Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የጊፍት ሪል እስቴት ጉዞ በስም ማጥፋት ዘመቻ ወደኋላ አይመለስም

$
0
0

ከጊፍት ግሩፕ ኩባንያ የህዝብ ግንኙነት መምሪያ

nlmqi6fn76e6fjt0pj5uይህ ጽሁፍ “ጊፍት ሪል እስቴት  ወደፊት ወይስ ወደኋላ” በሚል ርዕስ ‘አበበ ወርዶፋ’ በተባሉ ግለሰብ  ለተጻፈውና ጸሃፊው ‘ሪል እስቴቱ ጉዳት ያደረሰብኝ ደንበኛ ነኝ’ በሚል ሽፋን የኩባንያውን መልካም ስም ያለአግባብ ለመጉዳት በማሰብ እ.ኤ.አ ማርች  24 እና 25 ቀን 2015 ze-habesha.com እና satenaw.com ድረገጾች ላይ ለንባብ ላበቁት ሃተታ  የተሰጠ ምላሽ ነው።

ጸሃፊው በቂ ማስረጃ ሳይኖራቸው ግነት የተሞሉና ከሃቅ የራቁ መረጃዎችን በመደርደር በስሜት ብቻ ተነሳስተው ላቀረቡት ትችት መልስ ከመስጠት በፊት “ጊፍት ሪል እስቴት ማነው?” የሚለውን ጥያቄ መመለስ ተገቢ ይሆናል። ይህን ማድረግ የሚያስፈልገው በብዙዎች ዘንድ የታወቀ መልካም ስምና ዝና ያለውን ጊፍት ሪልእስቴትን እንደአዲስ ኩባንያ ለማስተዋወቅ ሳይሆን አንባቢ የሁለቱንም ወገን ጽሁፎች ሲያነብ በጉዳዩ ላይ ሙሉ ስዕል እንዲኖረው ማድረግ ተገቢ በመሆኑ ጭምር ነው።

በኢትዮጵያ የግል የሪል እስቴት ዘርፍ ለመሰማራት ቀዳሚ ከሆኑት ኩባንያዎች አንዱ ጊፍት ሪል እስቴት ነው፡፡ ጊፍት ሪል እስቴት ሲኤም ሲ እና ሃያት አካባቢ በተረከበው 16.3 ሄክታር መሬት ላይ በሶስት ፌዞች የተለያየ ዲዛይን ያላቸው ከ300 በላይ ዘመናዊ ቪላዎችንና ታውን ሃውሶችን እንዲሁም 44 ብሎክ         አፓርትመንቶችን በአጠቃላይ እስከ አንድ ሺህ የሚደርሱ አባወራዎችን መያዝ የሚችሉ መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ በተለያየ ደረጃ ለተጠቃሚዎች እያስተላለፈ ሲሆን አሁንም በመጠናቀቅ ላይ ያሉትን ጨምሮ አዳዲስ ግንባታዎችን በማካሄድ ላይ የሚገኝ ኩባንያ ነው።

ጊፍት ሪል እስቴት የሚያከናውነው የቤቶች ግንባታ ስራ ሰፊና በካፒታል ደረጃ ሲሰላም 2 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ኢንቨስትመንት ነው። በግንባታው ሂደት እስከ 2ሺህ የሚደርሱ በተለያየ የሙያ ደረጃ ላይ የተሰማሩ ሰራተኞችን በማሳተፍም ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር የቻለ ሃገርበቀል ኩባንያ ነው።

ጊፍት እንደ ቢዝነስ ግሩፕ ኩባንያ በሪል እስቴት ልማት ዘርፍ ላይ ለመሰማራት እቅድ ሲነድፍና ምክረሃሳቡን ለአዲስ አበባ አስተደደር አቅርቦ መሬት ሲረከብ ዓላማው ቢዝነሱን ማስፋት ብቻ አልነበረም።  ኩባንያው በመመስረቻ ሰነዱ ላይ ካስቀመጣቸው ተቀዳሚ አላማዎች (core objectives) ዋናው በሃገር ውስጥ እየኖሩ ደረጃውን የጠበቀ ምቹና ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ባለቤት መሆን ለሚፈልጉ እንዲሁም በውጭ ሃገራት እየኖሩ በሃገራቸው ውስጥ ማረፊያ የሚሆናቸውና ከሰለጠነው ዓለም ጋር ተመጣጣኝ ደረጃ ያለው መኖሪያ ቤት እንዲኖራቸው ለሚመኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ፍላጎታቸውን የሚያረካ አገልግሎት የሚሰጥ ሃገር በቀል ሪልእስቴት አልሚ መሆን ነው። ጊፍት ሪል እስቴት እስካሁን እያከናወነ ያለው ስራ ይህንኑ ዓላማ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ያተኮረ ነው።

