Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

በዚህ ሳምንት የተማርናቸው አምስት ነገሮች

$
0
0

ከ7 ኪሎ መጽሔት

1ኛ) ፖለቲካ ለብዙሃን “ውስጡን ለቄስ ነው”
ከሰባት ዓመታት በፊት የቅንጅት እስረኛ የነበሩት አቶ አንተነህ ሙሉጌታ “የሁለት ዓለም ሰዎች” በሚል ርእስ የኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞችን የሚመለከቱ የፍርድ ቤት ድራማዎች ላይ ያነጣጠረ መጽሐፍ ጽፈው ነበር። መጽሐፉን ያነበበ በዚህ ሳምንት በዞን ዘጠኝ ጦማርያን እና ጋዜጠኞች የፍርድ ሂደት ላይ የታየው ትዕይንት አይገርመውም። ችሎታ የሌላቸው አቃቤ ሕጎች፣ የመንግሥት ታዛዥ ዳኞች፣ ግራ የተጋቡ እና ያልተዘጋጁ የአቃቤ ሕግ ምስክሮች ላለፉት ኻያ ሦስት ዓመታት የፖለቲካ ችሎቶች ቋሚ ንብረቶች ኾነው ቆይተዋል። ታዲያ ከእነዚህ የፍርድ ቤት ሂደቶች ጋራ ተያይዞ በተደጋጋሚ የሚነሳው ጥያቄ “መንግሥት ራሱን በዚህ ደረጃ ከሚያዋርድ፤ እንዲሁም የማይረባ አማተር የደረሰው እና ያዘጋጀው የሚመስለውን ቴአትር ትቶ፤ ለምን ማሰር የሚፈልጋቸውን ያለ ፍርድ ቤት ሂደት ዘብጥያ አውርዶ አይገላገልም?” የሚል ነው። ጥያቄው ከሕጸጽ (fallacy) የመነጨ ነው። ይህ ሕጸጽ በእንግሊዝኛ ኢ-መደበኛ ስሙ Ubiquitous Political Junkie Fallacy ይባላል። ሕጸጹ አብዛኛውን ሰው የፖለቲካ ሱሰኛ አድርጎ የማየት አባዜ ነው። የዚህ ሐሳብ ተጠቂዎች በአብዛኛው ፖለቲካን በቅርቡ የሚከታተሉ አክቲቪስቶችና ጋዜጠኞች ናቸው።

