ግርማ ካሳ
Muziky68@yahoo.com
ሐምሌ 11 ቀን 2005 ዓ.ም
ሐምሌ 7 ቀን ደሴና ጎንደር የኢትዮጵያዉያንን ትኩረት ስበውት ነበር። በነዚህ ከተሞች የአንድነት ፓርቲ በጠራዉ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በሺሆች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን፣ በአገዛዙ ካድሬዎች የደረሰባቸዉን ጫናና ማስፈራሪያ ወደ ጎን በማድረግ፣ የሰላም፣ የዴሞክራሲ የነጻነት ጥያቄዎቻቸውን አሰምተዋል። «አምባገነንነት፣ ጭቆና፣ ዘረኝነት በቃን» ብሎ ሕዝቡ እንደተነሳ፣ በገልጽ የተያበት ሁኔታ ነዉ የነበረዉ። የኢትዮጵያዊ ጨዋነት መንፈስ በገሃድ የተንጸባረቀበት ቀን ነበር።
ሐምሌ 14 ቀን ትኩረቱ መቀሌ ይሆናል። ከአንድነት ፓርቲ ጋር በቅርበት የሚሰራዉ፣ በአቶ ገብሩ አስራት የሚመራው፣ አረና ትግራይ ለሉዓላዊነት ወይንም በአጭሩ አረና፣ በመቀሌ ማዘጋጃ ቤት ታላቅ ሕዝባዊ ስብሰባ ጠርቷል። መቀሌ – የጀግናዉ አጼ ዮሐንስ ከተማ!!!!!
አረናዎች በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ጠንካራ አቋም ያላቸው፣ የሕወሃት/ኢሕአደግ በዘር የመከፋፈል ፖለቲካን የሚቃወሙ፣ በትግራይ ዉስጥ ጠንካራ ሰላማዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ታጋዮች ናቸው።
ከአቶ መለስ ዜናዊ ሕልፈት በኋላ ሕወሃቶች የአረና አመራሮችን ወደ ሕወሃት እንዲመለሱ ጥሪ እንዳቀረቡላቸው ፣ ነገር ግን «ጠባችን እኮ ከመለስ ጋር አልነበረም፤ ግን ሕወሃት ከሚያራምዳቸዉ ፖሊሶዎች ጋር ነዉ እንጂ» የሚል ምላሽ በመስጠት፣ ጥያቄዎቹን አረናዎች ውድቅ እንዳደረጉ ከታመነ ምንጭ መረጃ ደርሶኛል።
አረናዎች፣ መድረክ በተባለዉ ስብስብ ዉስጥ በመስራት፣ መድረኩ ወደ ዉህደት እንዲመጣ ትልቅ ጥረት ያደረጉ ናቸው። በትግራይ ያሉ የአንድነት አባላትና አስተባባሪዎች፣ ከአራና ወገኖቻቸው ጋር፣ አንድ ጽ/ቤት እየተጋሩ፣ በጣም በተቀራረበ መልኩ እንደሚሰሩ ነዉ የምንሰማዉ። ከዚህም የተነሳ፣ አንድነትና አረና ይዋሃዳሉ የሚል ግምት ያላቸው ወገኖችም አሉ።
የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያን የሚወድ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት መስዋእትነት የከፈለ ጀግና ሕዝብ ነዉ። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም፣ በአንድ ጽሁፋቸው፣ ስለትግራይ ሕዝብ የጻፉትን ላዉጋችሁ። ሕወሃት/ኢሕአዴግ ስልጣን እንደጨበጠ ነበር። በመቀሌ የሕወሃትን ባንዲራ እንጂ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ አላማን ማውለብለብ አይቻልም ነበር። «አንድ መቀሌ ሄዶ የመጣ፣ አንድ የኔ ተማሪ የታዘበዉን ልንገራችሁ» ሲሉ ነዉ ፕሮፌሰር መስፍን የጻፉት። በየቤቱ ሰዉ በትንሹ፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ሰቅሏል። «በዉጭ ብንከለከልም፣ በቤታችን ግን እንሰቅላለን» ነበር ሕዝቡ የሚለው።
አዎ፣ ለሕወሃት/ኢሕአዴጎች ኢትዮጵያዊነት ቢናቅም፣ ኢትዮጵያን ባህር አልባ ማድረግ ቀላል ቢሆንም፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ እንደ ተራ ጨርቅ ቢቆጠረም፣ ለትግራይ ሕዝብ ግን ኢትዮጵያዊነቱ በልቡ የተቀረጸ ማንነቱ ነዉ። በሰርግ፣ በቀብር ስነ ስርዓት በገጠሪቷ ትግራይ ሁሉ ሳይቀር የኢትዮጵያ ባንዲራ ነዉ። ኢትዮጵያን በተመለከተ የትግራይ ሕዝብ ቀዳሚ እንጂ ደጀን ሆኖ አያውቅም። አይሆንንም። ኢትዮጵያዊነትን ያኔም ሕወሃት ሊያጠፋው አልቻለም። አሁንም ደግሞ አያጠፋዉምም።
ከትግራይ የሚደርሱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሕዝቡ በሕወሃት አገዛዝ የተማረረ ይመስላል። ለዉጥ ይፈልጋል። አማራጭ ይፈልጋል። የሕዝቡን ጥያቄ በማዳመጥ፣ አረና ትግራይና አንድነት አማራጭ ሆነው ቀርበዋል። ለዚህም ነዉ በገዢው ፓርቲና በነርሱ መካከል ያሉትን የጎላ ልዩነቶች ለማሳየት፣ ሐምሌ 14 ቀን በሚደረገዉ ታላቅ ሕዝባዊ ስብሰባ ሕዝቡ እንዲገኝ ቅስቀሳ እየተደረገ ያለዉ።
መቀሌም እንደ ደሴና ጎንደር፣ እንደገና የዲሞክራሲና የፍህት ደዉልን ትደዉላለች። እንደገና የትግራይ ሕዝብ በመቀሌ ማዘጋጃ ቤት ኢትዮጵያዊነቱን ያወጃል። እንደገና ታሪክ ይሰራል።
አንድ ብዙ ጊዜ የማስታወሰው አቶ ገብሩ አስራት የተናገሩትን አንድ አባባል ልጥቀስ። ከጥቂት አመታት በፊት ነዉ፣ አራና እንደ አሁኑ፣ ሕዝባዊ ስብሰባ ጠርቶ ነበር። ብዙ ሕዝብ ይሰበሰባል። የጥያቄና መልስ ወቅት አንዱ ይነሳና «እንዴት ከትግሬ ጠላቶች ጋር አብረህ ትሰራለህ? » የሚል ጥያቄ ይጠይቃል። ትግሬ፣ ኦሮሞ ፣ ከንባታ … እያሉ፣ ሰውን በዘር የሚለዩ፣ በአይምሮ የታመሙ፣ ብዙ ጠባቦችና ጎጠኞች መቼም በየቦታዉ አይጠፉም።
አቶ ገብሩ አስደናቂ መልስ መለሱ። «ማን ነዉ ትግራይን ለትግሬዉ ብቻ የሰጠዉ? ትግራይ የአማራዉም የኦሮሞውም ናት። የአማራ ክልል የትግሬዉ፣ የጉራጌው የኦሮሞው ነዉ። ኦሮሚያ የሶማሌ የአማራም የትግሬም ነዉ ….ማንም ኢትዮጵያ የማንም ጠላት አይደልም» ነበር ያሉት። ይሄ ነዉ እንግዲህ የሰለጠነው፣ የወንድማማችነትና የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ።
አረናም ሆነ አንድነት፣ «ሁሉም ኢትዮያጵያዊ በሁሉ የአገሪቷ ግዛት የመኖር፣ የመስራት፣ የመነገድ፣ የመምረጥ፣ የመመረጥ መብት አለው» ብለው ያምናሉ። አረናም ሆነ አንድነት «ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር እንዲኖራት መደረግ አለበት» ብለዉ ያማናሉ። አረናም ሆነ አንድነት ለሰላም፣ ለዲሞክራሲ፣ ለፍትህ፣ ለሕግ የበላይነት ይታገላሉ። አረናም ሆነ አንድነት የታሰሩ የሕሊና እስረኞች ሁሉ እንዲፈቱ፣ ሕዝቡን እያሸበረ ያለው የጸረ-ሽብርተኝነት ሕግ ተሽሮ ወይም ተሻሽሎ ዜጎችን በአገራቸው በነጻነት ቀና ብለዉ እንዲኖሩ ይታገላሉ።
እንግዲህ አስቡት ወገኖቼ፣ የምርጫ ወቅት አይደለም። ነገር ግን በአዲስ አበባ የተጀመረውን እንቅስቃሴን ተከትሎ በደሴና በጎንደር ሕዝቡ ድምጹን አሰምቷል። ወደፊትም ያሰማል። የፊታችን እሁድ ደግሞ በመቀሌ አረና በጠራዉ ስብሰባ የዲሞክራሲ ችቦ ይበራል። ከአስራ አምስት ቀናት በኋላ ደግሞ፣ ሐምሌ 28፣ እንደገና በመቀሌ፣ እንዲሁም በወላይታ ሶዶ የአንድነት ፓርቲ ሕዝቡን ይሰበስባል። በዚያኑ ቀንም በጂንካ፣ አርባ ምንጭና ባህር ዳር ሰላማዊ ሰልፎች ይደረጋሉ። ብዙ ሥራ እየተሰራ ነዉ። መስዋእትነት እየተከፈለ ነዉ።
እንግዲህ ኢትዮጵያዉያን በሁሉም መስክ፣ ድጋፋችንን ለአረና ሆነ አገር ቤት ለሚታገሉ ወገኖች ልንሰጥ ይገባል። በከፍተኛ ወከባ፣ በመቀሌ ጠንካራ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ከሚያደረጉት የአረና ወገኖቻችን ጎን እንቁም። በዚያ ያሉ ዘመድ ጓደኞቻችን ወደ ስብሰባው እንዲሄዱ እናበረታታ። በምንችለው መልኩ ትግሉን እንቀላቀል። ይሄ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም። ጉዳዩ የሰብአዊነትና የኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ነዉ።