ባለፉት ሳምንታት ህወሓት የተመሰረተበት 40ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የህወሓት መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የኢህኣዴግ ባጠቃላይ መጀመርያ በመቀሌ ቀጥሎ በኣዲስ ኣበባ ተሰባስበው ለኣንድ ወር ሙሉ የሃገሪቱን ሃብት ሲያባክኑና ሲዝናኑበት እንደከረሙ ተገንዝበናል። መቸም የኣምባገነኖች ጭንቀት ማስተንፈሻ ነው መሰለኝ፣ ህዝብ በረሃብና በስራ-ኣጥነት ሲጠቃ፤ ሃገርን በዴሞክራሲያዊ ስርዓት እጦት ስትታፈን ሁሉም ኣምባገነኖች ማስተዳደር ሲያቅታቸው ምክንያት እየፈጠሩ በሃገርና በህዝብ ንብረት እንዲህ መቀለዳቸው የተለመደ ለመሆኑ ሩቅ ሳንሄድ የደርግ ኢሰፓና የነፃድቃንማሌሊት ምስረታ ፌስታ ማስታወሱ በቂ ነው። ኣሁንም ሃገር በቀልና ዓለምኣቀፍ ጥናቶችእንደሚያስረዱት፣ ኢትዮጵያ የተጠመደችበትን ዙርያ-መለስ ቀውስና ህዝቡ እየደረሰበት ያለው ስቃይ መረኑ ኣልፎ ሃገሪቱ ጭራሽ ስርዓት-ኣልባ ወደ እምትሆንበት ደረጃ እያሽቆለቆለች መሆንዋን በጥናት የተደገፈ መረጃ ቢያቀርቡም፣ ግብዞቹ የኢህኣዴግ መሪዎች መራር ሓቁን ከመጋፈጥ ይልቅ፣ ሃገሪቱ የበለፀገች – ህዝቡ የደላው ይመስል፣ ኣሸሼ-ገዳሜ ሲሉ ይገኛሉ።
ህወሓት/ኢህኣዴግ 40ኛ ዓመት-በዓል ብሎ ቅጥ ያጣ ድግስ በጣለበት በኣሁኑ ወቅት፣ የሰቆጣ ህዝብ በከባድ ድርቅ ተጠቅቶ ቀየውን እየለቀቀ ወደ ኣጎራባች ክልሎች በመሰደድ ላይ ይገኛል። በስራ-ኣጥነት የተነሳ ለስደት የተዳረጉት ወገኖቻችን ከተሰደዱባቸው ሃገሮች በገፍና በግፍ እየተባረሩ መሆናቸው የዓረብያው፤ የሱዳኑ፤ የደቡብ ኣፍሪቃው … ይቆይልንና የስሞኑ የኬንያ ክስተት ኣንድ ተጨማሪ ኣሳዛኝ ኣብነት ነው። ለ40ኛው ዓመታቸው ፈንጠዝያ ሲባል ኢህኣዴጎች በመቀሌና ኣዲስ ኣበባ ያባከኑትን ከ100 (ኣንድ መቶ) ሚሊዮን ብር በላይ የህዝብ ሃብት፣ ኣይገባቸውም እንጂ የስንቱን ረሃብተኛና ስራ-ኣጥ ወገን ሕይወት በለወጠ ነበር። በኣሁኑ ወቅት ወገኖቻችን በድርቅ እየተጠቁ መሆናቸውንም የሚያውቁት ኣይመስልም። ቢያውቁስ፣ ፈንጠዚያው ሊያቋርጡ? ዘበት!
ሌላው የሰሞኑ ኣስቀያሚ ድራማ ባለጊዜዎቹ ኣምባገነኖች ለበዓላቸው ማጣፈጫ ብለው ፍፁም በተቆጣጠሩት መገናኛ ብዙሃን (ሚድያ) ሲለቁት የነበረው በውሸትና ማጋነን የተበከለ ኣሳዛኝና ኣስገራሚ ትረካቸው ነው። የሁሉንም ትረካ ዘግበን መተቸት ኣሰልቺ ሊሆን ነው። ስለሆነም ባልጠበቅኩት ሁኔታ ትኩረቴን በሳበው በጄኔራል ፃድቃን ኣስገራሚ ትረካ ላተኩር። ዳንኤል ብርሃኔ የ”ሆርን ኣፈይርስ” (HORN AFFAIRS) ጋዜጠኛ ነበር ቃለ-ምልልስ ኣካሂዶ በ12 የካቲት 2015 ዓ/ም/ፈ/ የፃድቃን ትረካ የለቀቀው።
ፃድቃን ባጠቃላይ በመረጃ ያልተደገፉ ብዙ ነጥቦች ያነሳ ቢሆንም በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ኣፅንኦት ኣድርጎ እንደተረከ የቃለ-ምልልሱ ዘገባ ያመለክታል፡፡ እኔም በነዚሁ ሁለት ጉዳዮች ላይ በማተኮር እውነታውን ላስረዳ፤ ሁለቱ ነጥቦቹም፣
1ኛ/ “የእርዳታ ገንዘብ ከህዝብ ቀምተን ለመሳርያ ስናውል ኣላውቅም”
2ኛ/ “ማሌሊት (ማርክሳዊ ሌኒናዊ ሊግ ትግራይ) መሰረታዊ ወታደራዊ ለውጥ ኣምጥተዋል” የሚሉ ናቸው። ኣንደኛውን ነጥቡ ዘርዘር ኣድርጎ ሲያስረዳ: “በ77 ዓ/ም በጣም የሚያሳዝን – ሁለመናህን የሚፈትሽ – የድርቅ ሁኔታ ነው የነበረው … በራያ ሃብታም የነበሩ ሰዎች ወደ ታጋዮች ቤዝ እየመጡ ከኛ ምግብ እየተካፈሉ የሚበሉበት ሁኔታ ነበር … ደርግ ካከማቸው እህል ስናመጣ ገበሬው ኣብሮን እንዲወስድ እናደርግ ነበር … ካመጣነውም እናካፍለው ነበር … 90% ስንቃችንም ትጥቁም ከጠላት ነበር የምናመጣው … መቶ ሺ (100ሺ) የሚሆን ህዝብ ከዛ ኣካባቢ ወደ ሱዳን ኣጓጉዘናል …” ይለናል።
የ 77 ዓ/ም ድርቅ በጣም ኣሳዛኝ ለመሆኑ ዓለም ያወቀውና እርዳታም በገፍ የቸረበት ስለነበር ኣከራካሪ ሊሆን ኣይችልም። የሚያከራክረው በድርቅ ለተጠቃው ህዝብ የተሰበሰበው እርዳታ የት ገባ ? የሚለው ከባድ ጥያቄ ነው። ፃድቃን ይህን ጥያቄለመመለስ ላይሳካለት ዙርያ- ጥምጥም ተጉዘዋል። ያልተጠየቀው ጥያቄ ለመመለስ ነበረ ጊዜ ያባከነው። ለብዙዎቻችን ኣሳሳቢ የሆነው ጥያቄ ግን ይኸው የተሰበሰበው እርዳታ የት ደረሰ ነው።
መጀመርያ ደርግ ካከማቸው እህል እየነጠቅን ህዝቡ እንዲወስድ እናደርግ ነበር፣ እናካፍለው ነበር ሲለን፤ ሰጪ (ለጋሽ) እንጂ ወሳጅ (ነጣቂ) እንዳልሆነ ለመምሰል ነው መሰለኝ ጥረቱ፤ ቢሆንም የእርዳታ ገንዘብ የት ገባ? ለሚለው ጥያቄ መልስ ኣይደለም። ከተነጠቀው እህል ህዝቡ ይካፈል ነበር የሚለው ለነገሩ ብንቀበልም፣ ወድያውኑ ኣለፍ ብሎ “100 ሺ ረሃብተኞች ከዛው ወደ ሱዳን ኣጓጉዘናል” ሲለን የተኩራራበት ማካፈሉ ቁምነገር ያለው መፍትሄው እንዳልሆነ ራሱ ይመሰክራል። በእውነት ማካፈል ከነበረ ያን ያህል ህዝብ ድንበር ኣሳልፎ ሱዳን ድረስ ማሻገር ለምን ኣስፈለገ?
ኣለፍ ብሎ ደግሞ “ 90% ስንቁም ትጥቁም ከጠላት ነበር የምናመጣው “ ሲል በስተጀርባ ያለው መልእክቱ ከውጭ እርዳታ ኣያስፈልገንም፤ በጉልበታችን ራሳችንን ችለን ነበር ትግሉንም ለህዝብ ማካፈሉንም ያካሄድነው ለማለት ነው። ይህ ትረካ ደግሞ በህዝቡ ስም ከመጣው የውጭ እርዳታ ለድርጅቱ መሳርያ መግዣ ኣልዋለም ለማለት ንጣፍ መሆኑ ነው። ይህ የንጣፍ መልስ ያነገበው የ90% ኣሃዝ ራሱ ቢመረመርም መረጃ-ኣልባና የተጋነነ መሆኑ እንገነዘባለን። የስንቅና ትጥቅ ምንጭ ትልቁ ድርሻ የያዛው በተለያየ መልክ ከህዝቡ የሚሰበሰበው ድጎማና ዋናው ግን ከለጋሽ ሃገሮችና ድርጅቶች በእርዳታ ስም የሚገባው ለስንቁም ለትጥቁም መግዣ የሚውል ገንዘብ እንደነበረ የማሕበረ-ኢኮኖሚና የውጪ ጉዳይ ሪፖርቶች ከማመላከታቸው ኣልፎ ተጨማሪ መረጃዎቹ የት እንደሚገኙ ለማወቅ እስከዚህ ከባድ አይደለም፣ ኣንዳንዶቹም ወረድ ብዬ እጠቅሳለሁ።
ፃድቃን “90% ስንቁም ትጥቁም ከጠላት ነበር የምናመጣው” በማለት በኣሃዛዊ ኣስደግፎ ነግሮን ሲያበቃ ኣያይዞ ደግሞ “ቺፍ ኦፍ ስታፍ ሆኜ ለሰራዊቱ የሚመደብ ገንዘብ ኣላውቅም ነበር፤ ከውጭም ከውስጥም የሚመጣ ገንዘብ የሚቆጣጠር ማሕበረ-ኢኮኖሚ የሚባለው ክፍል ነበር … ዋናው ነገር ዝርዝሩን ኣላውቅም” በማለት ከወዲሁ ከዋናው ጥያቄ ለመራቅ ይሞክራል።
በነገራችን ላይ ቺፍ ኦፍ ስታፉ ከጠላት የሚገኘው ስንቁም ትጥቁም 90% መሆኑ በኣሃዝ ከነገረን ዘንዳ በራሱ ድርጅት ለወገን ጦር የሚመደበው የስንቅና ትጥቅ መጠን ማወቅ እንዴት ይሳነዋል? “ቺፍ ኦፍ ስታፍ” ባጀቱ ካላወቀ ማን ሊያውቅለት ነው?
ቺፍ ኦፍ ስታፍ ፃድቃን ይህንን ጥያቄ ሲያጠቃልል “ከደርግ የምናገኘው ንብረት ከህዝብ ጋር ስንካፈል ነው እንጂ ከውጭ የሚመጣውን ገንዘብ ከህዝብ ቀምተን ለጦር መሳርያ ስናውል ኣላውቅም” ይላል በኣፅንኦት። ይህ ኣባባል ምንኛ ከሓቁ የራቀ መሆኑ ለመገንዘብ ፃድቃን ራሱ የነበረበት የ77ቱ የማሌሊት ማ/ኮ ስብሰባ ከህዝብ ቀምቶ የወሰነው የባጀት ምደባ ሬኮርድ (ሰነድ) መመልከት ነው። የሚገርመው፣ ስለዚህ ሰነድ/ሬኮርድ በተመለከተ ፃድቃን ብቻ ሳይሆን ሁሉም የኣመራሩ ኣባላት ኣንድ ቃልም መተንፈስ ኣይፈልጉም። ጉዱ ያለው ግን የያዘው በማይለቀው እዚህ ሰነድ ላይ ነው።
ይህን ግፈኛ የባጀት ምደባ ኣስመልክቶ በተለያዩ ኣጋጣሚዎች ገልጨዋለሁ። ወደፊትም መቋጫ እስኪያገኝ ድረስ መግለፄ እቀጥላለሁ፤ ለምን ቢባል በክፉ ቀን ትልቅ የህዝብ ክሕደት የተፈፀመበት ውሳኔ ነውና። በዛ የድርቅ ቀውጢ ወቀት (1977 ዓ/ም) የማሌሊት ምስረታ ለሌላ ጊዜ እንኳን ይተላለፍ ቢባል ሸራቢው ቡድን ኣሻፈረኝ በለዋል። ስለዚህም ቡድናዊ ድርጅት ለመመስረት በሓላፊነት የነበረው የህወሓት ታጋይ ሁሉ ህዝቡን በክፉው ቀን መርዳት እየቻልን ኣንድ ወር ሙሉ ወርዒ በተባለው ሸለቆ እየተደገሰ ተቀምጠናል። ይህ ድርጊት ራሱ የድርቅ ሰለባ ለነበረው ህዝብ ተጨማሪ ቅጣት ነበር።
