Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ሰማያዊ ፓርቲ በወልዲያ እና በሆሳዕና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን አደረገ

$
0
0

ሰማያዊ ፓርቲ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተሳኩ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ማድረጉን አስተባባሪዎቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ ፓርቲው ቅዳሜ መጋቢት 26/2007 ዓ.ም ከጠዋቱ 3 ሰዓት እስከ ቀኑ 7 ሰዓት በወልደያ ከተማ፣ እንዲሁም እሁድ መጋቢት 27/2007 ዓ.ም በሆሳና ከተማ ከ7 ሰዓት እስከ 10 ሰዓት ተኩል ህዝባዊ ስብሰባዎችን በማድረግ አማራጩን ለህዝብ እንዳቀረበ የስብሰባዎቹ አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
semayawi party
ወልደያ ከተማ ላይ ለተካሄደው ህዝባዊ ስብሰባ ዝግጅት ወቅት የገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና ፖሊስ ከፍተኛ ጫና እንዳደረገባቸው የገለጹት የፓርቲው የፋይናንስ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ወረታው ዋሴ በቅስቀሳ ወቅት ፖሊሶች ‹‹ቅስቀሳ በይፋ መፈቀዱን የምናውቀው ነገር የለም›› በሚል በቅስቀሳ ላይ የተሳተፉትን አባላት በማወከብ እንቅፋት እንደፈጠሩባቸው ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የከተማውን ከንቲባ ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናት ሰማያዊ ስብሰባ ያደረገበት አዳራሽ በር ድረስ በመምጣት ወደ ስብሰባው የሚገባውን ህዝብ ለማሸማቀቅ እንደሞከሩ ገልጸውልናል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ስብሰባውን እንዳያደርግ ከገዥው ፓርቲ ካድሬዎች የተፈፀመበትን ወከባና እንቅፋት ለምርጫ ቦርድ ቢያሳውቅም የምርጫ ቦርድ ተወካዮች ምንም ማድረግ እንዳልቻሉ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ይህም ሆኖ ሰማያዊ ፓርቲ ከ250 በላይ ህዝብ የተገኘበት ስኬታማ ህዝባዊ ስብሰባ እንዳደረገ አቶ ወረታው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ሰማያዊ ፓርቲ እሁድ መጋቢት 28/2007 በሀድያ ዞን ሆሳና ከተማ ጎፈር ሜዳ ላይ የአደባባይ ደማቅ ህዝባዊ ስብሰባ እንዳደረገ የሰማያዊ ፓርቲ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ተሰማ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ምንም እንኳ የገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና ፖሊስ በቅስቀሳ ወቅት አባላትን በማሰር፣ የመኪና ቅስቀሳዎችን በማደናቀፍ እንቅፋት ለመፍጠር ቢሞክሩም የሆሳና የሰማያዊ ፓርቲ ቅርንጫፍ ባደረገው ጥረት ከ500 በላይ ህዝብ የተገኘበት ስኬታማና ደማቅ ህዝባዊ የአደባባይ ስብብሰባ አድርገናል›› ሲሉ አቶ ሰለሞን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
ህዝባዊ ስብሰባዎቹ የሰማያዊ ፓርቲን የምርጫ ቅስቀሳ አካልና አማራጩን ለህዝብ ያስተዋወቀበት እንደሆኑ የገለጹት ኃላፊዎቹ በገዥው ፓርቲ በኩል ህገ ወጥ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሆነና እነዚህ ህገ ወጥ ተግባራት መቆም እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹አስፈጻሚው ኃይል ለህገ ተገዥ አይደለም፡፡ በማናለብኝነት የመምረጥና አማራጭ የማቅረብ መብት እየተደፈጠጡ ነው›› ያሉት አቶ ወረታው ዋሴ አሁንም ሰማያዊ ፓርቲ ገዥው ፓርቲ ለህግ ተገዥ እንዲሆን የበኩሉን ጫና እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

አቶ ሰለሞን በበኩላቸው ‹‹አፈናውን ተቋቁመን ህዝቡ ሰማያዊ ጎን እንደቆመ ለማሳየት ችለናል፡፡ ህዝቡ በገንዘብ፣ በሞራልም ከሰማያዊ ፓርቲ ጎን እንደሚቆም አሳይቶናል፡፡ እኛም ዜጎች ያለ መድሎ የሚኖሩበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንደምንመሰርት ቃል የገባንበት ነው›› ብለዋል፡፡

The post ሰማያዊ ፓርቲ በወልዲያ እና በሆሳዕና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን አደረገ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles