

Previous: Hiber Radio: “በሳዑዲ አረቢያው ላይ እንደተደረገው በየመን ላሉ ኢትዮጵያውያን መጮህ አለብን ተባለ.. የቻይና የባህር ሀይል አባላት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከየመን ከ200 በላይ የ10 አገር ዜጎችን ታደጉ…አቶ እንዳርጋቸው ፅጌን ለማስለቀቅ የእንግሊዝ መንግስት ዛሬም ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ ተጠየ.. የግብጹ ሚድያ ፕሬዝዳንቱ ከኢትዮጵያና ሱዳን ጋር የፈረሙትን ፊርማ የግብፅን ህዝብ አይወክልም አለ…የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ልደት ፕሮፌሰር መስፍንን ጨምሮ የተለያዩ የተቃዋሚ መሪዎችና ጋዜጠኞች በተገኙበት ተከበረ…እና ሌሎችም
$
0
0

(ኄኖክ የማነ)
ከአቶ ገብሩ ሕይወት ጋራ የሚመሳሰሉ ታሪኮችን ከገሃዱ ዓለም ይልቅ በልብ ወለዶች ወይም በሕይወት ትርጉም ላይ በሚያተኩሩ የፍልስፍና መጽሐፍት ውስጥ በቀላሉ ማግኘት ሳይቀል አይቀርም። የሕይወትን ትርጉም የተለያዩ ጸሐፍት አያሌ መመዘኛዎችን በመጠቀም ለማብራራት ይሞክራሉ። ከነዚህ አከራካሪ መመዘኛዎች አንዱ ሰዎች በኋለኛው የዕድሜ ዘመናቸው ላይ ኾነው ያሳለፉትን የሕይወት ዘመን የኋልዮሽ በመመልከት “ሕይወቴ የተሳካ ነበረ?” ለሚለው ጥያቄ በሚሰጡት መልስ ላይ ይመሠረታል። በዚህ ውጤት አግናኝ መመዘኛ ከተለካ የአቶ ገብሩ ሕይወት “እዚህ ግባ” የሚባል ትርጉም አልነበረውም ብሎ መከራከር ይቻላል። ለዚህ አስተያየት እንደ ምክንያት ሊቀርብ የሚችለው ነገር ደግሞ የቀድሞው የሕወሓት ባለሥልጣን ከዐሥራዎቹ ዕድሜያቸው ጀምሮ መላ ሕይወታቸውን የገበሩለት የትጥቅ ትግልም ኾነ የፖለቲካ ዓላማ በ64 ዓመታቸው በተሻለ ብስለት እና ስክነት ሲገመግሙት “ኢትዮጵያ በፍጥነት ሊቀየር የሚገባው አሳሳቢ ኹኔታ ላይ ትገኛለች።” የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሳቸው ነው።
gebru-book
አቶ ገብሩ በቅርቡ “ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ የትግልና የፖለቲካ ሕይወታቸውን ትርጉም የሚመለከቱ ከባድ ጥያቄዎች ያነሳሉ፤ “ያለፈውን ጊዜህን ይኼን ያህል ከተቸህ ጉዞህ ኹሉ ከንቱ ነበረ ወይ?፥ ባደረግኸውስ ትጸጸታለህ ወይ?” ፥ እና “ለመብትና ለነጻነት ሲሉ በሕወሓት/ኢሕአዴግ ተደራጅተው የተፋለሙትን፥ አካላቸውን እና ሕይወታቸውን ያጡትን ወገኖች አስተዋጽዖ መና አስቀረኸው ወይ?” ሊባሉ እንደሚችሉ ይጠቅሳሉ። ጸሐፊው ለነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጡት መልስ ለሦስት ዐሠርት ዓመታት ከልቡ አምኖበት ብዙ መስዋዕትነት የከፈለለት ዓላማ ያመጣውን ውጤት አጥብቆ የሚቃወም ሰው ሊፈጠርበት የሚችለውን አስጨናቂ የተቃርኖ ስሜት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። ይኼም ብቻ አይደለም፤ መልሱ በመጽሐፉ ውስጥ የሚስተዋለውን የአቶ ገብሩን በፖለቲካው ዓለም ብርቅ የኾነውን ቀጥተኝነትም ያንጸባርቃል። “በኔ ዕምነት በሕወሓት/ኢሕአዴግ የተሰለፍነውም ኾነ በሌሎች ድርጅቶች ተሰልፈው ደርግን የተፋለሙት ታጋዮች ኹሉ ታሪክ በአዎንታ መዝግቧቸዋል። እዚህ ላይ መታየት ያለበት እነዚህ ታጋዮች ያስገኙት ውጤት ሳይኾን ያነገቡት አምባገነንነትን ገርስሶ ፍትሐዊ ሥርዐትን የማስፈን ዓላማቸው ነው። ለዚህ ክቡር ዓላማ ማንኛውንም መስዋዕትነት የከፈለ ዜጋ ክቡር በመኾኑም በአገራችን ታሪክ ሊዘከር ይገባዋል።” ይላሉ አቶ ገብሩ ምላሻቸውን ሲሰጡ። በማስከተልም “ ይኽ ማለት ግን በዚህ የትግል ጉዞ የነበረው የፖለቲካ አካሄድ ቢያንስ ከዴሞክራሲ እና ከአገር ጥቅም አንጻር የነበረበትን መሠረታዊ ጉድለት መመርመር የለበትም ማለት ኣይደለም። የዕውነተኛ የፖለቲካ መጽሐፍ ፋይዳም ያሁኑንም ይኹን ያለፈውን ታሪክ ያለምንም ፍርሐት እና ወገናዊነት በነጻነት እንዲታወቅ ማድረግ ነው። ስለኾነም በዚህ መጽሐፍ ለኅሊናዬ ትክክል የመሰለኝን ኹሉ ለማስፈር በመሞከሬም ሰማዕታቱ የተሰዉለትን ዓላማ ለማክበር ሞክሬአለሁ” በማለት አቋማቸውን ይገልጻሉ።
ይህ የአቶ ገብሩ አመለካከት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ካሉ የተለያዮ አቋሞች አንጻር ሲታይ አወዛጋቢ ሊኾን ቢችልም፤ የታገሉለት ዓላማ አቅጣጫውን ስቶ አገሪቷን ከባድ ችግር ውስጥ እንደከተታት ቢያምኑም ቢያንስ በአንድ መመዘኛ ሕይወታቸው ጉልህ ትርጉም እንዳለው መከራከር ይቻላል። የቀድሞው ታጋይ እና ባለሥልጣን ዘግይተውም ቢኾን (በተወሰነ መልኩ ሳይፈልጉም ቢኾን) ራሳቸውን በጥልቀት መርምረው፥ ስህተት ነው የሚሉትን ተቀብለው፥ እንደ ጣዖት ይመለክ የነበረውን የቀድሞ ድርጅታቸውን በአደባባይ ለመተቸት እና ንስሐ ለመግባት፤ እንዲሁም ለሌላ ለውጥ ለመታገል እና ስህተታቸውን ለማረም ዕድል አግኝተዋል። ብዙ ነገር ቢያጡም ትልቅ ዋጋ ያለው አንድ ነገር አግኝተዋል ማለት ይቻላል።
Gebru Asrat
በዚህ ኹሉ መካከል ግን አንድ በማሻማ ኹኔታ ግልጽ የኾነ ነገር አለ፤ በአቶ ገብሩ ሕይወት ውስጥ የሚስተዋለው መራር የፖለቲካ እና የታሪክ ምጸት። እርሳቸው እንደሚያምኑት አምባገነናዊ ሥርዐትን እና ኢፍትሐዊነት ለማስወገድ የተደረገው መራር ትግል ያስከተለው ነገር ቢኖር- በደምሳሳው ሲታይ- በቅርጽ የተለየ በይዘቱ ግን አምባገነናዊ እና ኢፍትሐዊ የኾነ ሥርዐት “ማንገስ” ነው። ይኽ እጅግ መራር ምጸት ነው።
በመጽሐፋቸው ምረቃ ላይ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኝ አንድ አዳራሽ ውስጥ ከመገናኘታችን በፊት አቶ ገብሩን የማውቃቸው እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በመገናኛ ብዙኃን ነበር። ስለ እርሳቸው የነበረኝ አመለካከት ደግሞ ከሕወሓት ክፍፍል በኋላ አሸናፊው ወገን ስለ “አንጃው” መሪዎች በሚያሰራጫቸው መረጃዎች ተጽዕኖ ሥር የወደቀ ነበር። “ በድሮ በሬ ለማረስ የሚሞክሩ ተቸካይ ማርክሲስት ሌኒኒስት”፥ እንዲሁም ጽንፈኛ የትግራይ ብሔረተኛ እንደኾኑ አምን ነበር። ወደ ምረቃ አዳራሹ የሄድኹት በበርካታ ንዑስ ርዕሶች ከተከፋፈለው የመጽሐፉ ማውጫ ወደ ዐራት የሚጠጉ ትኩረቴን የሳቡ ጉዳዮችን ብቻ በዋዜማው አንብቤ ነበር። ዐራቱ ጉዳዮች የተደበላለቀ ስሜት የፈጠሩብኝ ቢኾንም፥ የመጽሐፉ ድርጁ ይዘት መጽሐፉን ሙሉ በሙሉ ለማንበብ ከፍተኛ ፍላጎት ፈጥሮብኝ ነበር። በምረቃው ላይ ለተነሱት ጥያቄዎች ደራሲው መልስ የሰጡበት መንገድ ደግሞ የማንበብ ፍላጎቴን ብቻ ሳይኾን ጸሐፊውን የማግኘት ፍላጎቴን አነሳሳው። በቀድሞው የ”ኢትኦጵ” ጋዜጠኛ አርዐያ ተስፋማርያም በኩል አንድ ቅዳሜ ተገናኝተን ለዐራት ሰዓታት ያህል ጥያቄዎቼን ሳዥጎደጉድባቸው ቆየኹ። ጥያቄዎቼን በተለመደው ‘ርጋታቸው በተቻላቸው ኹሉ ቀጥተኛ እና ግልጽ በኾነ መንገድ በትዕግስት መለሱልኝ። ይከተሉት የነበረው ርዕዮተ ዓለም ስህተት መኾኑን ለመረዳት ለምን የሕወሓት መከፋፈል አስፈላጊ እንደ ነበር፥ የአቶ መለስ አንዳንድ አስገራሚ ግለሰባዊ ባህርያት፥ ከሕወሓት ከተሰናበቱ በኋላ ስለደረሰባቸው ችግር እና ስለ ሌሎችም መጽሐፋቸው ውስጥ ያልተካተቱ ብዙ አስገራሚ ነገሮች አጫውተውኛል። አቶ ገብሩ እጅግ ትሑትም ናቸው። ተቋማዊ፥ ቤተሰባዊ፥ እና ግለሰባዊ ንቅዘት በተንሰራፋበት አገዛዝ ውስጥ በከፍተኛ ባለሥልጣንነት ቆይተው በሙስና ጨርሶ አለመታማታቸውን ሳስብ ደግሞ መጽሐፋቸውን የመገምገም ሥራዬን ወገናዊነት እንዳይጫነው መስጋቴ አልቀረም።