ማሌሊት ተመስርቶ እዛው ወርዒ የህወሓት/ማሌሊት ማእከላይ ኮሚቴ እቅድ ለማውጣትና ባጀት ለመመደብ ተሰበሰበ። በእቅዱ መሰረት ባጀቱ ለመመደብ የቀረበው ጥሬ ገንዘብ 100 (ኣንድ መቶ) ሚልዮን ብር ነበረ። ይህ ገንዘብ ፃድቃን እንደሚተርከው ከደርግ የተነጠቀ ኣልነበረም፤ ወይም ደግሞ ከህዝቡ የተዋጣ ኣልነበረም – በድርቅ የሚቆላው ህዝብ ስም ከውጪ ረዳቶች የተሰበሰበ ነበር። ይህ ገንዘብ በድርቁ ምክንያት ከግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ከተሰበሰበው ከፊሉ ሆኖ፣ የያኔ የማህበረ-ኢኮኖሚ ሃላፊ ኣውዓሎም ወልዱና የውጪ ጉዳይ ሃላፊ ስዩም መስፍን ለማሌሊት ምስረታ ከሱዳን ሲመጡ እግረመንገዳቸው በጆንያ ጭነዉ ያመጡት እንደነበረ እናውቃለን።
በባጀት ምደባው መለስ ዜናዊ የውሳኔ ሓሳብ ሲያቀርብ ” 50% ለማሌሊት ማጠናከርያ፣ 45% ለህወሓት ስራ ማስኬጃ፣ 5% ለድርቅ ጉዳተኞች” ብሎ ኣረፈው። ለድርቅ ጉዳተኞች 5% ብቻ መመደብ በቂ ኣይደለም፣ ከፍ ማለት ኣለበት የሚል ኣንድ ድምፅ ተሰማ፣ ይሁን እንጂ በማሌሊት ምስረታ የተሳከረው ማ/ኮ ተማፅኖውን ከጉዳይ ኣልቆጠረውም። እንዳውም የማሌሊት ኣፍላ ጀብደኞቹ “ማሌሊት ተጠናክሮ ድል ስንቀዳጅ የህዝቡ ችግር ይፈታል” ሲሉ ይደመጡ ነበር። ፃድቃንም በማሌሊት ምስረታ የምር ተዋናይ እንደነበረ ራሱ ስለገለፀልን በዛ ስካር ተጠምዶ ልመናውን ማዳመጥ እንደሚሳነው ግልፅ ይመስለኛል። የሆነሆኖ ኣሳዛኝና ዋናው ነጥቡ ከእርዳታው ገንዘቡ 95% ለህወሓት/ማሌሊት ለድርጅታዊ ስራ ሲውል 5% ብቻ በድርቅ ለተጎዳው ወገን “ተቸረ” ማለት ነው። ሓቁ ይኸው ነው። 95’ቱ ለራሱ ድርጅት ኣስቀርቶ 5’ቱ ብቻ ለህዝቡ የተወ ድርጊት ከህዝብ ጋር መካፈል ነው ወይስ ከተራበ ህዝብ ኣፍ መንጠቅ? ጄ/ፃድቃን?
ሰነድ የነከሰው ሓቅ ይህ ሆኖ እያለ የተለያየ የህወሓት/ማሌሊት ማ/ኮ ኣባላት (ኣረጋሽ፣ ገብሩ፣ ስብሓት፤ ኣውዓሎም፣ ፃድቃን…) በየወቅቱ በመረጃ ያልተደገፈ የተለያየ ዘገባ ሲሰጡ እንደቆዩ ሳንገነዘብ ኣልቀረንም። ከነዚህ ሁሉ ዘገባ ግን ለሓቁ የቀረበ የኣውዓሎም መሆኑ ባለፈው ፅሁፌ ዋቢ ጠቅሼ ዘግቤኣለሁ። መድገም ካስፈለገ ደግሞ፣ ‘ይህ ነውረኛ የበጀት ምደባ ኣስመልክቶ ኣምባሳደር-ነበር ኣውዓሎም ወልዱ ለኣዲስ ኣድማስ ጋዜጣ 27 ጥቅምት 2003 ዓ\ም ገጽ 21 ላይ ባሰፈረው መረጃ፣ “35% ለህዝቡ፣ 65% ለድርጅቱ ተከፋፍለዋል” ‘ ይላል።
ይህ የበጀት ምደባ በኣብዝሃው ማ\ኮሚቴ ስብሰባ ጸድቆ፣ ቃለ ጉባኤውም በጽሑፍ ሰፍሮ፣ በቴፕ ተቀድቶ በህወሓት ሰነዶች ማእከል ይገኛል። ይህ ሰነድ እያለ ለምን የባጡን የቆጡን መደርደር እንዳስፈለገ ይገርማል፣ ሰነዱን መዞ ማየት እየተቻለ። ከህወሓት ፋይሎች ኣልፎም የዓለምኣቀፍ የረድኤት ማሕበራትና እንደ ቢቢሲ የመሰሉ የሚድያ ተቋማትን ኣሁንም እያተራመሰ ይገኛል። በቴፕ የተቀዳና በፅሁፍ ቃለ-ጉባኤ የተያዘለት ይህ ኣስነዋሪ ክንዋኔ ለምን እንደሚያከራክር መገመት ኣይከብድም፣ ከተጠያቂነት ለመሸሽ ኣይደል? ግራም ነፈሰ ቀኝ መረጃውን መመልከት ስለሚቻል የጊዜ ጉዳይ እንጂ ተጠያቂነቱ ኣይቀርም። በነገራችን ላይ፣ ጋዜጠኛ ዳንኤል የእርዳታው ገንዘብ ጉዳይ ፃድቃንን መጠየቁ ላልቀረ ስለተጠቀሱት ቁልፍ የጽሑፍና የቴፕ ማስረጃዎች ማንሳት ለምን ኣልፈለገም? ሆን ብሎ ወይስ ባለማስተዋል?