እንደዚህ ዐይነት ግለሰቦች ሌሎች ሰዎች ልክ እንደ እነርሱ ፖለቲካን ቀን ከሌት የሚያመነዥኩ ይመስላቸዋል፤ ሐቁ ግን ከዚህ የተለየ ነው። የማሕበራዊ ሳይንስ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አብዛኞቻችን ፖለቲካን በቅጡ አንከታተልም፤ ከተከታተልንም ላይ ላዩን ነው። አምባገነን መንግሥታት ይህን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ፖለቲካን ከላይ ከላይ ለሚከታተሉ ብዙሃን ማሳየት የሚፈልጉት መንግሥታቱ ሥርዐት እና ሂደት የሚያከብሩ፤ ውሳኔዎቻቸውን በመደበኛ ተቋማት የሚያስወስኑ እና በዘፈቀደ የማይመሩ መኾናቸውን ነው። ይህን ለማሳየት ማስመሰል ይበቃቸዋል። ሥርዐት እንዳለ ማስመሰል የዐይነተኝት መንፈስ (aura of legitimacy) ያላብሳቸዋል። የፍርድ ቤት ትዕይነቱ በጥልቅ ሲመረመር ለመንግሥት አሳፋሪ ነው። ይኹንና ይህን ጥልቅ ምርመራ የሚያደርጉ ጥቂቶች ናቸው። የእነርሱ ድምጽ ብዙሃኑ ጋር የሚደርስበት መንገድ ከተዘጋ ንጉሡ ራቁቱን ቢኾን እንኳ ልብስ እንደለበሰ እያስመሰለ መቆየት ይቻለዋል።
Nile Countries
2ኛ) አቴናዊው ቱስይዲዴስ በአባይ ጉዳይ ልክ ነው
እ.እ.ኤ ከ460 እስከ 395 ዓ.ዓ የኖረው አቴናዊው የፖለቲካ ፈላስፋና ጄነራል ቱስይዲዴስ የጌም ቲዎሪ አባት ተደርጎ ይወሰዳል። ከቱስይዲዴስ ታላላቅ ሐሳቦች መካከል አንዱ የሐይል ልዩነትን አንጻራዊነት የሚያትት ነው። ጊዜና አውድን በሚገባ የሚያጤን እና የሚጠቀም ደካማ ባለጋራ በረዥም ጊዜ በብልሃት ጠንካራ ባላጋራን ሊገዳደር ይችላል። የአባይ ፖለቲካ ለዚህ ተምሳሌት ነው። የግብጽንና የኢትዮጵያን ፍጹማዊ ሐይል በግልጽ መለኪያዎች ብንገመግም ልዩነቱ በጣም ሰፊ ነው። ይህ ልዩነትም በአባይ ፖለቲካ ጉዳይ ላይ ለረዥም ጊዜ ሲንጸባረቅ ቆይቷል። እ.ኤ.አ. በ1959 ግብጽ ኢትዮጵያን ወደ ጎን አድርጋ ከሱዳን ጋር አባይን ለሁለት ለመጠቀም ስትስማማ ኢትዮጵያ ስምምነቱን አጥብቃ ብትቃወምም ከጩኸት አልፋ ጠጠር ልትገፋ አልተቻላትም። ዐፄ ሐይለሥላሴና ደርግ ግድብ ለመገንባት ቢነሱ ግብጽ የተለያዩ መንገዶችን (እርዳታ ማስከልከል፣ አማጽያንን መርዳት ወዘተ) ተጠቅማ ፈቅ እንኳ ሳይሉ እንዲያቆሙ አድርጋቸዋለች።

እ.ኤ.አ. በ2011 በግብፅ የሕዝብ አመጽ ተቀስቅሶ የመንግሥት አለመረጋጋት ማስከተሉ ለኢትዮጵያ ያልታሰበ ዕድል ፈጠረላት። ብርታኒያዊው አድሚራል ዊልያም ሄልሲ ለደካሞች እንዲህ ዐይነት ዕድል ሲፈጠር “strike fast, strike hard” ሲሉ እንደመከሩት ኢትዮጵያ ዕድሉን ለመጠቀም በፍጥነት ተንቀሳቀሰች፤ የግድቡ ግንባታ ተጀመረ፤ የአባይ ተፋሰስ አገሮችን ከግብጽ በተቃራኒ ማስተባበር ቀጠለ። በውስጥ ችግር ተወጥሮ ያልተረጋጋው የግብጽ መንግሥት ለዚህ እንቅስቃሴ ፈጣን አጸፋ ለመስጠት የሚያስችል ትንፋሽ አልነበረውም። ጀነራል ሲሲ ሥልጣን ላይ ወጥተው መንግሥትን ሲያረጋጉ ደግሞ መሬት ላይ ያሉት ኹኔታዎች ተቀይረዋል። ለ2014 ኹኔታዎች እንጂ ለ2010 ኹኔታዎች መልስ መስጠት እንደማይቻላቸው አውቀው ወደ ድርድር መጡ። የድርድሩ ውጤት የኾነው የፖለቲካ ስምምነት ግብጽ ሳታወላውልና ሳታመነታ ስትከላከለው የነበረውን የ1959 ኪዳን በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ጥያቄ ውስጥ ከቶታል። 2010 ላይ ኾነን ከአምስት ዓመት በሁዋላ ኢትዮጵያ እና ግብጽ የ1959ን ስምምነት አደጋ ላይ የሚጥል የፖለቲካ ውል ይገባሉ ተብሎ ቢነገረን ለማመን እንቸገር ነበር። የቱስይዲዴስን ነፍስ ይማር።
ali birra
3ኛ) ዐሊ ቢራ ብረት ነው
ለፖለቲካ ዘፋኞች ክብርና ተምሳሌትነትን እንደተጎናጸፉ ዘመንን መሻገር እጅግ አስቸጋሪ ነው። መጠነኛ የሐሳብ ለውጥ ካሳዩ ወይም ያሳዩ ከመሰሉ አድናቂዎቻቸው በድንገት ይገለበጡባቸዋል። ፖለቲካ የጋለ ስሜት የሚቀሰቅስ ጉዳይ በመኾኑ ከቀድሞ ተከታዮቻቸው የሚደርስባቸው ነቀፌታ ምሬት ያዘለ ነው። አንዳንዴ አደጋው የሚመነጨው ሐሳብን ከመቀየር ብቻ ሳይኾን ካለመቀየርም ነው። ዘመን ሲቀየርና ደጋፊዎቻቸው ሐሳባቸውን ሲለውጡ የፖለቲካ ዘፋኞች የቀድሞ አቋማቸውን ይዘው የሚቀጥሉ ከኾነ ዕጣ ፈንታቸው በሐሳብ ለውጥ ችግር ውስጥ ከሚገቡቱ የተለየ አይደለም። ተጠንቅቆ መጓዝም ዕድሜን በመጠኑ ያራዝም እንደኾን እንጂ ዘመን አያሻግርም። ዝናቸውንና ክብራቸውን ጠብቀው ዘመን የሚሻገሩ የፖለቲካ ዘፋኞች በአብዛኛው አጠቃላይ እና ዕቡይ በኾኑ ሐሳቦች ላይ የሚያተኩሩቱ እንጂ መሬት የሚነካ ጭብጥ የሚያነሱቱ አይደሉም። መዝፈን የጀመረበት ኢዮቤልዩ እየተከበረለት ያለው ታላቁ ዐሊ ቢራ የኦሮሞ ብሔርተኝነትን እና ጸረ ጭቆናን ያነገቡ መሬት የወረዱ ዘፈኖችን በማቀንቀን ይታወቃል። ሃምሳኛ ዓመቱን እያከበሩ ያሉት በተለያዩ ተቀናቃኝ ድርጅቶችና ጎራዎች ውስጥ የተሰለፉ እና ያልተሰለፉ ኦሮሞዎች ናቸው። የኦፕራይዱ ጸሐፊ መሐመድ አዴሞ እንዳስቀመጠው “ብሔራዊ ተምሳሌት፣ ጀግና፣ ፈር ቀዳጅ፣ የኦሮሞ ሙዚቃ ንጉስ” እያሉ የሚያንቆለጳጵሱት የአንድ ወይም የጥቂት የፖለቲካ ቡድን/ቡድኖች አባላት ብቻ ሳይኾኑ በፖለቲካዊ አቋማቸው እዚያና እዚህ የቆሙት ጭምር ናቸው። የኦሮሞ ብሔርተኛ ፖለቲካ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በነውጥና በውዝግብ ውስጥ እያለፈ ነው። ዐሊ በዚህ ታሪክ ውስጥ ቢያልፍም የተጎናጸፈው ሕየንተ ክብር ሳይፈርስ ለወርቅ ኢዮቤልዩ መብቃቱ ከድንቆች ያስመድበዋል።
bob geldof ethiopia
4ኛ) ቦብ ጌልዶፍ በጎ አድራጎትና ኢንቨስትመንትን እያምታታ አስቸግሯል

አየርላንዳዊው አቀንቃኝ ቦብ ጌልዶፍና ኢትዮጵያ የጋብቻ ቀለበት ካሰሩ ድፍን ሰላሳ ዓመት ሞልቷል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ጋብቻው የተመሠረተው በጌልዶፍ ደግ ሳምራዊነት ላይ ነበር። አሁን ግን ጌልዶፍ በኢትዮጵያ ስም ርዳታ መሰብሰብ እና ርዳታ ሰጪዎችን ሎቢ ማድረግ ትቶ ምዕራባውያን ባለ ሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ ሄደው ኢንቨስት እንዲያደርጉ መወትወት ጀምሯል። በዚህ ሳምንት በተለያዩ ዓለማቀፍ ሚዲያዎች ቀርቦ ሐሳቡን አስረድቷል። ነገር ግን ጌልዶፍ “ኢትዮጵያ ሄዳችሁ ኢንቨስት አድርጉ” ሲል ፈላስፋውና ኢኮኖሚስቱ አዳም ስሚዝ ባስቀመጠው የኢንቨስትመንት ጽንሰ ሐሳብ መንፈስ አይደለም። ስሚዝ እንደሚለው ኢንቨስትመንት ኢንቨስተሩ ለራሱ ጥቅም ሲል የሚገባባት ከግል ፍላጎት (private interest) የሕዝብ ጥቅም (public virtue) የሚገኝበት ነው። ጌልዶፍ የሚቀሰቅሰው ግን እንዲህ ሲል ነው። “ትኩረት ሳትሰጣቸው ቀርተህ በርካቶች መሞት የለባቸውም፤ አፍሪካ ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ ሊያስገኝ የሚችለው ጥቅም ሌላ ቦታ ከሚገኘው የላቀ ነው።” ይህ ሐሳብ ኢንቨስትመንትንና ደግ ሳምራዊነትን የሚቀላቅል ነው። ‘ድመት መንኩሳ ዐመሏን አትረሳ” ብለን እንለፈው።

abay Tsehaye
5ኛ) የቃላት ዕብሪተኝነት ያለመረጋጋት ውጤት ነው

ውስጣዊ ጽናት የማጣት (insecurity) ስሜት ችግር ያለባቸው መሪዎችና ፖለቲከኞች ችግራቸውን ለመሸፈን ከሚጠቀሙባቸው ማካካሻ ጠባያት መካከል አንዱ የቃላት ዕብሪተኝት እንደኾነ ሳይኮሎጂስቶች ይነግሩናል። ሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር፤ በመግለጫቸው ሲደነፉና ዕብሪት የተቀላቀላበቸውን ቃላቶች በተደጋጋሚ ሲጠቀሙ አስተውለናል። እነዚህንም መልሶች የሰጡት መፈናፈኛ ለሚያሳጡ ብቻ ሳይኾን ለገራገር የማብራርያ ጥያቄዎችም ነበር። ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እንዲህ ዐይነት መረን የለቀቀ ዛቻና ስድብ መጠቀም፣ ማንጓጠጥ እና ንቀት መደርደር ያልተለመደ አይደለም። አቶ መለስ ዜናዊ በዚህ የተካኑ ነበሩ። ሬድዋን ሁሴን፣ አባይ ጸሐዬ፣ ሽመልስ ከማልና በረከት ስምዖን ካላሽሟጠጡና ካልዛቱ የቦተለኩ አይመስላቸውም። ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ 24 ዓመት ኾኖታል። በእነዚህ ዓመታት ከ1997 በስተቀር በትረ ሥልጣኑን የሚነቀንቅ ከውጪ የመጣ ጠንካራ ግፊትና ጥቃት አልደረሰበትም። እንደብዙ የአንድ ፓርቲ አምባገነኖች የኢሕአዴግ መንግሥትም የተረጋጋ ረዥም ዕድሜ አሳልፏል። ነገር ግን የባልሥልጣነቱ የማይለወጥ ዕብሪተኝነት በስጋትና ባለመጽናት ስሜት እንደተዘፈቁ ጠቋሚ ነው። ናሲም ታሌብ የተባሉ ምሁር በአምባገነን ሥርዐቶች ዝግ መኾን ምክንያት የሚፈጠሩ የኢንፎርሜሽን ችግሮች (information problems) ተጠቂዎች ተገዢዎች ብቻ ሳይኾኑ የአገዛዙ መሥራችና አንቀሳቃሾችም ጭምር እንደኾኑ ያስረዱናል። እንደ ምሑሩ ከኾነ አምባገነኖች ስለ ራሳቸው ያላቸው እውቀት ከምናስበው በታች ደካማ ነው። የኢትዮጵያ ባለ ሥልጣናት የማያባራ የቃላት ዕብሪት ራስን ካለማወቅ የመነጨ አለመረጋጋት የፈጠረው ይኾን?

The post በዚህ ሳምንት የተማርናቸው አምስት ነገሮች appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>