በቅርብ ዓመታት ውስጥ በቀድሞ ባለሥልጣናት ከተጻፉ የፖለቲካ ግለታሪክ እና የትውስታ መጻሕፍት “ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ” ከአገራዊ ፋይዳ፥ ከግልጽነት እና ከተጠያቂነት፥ ከስፋት እና ከጥልቀት አንጻር ሲታይ ከሁሉም ከፍ ብሎ በሚገኝ ማማ ላይ ለብቻው ተቀምጧል ቢባል ማጋነን አይመስለኝም።በነዚህ መስፈርት በማያጠራጥር ኹኔታ ከወለል በታች የሚገኘው (አሁንም ሥልጣን ላይ እንዳሉ የሚያስቡ በሚመስሉት) በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የተደረሰው “ትግላችን” የተባለው መጽሐፍ ነው። በግል፥ በውስን፥ እና በጠባብ አጀንዳዎች ላይ የሚሽከረከረው የአቶ ስየ አብርሃ “ነጻነት እና ዳኝነት በኢትዮጵያ” ፥ የግብር ይውጣ በሚመስል ኹኔታ ይቅርታ ለመጠየቅ የሚዳዳው እና የደርግን ሥርዐት ወደ መከላከል የሚያዘነብል የሚመስለው የሻምበል ፍቅረሥላሴ “እኛና አብዮቱ” ከፍተኛ ትኩረት እና ተቀባይነት ያገኘው ነገር ግን “ይቅርታ” የሚባል ቃል የማይወጣው የአቶ ኤርምያስ ለገሠ “የመለስ ትሩፋቶች” ፥ ጠንከር ያለ የትንተና ችግር የሚታይበት እና የሕወሓትን የሽምቅ ውጊያ ታሪክ በማንቆለጳጰስ የተጠመደው የአቶ አስገደ ገብረሥላሴ “ጋሕዲ” እና የመሳሰሉት የየራሳቸው ሊጠቀሱላቸው የሚችሉ ጠንካራ ጎኖች እንዳሏቸው ባይካድም (ይኽ ምልከታ“ትግላችን” የሚመለከት አይመስለኝም) አቶ ገብሩ በመጽሐፋቸው በተደጋጋሚ እና በየአጋጣሚው አቋማቸውን እየፈተሹ ስህተት ኾኖ ያገኙትን “ ስህተት ነው” ማለታቸው፥ አስፈላጊ ሲኾንም ኃላፊነት መውሰዳቸው፤ በተጨማሪም ትልቁን አገራዊ ሥዕል በመመልከት ይበጃል የሚሉትን አቅጣጫ በጥናት ላይ ተመሥርተው ለማቅረብ መሞከራቸው መጽሐፋቸውን ልዩ ያደርገዋል።
“ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ”ም ቢኾን ግን እንከን አልባ አይደለም፤ በጭራሽ። እንደውም ያደነቅኹትን ግልጽነታቸውን እና ሃቀኝነታቸውን እስከ መጠራጠር ያደረሱኝ በመጽሐፉ ውስጥ ኾን ተብለው የተድበሰበሱ የሚመስሉ ፥ ፈጽሞ ያልተስተዋሉ እና ያልተወሱ አንገብጋቢ ጉዳዮችን ታዝቤአለሁ። ታዲያ አቶ ገብሩ ዐሥራትን ተጣድፌ አወድሻቸው ይኾን?