2ኛው የፃድቃን ነጥብ “ማሌሊት መሰረታዊ ወታደራዊ ለውጥ ኣምጥተዋል” የሚል ሲሆን ዘርዘር ያለ ትረካው ቀጥሎ እንመልከት።
“ከማሌሊት ምስረታ በፊት ከፍተኛ ችግር ነበር። ትልቅ ሓይል ይዘን የደርግን ትንሽ ሓይል የማናሸንፍበት፣ ብዙ ኪሳራ የምንከፍልበት፣ ወዴት ነው የምንሄደው … ውዥንብር የታየበት ወቅት ነበር። ከማሌሊት ምስረታ በኃላ ዲያለክቲካል ማቲርያሊስት … ሳይንቲፊክ በሆነ መንገድ ነገሮችን ማየት የጀመርንበት፣ ወታደራዊ ስራን እንደ ኣንድ ሶሻል እንቅስቃሴ ማካሄድ እንዳለብን መልስ ያገኘንበት ነው። የታጠቀ ህዝብ ስትራተጂ ከማሌሊት በፊት ኣልነበረንም፣ ኃላ ሰራዊቱን በሶስት ካታጎሪ (ደረጃ) ማለት 1ኛ- ዋና መቺ ሓይል፣ 2ኛ- በዞን የተደራጀ፣ 3ኛ- ከምርት ስራ ያልተላቀቀ ኣድርገን ኣስቀመጥን። ከወርዒና ተከዘ በረሃዎች ወጥተን ወደ ህዝብ ተሰማራን፤ በደጀን ኣመሰራረታችን ፍፁም የተለየ ኣቋም ኣመጣን፤ ራሳቸውን ችለው በማንኛውም ቦታ ሊዋጉ የሚቸሉ ባታልዮኖች ፈጠርን” ይላል።
እንደ ፃድቃን ኣባባል ማሌሊት ከመፈጠሩ ኣስር ዓመታት ቀደም ብሎ የነበረው መሰረታዊው የህወሓት ትግል ዋጋ ኣልነበረውም እንደ ማለት ነው። ባንድ ጀንበር ሰራዊትም ደጀንም ይታነፅ ይመስል፣ ማሌሊት ፈጠረችው ይለናል። ከከባዱ ድርቅ ጋር በ77 ዓ/ም ብቅ ያለው ማሌሊት ብዙም ሳይቆይ በ82 ዓ/ም ደብቁኝ – ሰውሩኝ ማለት ጀምሮ በ83 ዓ/ም እነ ፃድቃን ስልጣን ላይ ሲወጡ ማሌሊት የተባለው ቡድናዊ ስብስብ እንደ ጧት ጤዛ በኖ ጠፋ። ገና 6 ዓመት ሳይሞላው ተቀጨ። ለመሆኑ ለራሱ መቆም ኣቅቶት ስንዝር መቀጠል ያልቻለ ድርጅት እንዴት ነው በከባድ ትግል የታነፀው ህወሓትን ዋጋ ኣሳጥቶ፣ ብዙ ተዓምር ሰሪ ሆኖ የሚቀርበው? ጄ/ ፃድቃን?