ሪል እስቴቱ ግንባታ የሚያካሂድባቸው ሲኤምሲና ሃያት አካባቢዎች ለመኖሪያነት አንደኛ ደረጃ ተመራጭ  ከሆኑት የአዲስ አበባ አካባቢዎች በቀዳሚዎቹ ተርታ ላይ የሚገኙ መሆናቸውና የቦታውና የቤቶቹ ኢንቨስትመንት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መሄዱ በደንበኞች ዘንድ የጊፍትን ቤቶች ቀዳሚ ተመራጭ ሊያደርጓቸው ከቻሉት ምክንያቶች ዋናው ነው።ይህንን ሃቅ በሃገር ውስጥም ይሁን  በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኩባንያው ቤት የገነባላቸው ደንበኞች በተደጋጋሚ የሚናገሩት ነው።

ጊፍት ሪልእስቴትን በተመለከተ  እንደመረጃ ከላይ የሰፈሩትን ነጥቦች ካነሳን ከዚህ በመቀጠል  ጸሃፊው በሰነዘሯቸው ትችቶች ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ብቻ በማትኮር አንባቢ ሃቁን አገናዝቦ ይረዳ ዘንድ እውነታውን ለማሳየት እንሞክራለን።

ጸሃፊው የሪል እስቴቱ ደንበኛ አይደሉም

ጊፍት ሪል እስቴት ካሉት ከ300 የሚበልጡ ቤት የገዙት ደንበኞች ዝርዝር ውስጥ አበበ ወርዶፋ የሚባሉ ግለሰብ የሉም።ጸሃፊው ‘አበበ ወርዶፋ’ በሚል ስም የሪል እስቴቱ ደንበኛ እንደሆኑ በመግለጽ ሃተታ የመጻፋቸው ዋነኛ ዓላማ በአንባቢያን ዘንድ እምነት በማግኘት የስም ማጥፋት እቅዳቸው እንዲሳካ ከማድረግ የዘለለ አይሆንም። ሪል እስቴቱ ካልገለጸ በቀር አንባቢያን የኩባንያውን ደንበኞች ዝርዝር ለማወቅ አጋጣሚው እንደማይኖራቸው የሚገነዘቡት ጸሃፊው ይህንን ክፍተት በመጠቀም ራሳቸውን ጉዳት እንደደረሰበት ደንበኛ አድርገው ማቅረባቸው ትችታቸው በቀላሉ ተዓማኒነትን እንዲያገኝ መንገድ ይከፍታል። ነገር ግን ጸሃፊው አሳንሰው እንዳዩት ሳይሆን አንባቢ ይጠይቃል፣ያገናዝባል፤ይፈርዳልም።

በሌላ በኩል ጸሃፊው ጊፍት ሪልእስቴት ቤት የሚገነባላቸው ደንበኛ መሆናቸው እንዳይታወቅባቸው ሲሉ ወይም በራሳቸው የተለየ ምክንያት (መቼም ሪልእስቴቱ ለደህንነቴ ያሰጋኛል እንደማይሉ ተስፋ እናድርግና )  በብዕር ስም ተጠቅሜያለሁ ቢሉ እንኳን  ለሃቀኝነታቸው ጥቂት ማሳያዎችን ብቻ ማቅረብ ዳገት አይሆንባቸውም ነበር።

ለምሳሌ ከሪልእስቴቱ ገዝቻለሁ ያሉት መኖሪያ ቤት ጊፍት ከሚገነባቸው የተለያየ ዓይነትና ዋጋ ካላቸው ቤቶች ውስጥ የትኛው መሆኑ፣ለግንባታው ምን ያህል ዋጋ እንደከፈሉ ፣ቤቱ ከሶስቱ የጊፍት ሳይቶች የትኛው ሳይት ላይ እንደሚገኝና ከመሰል ተያያዠ መረጃዎች አንዱን እንኳን  ሳይገልጹ በደፈናው ‘ደንበኛ ነኝ’ ብለው ማለፋቸው ትችታቸው ገንቢ ሳይሆን አፍራሽ ዓላማ ያለው መሆኑን በግልጽ ያሳያል።ይህም በደንበኛ ስም አንባቢንና የጊፍትን ደንበኞች በማሳሳት ስም የማጥፋት አጀንዳ እንደያዙ ይመሰክራል። ይህን ሁሉ መረጃ መግለጽ አያስፈልገኝም ቢሉ እንኳን ኩባንያው ደንበኝነታቸውን ለማወቅና ያቀረቧቸውን ትችቶች ለመመዘን የሚችልበትን አንድም ተጨባጭ እውነት አለማስቀመጣቸው ግን ፍላጎታቸው መፍትሄ ማግኘት ሳይሆን ድርጅቱን በመልካም ዝናው የሚያውቁትን በውጭ ሃገራትና በሃገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለማሳሳትና የተዛባ ግንዛቤ እንዲይዙ የማድረግ ዓላማ ይዘው መነሳታቸውን ይመሰክራል።

 

የተዛቡና የሚጋጩ መረጃዎች

ይህንን እንዳለ ብንቀበለው እንኳን  የዛሬ 7ዓመት ከጊፍት ሪል እስቴት ቤት ገዝቻለሁ ያሉት እኚሁ ጸሃፊ “መቶ በመቶ ብትከፍሉ በፍጥነት ይደርስላችኋል ተብለን ስለነበር የቤቱን ዋጋ 100% ከፍያለሁ” ብለዋል። እውነቱ ግን የዛሬ 7 ዓመት 100% ከፍሎ ከሪል እስቴቱ ቤት የገዛ ደንበኛ የሌለ መሆኑ ነው። ከ 3 ዓመት ወዲህ ባሉት ጊዜያት ቅድሚያ 100% ክፍያ ከፍለው ቤት ለገዙ ደንበኞቹም ሪል እስቴቱ 6 በመቶ ቅናሽ አድርጎላቸው ቤታቸውንም ገንብቶ አጠናቆ አስረክቧቸዋል።

ጸሃፊው “ቤታችሁ በፍጥነት ይደርስላችኋል ተብለን 100% ከፈልን” ያሉትም ቢሆን ከእውነት የራቀ ነው።ሪልእስቴቱ ቅድሚያ ሙሉ ክፍያ ለሚፈጽሙ ደንበኞች  6% የዋጋ ቅናሽ ከማድረግ  ውጪ ቤታችሁን  ከ18 ወራት በታች በሆነ ጊዜ በፍጥነት ሰርቼ አስረክባለሁ የሚል ስምምነት ከየትኛውም ደንበኛ ጋር አልገባም። እኚህ ጸሃፊ በየትኛውም የጊፍት ደንበኛ እጅ ውስጥ የሚገኘውን ውል በማየት በቀላሉ መረጋገጥ ከሚችለው ከዚህ እውነት ተቃራኒ የሆነ ቃል እንደተገባላቸው በማስመሰል በተዛባና እርስ በርሱ በሚጋጭ መረጃ አንባቢን ለማሳሳት ሞክረዋል።

የጸሃፊው ሌላ ግድፈት የዛሬ 7 ዓመት 100% ከፍያ ፈጽመው ነገር ግን የቤታቸው ግንባታ መሰረት ከማውጣት አለማለፉን መግለጻቸው ነው። ጊፍት ሪል እስቴት ውል ገብቶ የቤታቸውን ግንባታ ከሚያከናውንላቸው ደንበኞች መካከል ብዙዎቹ ቤታቸውን በተለያየ የግንባታ ደረጃ ተረክበዋል። በቅርብ ጊዜ ከኩባንያው ቤት ለገዙ ደንበኞች እየተገነባ የሚገኘው መኖሪያ ቤት የደረሰበት ደረጃ የተለያየ ቢሆንም ቅሉ ጊፍት ሪልእስቴት በራሱ ወጪ ገንብቶ ሊሸጣቸው እየገነባቸው ከሚገኙ ቤቶች በቀር ደንበኛ ክፍያ ፈጽሞበት ሳይገነባ የቀረ አንድም ቤት የለም። በጽሁፉ ውስጥ  ይህንን ፍጹም የተጋነነና ከተዓማኒነት የራቀ ትችት ለማስፈር የተፈለገበትን ዓላማ የሚያውቁት ራሳቸው ጸሃፊው ብቻ ናቸው።

የባለቤትነት ማረጋገጫ ያለው ማን ጋር ነው!

ጸሃፊው በሃተታቸው ውስጥ “ጊፍት  ቤት ላስረከባቸው ህጋዊ ገዠዎች የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ ለመስጠት ፍቃደኛ አይደለም” የሚል ጭፍን ትችት አስፍረዋል።ከዚህ በተጨማሪም “የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ ሲጠየቅ የሚያመካኘው በመስተዳድሩ ላይ ነው” ብለዋል። ጸሃፊው በርግጥም የጊፍት ደንበኞችን አነጋግረው ከሆነ (እርሳቸው የጊፍት ደንበኛ ስላልሆኑ) የባለቤትነት ማረጋገጫ የመስጠት ሃላፊነት የማን እንደሆነና እስካሁን የዘገየውም በምን ምከንያት እንደሆነ በሚገባ ይገነዘቡ ነበር።