አቶ ገብሩ የድርሰታቸውን ጽሕፈተ-ምክንያት በሁለት ዐበይት ዓላማዎች ዙሪያ እንደሚያጠነጥን ያወሳሉ። አንደኛው “በሕይወት እያለን የምናውቀውን ታሪክ የሕወሓት/ኢሕአዴግ አመራር እያዛባው እና እየከለሰው ለአገዛዙ እንደሚመች የሚያቀርበውን ታሪክ በማስተካከል ረገድ የበኩሌን አስተዋጽዖ ለማድረግ” ሲኾን ኹለተኛው ደግሞ “ዕውነትን ፍለጋ ለሚሯሯጡት ይኼን ዐይነት መጽሐፍ ማዘጋጀቱ እንደ መነሻ እና እንደ አማራጭ ሊጠቅማቸው ይችላል” በሚል ዕምነት ነው። የመጽሐፉ ስኬት ከነዚህ ዓላማዎች አንጻር ከተለካ አቶ ገብሩ እጅግ ስኬታማ ኾነዋል ማለት ይቻላል። በዚህ ዳሰሳ “ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ”ን ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ጭብጦች አንጻር ለመቃኘት እሞክራለሁ።

1. ቅርጽ፥ አቀራረብ፥ መጠነ-ቅኝት (Scope)፥ እና ጥልቀት

እነዚህ ነጥቦች ከመጽሐፉ ይዘት ጋራ ቀጥተኛ ግንኙነት ባይኖራቸውም፤ ይዘቱ ሊፈጥረው በሚችለው ተጽዕኖ ላይ የማይናቅ ሚና ሊኖራቸው ይችላል። ከዚህ አንጻር ሲታይ መጽሐፉ የተለያዩ የአጻጻፍ ዘርፎች (Genres) ባህርያትን ቀላቅሎ የያዘ መኾኑ ደራሲው የሚፈልጉትን መልዕክት በጥሩ ኹኔታ ለማስተላለፍ ‘ረድቷቸዋል፤ ኾኖም አንዳንድ እንከኖችም ይታዩበታል።

2. ማርክሲዝም- ሌኒኒዝም እና ሕወሓት

አቶ ገብሩ በዝርዝር እና በተደጋጋሚ ከሚያነሷቸው ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ የማሌ ንድፈ-ኃሳብ እና በሕወሓት፥ አልፎም በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ የተጫወተው ወሳኝ ሚና ነው። በመጽሐፉ ውስጥ ከሠፈሩት ነገሮች ሰቅዘው ከያዙኝ (ካሳዘኑኝ እና ካሳቁኝ) መካከል ይገኙበታል።

3. አቶ መለስ ዜናዊ
“ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ” ውስጥ የሚገኙት አቶ መለስ ዜናዊ ፍጹም አስደናቂ ከመኾናቸው የተነሳ መጽሐፉን ለመክደን አዳጋች ያደርጉታል። አቶ መለስ ኒኮሎ ማኪያቬሊን ራሱን በመቃብሩ ውስጥ በኩራት ደረት ሊያስነፉ የሚችሉ፥ ከማኪያቬሊም በላይ ማኪያቬላዊ ናቸው። አቶ ገብሩም አንድ ቦታ ላይ አቶ መለስን በቀጥታ ሳይኾን ተግባራቸውን “ማኪያቬላዊ” በማለት ይገልጹታል። ከአቶ ገብሩ መጽሐፍ ለመረዳት እንደሚቻለው ሟች የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር በአንድ ጉዳይ ላይ ብቻ ወጥ አቋም ያሳያሉ፤ ለሥልጣናቸው አደጋ ሊፈጥር እንደሚችል እያወቁም ጭምር። በአዕምሮ ብቃታቸው እና በንድፈ ኃሳብ ትንተና ችሎታቸው ደግሞ በሕወሓት ውስጥ እምብዛም የሚገዳደር ተፎካካሪ የነበራቸው አይመስሉም።

4. ሉዓላዊነት እና ማኅበረ – ኢኮኖሚያዊ ፍትሕ

የ“ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ” አንኳር ድክመቶች በአብዛኛው ሉዓላዊነት እና ማኅበረ – ኢኮኖሚያዊ ፍትሕ ላይ ያጠነጥናሉ። ለአቶ ገብሩ “ሉዓላዊነት ማለት በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል በቻ ያለ የድንበር ጥያቄ ነው እንዴ?” የሚል መጠይቅ የሚያጭሩ ከመጽሐፉ ሽፋን ጀምሮ በርካታ ጉዳዮች ማንሳት ይቻላል። ውስጣዊ ሉዓላዊነት እና በሌሎች የኢትዮጵያ ጠረፎች ያሉ የድንበር ውዝግቦች የአቶ ገብሩን ትኩረት ብዙም የሳቡ አይመስሉም። ስለ ኢትዮጵያ የወደፊት አቅጣጫ በሚናገሩበት የመጽሐፉ የመጨረሻ ክፍል ደግሞ የማኅበረ – ኢኮኖሚያዊ ፍትሕን ወሳኝነት አስረግጠው ቢያብራሩም ከጉዳዩ ጋራ የተቆላለፈ እና ለማኅበረ – ኢኮኖሚያዊ ፍትሕ ግዙፍ እንቅፋት የኾነን ዐብይ ጉዳይ ቀደም ባሉት የመጽሐፉ ገጾች እንደነገሩ አከክ-አከክ አድርገው ያልፉታል።

Source: 7killo Magazine

The post “ያሳደግኹት ውሻ አሳጣኝ መድረሻ” ፥ የአቶ ገብሩ ዐሥራት እና ሊነበብ የሚገባው አነጋጋሪ መጽሐፋቸው appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>