“ትልቅ ሓይል ይዘን የደርግን ትንሽ ሓይል የማናሸንፍበት፣ ብዙ ኪሳራ የምንከፍልበት” ችግር ውስጥ ነበርን ይላል ፃድቃን። ሁሉም ታጋይ እንደሚያውቀው የህወሓት ወታደራዊ ፍልሚያ በ3 ደረጃዎች ማለፍ ነበረበት። 1ኛ/ በሽምቅ ውግያ ጀምሮ ከዛ 2ኛ/ ወደ ተንቀሳቋሽ 3ኛ/ና መጨረሻም ቋሚ በመሆን እድገቱንና ተልእኮውን ተከትሎ ተከናውነዋል። ይህ ሂደት ትግሉ “ሀ” ብሎ ሲጀመር የተነደፈና ተግባር ላይ የዋለ እንጂ ማሌሊት ብቅ ሲል ብቅ ያለ፣ ማሌሊት ሲጠፋ ደግሞ ኣብሮ ሊጠፋ የሚችል ኣልነበረም። ኪሳራ በተመለከተ ደግሞ በኣሃዝ የተደገፈ ጭብጥ የለውም። ይሁንና በ 17 ዓመታት ጦርነት የተሰዋው ታጋይ 54 ሺ ሲገመት፣ በባድመና ፆሮና ኣንድ ውግያ ላይ ያለቀው ወጣት ግን 50 ሺ እንደሆነ ይነገራል። ይህ ለማነፃፀሩም የሚከብድ ኪሳራ በብዙ ወታደራዊ ጠበብት ሲተች የመካከለኛው ዘመን (ሜዲቫል) ጦርነት ያስከተለው ኪሳራ ይመስላል እንደሚባል ፃድቃን ሰምቶ ይሆን?። እንግዲህ ጥያቄው “ዲያለክቲካል ማቲርያሊስት … ሳይንቲፊክ” ስትሆን እንዴት ነው ጭራሽ እጥፍ-ድርብርብ፣ ለንፅፅር ኣስቸጋሪ የሆነው ኪሳራ የተፈጠረው?
እንዲያው ጄ/ ፃድቃን ወርዶበት ነው እንጂ እላይ ወታደራዊ ለውጦች ብሎ በኣዲስ መልክ የጠቃቀሳቸው ነጥቦች፣ ድሮ ከማሌሊት ምስረታ በፊት፣ ህወሓት በንድፈ-ሓሳብ ይሁን በተግባር የሚያውቃቸውና ስራ ላይ ያዋላቸው ወታደራዊ ስትራቴጂዎችና ስልቶች ናቸው። ይህ ብቻም ኣይደለም፤ እነዚህ ወታደራዊ ስትራቴጂዎችና ስልቶች ኣያሌ ዘመናት ያስቆጠሩ፤ በቻይና፣ በቬትናም፣ በኣልጄርያ፣ በኣፍጋኒስታን፣ በይጎዝላብያ … ስራ ላይ የዋሉ ናቸው። ለፃድቃን ኣጉል ትረካ ምላሽ ለመስጠት ወደ ሳንዙ (500 ዓመታት ከክርስቶስ ልደት በፊት) ወይም ወደ ክላውስዊዝ (200 ዓመታት ወደ ሁዋላ) መሄድ ኣስፈላጊ ኣልመሰለኝም። እነ ማርክስ እነ ሌኒን ከነዚሁ ተውሰው ነበር የፃፉት። እነ ማኦ በቻይና፣ እነ ጂያፕ በቬትናም፣ ወዘተ. ይህንኑ የታጠቀ ህዝብ ስትራተጂ ከነባሮቹ የወታደራዊ ስትራቴጂ ጠበብት ተቀብለው በየሃገራቸው ተግባር ላይ ያዋሉት። ፅንፋኛ እስላሙ ታሊባን ማርክሰ-ሌኒኑ ሶቤት-ሕብረትን ኣሸንፎ ኣፍጋኒስታንን የተቆጣጠረበት ትግል ፃድቃን ከትረካው ጋር ማጣጣም ይችላልን?
ምናልባት ፃድቃን በማሌሊት ምስረታ ወቅት እንደ ኣዲስ ተገልጦለት ወይም የማሌሊት ፍቅሩ ኣሁንም ኣልለቅ ብሎት ይሆናል እንጂ ህወሓት ከመመስረቱ በፊትም ይኸው የታጠቀ ህዝብ ስትራተጂ በህወሓት መስራቾችና በነባሮቹ ታጋዮች ይታወቅ እንደነበር ላረጋግጥለት እወዳለሁ። ኣንድ ኣብነት ልጥቀስ፡ በ70ዎቹ መጀመርያ “ሓፋሽ ይንቃሕ፣ ይወደብ፣ ይተዓጠቕ” ማለት ሰፊው-ህዝብ ይንቃ፣ ይታጠቅ፣ ይደራጅ” የሚል መመርያ ተነድፎ ህወሓት ተግባር ላይ ያዋለው የዛ ዘመናት ያስቆጠረው የታጠቀ ህዝብ ስትራተጂ ተቀጥያ ነው ። ሰራዊቱም በሶስት ደረጃ ማለት 1ኛ/ በመደበኛ ሓይል 2ኛ/ ‘ከራቢት’ በሚባሉ ኣሃዱዎች የሚመራ ዞባዊ ሓይል 3ኛ/ ከምርት ስራ ያልተላቀቀ ‘ወየንቲ’ በሚበሉ የሚሊሻ ሓይል ተዋቅሮ ሲታገል እንደነበረ በትግሉ ያለፉ ሁሉም ታጋዮች ይቅርና የደርግ ወታደሮችም ሊነግሩ ይችላሉ። “ በ77 ዓ/ም ከወርዒና ተከዘ በረሃዎች ወጥተን ወደ ህዝብ ተሰማራን “ ለሚለው ልቅ ፈጠራው ደግሞ ከ68 ዓ/ም ጀምሮ ህዝቡን በየፈርጁ ሲያደራጁና ሲያታግሉ የነበሩ (በተለይ የክፍለ-ህዝብና የክርቢት) ታጋዮች ይታዘቡ ብል ለጊዜው ይበቃል።
“በደጀን ኣመሰራረታችን ፍፁም የተለየ ኣቋም ኣመጣን” ለሚለው፣ ፃድቃን የሚጨበጥ ነጥብ ኣላቀረበም ብቻ ኣይደለም። እንዳውም ደጀን እንዴት እንደሚመሰረትና ከግንባር ጋር ያለው የተቆራኘ/የተሳሰረ ግኑኝነት በቅጡ የያዘው ኣልመሰለኝም። ግንባር ያለ ደጀን እንደማያድግ ሁሉ፣ ደጀንም ያለ ግንባር ዘላቂ ኣስተዋፅኦ ኣይኖረውም። ይህንን መርህ ከጅምሩ ግንዛቤ ውስጥ ያስገባው ህወሓት ደጀኑና ግንባሩ በተመጣጣኝ ዕድገት እንዲጎለብት ኣድርጎ፣ ፃድቃን እንደሚለው ሳይሆን ከማሌሊት ምስረታ በፊት፣ ባንድ በኩል ህዝቡን በእድሜ፣ በፆታ፣ በሞያ ኣደራጅቶ፣ በብዙ ወረዳዎች ‘ባይቶዎች’ (ማሕበራዊ ኣስተዳደር) መስርቶ፣ በሌላው በኩል ሰራዊቱን ከባታልዮን ኣልፎ በብርጌድም ኣቋቊሟል። በህይወት የሌሉትን እነ ሓየሎም፣ ኢያሱ-ባጋ፣ መንጅር፣ ፀጋብርሃን ወዘተ. እንተወውና፣ በህይወት የሚገኙት ነባሮቹ የባታልዮንና የብርጌድ መሪዎች ይታዘባሉ ኣለማለቱ ምን ይባላል።
እዚህ ላይ ኣንድ መጠቀስ ያለበት ትልቅ ነጥብ ኣለ። በህወሃት ውስጥ ሲያከራክር የቆየው ‘ህዝባዊው’ የደጀን ኣመለካከት፣ በኢትዮጵያ ኣንድነት በሚያምነውና ትግራይን ለመገንጠል ሲያቀነቅን በነበረው ቡድን መካከል ግጭት ፈጥረዋል። ተገንጣዩ ቡድን በትግራይ ብቻ ደጀን እናጠናክር ሲል ተቃዋሚው ደግሞ የምንታገለውን ደርግ ሃገራዊ ሓይል ስለሆነ በኢትዮጵያ ደረጃ ደጀን ማጠናከር ይገባል ባይ ነበር። ይህ ኣቋም ፖለቲካዊ ትርጉም ነበረው፣ እሱም በኣንድ በኩል የኢትዮጵያ ኣንድነት ማጎልበት ሲሆን በተፃራሪው ደግም ኣንድነትን ማቀጨጭ ነበር። ኣስመሳዮቹ የመገንጠሉ ኣቋም ኣሁን ድረስ ሕገ-መንግስት የሚል ስም በሰጡት ፕሮግራማቸው ውስጥ ሸንክረውት ይገኛል። ያቅጣጫ ማጣት ውዥንብር እዚህ ላይ ነበር። ይህ ደግሞ በዋናነት ፖለቲካዊ እንጂ ወታደራዊ ውዥንብር ኣይደለም።
