Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ኢትዮጵያ አንድነት ፈተናዎች –ከአበበ ከበደ

$
0
0

የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ሃገር ኢትዮጵያ በቀደሙት ዘመናት ክፉ ነገሮችን የምትከላከል፣ የደጋጎችና የቅን ሰዎች መኖርያ እንደነበረች ታሪክ ያስረዳናል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃገሬን አትንኩ” ይል እንደሆን እንጂ ከማንም ጋር በልቶ፣ ጠጥቶ ከመሸበት የሚያድር የዋህ ፈሪሃ አምላክን የተላበሰ ሕዝብ ነው። ኢትዮጵያ ሕዝቡን በፍትህና በጥበብ የሚያስተዳድር ጀግና መሪንም የምታገኘው ከእግዚአብሄር ነበር። ኢትዮጵያ ሃገሯና ሊወር የመጣን ጠላት ድባቅ የምትመታው እግዚአብሄር ከፊት ቀድሞ ስለሚዋጋላት እንጂ ከሌሎች የበለጠ የፈረጠመ ጡንቻ ኖሯትም አልነበረም። ይህ ሁሉ ታሪክ ምስቅልቅሉ የወጣው ኢጣልያ ዳግም ኢትዮጵያን ከወረረች በኋላ ነው። ራሷ ኢጣልያ በኤርትራ የቆየችበት ዓመታትም ዋናውን የአንድነቱን ማብከኝያ መርዝ በቅርብ ሆና ለመቀመም የቻለችበት ኢትዮጵያን የጎዳ ዘመን ነበር። የኤርትራ ጉዳይ እንደመዥገር ሆኖ ከኢትዮጵያ ገላ ላይ አልላቀቅ ያለውም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው። የኤርትራ ከእናት ሀገሯ ጋር የተደበላቀችበት ጥበባዊ ሥራ በምእራብያውያኖች፣ በመካከለኝው ምሥራቅ ፖለቲካ መዘዝ፣ በግራ ክንፉ የሥልጣን ትንቅንቅ ሳብያና በፖለቲካ መሪዎቹ አናሳ ብስለት ምክንያት ተጨናገፈ። የግራው ክንፍ ፖለቲካም ከኢጣልያ መሠሪ አሰራር ልምዱን ባገኙ ኤርትራዉያን ፖለቲከኞች ሲመራ ቆይቷል። ሻዕቢያ የፊትና የኋላውን መመርመር ያልቻሉትን ግለሰቦች በመደለል፣ የነቁትን በማግለል፣ ላንዳንዱ ደግሞ ሥልጣን መዳረሻ የሚሏቸውን የሃሰት ሥልቶች አስታቅፈው፣ ሲቻል እያፋጇቸው ሳይቻል እያነታረኳቸው፣ ዓላማቸውን ከንቱ ለሆነውና እርባና ቢሱ የኤርትራ ግንጠላ አዋሉት። ኤርትራም በከንቱ ተገንጥላ ለመከራና ስደት ስትዳረግ ኢትዮጵያና የዋህ ሕዝቧ በቆሸሸው ፖለቲካ ውስጥ ተነከሩ።

የኢትዮጵያ ችግር በአብዛኛው መንፈሳዊ ነው። ፀሎት ሥጋዊ ሆኗል፣ ፖለቲካው አስመሳይ ሆኗል። ድህነቱ አዋራጅ ሆኗል። አብዛኛው ሰው ከደረሰበት ችግር ለመላቀቅ የእግዚአብሄርን መንገድ ትቶ ለምእራቡ ዓለም ሰግዷል። ለንዋይ መምበርከኩ ታቦትና ጽላት እስከመሸጥ ድረስ ደፋር አድርጓል። ስደቱ ማንነቱን ከመለወጡ አንስቶ ወደ ሌላ አሳፋሪ ድርጊት ተሸጋግሯል። አሁን ግን አምላክ በቃ እንዲለን ከዚህ በታች የምዘረዝራቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች ሳላንዛዛ ባጭሩ ለማቅረብ እሞክራለሁ። ይህ ከዚህ ቀደም ብዙ ቢባልለትም እኔ ለማስታወስ ያህል እንደገና እንዲህ አድርጌ አቀርበዋለሁና በጥሞና አስተውሉት።

