ኤልያስ ገብሩ በፌስቡክ ገጹ እንደዘገበው:-:-
ዛሬ መጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም፣ በከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በቂሊንጦ እስር ቤት የሚገኙት እና በእነዘላለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ ያሉ 10 ሰዎች ቀርበው ነበር፡፡ መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመቀበል እና ከ1-5ኛ ተራ ቁጥር ያሉ ተከሳሾች በእስር ቤቱ ደረሰብን ብለው ባቀረቡት አቤቱታ ላይ አስተያየት ካላቸው ለመቀበል መሆኑን የችሎቱ የግራ ዳኛ ገልጸዋል፡፡
የተከሰሾቹን የጽሑፍ አስተያየት በጠበቃ ተማም አባቡልጉ በኩል ቀርቦ ከመዝገብ ጋር ከተያያዘ በኋላ ተከሳሾቹ በየተራ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ የግራ ዳኛው በመናገር 1ኛ ተከሳሽን ‹‹በክሱ ላይ እንደቀረበው ወንጀሉን ፈጽመሃል ወይስ አልፈጸምክም?›› ሲሉ ጠየቁት፡፡
ዘላለምም ‹‹አቃቤ ሕግ ባላደረኩት ነገር ህጉን መደገፍ ስለሚሆንብኝ ምንም መልስ አልሰጥም›› ሲል ዳኛው ‹‹በሥነ ሥርዓት ሕጉ ክሱን ክደው ተከራክራል› በሚል መዝግበነዋል›› በማለት መዝገብ ላይ አሰፈሩ፡፡
2ኛ ተከሳሽ አቶ ሃብታሙ አያሌው በበኩሉ ‹‹የተባለውን ለነገር (ሽብር) አለማድረጌን ከእኔ በላይ የከሰሰኝ መንግሥት ጠንቅቆ ያውቃል፤ እረዳለሁም፡፡ አቃቤ ሕግ ለምን እንደከሰሰኝም አውቃለሁ፡፡ የቆምኩለትን ሕጋዊ ፓርቲንም አፍርሶታል፡፡›› ብሏል፡፡
3ኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ሺበሺም ‹‹ሽብር የሚባለውን ነገር የሰማሁት ከሟቹ ኦሳማ ቢንላዳንና ከዘቶ መለስ ዜናዊ ነው፡፡ አደረክ ለተባልኩት ነገር ሃይማኖቴ፣ ዓላማዬ …አይፈቅድም፡፡ በዚህ ምክንያት ቤቴ እንዲወሰድ ተደርጓል፡፡ እኔ አሸባሪ አይደለሁም፡፡ ኢህአዴግ አሸባሪ ነው፡፡ ለሽብር ሀሳቡም ፍላጎቱም የለኝም፡፡ መንግሥት ፓርቲዬን ለማፍረስ የፈነቀለው …›› ብሎ ሳይጨርስ ፍርድ ቤቱ ንግግሩን እንዲያቋርጥ አስገድዶታል፡፡
4ኛ ተከሰሽ አብርሃ ደስታ መናገር ከመጀመሩ በፊት ‹‹ድርጊቱን መፈጸም አለመፈጸምህን ብቻ ተናገር›› ተብሎ ከችሎቱ ተነግሮት ነበር፡፡
አብርሃም በተረጋጋ መንፈስ ‹‹መልሱ እሱ አይደለም፤ የፈለኩትን እናገራለሁ፡፡ ሀሳቤን ልግለጽ›› ሲል ተናገረ፡፡ ዳኞች ሳይዋጥላቸው እንዲናገር ፈቀዱ፡፡ ‹‹ክሴ ከአሸባሪ ጋር በመገናኘት …የሚል ነው፡፡ አሸባሪ ለሚፈልገው ዓላማ ሰላማዊ ያልሆነ /ሰውን የሚጎዳ ድርጊት የሚያስፈጽም ነው፡፡ ለእኔ ብቸኛው አሸባሪ ህወሃት/ኢህአዴግ ነው፡፡ እኔ ህወሃት/ኢህአዴግ ተቃዋሚ ነኝ …›› የግራ ዳኛው የአብርሃን ንግግር አቋረጡትና ‹‹ክሱ ላይ ህወሃት/ኢህአዴግ የሚል የለም፡፡ ክሱን መቃወም አለመቃወምህን ብቻ ተናገር›› አሉት፡፡ አብርሃም ‹‹ሕወሃት /ኢህአዴግ፣ ደህንነቱ ማፊያ ነው … ›› ዳኞቹ በድጋሚ አቋረጡት፡፡ አብርሃ ‹‹አልጨረስኩም›› ቢልም ዳኞቹ ከዚህ በላይ ሊሰሙት አልፈቀዱም፡፡
5ኛ ተከሳሽ የሺዋስ አሰፋም ‹‹ዛሬ ለመጨረሻ ጊዜ ነው የምናገረው፣ ስሙኝ›› ሲል ለችሎት ገለጸ፡፡ ዳኞቹ ክሱን መቃወም አለመቃወሙን ብቻ እንዲናገር ገለጹለት፡፡፡ የሺዋስ ‹‹ትንሽ ሁለት ደቂቃ የምትሞላ ንግግር ነች፡፡›› አላቸውና ቀጠለ፡፡ ‹‹ሕገ-መንግሥቱ በአንቀጽ 75/4 ላይ ልዩ ፍርድ ቤት ስለማቋቋም ይደነግጋል፡፡ ይሄ 19ኛ ችሎት የጦር ፍርድ ቤት ችሎት እየመሰለ ነው፡፡ ሕገ-መንግሥቱ ዳኞች ነጻ ስለመሆናቸው ይደነግጋል፡፡ የእኔ ችግር ችሎቱ ላይ ነው፡፡…›› ዳኞች የየሺዋስን ንግግር አቋረጡት፡፡ የሺዋስም ‹‹ዛሬ ብቻ ነው የምናገረው›› በማለት እንዲህ አለ፡- ‹‹በሕገ-መንግሥቱ ላይ ዳኞች ነጻ መሆን እንዳለባቸው ቢቀመጥም የመርማሪ እና ዐቃቤ ሕጎችን ሀሳብ ብቻ የሚሰማው፤ እኛን አይሰማ አሻንጉሊት ፍርድ ቤት ነው፡፡…›› የሺዋስም መናገር የቻለው ይሄን ብቻ ነው፤ ዳኞች ድጋሚ አስቁመውታል፡፡
6ኛ ተከሳሽ፣ ዮናታን ደግሞ ‹‹ያለፈቃድ እንድትናገሩን እየተገደድን ነው›› ብሏል፡፡ 7ኛ ተከሳሽ (ስሙን የዘነጋሁት) ‹‹የተቀነባበረ ክስ ስለሆነ ምንም ማለት አልችልም፡፡›› ሲል 8ኛ ተከሻሽ ባህሩ ታዬም ‹‹ሃይማኖቱንና ማኅበረሰቡን ከሚፈራ ህዝብ ውስጥ ወጥቼ እንዲህ አይነት ተግባር አልፈጽምም፣ አለፈጸምኩምም፡፡ …ጊዜ እውነቱን ይፈርዳል›› ሲል ቃሉን ሰጥቷል፡፡ 9ኛ እና 10ኛ ተከሳሾችም ‹‹ድርጊቱን አልፈጸምንም›› ብለዋል፡፡
ችሎቱም ‹‹ለአንድ ወር የለንም›› ካሉ በኋላ 15 የአቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ለግንቦት 13፣ 14 እና 17 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡
The post የነአብርሃ ደስታ, ሃብታሙ አያሌውና ሌሎችም የፍርድ ቤት ውሎ:- ‹‹እኔ አሸባሪ አይደለሁም፡፡ ኢህአዴግ አሸባሪ ነው፡፡ ለሽብር ሀሳቡም ፍላጎቱም የለኝም›› ዳንኤል ሺበሺ ‹‹የተባለውን ለነገር አለማድረጌን ከእኔ በላይ የከሰሰኝ መንግሥት ጠንቅቆ ያውቃል›› ሀብታሙ አያሌው ‹‹ለእኔ ብቸኛው አሸባሪ ህወሃት/ኢህአዴግ ነው፡፡ እኔ የህወሃት/ኢህአዴግ ተቃዋሚ ነኝ›› አብርሃ ደስታ ‹‹ይሄ 19ኛ ችሎት የጦር ፍርድ ቤት ችሎት እየመሰለ ነው›› የሺዋስ አሰፋ ‹‹ሃይማኖቱንና ማኅበረሰቡን ከሚፈራ ህዝብ ወጥቼ እንዲህ አይነት ተግባር አልፈጽምም›› ባህሩ ታዬ appeared first on Zehabesha Amharic.