Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ለምወደው እና ለማከብረው ሕዝብ እውነትን የሚገልጽ ውሃን የሚተፋ እንጂ እሳትን የሚተፋ ብዕር የለኝም።

$
0
0

ለአቶ መሃመድ ሙፍታህ -ከተማ ዋቅጅራ

በምስጋና እና በማሳሰቢያ ልጀምር።

Ketemaዘሐበሻ ላመሰግናችሁ እፈልጋለው ምክንያቱም የሚዲያ ተግባርን ስራ በአግባቡ እየተወጣችሁ እንዳለ ይሰማኛል። ከግራ ከቀኝ ያለውን ነገር ያለ አድሎ አቅርባችሁ ህዝብ እንዲያየው እና አስተያየቱን እንዲሰጡ ስላደረጋችሁ ለናንተ ትልቅ ቦታ እንዲኖረኝ አድርጎአል። በሚዲያችሁ የሚሰጠውን ትችት ዋጋ ቢስ እንደሆነ ያሳወቃችሁበት እና ነጻ ሚዲያን ለማይፈልጉት አፋኞች ለሚሰጡት ትችት በሙሉ መልስ የሆናችሁ ስለሆነ ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው። በመቀጠልም መሃመድ ሙፍቲህ ስለሰጠኸው የግል አሳብህ ላመሰግንህ እወዳለው። ምክንያቱም ሁሉም ነገር ወደ እውነት ወደሚነገርበት እና ህዝብ ፍርድን ወደሚሰጠው ወደትክክለኛው ሃሳብን በብዕር በመግለጽ ያልተማረው እንዲማር ያላወቀው እንዲያውቀው የማድረጉን ውይይት መምጣቶ ተገቢ ነው። ብዕር ብዙሃኑን የሚያሳውቅ፣ ብዕር ብዙሃኑን የሚያነቃ፣ ብዕር ብዙሃኑን እውቀትን የሚያስጨብጥ፣ የአለማችን የጥበብ ገላጭ ናት። አቶ መሃመድ ሙፍታን ሰለ አስተያየቶት ክብር አለኝ። ነጻነት ማለት ይሄ ነው። የኔም ሃሳብ ወደዚህ ነጻነት  እድንመጣ እና ሃሳባችንን እንድንገልጽ ነው። ሌሎችም የሙስሊም ሙሁሮች በእስላም ስም የሚደረገውን እንቅስቃሴ እስልምናን እንደማይወክሉ እንደዚህ ወተው ማስተማር ከቻሉ ድል ማለት ይሄ ነው።

ማሳሰቢያው ደግሞ አስተያየት ለምትሰጡ ሰዎች። አስተያየት ሰጪ ሶስት አይነት ሰዎች አሉ

1ኛ. በትክክል ጽሁፉን አንብቦ የራሱን ሃሳብ የድጋፍም ይሁን  የትችታዊ ሃሳብ ያቀርባሉ። እንደነዚህ አይነት አስተያየት ሰጪዎች እራሳቸውን ለውይይት በሰለጠነ መንገድ የሚያቀርቡ መጥፎንም ጥሩንም ተችተው የሚያልፉ ናቸው። እንደነዚህ አይነቱ አስተያየት ሰጪ ጥሩ አመለከካከት ያላቸው ናቸው።

2ኛ.ጭፍን ጥላቻ ያላቸው ሰዎች የሚሰጡት አስተያየት ነው።  እንደነዚህ አይነቱ የራሳቸውን ሃሳብ ብቻ በየትኛውም አቅጣጫ መስማት እና ትክክል እንደሆነ እንዲነገርላቸው አልያም እንድታሰማቸው የሚፈልጉ ናቸው። ወይ ማስረዳት የማይችሉ ወይ መረዳት የማይፈልጉ ሲሆኑ። እንደነዚህ አይነት ሰዎች ለደጋፊም ለተቃዋሚም አይሆኑም።