ኢትዮጵያ ማነችኢትዮጵያዊስ

ኢትዮጵያ ከሰባት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በኅልውና የቆየች እግዚአብሄር አላማውን ለመፈጸም ሲል ከሚታይና ከማይታይ መከራ እየከለለ ያቆያት የዋህና ጀግኖች ሕዝቦችን ያቀፈች በአፍሪካ ቀንድ አሕጉር የምትገኝ ሃገር ነች። ኢትዮጵያ የጽላቱና የታቦቱ ምስጢር የተገለጠባት፣ ጥንታዊ የሆነ የራሷ ጽሑፍ ያላት፣ ከእግዚአብሄር ምልክቷ ይሆን ዘንድ ልዩ ባንዲራን የለበሰች በአምላክ ልዩ ጸጋ የምትደዳደር ሃገር ነች። ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ መልኩን መቀየር አይቻለውም። ኢትዮጵያዊ ድህነት፣ ችግርና መከራ ተንበርካኪ የማያደርጉት ጀግና ነው።

ቅናት ምንድነው?

ከእግዚአብሄር ልዩ ጸጋን የታደለ ሃገርም ይሁን ግለሰብ አርፎ አይተኛም። ቀናተኛው ዲያቢሎስ ይግደራደራቸዋል። የቃል ኪዳኑ ታቦት ቤት የሆነችው ኢትዮጵያም ከቀናተኞች ዓይነጥላ አትሰወርም። የእግዚአብሄር ቃል ኪዳን መፈጸምያዋ እስራዔልም ብትሆን ችግሮች ተፈራርቀውባታል። ዲያቢሎስ እስራኤልንም ኢትዮጵያንም ፋታ አይሰጣቸውም። እናንተ እሥራኤሎች ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ አይደላችሁም” የሚለው የእግዚአብሄር ቃልም እሥራኤል በኢትዮጵያ ላይ ፊቷን እንድታዞር ያደርጋታል። መንፈሳዊ ቅናት ተፈጥሯዊ ነው፣ መጠኑ የበዛ ሥጋዊ ቅናት ግን የሰይጣን ነው። ያእቆብ በልጆቹ መካከል ያደረገው ልዩነት ነው ቅናትን አሳድጎ ታናሽ ወንድማቸውን ዮሴፍን ወደ ጉድጓድ እንዲወረውሩ የገፋፋቸው። ኢትዮጵያውያኖች ቀድሞ በግዕዝ ቋንቋ ይጠቀሙ ነበር። የኋላ ኋላ እስከዛሬ ድረስ የመንግሥቱ መጠቀምያ የሆነው ቃንቋ አማርኛ ግዕዙን ተካ። በአማርኛ ቋንቋ ላይም ቅናት ተበራከተ። ኢትዮጵያ ሁሉንም ታላላቅ ኃይማኖቶች ማለትም ክርስትናን፣ እስልምናንና የአይሁድ ኃይማኖትን አካታለች። ሶስቱ ኃይማኖቶች በመሃላቸው የቀኖና ልዩነት አላቸው። ልዩነት ውበት መሆኑ ቀርቶ ውዝግብ የሚያደርገው ቅናት ነው። ዮዲት ጉዲት በአይሁድ ኃይማኖት ሥር ለማካተት እልቂትን ስታመጣ ግራኝ መሃመድም ወደ እስልምናው ለመጠቅለል ለአስራ ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ላይ አውዳሚ ዘመቻ አወጀባት። ቅናት ከብልሹ ስሜት ይመነጫል። አንዳንድ ጊዜ ከፍርሃት አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የፍላጎት መጠን መንዛዛት የቅናትን ስሜቶች ያሳድጋሉ። ኢትዮጵያ ዙርያዋን በከበቧት ቅናቶች ሳብያ ዘወትር ትመሰቃቀላለች፣ ትቦረቦራለች፣ ትከሳለች። ከእጇ የጎረሱት፣ ውሃዋን የተጎነጩት እንኳን ተረከዛቸውን ያነሱባታል። በገዳማቱ ባሉ እውነተኞች አባቶችና እናቶች ጸሎት ይኸው በኅልውና አለች።

