Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ትርትር …. –ከሥርጉተ ሥላሴ

$
0
0

 

ከሥርጉተ ሥላሴ 21.03.2015 /ሲወዘርላንድ – ዙሪክ/

እኔ እላላሁ እንዲህ —- ዓለም „ሰው“ ለሚለው ቃል የሚመጥን፣ አቅም ያለው ድርጊትም ትርጉምም የላትም። ፍቅር ግን አለው።

ጠፋብኝ – መንደሩ

የብትንድር  – ግብሩ፤

ንክንኩ – ዛለእግሩ

ንክንፋስ – ምግባሩ

ትርትር ሆነ – በትሩ።

ከሥርጉተ ሥላሴ 02.023.2014 (ሲዊዘርላንድ - ዙሪክ)

ከሥርጉተ ሥላሴ 02.023.2014 (ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ)

እኮ ስለምን ይለፍ እንሰጠዋለን?! እኮ ለምን ይፈቅድለታል? ምን ለማትረፍ? እያዘንኩ ልጀምረው። እኛ በእኛ ላይ ወይነናል። እኛ በእኛ ላይ ሸፍተናል። እኛ በእኛ ላይ ጥቃት እዬፈጸምን – ይመስለኛል። እኮ ለምን? ምን ለማትረፍ? ሃዘኑ እያርመጠመጠኝ ልቀጥለው – እስቲ። ዘሃ ግራው የጠፋበት ዘመን ….

ወያኔ አሸንፎናል ወይንስ አላሸነፈንም? ወያኔ በመንፈሳችን ላይ ጫና መፍጠር ችሏል ወይንስ አልቻለም? እኛስ የመንፈሳችን ስደት ወደ ወያኔያዊ ማንፌስቱ አድርገነዋልን ወይንስ ነፃ ወጥተናል? ዳኛው ህሊናችን ይበይንበት።

አሁን ለእኔ የዲ/ዳንኤል „የአገው ብሄረሰብ አባልነት ወይንም የትዳር አጋሩ ‚ትግሬነት‘“ ምን ይፈይድልኛል ለእኔ ጉዳዬ ነውን?“ በነገራችን ላይ የአገው ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ሥልጣኔ ጉልህና ደማቅ ድርሻ የነበረው፤ ግን አቅም ያለው ዕውቅና ያልተሰጠው፤ ብዙም ያልተባለለት ነው። ሌላው የማንዲጎ ጎንደር ተወልዶ ማደግ ምንስ ዕሴት አለው? እራፊ የቀረች መሬት አንድ አረም በቀለባት ተብሎ መከራ ማዬት። የመጣው ሁሉ እንደ ጥንቸል ቤተ – ሙከራ መሆኑ መፈጸሚያ አልበቃ ብሎ ብተውት ምን አለ ጎንደርን ባዕቱ እኮ ህማማት ላይ ነው። ስለምንስ ብሩኩ ቡቃያ የበቀለበት ዬባለቅኔው! ዬቴዲ እትብት የተቀበረበት አልተጠቀሰም። አስፈላጊ ከሆነ ለንጽጽርም ይረዳ ነበር – አረም አብቃዩና ፍሬ ዘለቁ። ይገርም ነው። የአቶ ኤርምያስ ግማሽ ኦሮሞነትና አማራነት ምን ጠቃሚ ጠረን አለው?“ ወይንም የትናንት በሥርዓትና በሀገር ደረጃ የተከወነ ዛሬም ያለ ኢትዮጵያን የማጥቃት የውጭ ዝንቅ – ገብ ሂደት ከእኛ ጋር ተዋልደው፣ ተጋብተው፣ ተዛምድው ያሉ ወገኖች እዬነቀሱ „የዚህኛው የዛኛው ብሄረሰብ ሃይማኖት ነገድ አባል አይሁድ ምንትስ ማለትስ ምን አመጣው?“ ለዛሬ ወይንስ ለነገ በረከት ይሆናልን? ዛሬም እዬተሰደድን፤ ዛሬም ጥገኝነት እዬጠዬቅን፤ ዛሬም እርዳታ እዬጠዬቅን፤ ዛሬም ከውጭ ሀገር ዜጎች ጋር እዬተጋባን፤ ልጆች እዬወለድን ትናንት እንዲህና እንዲህ ነበሩ በስተጀርባ እከሌ የሚባል ሀገር ነበር ማለቱ ይገባልን? ነገም እኮ ኢትዮጵያ ተለይታ ደሴት ሀገር ልትሆን አትችልም። አስፈላጊው የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከመላው ዓለም ጋር ጠንክሮ ቀጣይ ነው።

ህም! ለነገ ደግሞ ስደተኞችን ለይቶ መተንተኑስ … ክቡሩን የሥጋ – ወደሙ ጋብቻ ከማፈናቀል አንፃርስ ይህ ዝንባሌ  ሃይማኖታዊ ነውን? „ትግሬ“ የትዳር አጋሩ የሆነ ሁሉ በሚፈጽመው የራሱ አሉታዊ ሆነ አዎንታዊ ተግባር ባለቤቱ እያለ ሌላ መንጠላጠያ ሳቢያ መፈለጉ ምን አስፈለገ? ስለምን በምክንያቱ ላይ አናተኩርም? ለዚህም ነው መፍትሄ አመንጭነታችን ታቱ የሚለው። የሚነካካ ነገር ይፈለጋል። የሚወገዝ ነገር ይፈለጋል። ነገ ደግሞ በዚህ ጎሳዊ ማንፌስቶ ተገደው በጠበንጃ ታፍነው የዕለት ኑራቸውን የሚገፉት እዬተነጠሉ ስደት ይታጭላቸዋል። መልካም ነገሮችም አብረው ይናዳሉ – ጥናት አልባ በሆነ ሁኔታ። የሀገር ሃብትነቱ ይዘላል። ለዚህ ከሆነ የነፃነት ራህቡ … ቁርጭምምጭሚቱ ውልቅ ይሆናል። ዛሬም እኮ መስዋዕት የሚከፍሉ ወገኖቻችን አሉበት። በእግር ብረት ሥር ሆነው ስለነፃነት ግንባራቸውን የሚሰጡ – ማገዶዎች አሉበት። በሌላ በኩልም ዬአካላቸውን ካቴና ችለው ኃላፊነት ወስደውም ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳደሩ፤ ዱላውንም – መፈንከቱንም ግልምጫውንም የወያኔን የቻሉ። ዓይን እያዬ ጆሮም እዬሰማ …. ህ!

ብቻ ለእኔ ዜሮ ሲደምር ዜሮ ወይንም ዜሮ ሲባዛ በዜሮ ሆኖ ነው ያገኘሁት። የሚጠቅመው ለምሳሌ፤  ሥርጉተ በተሰማራችበት፤ ወይንም ኃላፊነት ወስዳ በምታራምደው – እምነት ወይንም የፖለቲካ መስመር፤ ያጠፋቸውን ነገር ነቅሶ በማውጣት፤ በትኖ በመተንተን እሷኑ እራሷን ሞግቶ ማሸነፍ፤ ወይንም እድትታረም ማደረግ ነው እንጂ ሥርጉተ ያደገችበት ማህበረሰብ ወይንም ነገድ አብሮ መወቃት – መታጨድ የተገባ አይደለም። እኔ ላጠፋሁት – ለበደልኩት – ላባከንኩት – ለተሻማሁት ጊዜ ተወቃሿ እኔ ብቻ እንጂ ሌላ ቦታ ስደት መሄድ አያስፈልግም።  „ትግሬነት፤ ኦሮሞነት፤ አገውነት፤ አማራነት፤ ጎጃሜነት፤ ጉራጌነት፤ ሃድያነት፣ እስራኤላዊነት ወዘተ – ወዘተ“ የወል መጠሪያ ነው። በዛ ብሄረሰብ ስንት መልካም ሰዎች፤ ስንት ደጎች፤ ስንት አብነቶች ስንትስ የአደራ ናሙና ዜጎች አሉን? እልፍ ናቸው …

በዛ የማህበረሰብ ማዕቀፍ ስንት አንቱዎች፤ ስንት ሊቀ – ሊቃናት፣ ስንት ቅዱሳን አሉ? እልፎች። …. የተጸዎዖ ስም እኮ የወጣበት ምክንያት እኔን እንዲገልጽ ሆኖ ነው። የወል ሥምም እንዲሁ። ….. የወሉን ሥነ – ሞራል፣ ሥነ – ምግባር ሥነ —- ኑሮ፤ ሥነ – ታሪክ እንዲገልጽ ነው። በአንድ ማሳ አረም ይበቅላል። ፍሬ የሚሰጥም እጽዋትም ይበቅላል። አረሙ ከማደጉ በፊት ዘር እንዳያበላሽ ተነጥሎል ይነቀላል። ፍሬ ዘለቁ ደግሞ እድገቱ እንዳይደናቀፍ ተመጣጣኝ አዬርና ህልው የሚያድርጉ ነገሮች ይሟሉለታል። አሁን እኛ እያደረግን ያለው ግን እንደዛ አይደለም። ሁሉንም አረም እያደረግነው ነው። ትውልድን ለማተካካት ድርሻን በዚህ መልክ መከወን ሰባራ መንገድ ነው። ማንዘርዘሪያ ዬት ይገዛ ይሆን?! ይህ ማለት ግን በዳይም – ተባዳይም፤ የበለጠ እጁን ተጠቃሚ የለም ማለት አይደለም። ከጎሳ ፓሊሲ የሚጠበቁት አሳሮች ሁሉ እስከፈለጋቸው ድረስ፤ በረዶው ሁሉ እስኪበቃው አድቅቆናል ወረራውም – ደቁሶናል። ህልማችን በመሰሉ አይጓዝ ነው ብልሃቱ። ተሽሎ መገኘት የሚባል ብሂል አለ ….

የሆነ ሆኖ „ዛሬ የአማራ ወጣቶች እራሳችን መቻል እንችላለን። ስለዚህ እንገንጠል“ የሚል ጥያቄ እንዳነሱ አንብቤያለሁ። ብዕሯ መከፋቷንም አብራ ጨምራ ግልጻለች። እኔም በተደሞ ነበር ያነበብኩት። እንዲሁም በዚህ ዙሪያ ልንሠራበት የሚገባውን ተግባር እያወጣሁ እያወረድኩ እያለ፤ ቀጣይ ጹሑፍ በተከታታይ ወጣ። ዘር ቆጠራው ቀጠለ። ዝንቅንቅ ያለ- ጭብጡም የተቦጫጨረ – ጉድ። „አይሁድ፣ አገው ወዘተ ወዘተ .. ምንትሶ ቅብጥርሶ“ ምን ያድርጉ እነዚህ ወጣቶች!? ወያኔ በፓሊሲ ደረጃ ጎሳዊ ሶሻሊስትን ንድፈ ሃሳብ ፀንሶ – ወልዶ – አሳድጎ – እዬበተነ እኛ ደግሞ በራሳችን መንፈስ የወያኔ ሃርነት ትግራይን ማንፌስቶ ፍለጋ ስደት ፈቃጅ እንሆንለታለን። እያንዳንዷ የዚህ መሰል ስንጥርና ስንጠቅ ሂደት በኢትዮጵያዊነት ላይ ጫና እዬፈጠረ ስለመሆኑ ከልብ ማሰብ ያስፈልጋል። አንዳንድ ወገኖችን ስታወያዩ ተቆርቋሪነታቸው በሁለመናነት ታያላችሁ። ከዛ – ከዛማ ደስ ብሏችሁ አብራችሁ ስትወያዩ መጨረሻ ላይ መዳራሻቸው ከጎሳቸው ላይ ይሆናል። ስለምን? እኛም አብረን በጎጥ፣ በመንደር ዶክተሪን እንዲህ ብልዩነት መስመር ተመስጠን እዬሠራንበት ስለሆነ። ማርክ ቢሰጥ … ውስጣችን ስለ መውደቁ ማወቅ ቀላል ነው። ለዚህም ነው የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ ጥቃት በሰነዘረባቸው ላይ ተባደግ ዕይታ የሚኖረን፤ አርበኛ በላይነሽን የሚያደንቅ ርዕዮትን አይጨምርም፤ ርዕዮትን የሚል ኦልባና ሊሊሳን አያክልም፤ ኦልባና የሚል አንዱአለምን አያካትም፤ አንዱአለም የሚል አቡበከርን ይዘላል፤ አቡበከር የሚለው አብርሃምን ይተዋል፤ አብርሃም የሚለው አንዳርጋቸውን ይሰርዛል ወዘተ .. ወዘተ ። ቃል የማውጣት አቅም ያንሳል። መርምሩት – ወገኖቼ በትህትህና፤ አቅማችን ዋጥ የሚያደርገውን አሳማውን ዝንባሌ ….

ይህም ብቻ አይደለም በተገኘው አጋጣሚ ክፍተት የሚፈጥሩ ነገሮች መደፈን ሲጋባቸው – ይሰፋሉ።  „ሊቃውንተ ቤተክርስትያን እኔን ሲያስተምሩ „ነብዬ መሃመድ“ ብሎ መጥራት ወንጀል ነው ብለው አልነበረም። ይልቁንም ማዕድ ላይ እያሉ „‘አላህ አክብር‘ ሲታወጅ፤ እኛ ማዕድ ላይ ሆነን አነሱ ግን ፈጣሪያችን ያመሰግናሉ ይሉ ነበር – በአድናቆት፤ ዝናብ ሲኮርፍ እባካችሁ ለእነሱ ንገሩ ድዋ – ያድርጉ፤ እኛም ምህላ ለሁለት ሰባት እናደርጋለን ሲሉ‘ የዓለም ሊቃውንት 100 ድንቅ ካሏቸው የሥነጹሑፍ ምርቶች ውስጥ ነብዬ መሐመድ አንዱ ናቸው ሲሉ ነበር ያነበብነው“ እንዲህ ሁሉም ነገር መጫሪያ ፈላጊ ሆኖ ቋፍ ላይ ባለበት፤ ሆድ በባሳው ወቅት፤ በግልም በጋራ ዕንባን አምጦ፤ አልቅሶ ውሎ በሚያድርበት የጨለመ – ምዕራፍ ላይ ሆነን እንዲህ ባሉ ጠመዝማዛ የአረም ቅንጦቶች መጓዙ ዛሬንም አያበረክትም። ነገንም አያሰመርቅም። የትናንት አደራንም አያሰነበትም። ተከታይም – አያገኝም። አንድ መምህር ለትምህርቱ አጋዢ ማነጻጸሪያ ወይንም መንተራሻ ቢያስፈልገው መንቀሳቀስ እንዳይችል እስር እኮ እዬተበዬነበት ነው – ህም! ሥምም ማዕቀብ – ድንበር ተጣለበት። ወዮ ነፃነት! በለስ ቢቀናሽ ሥንት የቤት ሥራ እንዳለብሽ እስኪ መትሪው —-

እኛም እኮ መሃመድ የሚባሉ ብዙ ደሞች አሉን እኮ። መሃመድ በሚል ሥያሜ የሚጠሩ የነገ ሀገር ተረካቢ ልጆች አሉን። ወገኖቼ „መሃመድ“ የሚባል ጓደኛ፤ የሥራ ባልደረባ፤ ባለ ሱቅ፤ ጎረቤት ወዳጅ ቢኖራችሁ ሥሙን ስትጠሩ በጥቅሻ ሊሆን ይሆን?! ምን አይነት አሲዳዊ ፍሰት እንደሆነ ለእኔ ግራና ወልጋዳ ነው። ግብጽ ላይ እኮ የቅዱስ አባታችን የአቡነ ተ/ሃይማኖት በክብርና በሞገስ መታሰቢያ አለ። http://en.wikipedia.org/wiki/Tekle_Haymanot። በሀገረ ግብጽ በገዳማት ያሉ ደናግል ሆኑ ማህበረ ምዕመናኑ መጠሪያም እንደ ሀገራቸው የአጠራር ዘይቤ ሲሆንም ቋንቋውም እንዲሁ። ዘልቀን ብንገባበት ያነንም እንወነጅል ይሆን? የትኛውም ዓለም ቅዱስ ጊዮርጊስ መታሰቢያ ብቻ ሳይሆን እልፎች ይጠሩበታል። … እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ስለምን ሃጢያተኛ በዛ? ለሚለው ዲያቢሎስ ስለሚያስታቸው ነውና ስለምን ከዲያቢሎስ ጋር እርቅ አታደርግም ብላ አምላኳን ፈጣሪያዋን ስለመጠዬቋ ከታምሯ ላይ አለ። የእሷ ጭንቀት ለኢትዮጵውያን ብቻ አልነበረም፤ ለዓለም እንጂ። … ቅዱሳን ሀገር የላቸውም፤ የትም ቦታ በዬትኛውም ሁኔታ ሊፈጠሩ ሊላኩ ይቻላሉ።

እንዲህ መላ ተቋማት ኢትዮጵያዊነትን የሚያውጁ በመንፈስም በአካልም ጦር በተመዘዘባቸው ወቅት „ወደ ማንነት ማዬት“ አምራጭ የለሽ መፍትሄ ሆኖ ሳለ፤ የቁርሾ ጉድፍ መበተን በፍጹም ሁኔታ ከትውልዱ ድርሻ ውጪ ነው – ለእኔ። እርግጥ የበለጠውን ጉዳት የሚያውቁት የዬአካባቢው ተወላጆች ስለሆኑ፤ ለመረጃ ልውውጥ ካልሆነ በስተቀር ለነገ የኢትዮጵያዊነት አቅም መቅኖ ግን የግልሰቡን ጎሳ ወይንም ባዕት እዬነጠሉ ማቅረብ፤ ተጠያቂም ለማደረግ ማስላት እጥፍ ድርብርብርብ ኪሳራ ነው። የዚህን የእኛ ትውልድ ዋንኛ የተልዕኮም ዕጣም ሆነ አቅጣጫም ቅርጭጭታም፤ ቀጫጫም ያደርገዋል – ባይ ናት ሥርጉተ – ሥላሴ።

ሰው በማንነቱ፣ በእሱነቱ፣ ከውስጡ ነፃነት እንዲሰማው ያስፈልጋል። ሲተችም፣ ሲጽፍም ነፃ ሆኖ መፃፍ የሚችለው በዚህ መንፈስ ሲሆን ብቻ እንጂ ገና ከዚህ አካባቢ እትብቴ ስለተቀበረ፤ ወይንም ሃይማኖቴ ይህ ስለሆነ ወይንም ነገዴ ይህ ስለሆነ፤ ወይንም የትዳር አጋሬ እንዲህ ስለሆነች ብሎ ስጋት ሊኖርበት አይገባም። ቀጥ ብሎ ለመቆም በራሱ የተማመነ፤ ማንነት ካለ እራሱን ገልጦ ውስጡን ማሳዬት ይቻላል። ውስጡን ማዬት ከተቻለ የጎሸውን ለማጥራት፤ እንክርዳድና ግርዱን መለዬት ብቻም ሳይሆን ጤናማና አዎንታዊ መንገድ ለመደልደልም ያስችላል። የተጎዳውንም አይዞህ ከጎንህ ነን ለማለት ይረዳል። ይህን እኛው ከነፈግነው ግን የድብብቆሽ ጨዋታ ይሆናል። የድብብቆሽ ጨዋታ ደግሞ ራዕዩን የድቡሽት ቤት ያደርገዋል፤ ርህራሄ – የለውምና። ከሁሉ በላይ ለወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ በፈቃድ እጃችን ሰጥተናል ማለት ነው። ተወረናል። አቅምም አይኖርም የጎሳ ማንፌስቶን የመተቸት፤ የማውገዝና የመታገል። ነገም ወጮፎው ያዬለበት ዳመናማ ነው።

በአንድ ሥርዓት ውስጥ እልፎች ሠርቶ በማደር መኖር ግድ ይላቸዋል። ሌላም ሃላፊነት አለባቸው። እኛ ትተነው የመጣነውን ትውልድን የመተካት። ከዚህ ውጪ አማራጭ የለም። ስደቱም ቢሆን የአንድ ሀገር ህዝብ እንዳለ ሊሰደድ ከቶውን አይችልም። ጫካ ልግባ ቢልም እንደዚሁ። እኛ ደግሞ አንድ የነፃነት አርበኛ እስረኛ ቤተሰብ አብልተን ለማሳደር የምንችል አይደለንም። እንኳንስ ለእልፍ አለንልህ በማለት ለኑሮው መደጎም። ቀላሏን በወር አንድ ብር በዓመት በነፍስ ወከፍ 12 ብር እንደዬአለንበት ሀገር ማዋጣት እንኳን የምንፈቅድ አይደለንም። በእጃችን አለን የምንላት ቤሳ ሳንቲም የለንም። አቅም ያለው እራሱን በራሱ የሚያስተዳደር ተቋም ለዘር – የለንም። እንኳንስ ከዚህ የላቁ ነገሮችን ለመከወን። ፕሮጀክቱን ለመዘርጋት ቢታሰብም እንኳን፤ ፕሮጀክቱ ከመፈጠሩ በፊት ለራዕዩ ቀብረ – ሥርዓት ይታወጃል። /እራሴ ሞክሬ አይቸዋለሁ/  10 ሺህ ወገን በወር አንድ ብር ቢያወጣ 10 ሺህ ይሆናል በዓመት ደግሞ 120ሺህ …. ይሆን ነበር። ከሁሉ በላይ መንፈስን ወጥ አድርጎ የመግራት፤ አቅሙም አንቱ ነበር ተጨማሪ የኃይል አምንጭነቱም ጉልላት ይሆን ነበር። ሌሎችም ዕምቅ ትርፎች አሉበት ምህረት እርቅ ተስፋ ፍቅር ወዘተ … ለማንኛውም መድረስ አለመቻል ነው መጠነ ሰፊው ህዝብ ተጎጂ ሆኖ ግን ሰጥ ለጥ ብሎ እዬተገዛ ያለው። መድረስ አንችልማ? ቅልብጭ ያለው እውነት ቁምነገርም ይሄው ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ ቁልጭ ያለ ባርነት ነው ያለው። ዴሞክራሲ ከባርነት ነፃ ለወጡ ሀገሮች ነው። „ እዬዬም ሲደላ ነው።“ የኛው ግን ከጎጥ አገዛዝ ባርነት ገና አልወጣነም። በዚህ ሁለመናው እራስ ከእግር በሆነ ሁኔታ ላይ ሁነን ተጨማሪ ችግር ለዛውም ጥላቻ- ንቀት – ዘር በጣሽ መስመር ስንቀጣጥል ወይንም ስናመርት ውልን እናድራለን። — ምግለት!

ለመሆኑ አዲስ ሥርዓት ተሳክቶ ቢመሠረት ከሥራአቱ ጋር የሠራህ እዬተባለ ደግሞ ሌላ የስደት መንገድ፣ የመከራ ዘመን ልናጭለት ይሆን – ለዚህ መከረኛ ህዝብ? ህ! ዛሬ ሥልጣን ላይ ያለው የትግራይ ወያኔ ሃርነት ማንፌስቶ ነው። ነገ ይህ ማንፌስቶ አመድ ቢሆን፤ በዚህ ሥያሜ ሥር የነበሩ በሥርዓቱ ውስጥ ሠርተው ለማደር እንደ ሌሎች ይገደዱ የነበሩ የነገዱ አባሎች ወገኖቻችን ከእነሱ ጋር የተገባ፤ የተዋለደ ወገን አብሮ በነቂስ የበቀል መሻሪያ ሊሆን ነውን?! ሃራም ጋብቻ፤ ሃራም ጉርብትና፤ ሃራም አበልጅነት ሊባል ነውን? የጋራችን ልጆች ደግሞ እኮ አሉ። ለማን ነው ድካሙ?! ለቀጣዩ ትውልድ አይደለንም? ልጅነት እኮ የአንድ ነጠላ ቤተሰብ ብቻ አይደለም። ኃላፊነቱ የማህበረስብ ነው። እርክክብ አለ – የትውልድ። እንዲህ ያለ የተጋጋጠ ወይንም ጠረኑ የተነነ – ብዕር ለእኔ አረም የዘራ፣ አረም የሚያመርት፤ አረም የሆነ መንፈስ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነቱን ወዶ ስደት የላከ ነው። እራሱን አጥቷል በፈቃዱ። „ተቆርቋሪነት“ ትልቅ ተልዕኮ አለው። እጅ – ለእጅ፤ ደም – ለደም፤ ሥጋ – ለሥጋ፤ የሚያያዝባቸው ሊቃናተ – ሁነቶች እረቂቃን ናቸው።

እንጃ! እንዴትና እንዴት ይሆን እምናስበው? ከቱግታ ወጥተን ተግ ላይ እንስከን፤ ኢትዮጵያዊነት በዕውን በውስጣችን ካለ፤ እንዲሁም ያ ክቡር ሰንደቅዓላማ በወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ ህግ ስለታሰረበት ወገን፤ — የለበሰው፣ ሰንደቁን ያፈቀረ ምክንያት ተፈልጎ ግዞት መላኩ እያገላበጠ መንፈሳችን – ከቀቀለው። እባካችሁን እራሳችን ‚እራሳችን‘ እንዲቀማው አንፍቀድለት?!!!

ወደ ራሳችን እንመለስ – በአክብሮት። ወደ ክብራችን እንመለስ – በዘንካታ ትህትና፤ ወደ ውስጣችን እንይ – በጀርጋዳ ቅንነት፤ ወደ ሥነ – ትውፊታዊ ህይወታችን እናስተውል – ከልባችን። የውበታችን ረቂቅነት ከልባችን ይግባ፣ ከደማችን ጋር ይመሳጠር – ያውጋም። ግልቢያ – ለፈረስ ነው፤ ስግረትም – ለወንዝ፤ በረራም – ለወፍ፤ የሰው ልጅ አላምጦ መዋጥ አለበት። „አደራ ለዛውም – የሀገር አደራ፤ አደራ ለዛውም – የዜግነት አደራ፤ አደራ ለዛውም የአኩሪ ታሪክ ባላቤትነት መለያነት – የነፃነት አደራ አለብን፤ አደራ ትውልድን ገንብቶ የመተካት ውድ አደራ አለብን። አደራ በመሆን የከበረ የፍቅር ልዑቅ አደራ አለብን“ ለዚህ እንማስን። የጠላትን ጥቃትን የሚቋቋም ሙሉ አኃታዊ ሥነ ምግባርን አምጠን እንውለደው። የጥቃታችን መሠረተ ፍሬ ነገር የጎጥ ዶክተሪን ነውና።

የትም ሀገር የተሰደደ ወይንም ሊሰደድ ያሰበ፤ ወይንም በትምህርት – በጋብቻ፤ ውጪ የሚወጣ ሁሉ መጀመሪያ ፎርሙን የሚሞላው „ኢትዮጵያዊ“ ብሎ ነው። ወያኔ የፈጠረውም ይሁን እኛ እያመጣን ያለው ልጥፍ ልሙጥ ጉድ ለውጭ ሀገር ዜጎች እራሱ ባዕድ ነው። የሚገርመው በዚህ ማንነት ውስጥ ኑሮ ከተደላደለ በኋላ የተገለበጠ እራስን ያልሰጠ መሽሎክ ይታያል። እሱን ህሊና ይዳኘው። ነገም ቢሆን ኢትዮጵያ የሚለው ሥያሜ ይጠፋል ብሎ ማሰብ መሽቶ አይነጋም ማለት ነው። ወይንም አህጉራት ሁሉም ሰባቱ ውቅያኖስ ይሆናሉ ብሎ ማለም ነው። የዕውነት ፍልቀቱ ዳርቻ የለውም። ኢትዮጵያዊነት ዕድሜውን መገደብ አይቻልም። ዘላቂ ነውና … ። የጎሳ ራዕይ በራሱ ጊዜ በመዳህኒዓለም ጥበብ ከስሟል። በዬትም ዓለም ከእንግዲህ እንደበፊቱ ቁልምጫ የለም።