3ኛ. ወያኔ ሆን ብሎ  ለዚህ አላማ ያሰማራቸው ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ከ3-5 በክርስቲያን ስም ከ3-5 በእስላም ስም ከ3-5 በኦሮሞ ስም ከ3-5 በአማራ ስም ከ3-5 በትግሬ ስም እያለ ይቀጥላል። እንደነዚህ አይነት ሰዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ለዚህ ስራ አንዱ ከአንዱ እንዲጋጭ በመንግስት ከፍተኛ ብር የሚከፈላቸው እና የነጻ ሚዲያን የማንቋሸሽ ስራ የሚሰሩ ካድሬዎች አሉ። እነዚንም የመሳሰሉትን ከግምት ውስጥ በመክተት ነገሮችን ከተለያየ አቅጣጫ እንደሚመጡ መረዳት ተገቢ ነው።

ወደ ቁምነገሩ ስገባ ኢትዮጵያ ክርስቲያን፣ እስላም፣ ዋቄፈና፣ ደብተራውም፣ ጠንቋዩም እምነት የሌለውም በህብረት የሚኖሩባት አገር ናት። እኔ መግለጽ የፈለኩት ግን አቶ መሃመድ የተረዱት አይመስለኝም። ምክንያቱም ለዚህ ጥቃት ኢትዮጵያ ውስጥ በሚፈጠረው የፖለቲካ እንቅስቃሴ መሃል ኢራቅ፣ ሶሪያ፣ ሊቢያ፣ የመን፣ የመሳሰሉት የአገራቸው ፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት በሚደረገው እንቅስቃሴ የራሱን ሃይል አደራጅተው ታላቅ ጥፋት ያደረሱት እዚህ ጋር አሜሪካ ናት ወይም እስራኤል ናቸው የፈጠሩአቸው  የሚለውን ትንታኔ ውስጥ አልገባሁም መግባትም አልፈልግም እሱ እራሱን የቻለ ሰፊ ጥናት እና ሰፊ ገለጻ የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው። ዋናው ጉዳይ በነዚህ አገራት ውስጥ የተፈጠረው ችግር በውስጥ የፖለቲካ መቃወስ ምክንያት ነው። የኔም ስጋት እነዚህ ሃይሎች በኢትዮጵያ ፖለቲካው እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ  ወደ መለውጡ ሁኔታ እያመራ እና  የተወጣጠረ ነገር ስላለ ለሰላማዊው ህዝብ ለክርስትናውም ለሙስሊሙም ለሁሉም… ከሩቅ ያየነው ቤታችን እንዳይገባ ቀድሞ ለፖለቲከኖች እና ለህዝቡ ግንዛቤን መስጠቴ በኢትዮጵያ ሙስሊም በሙሉ የተደረገ ጥቃት አድርገህ ማቅረብህ ስህተት ነው። የግሎን ሃሳብ የሁሉም ሙስሊም አድርገው ማቅረብ በራሱ ከስህተ ሁሉ የከፋ ስህተት ነው። ጽሁፎን ሊደግፉ የሚችሉትን ያህል ያን ያህል አልያም እጥፍ ሊሆን የሚችሉ አንባቢም ሊቃወሞት እንደሚችሉ መገንዘብ ይኖሩቦታል። የርሶን ጽሁፍ መነሻ አድርጌ በሌሎች አማኒያን ላይ የተቃጣ ጽሁፍ ብዬ ላቀርብ በየትኛውም አቅጣጫ ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ እና ኢፍትሃዊ ነው። እዚህ ጋር የተገነዘብኩት እርሶ  መስማት የሚፈልጉት ብቻ መስማት የሚፈልጉ አልያም እንዲነገርሎ የሚፈልጉትን  ብቻ እንዲነገርሎ የሚፈልጉ ሰው መሆኖን ነው።

አቶ መሃመድ ትንሽ ወደኋላ ሄደውም ታሪክን ለመጥቀስ ሞክረው ነበረ። አጼ ዮሐንስ እስላሙን ህብረተሰብን ጨፍጭፈዋል ብለውን ነበረ። ይህ የሚወገዝ ጉዳይ ነው። እኔም አወግዘዋለው። ከፖለቲካው አለም ወጥተው  ሃይማኖታዊ ክርክር  አስመሰለቦት። እዚህ ጋር ግን እርሶ ትክክለኛ ሰው ቢሆኑ ኖሮ ግራኝ መሃመድ በክርስቲያኖች ላይ ያደረሰውንም ጭፍጨፋ  ጠቅሰው ማለፍ ሲኖርብዎ እርሶ ግን የራስህን ስሜት ብቻ እንጂ እውነትን ሊነግሩን ያለመፍቀዶ ለምን ይሆን?። አቶ መሃመድ ሚዛናዊ የሆነ ንግግር እና  እውነተኝነትን የተላበሰ ነገሮችን ማቅረቡ ተገቢ ነው። ተድበስብሶ የሚታለፍ ነገሮች በሙሉ በውስጡ የተደበቁ ነገር እንዳሉ የሚያሳዩ ናቸው።

ጽሁፌንም ከድምጻችን ይሰማ ጋር አገናኝተውታል። ይሄ ደግሞ ሌላው የስህተት እራስ ነው። እኔ ድምጻችን ይሰማ ላይ ምንም ተቃውሞ የለኝም። የኔም አስተያየት ድምጻቸው ይሰማ ነው። ወያኔ የሙስሊሙን ህብረተሰብ ሃይማኖት ውስጥ ገብቶ ድምጻቸውን አፍኗል። ለዚህ የመብት ጥያቄ የኔም ጥያቄ ነው። በዚህ አጋጣሚ የሙስሊሙን ድምጽ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሰሙ ሃጂ ነጂብ መሃመድ እንዲሁም ዑስታዝ ካሊድ ዑመር እና ጋዜጠኛ ሳዲቅ መሃመድን  ከልቤ የማደንቃቸው እና በመነጋገር የሚያምኑ የሁሉንም ድምጽ የሚሰሙ የራሳቸውንም ድምጽ የሚያሰሙ እና በማስተዋል የሚጓዙ አገላለጻቸውን ጭምር የማከብርላቸው ሙስሊም ወንድሞቼ ናቸው። እዚህ ጋር ሊሰመርበት የሚገባው ክርስቲያን ሁሉ ቅዱስ ነው ማለት አንችልም ክርስቲያን ሆኖ ክፋትን የሚያራምድ አለና ስለዚህ ይህንን ክፋትን የሚያራምደውን ግለሰብ ክርስቲያን ስለሆነ  ብቻ የሚሰራውን የጥፋት ስራ ልንደብቅለት ወይም ልንደባብስለት አይገባም። ሙስሊሙ  ውስጥም ሁሉም ቅዱስ አይደሉም ከመሃል ክፋትን የሚያራምድ አለና ስለዚህ ይሄንን ክፋትን የሚያራምደውን ግለሰብ እስላም ስለሆነ ብቻ መጥፎ ስራውን ልንደባብስለት አይገባም። ለክፋት አራማጆች የምንደብቅላቸው አልያም የምደባብስላቸው ከሆነ ግን አደጋ አለው ነው የኔ  ሃሳብ። እንደ ዜጋ በቅን ልቦና ያሰብኩትና ያስቀመጥኩት ቁም ነገር ይሄ ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ ሙስሊም ህብረተሰብ የተቃጣ እሳታዊ ብዕር አይደለም። እንዲህም እንዳላሰብኩ  አንባቢው ከጽሁፌ ሊረዳ ይችላል። ለአስረጅነት ከጽሁፌ ጋር አያይዤ የማቀርባቸው ሊንኮችን አይተው መልሶትን እንደሚሰጡኝ ተስፋ አደርጋለው? እኔ ካለመረጃ አይደልም የምናገረው ከመረጃ ጋር ነው እርሶም መረጃዎችን ማቅረብ ቢችሉ ጽሁፎ ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል።በጽሁፎ ርዕስ ላይ እንደገለጹት ፍራቻ እንዳለኝ እና በመሃልም ላይ ዋጋ እንደምከፍል ነግረውኛል። እዚህ ጋር እንዲያውቁት የምፈልገው ስለ እውነት ማንኛውንም ነገር የመቀበል ጉጉት እንጂ ፍራቻ የለኝም። ክርስትና ውስጥ ፍራቻ የሚባል ነገር የለም። ከፈራ እርሱ እምነት የጎደለው ነው። ስጋን የሚገሉትን አትፍሩ ነገር ግን ስጋንም ነፍስንም በአንድ ላያጠፋ የሚችለውን  እግዚአብሔርን ፍሩ ይላ መጽሐፍ ቅዱስ። ስጋን የሚገድሉትን ቅንጣት ያህል እንደማልፈራ እና እውነትን ይዜ የምጓዝ ክርስቲያን ነኝ። በሐይማኖቴ የሚመጣውን መከራ በሙሉ በደስታ ነው የምቀበለው ነገር ግን ክርስትናን በግድ ተቀበሉ ብዬ በሌሎች ላይ  መከራ መጫን ግን አልችልም። እምነት የግል ስለሆነ ክፉም ቢሰራ ደግም ቢያደርግ ዋጋን ከፋዩ እግዚአብሔር  ስለሆነ ፍርድን ለእግዚአብሔር እንተው።

አቶ መሃመድ ISISን እርሶ እንደሚቃወሙት እና እስላምን እንደማይወክል ነግረውናል። ይሄ ያስማማናል የጋራ ጠላታችን ስለሆነ አብረን እንመክተዋለን። ይሄ ትክክለኛ ሃሳብ ነው። ወደፊትም እንደዚህ ISIS ስህተተና እንደሆነ እና አረመኔአዊ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ እያስተማሩ ቢቀጥሉ እና ብንሰማ  ደስተኛ ሆነን ተደጋግፈን እንጓዛለን። ነገር ግን ይህ አልሆነም ዝምታው በዝቷል። ይሄ አደጋው ደግሞ  ለሁሉም ዜጋ ነው። የኢትዮጵያም ፖለቲካ ሁኔታ አስጊ ደረጃ ላይ ነው። ትግሉ ስለበረታ በዚህ መሃል አደጋ አገራችን ላይ እንዳይመጣ  ክርስቲያኖችም እስላሞችም ዋቄፈናም ይሁዲዎችም ፖለቲከኞችም ጥንቃቄ ማድረግ አለብን ማለቴ እስላምን ታርጌት ያደረገ ሊባል ባልተገባ ነበረ። እዚህ ጋር የጸሃፊውን ዝቅ ያለ የአስተሳሰባዊ እይታ እንዳለው እመለከታለው።

በመጨረሻም ላስተላልፈው የምፈልገው ነገር ሁሉም ሃይማኖት ውስጥ ሊታይ የሚገባው ሰው በሰውነቱ ብቻ ሊከበር ይገባዋል። የአንዱን እምነት ካልተቀበልክ ብለን ሊጫንበት የሚገባ ግዴታ  መቀመጥ አምላክ የማይፈቅደው ነው። ነገር ግን ሙስሊም ትክክለኛ እምነት ነው ብሎ ማስተማር ይችላል አስተምሮም  ወደ እስልምና ሊቀይር ይችላል። ነገር ግን የተቀያሪው ቤተ- እምነት እምነቱን በቀየረው ላይ የሞት ፍርድ መፍረድ ግን በምድርም በሰማይም መንግስት ዋጋ ያስከፍላል። ክርስትና ትክክለኛ እምነት ነው ብሎ ማስተማር ይችላል አስተምሮም  ወደ ክርስትና ሊቀይር ይችላል። ነገር ግን የተቀያሪው ቤተ- እምነት እምነቱን በቀየረው ላይ የሞት ፍርድ መፍረድ ግን በምድርም በሰማይም መንግስት ዋጋ ያስከፍላል። ስለዚህ የግለሰቡ ሃሳብ ወደፈለገበት አምኖ  በሚንቀሳቀስበት ግዜ መብቱ ሊከበርለት ይገባል ነጻነት ማለት ይሄ ነው። ሁሉም ሰው እራሱን ይወዳል  በራሱ ውስጥ ደግሞ  የሚያምነው አምላክ አለ። የሰውየውን የግሉን እምነት ልንተች እንችል ይሆናል ትክክልም  አይደለህም ልንለው እንችላለን። ነገር ግን የኛን እምነት ካላመንክ መጥፋት አለብህ ማለት ግን አይቻልም።

ከዚህ ቀጥዬ የምልክሎትን ሊንኮች ተመልክተው ምላሾን እንደሚለግሱኝ ተስፋ አደርጋለው። ጥቂት ሙስሊሞች ለሚያነሱት ጥፋት ፈጥነው ከእስላም ወንድሞቻችን መልስ ቢሰጥባቸው እና ቢያወግዟቸው ብዙ ስራዋችን መስራት ይቻላል። እኔም ያየሁትንና የሰማሁትን የማውቀውን ጽፌአለው።ጽሁፌም ለነጻነት ለፍትህ የሚታገሉትን ሙስሊም ደግፌ እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል። ከእስላም እህት እና ወንድሞች ጋር አብሬ ተጫውቼ በፍቅር ያደኩና አሁንም በፍቅር የምንጫወት እስላም ጓደኞች  አሉኝ። የኔ ፍራቻ እስላም ወጎኖቼ ሳይሆኑ በእስላም ስም ሰይፍ ይዘው የሚነሱትን ነው። አቶ መሃመድ ይህ ደግሞ  ስጋቱ ለእስላሙ ህብረተሰብ ጭምር ነው። ወይንም ደግሞ እርሶ ከዚህ የተለየ የውስጥ አጀንዳ ካሎት ጽሁፌ ላይስማማዎት ይችላል። ይሄንን ሊንክ ይመልከቱት http://www.independent.co.uk/voices/comment/iraq-crisis-how-saudi-arabia-helped-isis-take-over-the-north-of-the-country-9602312.html እነዚህ ጉሩፖች እንኳን ሌላ ሃይማኖት ላለው ይቅርና ለእስላሙ የማይተኙ ደም አፍሳሾች መሆናቸውን እየተመለከትን ነው። ስለዚህ እስላም ክርስቲያን ዋቄፈና ፖለቲከኞችም  አብረን እንታገላቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚመጣው አይቀሬ ለውጥ ምክንያት በሚፈጠረው ክፍተት እነዚህ ግሩፖች ወደአገራችን እንዳይገቡ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን እንጂ ቸል ብለን ወይም ደባብሰን ለማለፍ መሞከራችን ከአደጋው አያስቀረንም ቅድሚያ ጥንቃቄ ካደረግን ግን በህብረት እንመክተዋለን የሚል ድምዳሜ ያለው ጽሁፌን አቶ መሃመድ  ወደ ሃይማኖታዊ ገጽታ ለውጠውት አጠቃላይ የኢትዮጵያ እስላም ላይ የተቃጣ ብለው ያቀረቡት ግን አንባቢው ብቻ ሳይሆን እርሶም ረጋ ብለው ጽሁፌን ከተረዱት ከኔ ጎን እንደሚሰለፉ ተስፋ አደርጋለው።  ነገር ግን የግሎት ሃሳብ ከሆነ እቀበላለው ።የሁሉም ሰው ሃሳብ የተለያየ ስለሆነ ። እስላሙን ሁሉ ወክለው ግን የተናገሩትን ንግግር ከምን አንጻር እንደሆነ ባይገባኝም ፍርዱን ለአንባቢ ትቼዋለው።

የተወሰኑ ጥያቄዎች ልጠይቆት እና  ሃሳቤን ልቋጭ

1ኛ ISIS የሚደግፉ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም የሉምን? ወደ አፍጋኒስታን ኢራቅ ቱርክ  የሚሄዱት አንድ አንድ ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞችን  እንዴት ይመለከቷቸዋል? ኢትዮጵያ፣ ኤርትሪያ፣ ሱማሊያ፣ የሆኑ የሌላ አገር ዜግነት ኖሮአቸው ወደነዚህ ጉሩፖች መቀላቀላቸው ምንን ያመለክታል? ላገራቸው ነጻነት ነውን? BBC በቅርቡ የዘገበው ሶስት ከሃያ አመት በታች ያሉ የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው  ይሄንን ግሩፕ መቀላቀላቸውን ዘግቦ  ነበረ ከነዚህ ውስጥ አንዷ የአስራ ሰባት አመት የሆነች ሴት ኢትዮጵያዊ ሙስሊም እንደሆነች አሳይቶን ነበረ  በርሶ እይታ ይሄ ድርጊት ምንድንው? በዚህ አይነት እንቅስቃሴ የተሳተፉትን ዜጎች ህብረተሰቡ እንዲያውቃቸው መደረጉ አቶ  መሃመድ ለርሶ  ጠቅላላ ሙስሊምን ይወክላል ያስብላልን? የነዚህን እንቅስቃሴ ማጋለጥ ለምን ኢትዮጵያ ሙስሊም ላይ ሁሉ እንደተነገር አድርገው ማቅረብ ለምን ፈለጉ? ወይስ ይሄ እናንተን አይመለከትም ዝም በሉ ማለቶት ነው?

http://www.cbc.ca/news/world/shamima-begum-amira-abase-kadiza-sultana-what-we-know-about-isis-bound-teens-1.2967193

2ኛ. አያይዜ ያቀረብኩሎትን ሊንኮች  በኢትዮጵያ ላይ በአንድ አንድ አክራሪ እስላሞች የተደረጉ ድርጊቶች ናቸው። ስለዚህ ምን ይላሉ?  እንደዚህ አይነቱ እንቅስቃሴ ህብረተሰባችን ላይ ያደረሰውን ቀውስ ድርጊቱን ኮንነው እና አውግዘው አስተምረው ይሆን? ከሆነም በመረጃ አስደግፈው ቢያሳዩኝ?                                                                    https://www.youtube.com/watch?v=me1joZHo0Zohttps://www.youtube.com/watch?v=lemvyk5KCp8 ,                                               https://www.youtube.com/watch?v=aVm_AscRaRo

3ኛ. ISIS እስላሚክ ስቴት ብለው ባስቀመጡት አገራት ካርታ ላይ ምን አይነት አስተያየት አሎት?

https://www.google.no/search?q=ISIS+MAP&safe=active&biw=1366&bih=624&tbm=isch&tbo=u&source=univ&sa=X&ei=4R3uVMv-H6b-ygPZhYDYBQ&ved=0CBwQsAQ

አቶ መሃመድ ሙፍታህ ወደ  መድረኩ ስለመጡ እንዘህን ጥያቄ መልሰው ይውረዱ።

መጥፎን ድርጊቶችን ሁላችንም በህብረት እናውግዘውና  እንከላከለው እላለው።

ከተማ ዋቅጅራ                                                                                                                                     25.02.2015                                                                                                                                                            Email- waqjirak@yahoo.com

The post ለምወደው እና ለማከብረው ሕዝብ እውነትን የሚገልጽ ውሃን የሚተፋ እንጂ እሳትን የሚተፋ ብዕር የለኝም። appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>