Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ፓትርያርኩ ቋሚ ሲኖዶሱን በመተላለፍ በድጋሚ መመሪያ ሰጡ፤ ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለከፍተኛ ውዝግብ እንደሚዳርግ በመግለጽ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን ያገነዘበ ተለዋጭ መመሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል

$
0
0

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፡-

  • ‹‹የአ/አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያርኩ ልዩ ሀ/ስብከት ነው›› የሚለውን ድንጋጌ ተገን አድርገዋል
  • የወቅቱ ዋና እና ምክትል ሥራ አስኪያጆች ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እንዲዛወሩ አዝዘዋል
  • የሀ/ስብከቱ ብልሹ አሠራር የቀጠለው ‹ሥዩማኖቹ› በወቅቱ ሥራ ባለመጀመራቸው ነው ብለዋል

aba-mathias

  • ተጠሪ
    ነታቸው ለቅዱስ ሲኖዶስም ለፓትርያርኩም የኾኑት ረዳት ሊቀ ጳጳሱ አልተስማሙበትም
  • የረዳት ሊቀ ጳጳሱ ድርሻ ከሌሎች ሊቃነ ጳጳሳት ተግባርና ሓላፊነት በተለየ አልተዘረዘረም
  • የአ/አ ሀ/ስብከትን ልዩ ኹኔታዎች ያገናዘበ የሥራ አስኪያጆች አሿሿም ዝርዝር አልወጣም
  • ፓትርያርኩንና የሀ/ስብከቱን ረዳት ሊቀ ጳጳስ የሚያስማማ ተለዋጭ መመሪያ ይሰጠኝ

ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ከረዳት ሊቀ ጳጳሳቸው ስምምነት ውጭ በራሳቸው ቀጥተኛ ውሳኔ ለሠየሟቸው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ምክትል ሥራ አስኪያጆች፣ በዛሬው ዕለት የምደባቸው ደብዳቤ እንዲደርሳቸው ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ ለኹለተኛ ጊዜ መመሪያ ሰጡ፡፡

‹‹ሕጋዊ አሠራርን በእጅጉ የሚፃረር ነው›› በሚል ከረዳት ሊቀ ጳጳሱ ጠንካራ ተቃውሞ የገጠመውንና ከሕገ ቤተ ክርስቲያን አንጻር በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ የአፈጻጸም ጥያቄዎች የተነሡበትን ያለፈው ሳምንት የመጀመሪያ መመሪያቸውን ያስታወሱት ፓትርያርኩ፣‹‹የተሰጠው አመራር ባለመፈጸሙ በሀገረ ስብከቱ ያለው ብልሹ አሠራር እንዲቀጥል እየተደረገ ነው፤›› በማለት ነው መመሪያውን ለኹለተኛ ጊዜ የጻፉት፡፡

ፓትርያርኩ ከልዩ ጽ/ቤታቸው በቁጥር ል/ጽ/312/10/2007 በቀን 14/7/2007 ዓ.ም. ድጋሚ መመሪያ በሰጡበት በዛሬው ደብዳቤአቸው፣ የወቅቱ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን እና ምክትል ሥራ አስኪያጁ መ/ር ኃይለ ማርያም ኣብርሃ ከሓላፊነታቸው መነሣታቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ደረጃቸውን በጠበቀ ኹኔታ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ተዛውረው እንዲሠሩ›› እንዲደረግና ይኸው መመሪያም በዛሬው ዕለት ተፈጻሚ እንዲኾን በጥብቅ አስታውቀዋል፡፡

የፓትርያርኩ የሹመት መመሪያ ‹‹በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅራዊ ሒደት ያልተለመደ ነው›› ያሉት በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በበኩላቸው፣ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅም ኾነ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ተጠሪነት ለቅዱስ ፓትርያርኩ ኾኖ እንደማያውቅና መኾንም እንደማይችል ለቅዱስነታቸው በአድራሻ በጻፉት ደብዳቤ በማስታወስ አካሔዱ ከሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ ከቃለ ዐዋዲ ደንቡ እና ከሀገሪቱ የሕግ አሠራር ጭምር ውጭ ኾኖ እንደተመለከቱት ገልጸዋል፡፡

አሠራሩ የሕግ ድጋፍ የሚኖረው፣ የሀገረ ስብከቱ ረዳት ሊቀ ጳጳስ መርጦ አቅርቦ ከጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ጋር ጭምር የጋራ ስምምነት ሲደረስበት እንደኾነ ብፁዕነታቸው አስገንዝበዋል፡፡ አሠራሩ እንደ አጠቃላይ ሲታይ ከትዝብት ላይ የሚጥል መኾኑን በመጥቀስም‹‹ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሰላማዊ አሠራር ለኹላችንም ሰላም›› ሲባል ፓትርያርኩ ውሳኔአቸውን እንደገና እንዲያጤኑ አሳስበዋቸዋል፡፡ የሹመት መመሪያውን እንዲሰሙት የተደረገው በግልባጭ ቢኾንም በተካሔደው የሥራ አስኪያጅ ምርጫ እንደማይስማሙና የመመሪያውን ተፈጻሚነት ለማስተናገድ እንደሚቸገሩም አስታውቀዋቸዋል፡፡

የፓትርያርኩ ተደጋጋሚ የሹመት መመሪያ በአድራሻ ሲጻፍላቸው፣ መመሪያው ከቤተ ክርስቲያን ሕግና ደንብ አኳያ እንዲጤን የሚያሳስበው የረዳት ሊቀ ጳጳሱ ደብዳቤ ደግሞ በግልባጭ የደረሳቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ማቴዎስም፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ የቋሚ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ ወቅት፣ የቅዱስነታቸውን አባታዊ መመሪያ ለማስፈጸም ዝግጁ መኾናቸውን ነገር ግን አፈጻጸሙ አከራካሪ ሐሳቦችን ስለሚያስነሣ የሚያስከትለው ውዝግብና አለመግባባት አስቀድሞ በስፋት እንዲጤን ጠይቀው ነበር፡፡

ቋሚ ሲኖዶሱን በርእሰ መንበርነት የሚመሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሐሳብ በአጀንዳ ተይዞ እንዳይደመጥ ለማድረግ ‹‹ውሳኔ ነው፤ መታየት አይችልም›› በማለት ቢቃወሙም ቋሚ ሲኖዶሱ ብፁዕነታቸው አስተያየታቸውን በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ትእዛዝ በመስጠት ለቀጣይ ስብሰባ እንዳሳደረው ተዘግቦ ነበር፡፡ በዚኽ ኹኔታ ውስጥ ነው ፓትርያርኩ ሥዩማን ሥራ አስኪያጆቻቸው ሥራ እንዲጀምሩ የሹመት ምደባው በዋና ሥራ አስኪያጁ በኩል በዛሬው ዕለት እንዲጻፍላቸው ለኹለተኛ ጊዜ‹‹በጥብቅ አስታውቃለኹ›› በማለት ያዘዟቸው፡፡

Source:: haratewahido

The post ፓትርያርኩ ቋሚ ሲኖዶሱን በመተላለፍ በድጋሚ መመሪያ ሰጡ፤ ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለከፍተኛ ውዝግብ እንደሚዳርግ በመግለጽ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን ያገነዘበ ተለዋጭ መመሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles