ታላቅ የትዊተር ዘመቻ – መጋቢት 21/2007
ቅዳሜ መጋቢት 12/2007
ካሁን ቀደም ስኬታማ መሆን የቻለ እና ለሁለት ሰዓታት የቆየ የትዊተር ዘመቻ ማድረጋችን ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የተጠቀምነው ሐሽታግም የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት ማግኘት ችሎ ነበር፡፡ ሁለተኛው የትዊትር ዘመቻችን የሚካሄደው መጋቢት 21/2007 ሲሆን ዋነኛ ጭብጡ ‹‹የህዝብ ወኪሎችን በነጻ ከማሰናበት ያነሰ ብይን አንቀበልም!›› የተሰኘ ነው፡፡
እንደሚታወቀው በድምጻችን መርጠን የላክናቸው ወኪሎቻችን በመንግስት የሐሰት ክስ ሲንገላቱ ቆይተው በያዝነው ወር መጨረሻ መጋቢት 30/2007 ለብይን ተቀጥረዋል፡፡ ዛሬ ላይ በወኪሎቻችን መታሰር የታሰርነውም ሆነ የተከሰስነው እኛው የወከልናቸው ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች መሆናችን ከጅምሩም አንስቶ ሲረጋገጥ የቆየ እውነታ ነው፡፡ ሊካድ በማይችልበት ደረጃ ላይም ደርሷል፡፡ በመጋቢት 30 በወኪሎቻችን ላይ የሚሰጠው ብይንም በእኛ በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ የሚሰጥ ብይን መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ለዚህ እውነታ ታሪካዊ ምስክር ለመሆን የፊታችን መጋቢት 21/2007 ሁለተኛውን የትዊተር ዘመቻችንን እናደርጋለን።
የዘመቻው ዝርዝር አፈጻጸሞች እና መርሃ ግብሮች ከፊታችን ባሉት ቀናት የሚገለጹ ሲሆን እስከዚያው ግን አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ እና በቂ የቅስቀሳ ስራ መስራት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ዘመቻውን ከወዲሁ ላልሰሙት ሁሉ በማሰማትም የተሳታፊዎችን ቁጥር ማሳደግ ይገባናል፡፡ ለዚህ የቅስቀሳ ስራ እንዲያግዝ የፌስቡክ ፕሮፋይል ፎቶ እና የከቨር ፎቶ ተዘጋጅቶ በገጻችን ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን ሁላችንም የፕሮፋይሉን ፎቶ እንደፕሮፋይል፣ የከቨሩን ፎቶ ደግሞ ለግል የፌስቡክ ግድግዳችን በከቨር ፎቶነት በመጠቀም ላልሰሙት ሁሉ ለማሰማት ጥረት እናደርግ ዘንድ በአላህ ስም እንጠይቃለን!
‹‹የህዝብ ወኪሎችን በነጻ ከማሰናበት ያነሰ ብይን አንቀበልም!››
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር
The post “የህዝብ ወኪሎችን በነጻ ከማሰናበት ያነሰ ብይን አንቀበልም!” – ድምፃችን ይሰማ appeared first on Zehabesha Amharic.