ጊፍት ለገነባቸውና ለደንበኞቹ ላስረከባቸው ቤቶች የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር እንዲሰጠው በአሰራሩ መሰረት የየካ ክፍለከተማንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽህፈት ቤቶችን በተደጋጋሚ ጊዜ ጠይቋል። በአፈጻጸሙ መዘግየት ሳቢያም እስከላይኛው የአስተደደሩ የስልጣን እርከን የደረሱ ተደጋጋሚ አቤቱታዎችን አቅርቧል። ድርጅቱ በክፍለከተማው በኩል የገጠመውን የአገልግሎት መዘግየት ችግር ለመፍታትና የጀመረውን የቤቶች ልማት በውሉ መሰረት አጠናቅቆ ለደንበኞቹ ለማስረከብ ያደረጋቸው ጥረቶች ተገቢ ባልሆኑ አሰራሮች ተጓተዋል። ይህንንም ለሚመለከታቸው አካላት አሳውቋል።ጊፍት ምን ያህል ጊዜ በጉዳዩ ላይ ከአስተዳደር አካላቱ ጋር ውይይት እንዳደረገ ከተጻጻፋቸው ደብዳቤዎች ጭምር ጉዳዩን መረዳት ለሚፈልግ አካል ማሳየት ይችላል።

ያም ሆኖ እስካሁን ኩባንያው ጉዳዩ ሲጓተትበት ቢቆይም በቅርቡ በተደረጉ ጥረቶች ግን ችግሩ እልባት ለማግኘት ወደሚችልበት መስመር ገብቷል።በአሁኑ ወቅት ከኩባንያውና ከክፍለከተማው የህግ ክፍል ጋር በመሆን  በጋራ የማጣራት ስራዎች እየተሰሩ ነው።ጊፍት ይህ ችግር በቅርብ ጊዜ አልባት እንደሚያገኝ ያምናል።

ጸሃፊው እንዳሉት ጊፍት ለደንበኞቹ ካርታ ባለመስጠት ተጠቃሚ አይደለም። በተቃራኒው በቅርቡ መፍትሄ የሚያገኝ ቢሆንም ካርታው ከላይ በተገለጹት ምክንያቶች በመዘግየቱ ምክንያት የተወሰኑ ቤታቸውን የተረከቡ ደንበኞች የመጨረሻውን ክፍያ እንዳይፈጽሙ እንቅፋት ሆኗል። በዚህም ኩባንያው  ከተወሰኑ ደንበኞች ገቢ መሰብሰብ አልቻለም። ይህም የኢንቨስትመንቱን ወጪ ሸፍኖ ስራውን ለማቀላጠፍ በገቢ አሰባሰብ ስርዓቱ ላይ ጫና አሳድሯል። በሌላ አነጋገር አስተዳደሩ  የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ አለመልቀቁ ለኩባንያውም ጉዳት ነው።

እውነቱ የህ ሆኖ ሳለ ጸሃፊው  ጊፍት የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተሩን በእጁ ይዞ ለደንበኞቹ መስጠት እንዳልፈለገ አስመስለው ተችተዋል። ዓላማቸው የኩባንያውን ስም ማጥፋት ባይሆን ኖሮ “ጊፍት የደንበኞቹን ካርታ መያዙ የራሱን ገቢ ከማስቀረት የዘለለ ምን ይጠቅመዋል?” የሚል ቀላል ጥያቄ በመጠየቅ ብቻ መልሱን ከራሳቸው ማግኘት ይችሉ ነበር።

የመንገዱ ጉዳይ

ጸሃፊው ወደጊፍት ሪልእስቴት ፌዝ ሁለት ሳይት የሚወስደው መንገድ አለመሰራቱን በተመለከተ ኩባንያውን ተጠያቂ ለማድረግ የግራውን ከቀኝ እያጋጩ ማስረጃ አልባ ክስ ዘርዝረዋል። እንደእውነቱ ከሆነ “ቤቴ መሰረቱ ብቻ ነው የወጣው” በሚል አቤቱታ ትችታቸውን የጀመሩት ግለሰብ ‘ወደቤቴ የሚወሰድ መንገድ አልተሰራልኝም’ የሚል ክስ መጨመራቸው ራሳቸውን በራሳቸው አቃርኗቸዋል።

ጊፍት አሁን ሙሉ በሙሉ ቤት ወደገነባበት ፌዝ ሁለት ሳይት የሚወስደው መንገድ በሪልእስቴት ፕላኑ ላይ በግልጽ ተለይቶ የተቀመጠና የተፈቀደ ነው። ነገር ግን በመንገዱ ላይ ጥቂት ነዋሪዎች በህገወጥ መንገድ ቤት የገነቡ በመሆኑ አስተዳደሩ ወይ ህገወጥ ግንባታውን እንዲያስነሳ ካልሆነም ተለዋጭ መንገድ እንዲያዘጋጅ ከበላይ አካላት ጭምር በደብዳቤ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል። እስካሁን ድረስ ግን ትዕዛዙን ተፈጻሚ አላደረገም። ይህም የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ባለስልጣናትን ጨምሮ የከተማ ስራ አመራርና ማኔጅመንት ኢኒስቲቲዩት ባለሙያዎች ጭምር ያጠኑትና ችግሩ የአስፈጻሚው አካል በመሆኑ ላይ መግባባት ላይ የተደረሰበት ፣በፍጥነት መስተካከል  እንደሚገባውውም ውሳኔ የተሰጠበት ጉዳይ ነው። ጊፍት በዚያ ሳይት ያሉትን ቤቶች ለደንበኞቹ ሙሉ በሙሉ አስረክቦ እስኪያጠናቅቅ የመንገዱ ጉዳይም እልባት እንደሚያገኝ ተስፋ ተሰጥቶታል።

ጸሃፊው ወደዚሁ ሳይት በጊዜያዊነት የሚገባበት መንገድ ኮብልስቶን ያልተነጠፈው ጊፍት መዋጮ ባለመክፈሉ ነው የሚል ትችት አስፍረዋል።አስተዳደሩ ወደሪልእስቴቱ የሚገባውን በማስተርፕላን ተለይቶ የተቀመጠ መንገድ አስከብሮ ነጻ ማድረግ ባለመቻሉ ሳቢያ ግለሰቦች ለህገወጥ ተግባራቸው መጠቀሚያነት ቢያውሉትም ሪልእስቴቱ ግን ውሳኔው ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ ለግንባታ ስራው በጊዜያዊነት የሚጠቀምበትን መንገድ አልምቷል። ይህንን መንገድ በበጋና በክረምት ለመጠቀም በሚያስችል ሁኔታ በኮብል ስቶን ለማሰራትም ከአስተደደሩና በሳይቱ አካባቢ ከሚኖሩት ግለሰቦች ጋር በተደረገ ውይይት ጊፍት ለልማት ከተጠየቀው ገንዘብ ውስጥ 150ሺህ ብር ያለምንም ማቅማማት አዋጥቷል። ከአካባቢው ነዋሪዎች የተሰበሰበው ገንዘብ 40ሺህ ብር ብቻ ስለነበር በቂ ገንዘብ እስኪሰበሰብ ድረስ ኮብልስቶኑ ሳይነጠፍ ዘግይቷል። ከአንድ ወር በፊት ኩባንያው የመንገዱ ስራ ያልተጀመረበትን ምክንያት በተመለከተ የሚያስተባብረውን የአካባቢውን  አስተዳደር ማብራሪያ ሲጠይቅም የልማት ኮሚቴው ላይ በነበሩት  ክፍተቶች ሳቢያ ስራው መዘግየቱ ተነግሮታል።ጊፍት ስራው ከተጀመረ ለአካባቢ ልማት ማንኛውንም ድጋፍ ከማድረግ የማይቆጠብ መሆኑን አሳውቋል።የባለሙያና የማሽን እገዛ ካስፈለገም ድጋፍ እንደሚያደርግ በቅርቡ ከክፍለከተማው ስራ አስፈጻሚ ጋር በጉዳዩ ላይ ባደረገው ውይይት ቃል ገብቷል። ከብዙ ጊዜያት መባከን በኋላ በቅርቡ የፍሳሽ ማስወገጃ ትቦ የመቅበር ስራ እየተሰራ ነው።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ጸሃፊው ግን ሁሉንም ችግሩን ወደጊፍት ሪልእስቴት በመግፋት ደንበኞች በኩባንያው ላይ እምነት እንዲያጡና የአካባቢው ነዋሪዎችንም ከሪልእስቴቱ ጋር በማቃቃር  እንደህልውናቸው ጠላት እንዲያዩት ሆን ተብሎ የታቀደ ማስረጃ አልባ ሃተታ አቅርበዋል። ይባስ ብለው “ለወረዳው አስተዳደርና ለክፍለከተማው  ሪልእስቴቱ እምቢ ባይ በመሆኑ ከአቅማቸው በላይ ሆኗል” የሚል ኢተዓማኒ መረጃ ተጠቅመዋል።አካባቢውን ለማስተዳደር፣ ህግና ደንብ ለማስከበርና ለማስፈጸም ሃላፊነት የተሰጠው አስተደደር ለሚመራው ህዝብ አንድን ኩባንያ “ከአቅሜ በላይ ነው” ብሎ አቤቱታ ሲያቀርብ ምናልባት ከእኚህ ጸሃፊ በቀር ማንም ሰምቶ አያውቅም።

ጸሃፊው በአላዋቂ አተያይ የቃኙት የአካባቢ ልማት ለኩባንያዎች የኮርፖሬት ማህበራዊ ሃላፊነትን የመወጣት የሞራል ሃላፊነት እንጂ በውልና በአስተደደራዊ ጫና የሚተገበር ስራ አይደለም። ጊፍት በውዴታ አስተዋጽዖ አደርጋለሁ ብሎ የገባበት ይህ የአካባቢ ልማት በጋራ ርብርብ ተፈጻሚ ሆኖ ህብረተሰቡ ሲጠቀም ማየት ከአላማዎቹ አንዱ ነው።ጊፍት በአካባቢያዊና ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ሁሌም ቀዳሚ ተሰላፊ የሆነ ፣ ማህበራዊ ሃላፊነቱን በመወጣት በኩል የተከበረ ስም ያለው ተቋም ነው። ለቀይመስቀል ህንጻ ማሰሪያ የለገሰውን ከ6መቶ ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ ቤት ጸሃፊው ራሳቸው በጽሁፋቸው ማጠናቀቂያ ለአሉታዊ ሃሳባቸው ማጠናከሪያ ምሳሌ ቢያደርጉትም አልካዱትም። ጊፍት  ማህበረሰቡን አግልሎ ገንዘብ ለመሰብሰብ ብቻ ያለመ ኩባንያ ቢሆን ኖሮ አንጋፋ ሆኖ የሚሳተፍበትን የሪልእስቴት ኢንቨስትመንት ዛሬ ድረስ ማቆየት ባልቻለ ነበር።

የመሰረተ ልማት ጥያቄ  የጊፍት ጥያቄ ብቻ ነውን?

ጸሃፊው በመጨረሻ ላይ በግልጽ በሚያስታውቅ ግነት ያነሱት የውሃ፣የመብራትና የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች ጉዳይ የጊፍት ሪልእስቴት ብቻ ሳይሆን የመላው አዲስ አበባ ችግር መሆኑ ጠፍቷቸው አይደለም። በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የትኞቹም የሪልእስቴት አልሚዎች ከገጠሟቸው ዋና ዋና ችግሮች ተጠቃሾቹ እነዚህ ጸሃፊው ከላይ የጊፍት ስህተቶች አስመስለው ሊያቀርቧቸው የሞከሯቸው የመሰረተ ልማት ችግሮች ናቸው።ዛሬ እንኳን በከተማ ማስፋፊያ አካባቢ አዲስ የሚመሰረት መንደር ቀርቶ በመሃል ከተማ የሚገኝና ከ50 ዓመት በላይ የቆየ ነባር መንደር ጭምር የውሃ መጥፋትና የመብራት ሃይል መቆራረጥ ችግር ያጋጥመዋል።ይህ ከከተማው መስፋት፣ከህዝብ ቁጥር መጨመርና ከውሃና ከሃይል ፍላጎት ማደግ ጋር በተያያዘ የተከሰተ የጋራ ችግር ነው። መንግስት ለሪልእስቴት አልሚዎች መሬት ሲሰጥ የውሃና የመብራት መስመር የመዘርጋት ሃላፊነት እንዳለበት ቢያውቅም በአቅም ማነስና በሃብት ውስንነት ሳቢያ በተፈለገው ጊዜ አገልግሎቱን ማድረስ አልቻለም። ማንኛውም አካል ይህ ችግር ተፈትቶ ከተማዋ ለኑሮና ለነዋሪዎቿ ምቹ ሆና ማየት ይናፍቃል።

ጊፍት ሪልእስቴትም ቤት የገነባው አዲስ አበባ ውስጥ አንደመሆኑ በከተማው ቤት ልማት ላይ የተሰማሩ  አቻ ኩባንያዎች ከገጠማቸው የተለየ ችግር አልገጠመውም። የጊፍት ሪልእስቴት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ይህን ጊፍትን ብቻ ሳይሆን የሃገሪቱ ሪልእስቴት ዘርፍ በሚፈለገው ሁኔታ ላለማደጉ እንቅፋት የሆኑበትን መሰረታዊ ችግሮች በተመለከተ በአዲስአድማስ ጋዜጣ ለቀረበላቸው መሰል ጥያቄ በሰጡት ምላሽ በግልጽ ያስቀመጧቸውን ነጥቦች መጋቢት 5 ቀን 2007 ዓ.ም ከወጣው የጋዜጣው እትም ገጽ 14 በንግድና ኢኮኖሚ አምድ ላይ በማንበብ እውነቱን መረዳት በዚያውም አዕምሯቸው ውስጥ ላለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ይችላሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፉት ዓመታት ጊፍት ግንባታ ወዳካሄደበት ፌዝ ሁለት ሳይት የውሃና የመብራት መስመር እንዲዘረጋለት በተደጋጋሚ ጊዜ ጠይቋል። የሚመለከታቸው አስፈጻሚ አካላት ዛሬ ነገ ከሚሉ ተስፋዎች የዘለለ አጥጋቢ  ምላሽ መስጠት ባይችሉም።ያም ሆኖ ኩባንያው ሳያሰልስ ጉዳዩን በመከታተሉ  ከዓመታት ጥረት በኋላ ችግሩን ከመሰረቱ ለመቅረፍ ወደሚቻልበት ምዕራፍ አድርሶታል። በአስፈጻሚ መስሪያቤቶቹ የተጀመሩት ስራዎች ሲጠናቀቁ የደንበኞች ጥያቄ ምላሽ ያገኛል የሚል ዕምነትም አለ።

እንዲያም ሆኖ ቤታቸውን ተረክበው የገቡ ነዋሪዎች በውሃና በመብራት እጦት እንዳይቸገሩ ኩባንያው ተጨማሪ ወጪ በማውጣት ጊዜያዊ መስመር በመዘርጋት አገልግሎቱን እንዲያገኙ ለማድረግ ሞክሯል። ለስራ የሚጠቀምበትን የኤሌክትሪክ ሃይል ለነዋሪዎች በማከፋፈል ችግራቸውን በጊዜያዊነት ለመፍታትም ጥሯል። ይህ ችግር የጋራ ችግር መሆኑን ደንበኞቹ ይገነዘባሉ። ጸሃፊው የግራውን ከቀኝ እየቀላቀሉ ‘የምርጫ ክርክር ማየት አልቻልንም’ ብለው እንዳጋነኑትና ፍሪጅ አስነስቶ ቴሌቪዠን የማያሰራ ሃይል  እንዳሉት ሳይሆን ሊጠቀሙበት የሚችሉትን ሃይል ነው ያከፋፈላቸው። ጸሃፊው ለወቀሳቸው ማጠናከሪያ አጋንነው ቢያቀርቡትም ይህንን ማድረግ የኩባንያው ሃላፊነትም ጭምር ነውና ምስጋና የሚሻበት ጉዳይም አይደለም ።

ጸሃፊው በመጨረሻ “የኩባንያው ሃላፊዎች ደንበኞችን አያነጋግሩም” የሚል ጭብጥ ለአንባቢ ለማስያዝ “ሃላፊዎቹ ቢሮ  ዘግተው ይጠፋሉ” የሚል ቃል ተጠቅመዋል። እሳቸው በጽሁፋቸው መግቢያ ላይ “በተደጋጋሚ ጊዜ አነጋግሬያቸዋለሁ” ያሏቸውን የድርጅቱን ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ ከቢሮ ውጪ የት አግኝተው አነጋግረዋቸው እንደሆን ቢጠቅሱት የራሳቸውን ሃሳብ በራሳቸው ከማፍረስ ያድናቸው ነበር። በመሰረቱ የሪልእስቴቱ ሃላፊዎችም ሆኑ ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ከስራ ሰዓት ውጪም ቢሆን ሁልጊዜ በቢሯቸው ደንበኞችን እንደሚያስተናግዱ ራሳቸው ደንበኞች ምስክር ናቸው። በጊፍት ሪል እስቴት ደንበኞች ቀን ሳይወሰንባቸው ስድስቱንም የስራ ቀናት መጠቀም ይችላሉ፣እየተጠቀሙበትም  ነው። ጸሃፊው በይመስላል ከመጻፍ ይልቅ የአዲስ አበባ ነዋሪ ከሆኑ ቢሮ መጥተው የሚያነጋግራቸው አጥተው ከሆነ በግልጽ ቢናገሩት መልካም ነበር። ማስረጃ አልባ ክስ ክፋቱ ከስም ማጥፋት አለመዝለሉ ነው።

