ከቦጋለ አበበ
በአጭር ርቀት ስመ ገናና የሆኑት አሜሪካዊው ታይሰን ጌይ እና ጃማይካዊው አሳፋ ፖል ሰሞኑን ባደረጉት ምርመራ አበረታች መድኃኒት ተጠቃሚ መሆናቸው እንደተረጋገጠ ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የምንጊዜም የመቶ ሜትር ሁለተኛው ፈጣን አትሌት የሆነው ጌይ አበረታች መድኃኒት እንደተጠቀመ ይፋ ያደረገው የአሜሪካ ፀረ-አበረታች መድኃኒት ኤጀንሲ ነው፡፡ ተቋሙ ባለፈው ዓርብ ይፋ እንዳደረገው የሰላሳ ዓመቱ ጌይ ባለፈው ግንቦት ከውድድር ውጪ ባደረገው ምርመራ አበረታች መድኃኒት ተጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
አራተኛው የዓለምአችን ፈጣን አትሌት ፖል ደግሞ ባለፈው ሰኔ በተካሄደው የጃማይካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ አበረታች መድኃኒት መጠቀሙ ተደርሶበታል፡፡ በዚህም ቅጣት ይጠብቀዋል ተብሎ እንደሚገመት ዘገባው ያስረዳል፡፡
ባለፈው የለንደን ኦሊምፒክ የአራት በአራት መቶ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ የሆነው ጃማይካዊው ሺሮን ሲምሰን ከፖል ጋር ተመሳሳይ የሆነ አበረታች መድኃኒት ተጠቅሟል መባሉ ይታወሳል፡፡ ይህም በጃማይካ አትሌቶች ላይ ጣት እንዲቀሰርባቸው አድርጓል፡፡
ፖል በአሁኑ ወቅት የአገሩ ልጅ ዩሴን ቦልት የመቶ ሜትርን ክብረወሰን ከመጨበጡ በፊት የርቀቱ ንጉስና አገሩን በቤጂንግ ኦሊምፒክ የአራት መቶ ሜትር አሸናፊ እንድትሆን ያስቻለ አትሌት ነው፡፡
ፖል እና ጌይ አበረታች መድኃኒት ተጠቃሚ ሆነው መገኘታቸው የስፖርት ቤተሰቡን ያስደነገጠ ክስተት ሆኗል፡፡ የስፖርቱ ባለሞያዎችም በሁለቱ አትሌቶች ላይ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አስተያየት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
የቢቢሲው የአትሌቲክስ ተንታኝ ኮሊን ጃክሰን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከሰነዘሩ አንዱ ነው፡፡ ፖልና ጌይ ታላላቅ አትሌቶች መሆናቸውን በመግለፅ አስተያየቱን የጀመረው ኮሊን ሁለቱ አትሌቶች በስፖርቱ ውስጥ የማይሽር ጠባሳ ጥለዋል ብሏል፡፡
«አበረታች መድኃኒት የተገኘባቸውን አትሌቶች ይቅርታ ልናደርግላቸው አይገባም፣ እነዚህ አትሌቶች ላይ ከባድ ቅጣት መጣል ስፖርቱን ሊጎዳው ይችል ይሆናል፣ ይሁን እንጂ ለስፖርቱ መልካም ገፅታ ስንል ጉዳዩን ችላ ልንል አንችልም፣ መጪውን ትውልድ ማስተማር የምንችለውም በዚህ መንገድ ነው» በማለትም ኮሊንስ አስተያየት ሰጥቷል፡፡
ፖል በዘንድሮው ዓመት መቶ ሜትሩን በ9፡88 ቢሮጥም ጃማይካን ወክሎ ከወር በኋላ በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ አይሳተፍም፡፡ ፖል አበረታች መድኃኒት ተጠቃሚ እንደሆነ ከተረጋገጠ በኋላ በሰጠው አስተያየት፤ መድኃኒቱን ሆን ብሎ እንዳልተጠቀመ አስረድቷል፡፡
«ለቤተሰቦቼ፣ ጓደኞቼና በዓለም ላይ ላሉ ደጋፊዎቼ መናገር የምፈልገው አበረታች የተባለውን ንጥረነገር ሆን ብዬ ወይንም አውቄ እንዳልተጠቀምኩኝ ነው፣ ያልተፈቀደ ነገር እንዳላደረኩም እርግጠኛ ሆኜ መናገር እችላለሁ» በማለት ፖል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ2007 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመቶ፣ ሁለት መቶና አራት በአራት መቶ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ የሆነው ጌይ አበረታች ንጥረነገር ለመጠቀሙ ማስረጃ የሚሆን ሁለተኛውን የናሙና ምርመራ ውጤት እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡
ጌይ የመጀመሪያው የምርመራ ናሙና ላይ በተገኘበት አበረታች መድኃኒት ጉዳይ በሰጠው አስተያየት፤ አበረታች መድኃኒት በራሱ እጅ እንዳልተጠቀመና የሆነ ሰው ሆን ብሎ ሰጥቶት ሊሆን እንደሚችል አብራርቷል፡፡
«ከዚህ በፊት በእንደዚህ ዓይነት ጉዳይ ላይ ስሜ ተነስቶ አያውቅም፣ አበረታች መድኃኒት ተጠቅሜ አላውቅም የሆነ ሰው ግን በማላውቀው መንገድ እንድጠቀም አድርጎኝ ሊሆን ይችላል» በማለት ጌይ አስተያየቱን ለቢቢሲ ሰጥቷል፡፡
ጌይ ከሁለተኛው የናሙና ምርመራ ውጤት በኋላ የትኛውንም ቅጣት ለመቀበል ዝግጁ እንደሆነ በመናገር በሌላ ጊዜ ዳግም ወደ ውድድር እንደሚመለስ ያለውን ተስፋ ገልጿል፡፡
ጌይ በጉዳዩ ላይ የሰጠውን አስተያየት ተከትሎ ምርመራውን የሚያካሂደው ኤጀንሲ አትሌቱ በሰጠው መልካም አስተያየት እንደተደሰተ ገልፆ የሁለተኛውን የናሙና ምርመራ ውጤት ሕጋዊ በሆነ መልኩ በቅርቡ እንደሚያሳውቅ አረጋግጧል፡፡
ጌይ በመቶ ሜትር 9፡69፣ በሁለት መቶ ሜትር ደግሞ 19፡58 የሆነ የራሱ ምርጥ ሰዓት ያስመዘገበ አትሌት ነው፡፡ ጌይ ባለፈው የለንደን ኦሊምፒክ አራት በአራት መቶ ውድድር የብር ሜዳሊያ አሸናፊና በዓለም አሉ ከሚባሉ ታዋቂ አትሌቶች አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ፖል በመቶ ሜትር 9፡72፣ በሁለት መቶ ሜትር ደግሞ 19፡90 የሆነ ፈጣን ሰዓት ከማስመዝገቡ በተጨማሪ እ.ኤ.አ 2007 ላይ የአጭር ርቀት ክብረወሰኖችን በስሙ ማስመዝገብ የቻለ አትሌት ነው፡፡
ፖል በቤጂንግ ኦሊምፒክ የአራት መቶ ሜትር ዱላ ቅብብል የወርቅ ሜዳሊያ፣ እ.ኤ.አ በ2004ና 2008 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተመሳሳይ ርቀት የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል፡፡