ለማንኛውም መለመድ ያለበት መንገድ ለዛሬም ለነገም፤ የትኛውም ወገኔ እኔ ባጠፋሁት፣ በፈጸምኩት ስህተት ብቻ ሳይሆን፤ ስህተት ነው ብሎ ባሰበው ወይንም በሚመስለው ወይንም ስህተት ነው በሚለው ቢፈልግ ይክተፈኝ፤ ይተርትረኝ፤ ይፍለጠኝ፤ በመዶሻ ይቀጥቅጠኝ። ከቻልኩ ሙግቴን አቀርባለሁ፤ ከናቅሁት ደግሞ እተወዋለሁ፤ ነገር ግን ዕትብቴ የተቀበረበት ክ/ሀገር ሆነ ነገዴ ወይንም የሃይማኖቴን ዶግማ ግን መንካት የለበትም። በፍጹም። ትዳሬና አካሌም። ደግሞ ነፃነት የዘር ሀረግ ቆጠራ ቀመር አይደለም። ነፃነት ያደገና የሰለጠነ – ሰው የመሆን፤ እንደ ሰው ለመኖር ፈቃዱን ሰው የመስጠትም ሆነ የመንሳት መብት እንዴለለው የሚገልጽ ልዩ ክስተታዊ የእኩልነት አምክንዮ ነው። ነፃነት በጭነት አይተረጎምም። ጓዘ ቀላል ነው።  ….

በመጨረሻ እምለው ኢትዮጵያ ሀገራችን የአድምታ ሚስጢር ልዑላን ዲታ ናት – ተርፎም ይናኛል። ንባቡን፣ ትርጉሙን፤ ማመሳጠሩን ዓራት ዓይናማዎች አሉበት። ክህነተ ሥልጣን የመስጠትም የመነሳትም አቅም ያለው ሃይማኖታዊ ዶግማ በማስፈጸም ከአቨው ነው። ለነገሩ ሥልጣነ ክህነት ሰውኛም አይደለም። „ካልተሠራበት እሳት ሆኖ ያቃጥላል“ ይላሉ – አቨው። ጠያቂውም መዳህኒተአለም ነው፤ እንደ ሥራው ይላል መጸሐፉም። ባለቤቱ „ቅብዕ – ሥልጣኑን“ ቢያረክሰው እንኳን „ተመሥጥሮ ክብሩ አለ“ ይላሉ – አቨው። ስለዚህም „አትዳፈሩት!“ ብለው በአፅኽኖት ይመክራሉ። ለነገሩ እኔ „እኔን“ ሳከብረው ሌላውም እኔን ያከብረኛል። እኔ ሌላውን ሳከብረው ከሌላው ጋር ያሉ መንፈሶች ሁሉ እኔን ያከብሩኛል። ስጥለው ክብሬን የትም ደግሞ ሁሉም የክብረት መንፈስ ይሸሸኛል።

እህ! ሌላስ ያደግነበት ማህበረሰብ እኮ ታላቆችን ወንዶች ጋሼ፣ አይዋ፤ እያያ፤ ጥላዬ፣ ጋሻዬ ብለን አክብርን አቆላምጠን አልበረንም የምንጠራው፤ ሴቶችን እትዬ፣ አቫዬ፣ እቴ-ወለላዬ፣ እታታ፣ እታለም፤ እቴዋ፤ እቴ-አባባ፤ እቴ-አንጀቴ፤ እቴ-ማሬ አልነበረም? ብልህ አዋቂዎችን፤ ማር፣ ቀኝ ጌታ፤ የኔታ፣ ብላቴ፣ ጌታ፣ አለቃ አልነበርንም፤ እንኳንስ ዬሥርዓተ – ቤተክርስትያናት ዓዕማዳተ – ሃውልተ – ሚስጢራት ያለበት „ዲቁና“ ወይንም „ነብይነት“። እንደ ወርዳችን እና ቁመታችን ልክ ቢኖረን መልካም ነው። ልቅነት የእኛ አልነበረም። ጎንደሬም ሲተርት „ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል“ ይላል። ልብ ይስጠን አምላካችን። ከእኛ በመንፈስ በላቀ ጥንካሬና ጽናት ሆነ፤ በማገዶነት የተሻለውን የሚያደርጉት ግን ያልበሉትን ዕዳ እንዲከፍሉ የተገደዱትን አዲስ የትውልዱ – የዘመኑ ባለቤቶች /ግርድ – ድቃቂ – እንክርዳድ/ እዬዛራን አናምሳቸው – እባካችሁን /// //////  መሸቢያ ሳምንት – ለእኔዎቹ። ውዶቼ ዘሃበሻ! እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል።

ኢትዮጵያዊነት አሸናፊ ቀለማም ማንነት!

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

The post ትርትር …. – ከሥርጉተ ሥላሴ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>