እንደማጠቃለያ

አንባቢ ይህንን ለጸሃፊው የተሰጠ ምላሽ ሲያነብ “ጊፍት ሪልእስቴት ከማንኛውም ችግር የጸዳ ነው” የሚል መልዕክት ለማስጨበጥ ታልሞ የተጻፈ አድርጎ እንዲገነዘበው ኩባንያው ፍላጎቱ አይደለም። ከላይ ለመግለጽ እንደተፈለገውና ጸሃፊው ራሳቸው በመንደርደሪያቸው እንዳስቀመጡት በኢትዮጵያ የሪል እስቴት ዘርፍ ከጀማሪነት ደረጃው ከፍ ባለ እርከን ላይ እንዳይቀመጥ ባደረጉት በብዙ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ውስጥ ያለ ዘርፍ ነው። እነዚህ ችግሮች በኩባንያዎቹ ላይ ሲጫኑ ደንበኞችም ችግሩ የሚያስከትለውን ጫና በከፊልም ቢሆን መሸከማቸው እውነት ነው።ያም ሆኖ ጊፍት ሪል እስቴት በተቻለ መጠን ደንበኞች ለከፈሉት ገንዘብ እርካታ አግኝተው የሚወጡበት ሰርዓት እንዲፈጠር ጥረት እያደረገ ነው።ቅሬታዎች ቢኖሩም ቅሬታዎቹን “ደንበኛ ሁሌም ትክክል ነው” በሚለው የኩባንያው መርህ መሰረት በማስተናገድ  በጋራ መግባባት የተጀመሩትን ስራዎች ለማጠናቀቅ ቁርጠኛ ፍላጎትና አቋም አለው። ነገር ግን ሆን ተብሎ የኩባንያውን መልካም ስምና ዝና በሃሰት መረጃዎች ለመጉዳትና በደንበኞቹ ዘንድ እምነት እንዲያጣ ለማድረግ እንደ ‘አበበ ወርዶፋ’ ባሉ ግለሰቦች የሚፈጸሙትን ደባዎችን ኩባንያው በዝምታ ሊያልፈው አይችልም። አንድን በህግ የህግ ሰውነት የተሰጠው ኩባንያ ስም ማጥፋት በህግም በሞራልም ተቀባይነት የሚኖረው አይሆንም።

ጸሃፊው በውጭ ሃገራት ሰፊ ጎብኚዎች ባሏቸው ze-habesha.com እና satenaw.com ድረገጾች ላይ ጽሁፋቸው እንዲታተም ያደረጉት ሆን ብለው የሪልእስቴቱን ደንበኛ የሆኑ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን አመለካከት ለመበረዝና ድርጅቱን ለማጣጣል እንዲሁም ኩባንያው ላይ እምነት እንዳይኖራቸው ለማድረግ መሆኑን ጊፍት ሪል እስቴት ይገነዘባል። ጸሃፊው “የኩባንያው ብዙ ደንበኞች በውጭ ሃገራት ስለሚኖሩ ቢበዛ ጮኸው ይሄዳሉ በማለት ሃላፊዎቹ ምላሽ አይሰጡም” ላሉት በርግጠኝነት የድርጅቱ ደንበኛ አለመሆናቸውን ያመለክታል። ምክንያቱም ኩባንያው በዘረጋው የመረጃ ግልጽነት ስርዓት እያንዳንዱ ደንበኛ በኩባንያው ኦፊሺያል ዌብሳይት ላይ በተከፈተለት አካውንት የቤቱ ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ በፎቶግራፍ ጭምር እንዲያይ የሚደረግ ከመሆኑ በተጨማሪ የተለያዩ መረጃዎችን እንዲሁም ደንበኛው ያለውን ማንኛውንም አስተያየትና ቅሬታ በኢሜይል መልዕክቶች በመለዋወጥ የየዕለት ክትትልና ግንኙነት ያደርጋል።

እነዚህ ሁሉም የጊፍት ሪልእስቴት ደንበኛ የሚያውቃቸው ከላይ የተጠቀሱት መረጃዎች የጸሃፊውን መረጃ ትክክለኛ አለመሆን ያሳያሉ። ከዚህ በተጨማሪም ዌብሳይቱ ላይ የሰፈረው ጽሁፍ የሁሉም የጊፍት ደንበኞች እምነት አለመሆኑን ቢያንስ ይህ ጽሁፍ ለድረገጹ እስከተላከበት ቀን ድረስ የጸሃፊውን ሃሳብ ደግፎ አስተያየት የሰጠ አንድም ሰው አለመኖሩ  ቀላል ማሳያ ነው። በመጨረሻም  ጸሃፊው በርዕስነት ለተጠቀሙበት “ጊፍት ሪል እስቴት ወደፊት ወይስ ወደኋላ?” የሚል ጥያቄ ኩባንያው አጭር ምላሽ ሊሰጣቸው ይወዳል። “የጊፍት ሪል እስቴት ጉዞ በስም ማጥፋት ዘመቻ ወደኋላ አይመለስም !”

በዚህ አጋጣሚ ጊፍት ሪል እስቴት ስሙ ተጠቅሶ ለወጣበት ጽሁፍ ተገቢ ነው ያለውን ምላሽ ሲልክ ze-habesha.com እና satenaw.com ድረገጽ ሃላፊነት እንደሚሰማቸው ሚዲያዎች ተቀብለው ለንባብ በማብቃታቸው ኩባንያችን ከፍ ያለ ምስጋናውን ሊያቀርብላቸው ይወዳል።

 

The post የጊፍት ሪል እስቴት ጉዞ በስም ማጥፋት ዘመቻ ወደኋላ አይመለስም appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles