ይህ ጽሁፍ በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ቁጥር 72 ላይ ታትሞ ወጥቷል
- የተሳሳተ ምርት መምረጥ
ፊትን መታጠብ በጣም ቀላል እና የተለመደ የዕለት ተዕለት ተግባር ይመስላል፡፡ ይሁን እንጂ ፊታችንን በምንታጠበብት ወቅት የምንጠቀማቸው አንዳንድ ምረቶች የፊት ቆዳችን ላይ የትየለሌ ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ ከእነዚህ የቆዳችግሮች ውስጥ ድርቀት፣ የማቃጠል ስሜት፣ የወዝ መብዛት እና የቆዳ መሰነጣጠቅ በቀዳሚነት ስማቸው ይነሳል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመከላከል በዋናነት ስልምንጠቀማቸው የፊት ቆዳ ማፅጃዎች ምንነት እና አዘገጃጀት ማወቅ ጠቃሚ ነው፡፡ በተለይ በተለይ የማፅጃዎቹን ይዘት አውቆ መምረጥ መቻል ያለምንም የጎንዮሽ ጉዳት የምርቶቹ ተጠቃሚ ለመሆን ይረዳል፡፡
- ከልክ በላይ መታጠብ
አንዳንድ ሰዎች ፊታቸውን አያምኑትም፡፡ በቀን አስሬ መታጠብ ይቀናቸዋል፡፡ በወጡ በገቡ ቁጥር ውሃ ፊታቸውን ማስነካት የዘወትር ተግባራቸው ነው፡፡ የፊት ቆዳን በቀን አንድ ጊዜ አልያም ሁለት ጊዜ መታጠብ ይመከራል፡፡ ከሁለት ጊዜ በላይ ፊትን ሙልጭ አድርጎ መታጠብ በአንፃሩ የተለያየ የፊት ቆ ችግር የስከትላል፡፡ ችግሩ የሚከሰትበት አንዱ ምክንያት በተደጋጋሚ እጥበት ምክንያት የሚከሰትን ድርቀት ለመከላከል ቆዳችን ከልክ በላይ ዘይት መሰል ነገር ለማምረት ግዴታ ውስጥ ስለሚገባ ነው፡፡ ሜክአፕ፣ ሰንስክሪን እና መሰል መዋቢያዎችን የማትጠቀሙ ከሆነ እና ያን ያህል ላብ ፊታችሁ ላይ ከሌለ ምንም አይነት ማፅጃ ሳትጠቀሙ ለብ ባለ ውሃ ብቻ ፊታችሁን ማታ ማታ ታጠቡ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቆዳችሁ ምንም አይነት መዋቢያ የማይጠቀምበት እረፍት መስጠትም መልካም ነው፡፡
- ከልክ በላይ የጋለ ውሃ መጠቀም
ሞቃት ውሃ የፊታችንን ቆዳ ቀዳዳ ክፍት ያደርጋል፣ ቀዝቃዛ በሌላ በኩል ይዘጋል የሚል የተሳሳተ አመለካከት አለ፡፡ እውነታው ግን ፊታችን ላይ የሚገኙ ቆዳዎች ራሳቸውን የመክፈትም ሆነ የመዝጋት አቅም የላቸውም፡፡ እንደውም በሞቃት ውሃ ከልክ በላይ ቆዳችሁን በማጠብ ከፍተኛ ድርቀት ወይም አላስፈላጊ የሆነ ከፍተኛ የ‹ሴበም› ምርትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ የሚመከረው ለብ ያለ ውሃ መጠቀም ነው፡፡
- ከልክ በላይ ‹ስክራብ› ማድረግ
የፊት ቆዳ ላይ የሚገኙ የሞቱ ህዋሶችን ቀርፎ በተለያየ መንገድ ማንሳት (ስክራብ) ተገቢ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይሄም በልኩ መሆን መቻል አለበት፡፡ እነዚህን ህይወት የሌላቸው ህዋሶች ለማስወገድ ተፈጥሯዊ የሆኑ ነገሮችን መጠቀም ይመከራል፡፡ ከስኳር እና ከፍራፍሬዎች የሚገኝ አሲድ ተመራጭ ቆዳን ‹‹ስክራብ›› ማድረጊያ ናቸው፡፡ ቢበዛ ቢበዛ በሳምንት ሁለት እና ሶስት ጊዜ ብቻ ስክራብ አድርጉ፡፡ ስክራብ በምታደርጉበት ወቅት ቆዳችሁ ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንዳይደርስ ከመታጠቢያ ፎጣ ይልቅ ጣታችሁን ተጠቀሙ፡፡
- በበቂ ሁኔታ አለመታጠብ
የፊት ቆዳን በአግባቡ አለመታጠብ የፊት ቆዳ ቀዳዳዎች እንዲደፈኑ እና ድርቀት እንዲከሰት ያደርጋል፡፡ ጠዋት ከእንቅልፋችሁ ተነስታችሁ ስራ ለመጀመር ጥድፊያ ውስጥ ሆናችሁም ይሁን ማታ ድቅቅ ብላችሁ ቤታችሁ ገብታችሁ ከመተኛታችሁ በፊት ፊታችሁን በሚገባ መታጠባችሁን አትዘንጉ፡፡
- የፊት ቆዳን የሚያቃጥሉ ምርቶች መጠቀም
ፓራቢንን የመሳሰሉ አርቴፊሻል ማቆያዎችን፣ መአዛቸው ደስ የሚያሰኙ ማቅለሚያዎችን ወዘተ በአለመጠቀም ለቆዳችሁ ውለታ ዋሉ፡፡ ሶዲየም ሎውሪል ሰልፌት ሌላኛው ልናስወግደው የሚገባ ንጥረ ነገር ነው፡፡ ምንም እንኳ የፈራረሱ ነገሮችን ለማፅዳት ጠቃሚ ቢሆንም በአመዛኙ ቆዳ እንዲቃጠል ያደርጋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ለአንዳንድ ሰዎች አለርጂም ጭምር ነው፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን የምትጠቀሙት ምርት ውስጥ ምን ምን አይነት ነገር በምን ያህል መጠን እንደሚገኝ ለመረዳት ሙከራ አድርጉ፡፡
- በፎጣ ፊትን መወልወል
ፊታችሁን በእጃችሁ አሻሹ እንጂ በፎጣ አትወልውሉ፡፡ በፎጣ ፊትን መወልወል ደስ የሚያሰኝ ነገር ቢሆንም በሌላ መልኩ ግን ቆዳን ሊልጥ እና ጉዳት ላይ ሊጥል ይችላል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በአቅራቢያችሁ የሚገኝ አገልግሎት ላይ የዋለም ይሁን ያልዋለ ፎጣ ዝም ብላችሁ አንስታችሁ አትጠቀሙ፡፡ አንድ ሰው የሚጠቀምበትን ፎጣ ሌላ ባይጠቀምም መልካም ነው፡፡ ንፁህ እና ለስላሳ ፎጣ መርጣችሁ ፊታችሁን ጠራርጉ፡፡
- ፊት እስከሚደርቅ መጠበቅ
ፊታችሁን ከታጠባችሁ በኋላ ወዲያውኑ እርጥበቱ ሳይጠ ፋፊታችሁን ለማለስለስ የምትጠቀሟቸውን መዋቢያዎች ተቀቡ፡፡ ፊታችሁ ከደረቀ በኋላ መዋቢያዎችን መቀባት የተቀባችሁት ማንኛውም ነገር የቆዳ ቀዳዳዎች ዝግ ስለሚሆኑ ወደ ውስጥ ለመግባት ይቸገራል፡፡ በዚህ ምክንያት ፊታችሁ እንደ አብለጨለጨ ሁሉ ትውሉ ይሆናል፡፡
- ብዙ ገንዘብ ማውጣት
ለፊት ቆዳ ጤንነት አጠባበቅ አቅም እስካለ ድረስ ምንም ገንዘብ አለማውጣት ትክክለኛ ውሳኔ ላይሆን ይችላል፡፡ ቀላል እና ተፈጥሯዊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን የያዙ የፊት ቆዳ ማፅጃዎችን ተጠቀሙ፡፡ ከዚህ ውጪ ውድ የሆኑ በአናቱም ተፈጥሯዊ ያልሆኑ የፊት ቆዳ ማፅጃዎችን መጠቀም አይመከርም፡፡ ይህ ተግባር ኪስንም የፊት ቆዳንም አንድ ላይ ይጎዳል፡፡
- ዘይት ነክ ማፅጃዎችን መፍራት
ረዘም ላለ ጊዜ ዘይት ነክ ማፅዎች እና ቅባቶች የቆዳ ቀዳዳዎችን ይደፍናሉ የሚል የተሳሳተ እምነት ነበር፡፡ ይህ እምነት ግን አሁን እየተቀየረ ነው፡፡ አጥኚዎች አሁን ቆዳን በዘይት ማፅዳት ጠቀሜታ ሊኖረው እንደሚችል በመግለፅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ወዝ የሚበዛባቸው የፊት ቆዎች እንኳ በዚህ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ዘይት ዘይትን ያሟሟል፡፡ ጥሩ ጥሩ የቆዳ ማፅጃ ዘይቶች ቆዳ ቀዳዳ ውስጥ የሚገኙ ቆሻሻዎችን እንዲሁም ባክቴሪዎችን ያፀዳሉ፡፡ የተጎዳ ቆዳን ለማከም ይረዳሉ፡፡ በመሆኑም ተፈጥሯዊ የሆኑ የአትክልት ዘይት ይዘት ያላቸውን ማፅጃዎች ተጠቀሙ፡፡
እንደዚህ አይነት ማፅጃዎችን በቀላሉ ማግኘት የማትችሉ ከሆነ እንኳ ጥራት ያላቸውን የአልሞንድ እና ሱፍ ዘይቶችን እንድትጠቀሙ ይመከራል፡፡ ኮኮናት እና ወይራ ዘይት ለአንዳንዶች በጥሩ ሁኔታ እንደሚሰሩ ቢታወቅም ለአንዳንዶች ግን ራሱን የቻለ ችግር ያስከትላሉ፡፡ በቀስታ ዘይቱን ፊታችሁ ላይ በጣታችሁ ከቀባችሁ በኋላ ለብ ያለ ውሃ ውስጥ በተነከረ ለስላሳ ጨርቅ መልሳችሁ ጥረጉ፡፡ የፊት ቆዳችሁ ቀዳዳዎች በየጊዜው ፊታችሁ ላይ ቀርቶ በሚጠራም ዘይት እንዳይደፈን ሙልጭ አድርጋችሁ በጥንቃቄ የፊት ቆዳችሁን አፅዱ፡፡
The post Health: 10 ትልልቅ የፊት አስተጣጠብ ስህተቶች appeared first on Zehabesha Amharic.