ቅናት በዘመናዊ ፖለቲካ ሲቀመም

ከኢጣልያ ዳግም ወረራ በኋላ ኢትዮጵያን የሚያጠፋው መርዘኛው ፖለቲካ በቅኝ ግዛት በተያዘችው በኤርትራ ውስጥ ይቀመም ጀመር። ኢትዮጵያ ብሄረሰቦች የሚጨቆኑባት ሃገር ነች አሉ። አማርኛ ቋንቋን መጨቆና መሣርያ አድርጎ ለማሳየት ከቅኝ ግዛት አስተዳደሩ ውክልናን ያገኙ ሰዎች ከማርክሲዝም ሌኒኒዝም ቀኖና ጋር ለውሰው የቀድሞ ቅናታቸውን አነባብረው አማራው ሌሎች ብሔረሰቦችን በጭቆና ይገዛል” የሚል አጥፊ ሃሳብ ፈበረኩ። ተከታታይ የነበረውን የኢትዮጵያ መልካም አስተዳደር ላንዴና ለመጨረሻ ለመናድ ከ ሀ እስከ ፐ ያለውን አማርኛ ፊደልንና አማራ ሕዝብን ጨቋን ጭራቅ አድርጎ የመሳሉ ተልዕኮ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ማህበራዊ አኗኗርንና የዋህነቱን በሚገባ ለሚረዱት ሠርጎ ገብ አጥፊዎች የቤት ሥራ ተደርጎ ተሰጠ። በዚሁ መሠረት የሻዕቢያ ተላላኪዎች በተማሪው እንቅስቃሴ ኋላም በተለያዩ ጊዜዓት በተመሰረቱት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በደርግም ጭምር፣ ሠርገው በመግባት ሌሎች ኢትዮጵያ በሚጠሉ ሃገሮች እየታገዙ ለኤርትራ ግንጠላና አዋሉት። ስለዚህ ጉዳይ ብዙ ስለተባለ ይህን ብቻ ባጭሩ አስቀምታለሁኝ። ሻዕቢያ በዲያቢሎስ ቅናት ተገፋፍቶ አማራን ጭራቅ አድርጎ ስሎ ሲያበቃ ጥቂት ግለሰቦችን በማሰባሰን ፀረ አማራውን ኦነግን መሠረተ። ይህ ትልቁ መሠርያዊ ተግባር ለጊዜው ተሳክቶለት ራሱ ሻዕቢያ ኤርትራን ሲያስገነጥል፣ ማለሊት ኋላም ሕወሃት ለስልጣን በቅቶ ሻዕቢያ ሠራሹን ኦነግን እንደ ጉም በተነ። እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ስለሚጠብቅ ቋንቋቸውን አደበላልቆ በሻዕቢያና ሕወሃት መካከል ያለውን ስምምነት በብረት መጋረጃ ጋረደው። ሆኖም ግን ሕወሃት ከወንድሙ ሻዕቢያ በተማረው መሠረት አማራን ይበልጥ ጭራቅ አድርጎ ስሎ በርካታ ዘርን ማዕከል ያደረጉ ድርጅቶችን ፈጠረ። አማራ ሊመጣባችሁ ነው ራሳችሁን ጠብቁ” እያለ እያሞኛቸው በስልጣን ወንበሩ ላይ ለረዥም ዓመታት ተቀመጠ።

መፍትሄ ያመጣሉ ብዬ የገመትኳቸው ሃሳቦች

አንደኛ፣ እኛ ኢትዮጵያውያኖች ዘመናዊው ዘመነ መሳፍንት ውስጥ ሳናውቀው ድንገት ተዘፍቀናል። በመሆኑም በአጼ ቴዎድሮስ፣ አጼ ዮሃንስና አጼ ሚኒልክ ዘመን የነበረውን የቀደመውን ፍቅርና አንድነትና ጀግንነት ዳግም መመለስ ይገባቸዋል። ሶስቱም ነገሥታት አማርኛ ቋንቋን የመንግሥት ቋንቋ አድርገው ይጠቀሙበት ነበር እንጂ አማራን ጨቋኝ አድርገው አልሳሉም። ራዕያቸውም ሆነ የነጋ ጠባ ምኞታቸው ኢትዮጵያን አንድ ማድረግና ከውጭ ጠላቶቿ መጠበቅ ነበር። አጼ ቴዎድሮስ ራዕያቸው አንድነት በመሆኑ ነው ሃሳባቸውን የተቃወሟዋቸውን የራሳቸውን ዘመዶች ሳይቀር ያስወገዱት። አጼ ዮሃንስ አማራን ቢጠሉ ኖሮ አማርኛን አስወግደው በትግሬኛ ቋንቋ ለመተካት ሙከራ ያደርጉ ነበር። አጼ ሚኒልክ በዘር ቢያስቡ ኖሮ ራስ ጎበናን፣ ፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስ ወይም ደጃዝማች ባልቻን ለትልቅ ሥልጣን አያበቋቸውም ነበር። እኛ ኢትዮጵያውያኖች ይህን መልካም መንፈስ ዳግም እንድንላበስ ማስተዋላችንን ዳግም ማደስና ለመሆኑ ወዴት እየተጓዝን ነው?” ስንል መጠየቅ እንዲሁም መፍትሄ ማፈላለግ ይኖርብናል።

ሁለተኛ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን አባቶች በቤተ ክርስትያኗ መሃከል የተፈጠረውን ክፍፍል ለመቅረፍ መንፈሳዊ መላ ማፈላለግ የሚኖርባቸው ይመስለኛል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ኃያል የነበረውን የቅኝ ግዛት ወረራርን ለመቋቋም ከጀግኖች አባቶቻችን ጋር አብራ መዝመቷን ከታሪክ ተምረናል። በግራኝም ሆነ በኢጣልያ ፋሺስት ወረራ ዘመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በዱር በገደሉ ተሰዳ እየጸለየች እስከዛሬ ገድላቸው ምሳሌና ጥንካሬ የሆነልንን እንደነ አቡነ ተክለሃይማኖትንና አቡነ ጴጥሮስን የመሳሰሉ መስዋዕቶችን አፍርታለች። ዛሬ በስደት የሚኖሩት ወገኖች ለሁለት ተከፈለው ከፖለቲካ ጉዳይ በባሰ ሁኔተ የሚነታረኩትና አንዱ ባንደኛው ላይ እጁን የሚቀስረው በሃገር ቤትና በውጭ ሁለት ሲኖዶሶች በመኖራቸው ሳብያ ነው። ተሳስቼ ከሆነ እርማቱን ለመቀበልና ለመማር ዝግጁ ነኝ። ቤተ ክርስትያኗ ለሁለት መከፈሏ ለጠላት እንዲሁም ኢትዮጵያን ለሚጠሉት ሁሉ አመቺ ሆኗል። እውነትን ደፍሮ የሚናገር ራሱን በንሥሃ አድሶ በቅዱስ ቁርባን አጽድቆ የሚተጋ፣ ለሌሎች ምስክርነቱን በተግባር የሚያሳይ፣ ግዳጁ በሥራ የሚታይ ጠፋ። ስነምግባር ተወላግዶ ግብረገብነት ተሰውሮ፣ ኃይማኖት ተንቃ፣ የሚፈራ የሚከበር ተዉ የሚል ዳኛ ጠፍቶ ሁሉም አንደኛውን ተገን አድርጎ እንዳሻው ይናገራል። ዲያቆኑ ቄስ፣ አስመሳዩ ዳኛ፣ ጉልበተኛው አገልጋይ፣ አዝማሪው ዘማሪ፣ ባለገንዘቡ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው እስኪቀርቡ ድረስ ታሪካዊዋ ቤተክርስትያናችን ህልውናዋ ደበዘዘ። ስለዚህ ጉዳይ በጥልቀት ለመናገር በቂ እውቀት የለኝም ነገር ግን የቤተክርስትያኗ ዋናው ሲኖዶስ መንበረ ፓትርያርክ ሃገር ውስጥ እግዚአብሄር እመረጣት ቅድስት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲቆይ በሃገርም በውጭም የሚገኙ መንፈሳዊ አባቶች እርቀ ሠላምን ፈጥረው፣ እግዚአብሄርን በጽኑ ተመርኩዘው በመጾም፣ በመጸለይና በእምነተ ተግባር በመንደርደር መንፈሳዊው ትግሉን በማጎልበት ኅያውን ቅርስ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲያስተላልፉ ስል ተንበርክኬ ልመናዬን አቀርባለሁ። ማንም ለእግዚአብሄር ሲል ቢሸነፍ በሰማዩ አባታችን እግዚአብሄር ዘንድ ትልቅ ሥፍራን ይጎናጸፋል። የምድር ነገሥታት ወይም ተጻራሪ አቋም ያላቸው ድርጅቶች እንኳን በዲፕልማሲው ስልት እየተግባቡ ጦርነትንና መናቆርን ያስቀራሉ እንኳንስ የእግዚአብሄርን አደራ የተሸከሙ ታላላቆቹ አባቶች ይቅርና። ቤተክርስትያናችን አንድነቷ ሲመለስ የሃገሪቱ መንፈሳው ችግር ይቀረፋል።

ሶስተኛ፣ ቢቻል የተማረው፣ የተመራመረው በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ወደ ሃገሩ መመለስ ይገባዋል። ለሃገሪቱ ሙያዊ አስተዋጾ ማቅረብ የሚችሉት ሃኪሞች፣ ማምህራን፣ መተርጉማን፣ ደራስያን፣ መሃንዲሶች፣ የተግባረ ዕድ ባለሙያዎችና የማህበራዊ ሣይንስና ወታደራዊ ጠበብት ባጠቃላይም በችግሯ ጊዜ አብረዋት ሆነው አይዞሽ ሊሏት የሚገባቸውና በሰላማዊ ትግሉ የሚሳተፉ ደፋሮች ሁሉ ቢመለሱ ሃገሪቱ አሁን ከተዘፈቀችበት መከራ ትገላገላለች የሚል እምነት አለኝ። የተማረው ሁሉ ከተሰደደ የሥራ ዕድል እንዴት ይፈጠርሠብሎችንና ንጥረነገሮች ተቀምመው ለምርት ውጤት እንዴት ይብቁሃገሪቱን ከውጭ ጠላት ማን ይጠብቅበአሜሪካና አውሮፓ ላሉት ስደት ትልቅ የገቢ ምንጭ ወይም የድሎት ቤት መሆኑ ቢታወቅም እንኳን በሌላ በኩል ደግሞ ስደት የቅድስቲቱ ኢትዮጵያን ስም ማጉደፉን ልንገነዘብ ይገባናል። ስደት ኢትዮጵያዊና እስራኤላዊ ላይ አያምርም። ዜግነት በመለወጡ ከኢትዮጵያዊነት ቀለም ማምለጥ አይቻልም። ሠበባ ሠበብን ከምረው ራሳቸውን በማታለሉ ስልት የሚኖሩ ሁሉ እርካታ በሌለበት ሕይወት የሰባውን፣ የላመውን፣ የጣመውን እየበሉ መኖር ብቻ ነው ትርፋቸው። ኢትዮጵያዊነትን ለመለወጥ የሚያበቃ ኅሊና የማይታዘበው እውነተኛ ሠበብ ከቶም የለም።

አራተኛ፣ አማራው ጭራቅ አለመሆኑን የሚያሳይ አዲስ በቅን መንፈስ ላይ የተመሠረተ የቃል ኪዳን ማህበር ሊመሰረት ይገባል። የዚህ ማህበር አባል ሊሆኑ የሚገባቸው እውነተኞችና ራሳቸውን ለሃገሪቱ ሲሉ መሰዋዕት ለማድረግ የተዘጋጁ ከበቀልና ጥላቻ የራቁ ማስተዋልን የተላበሱ እንዲሁም ራስን በንሥሃ አንጸው ለኢትዮጵያዊነት የሚበቁ ደጋጎች ሊሆኑ ይገባል። አባላቱ ኢትዮጵያዊ የሆኑ፣ በውጭ ሲኖሩ ዜግነታቸውን ያለወጡ፣ በማንነቱ ቀውስ (identity crisis) ያልተበከሉ ወይም የለወጡትን ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸውን ሊያስመልሱ የተዘጋጁ ሊሆኑ ይገባል። አታክልትን ውሃ እንጂ ማር ቢያጠጡት አይበቅልም። ሃቀኛና ለመስዋትነት ያልተዘጋጁ ሰዎችን አባል ማድረግ ድርጅትን በቁጥር ብዛት ማሳደግ እንጂ በዓላማ፣ ተግባርና ጥራት አያጸናም። እውነተኞችና ደፋሮች ጥቂት ሊሆኑ ይችላሉ። ጥቂት እውነተኞች ግን ኃይላቸው ጠንካራ ነው። ቆራጥ ዓላማ የጽናት ድምር እንጂ የሰዎች ብዛት ብቻውን ቁጥር ነው። ዛሬ በተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ምክንያት በዘፈቀድ ወደ ቤተክርስትያን የሚመላለሱትንም ሆነ ለማህበራዊ ጥቅም ሲሉ ልዩ ልዩ ድርጅቶችን የተቀላቀሉትን ወገኖች በማስተማር ወደ ትክክለኛ አስተሳሰብና እውነት እንዲመለሱ ለማድረግ የተማሩት፣ የተመራመሩት ሁሉ የማስተማር ግዴታ ቢኖርባቸውም የኃይማኖት አባቶች ደግሞ ከእግዚአብሄር የተቀበሉት ልዩ አደራ አለባቸው። 

አምስተኛ፣ እንደ ግንቦት ሰባት ያሉት የፖለቲካ ድርጅቶች ከሻዕቢያ ጋር ያሰሩትን የቃል ኪዳን ቀለበት እንዲያወልቁ በቅጡ መገሰጽ ያስፈልጋል። ሻዕቢያ እንኳንስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርና አቅፈው ደግፈው፣ ገንዘብ አዋጥተው ሰልለውና አሰልለው ለስልጣን ላበቁት ወገኖቹም እንኳን በጎ አልሆነም። ሻዕቢያን መፍትሄ ያመጣልናል” ብለው ያሰቡት ትላልቆቹ ሰዎች ቀድሞ በትምህርት ቤት ሲማሩ አይጥ ሞቷን ስትሻ ስታበዛ ሩጫ፣ ሄዳ ታሸታለች የድመት አፍንጫ” የተባለውን የታሪክና ምሳሌ መጽሔትን ምሳሌያዊ አነጋገር አላነበቡም አይባልም። ህወሐትን ለመጣል ሻዕቢያን የመጠጋቱ ስልት እማዬ፣ ድመት የኛን የመሰለ ለስላሳ ቆዳ አለው የቀይ ስጋ ቁንጮ ራሱ ላይ ያለው ዶሮ ነው የሚያስጠላው” በማለት እናቷን ልታደናግር እንደሞከረችው የትንሽቱ አይጥን ተላላ ሃሳብ የመከተል ዓይነት ስልት ነው። ሻዕቢያን የጋረደው ራሱ እግዚአብሄር ነው። ይህ ሊገባን እንዲችል አድርጎ አምላክ ብዙ ቅድመ ሁኔታዎችን ፈጽሟል። መገንጠሉ ባዶ ፖለቲካ ከመሆኑ አንስቶ ኢትዮጵያን መጠበቁ ራሱ ዋነኛ ምልክቶች ናቸው። አቶ ኢሳያስ ይህን እውነት አልተረዱም አይባልም ግን ሕዝቡን ይቅርታ ለመጠየቅ ባህርያቸው ገና አልፈቀደላቸውም። ኢሳት ባቀረበላቸው ቃለ መጠይቅ ላይ በግራው ፖለቲካ ላይ ያካበቱት ችሎታቸውን በእብሪት መልክ እንደገና ሊያስረዱን ሞክረዋል። አቶ ኢሳያስ ብዙ ምልክቶችን አይተዋል፣ ኢትዮጵያ የእግዚአብሄር የቃል ኪዳን ሃገር መሆኗንም ተረድተዋል ነገር ግን የኢትዮጵያን ቅድስትነትና የታሪኳን ገናናነት ገና አልተቀበሉም። ሻዕቢያ ቀድሞውንም ቢሆን እንደነ ፕሮፌሰር ጌታቸው፣ዶክተር ታዬ ወልደሠማያት፣ ዶክተር አሰፋ ነጋሽ የመሳሰሉት ደፋሮቹንና ሃቀኞችን የፖለቲካና ታሪክ አዋቂዎች እንዲገለሉ የሚያስደርገው ኢትዮጵያን የማዳከሙ ዓላማ እንዲመቻችለት ነው። ሻዕቢያ እውነተኛ ኢትዮጵያዉያን ድርጅቶችንና ማህበሮችን እንዳይጠጉ ለማድረግ እንደ ፈረስ በሚጋልብባቸው ተላሎች፣ ወረተኞችና ጥቅመኞች ይታገዛል።

ስድስተኛ፣ ቀድሞ እሽቅድምድሙ የኢትዮጵያ አንድነትን ማጎልበትና ልዕልናዋን ማስጠበቁ ላይ እንጂ ለስልጣን መራወጡ እንዲህ እንዳሁኑ አሳፋሪ አልነበረም። የቀደመውን እንኳን ትተን የቅርቡን አንስተን ብንወያይ በንጉሡም በድርግም ዘመንችሎታ” እንጂ ዘር” ለስልጣን ክህሎቱ የሚያበቃ መስፈርት አልነበረም። ይህ የተበላሸው በግራው ፖለቲካ አስተሳሰብ ከአልቤንያ ኮሙኒስቶች ካባ የለበሰው ህወሐት ስልጣኑን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ነው። ሥልጣን የአንድነቱ ማስጠበቅያ መሳርያ መሆኑ ቀረ። ህወሐት በአናሳ ብሄረሰቦች ስም ሳይቀር የዘር ድርጅት መስርቶ መሳለቅያ አደረጋቸው። በመሆኑም ይህን የተሳሳተ ምግባር ለመቀየር ሁሉም ዘሩ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ማስረዳት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያዊነት ኃይማኖት፣ ጀግንነትና አንድነት ነው። ዛሬ አስፈሪ ሆኖ የሚታየውን በሻዕቢያ የሚታገዙትን የአልሻባብንና ኦነግን የሽብር ዛቻ ለመቋቋም ኢትዮጵያዊነትን ይበልጥ ማጎልበት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ የታላላቆቹ ኃይማኖቶች እስልምናና ክርስትና የጋራ መሰባሰብያ ቤት ነች። ይህ ሃገራዊ ጉዳይ ልል እንዲሆን የሚያደናግሩትን እውስጣችን የተሸሸጉትን የሻዕቢያ ጉዳይ ፈጻሚ ተላላኪዎችን ልንነቃባቸው ይገባል። ሌላው ቀርቶ ትግራይዋን ወገኖችን በማስጠላትና በማስገለል ድርጊቶቻቸውና ቅስቀሳቸው ላይም ቢሆን መተባበር የለብንም። ትግራይ የሚኖረው ወገናችንም ቢሆን እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በደሎች የሚፈራረቁበት ሕዝብ ነው።

ሰባተኛ፣ ባዶ ስሜት ሊወገድ ይገባል። ባዶ ስሜት ሙያን ገደል። ባዶ ስሜት ጋዜጠኛ ሆነ። ባዶ ስሜት ፖለቲከኛ ሆነ። ባዶ ስሜት ጦረኛ ሆነ። ባዶ ስሜት ፓስተር፣ ቄስ ሼህ ሆነ። ከንቱ ስሜት እንደስካር ነው፣ እመስዋትነቱ መንደር ጫፍ ላይ ሳያደርስ ድንገት ይበናል። ልበ ደንዳናነት፤ ለጥቅመ ጥቅሞች ማነፍነፍ ወይም ፍርሃት ባዶ ስሜትን ያመነጫል። ልባቸው ያልተለወጠውን፣ ድፍረት ያለበሱትን፣ ሃቅን ያልተመረኮዙትንና ያልተማሩትን ያልተመራመሩትን ማሰለፉ ሽንፈትን ይጋብዛል። ለጥቅም በተሰለፉ ሰዎች ብዛት ድርጅት ቢፈላ ጠብ የሚላ ነገር የለም። ባዶ ስሜተኞች በዝተው እውነተኞች ካህናት የተናቁባትና ኃይማኖታዊ ምግባርን የማይተገብሩ ሰዎች የበዙባት ቤተክርስትያን መንፈሳዊነቷ ደካማ ነው፣ አታስተምርም፣ በቅዱስ ኪዳኑ ኃይማኖት አታፀናም፣ ፍቅር አታላብስም፣ ይቅር ባይ ልብ አትፈጥርም፣ ፍሪ አታፈራም፣ ቅንነት አታጎለብትም፣ ምዕመናን ያልተንዛዛ የኑሮ ሥርዓት እንዲከተሉ ወይም ሕይወትን በመልካምነት እንዲመሩ አታደርግም። ባዶ ስሜተኞች የበዙባት የፖለቲካ ድርጅትም መካን ነች። ለሥጋዊ ጥቅሙ የሚያደላና ለዕለት ኑሮው የሚጨነቅ ግለሰብ ለኃይማኖቱ፣ ለኢትዮጵያዊነቱም ሆነ ለወገኑ ደንታም የለውም። ደንታ ያለው እንዲመስል በባዶ ስሜት ይወራጫል፣ ያዙኝ ልቀቁኝ ይላል። ሲለቁት ደግሞ ተግባር የለም።

እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይጠብቃል።

Comment

The post ኢትዮጵያ አንድነት ፈተናዎች – ከአበበ ከበደ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>