የደጀኑ ጉዳይ ከሻዕብያ ጋርም ለረጂም ጊዜ ኣጋጭቶናል። ሳሕል በረሃ ላይ የመሸገው የሻዕብያ ጦር የሳሕል ተራራዎች ታቅፎ ይኖራታል እንጂ ደርግን ኣያፈርስም። ደርግን ድል ማድረግ ከፈለገ የታጠቀ ህዝብ ስትራተጂ ተከትሎ ለተግባራዊነቱ የደጀን መሰረት ወደ ሆነው ህዝቡ መሰማራት ኣለበት ብሎ ህወሓት የመከተው ድሮ ጤዛዋ ማሌሊት ብቅ ከማለትዋ 5 ዓመታት በፊት ነበር።
ከጤዛዋ ማሌሊት ምስረታ ጀምሮ “ዲያለክቲካል ማቲርያሊስት … ሳይንቲፊክ በሆነ መንገድ ነገሮችን ማየት” እንደጀመረ የሚተርክልን ፃድቃን ከተጨባጭ ሓቁ ጋር ምን ያህል እንደተራራቀ ኣንድ ኣብነት ላክል። የማሌሊት ቡድን ህወሓትን እንደተቆጣጠረ ታጋዩ ብሄራዊ ስሜቱ እያላላ፣ ባንፃሩ ሃገራዊ ስሜቱ እያጎላ ስለሆነ ይህ ኣዝማምያ እንዲቀለበስ ተብሎ መቀስቀሻ ፅሁፍ ተዘጋጅቶ ቅስቀሳው ለወራት ተካሂደዋል። በመሆኑም የደርግ መውደቅያ ተቃርቦ ታጋዩ ወደ ማህል ኢትዮጵያ ዝለቅ ሲባል፣ “ለምን? ያስተማራችሁን በትግራይ ብቻ እንድንወሰን ኣይደል እንዴ?” ማለት ጀምሮ ግንባሩንም እየጣለ ወደየቤቱ መመለስ ቀጠለ። በዚሁ ወቀት ጨካኙ የማሌሊት ቡድን ካድሬዎቹን ኣሰማርቶ በታጋዩ ላይ መረን የለቀቀ ግፍ ፈፅመዋል። ‘ጎሓፍ’ (ውዳቂ) እየተባሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጋዮች ተረሽነው የጅምላ መቃብር ውስጥ ተጥለዋል። ከዛ ቁጥር በላይ ደግሞ በእስር ተሰቃይተዋል። የስነ ኣእምሮ ጥቃት የደረሰባቸው ጥቂት ኣይደሉም። ይህና ኣያሌ ተመሳሳይ ድርጊቶች ስናሳ ፃድቃንን የቱ ላይ ነው ሳይንቲፊክ የሆናችሁት ብለን መጠየቅ እንችል ነበር፣ ሆኖም ወደ ተራዘመ ንዝንዝ ከመግበት ይልቅ ከናአካቴው ራስዋ መቆም ያቃታት ማሌሊት የት ገባች ብሎ ባጭሩ መጠየቁ የሚሻል ይመስለኛል። የተመደበላት 50 ሚልዮን ብር ኣልበቃ ብሎ ነው ? ወይስ ቡድናዊ ተልእኮዋ፣ ማለትም ተቃዋሚዎቹን የመምታት ግዳጅዋን ከፈፀመች በቃ ኣታስፈልግም ተብላ ተጥላ ነው።
በማጠቃለል “ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል” ሆነና በቁምነገር ለቁምነገር ያልተፈጠረችው ጤዛዋ ማሌሊት የውሃ ሽታ ከሆነች እነሆ 20 ዓመታት ኣልፏታል። ፃድቃን ደግሞ የህወሓት 40ኛ ዓመት መዘከር ትቶ፣ ለሸር የተጠፈጠፈችውን ቡድናዊ ድርጅቱን ማሌሊት ሲያሞግስ መደመጡ ብዙዎችን ሳያሳስብ ኣልቀረም።ይሁን እንጂ ይቺ ለሸር ብቅ ብላ የከሰመችው ድርጅት የፈጠረችው ምስቅልቅል ግን ኣሁንም ህዝቦቻችንን እያተራመሰ፣ ሃገራችንን እያደማ ይገኛል። ኣቅጣጫ-የለሽ ውዥንብር ይሉታል ይህ ነው። በማህሉ ሃገር ወደብ ኣልባ፣ ህዝብ መብት ኣልባ፣ ወጣት ስራ ኣልባ ያደረገችው ሳይንቲፊክዋ ማሌሊት ለራስዋም ባትሆን ቢያንስ ፈጣሪዎችዋን ግን ለጊዜውም ቢሆን ጌቶች ኣድርጋቸዋለች።
ህዝባዊ ስርዓት ያልተመሰረተበት ሃገር ለጥቂቶቹ ገነት፣ ለብዙዎቹ ሲኦል መሆኑ ኣልቀረም። ኢትዮጵያ ኣንድዋ ኣብነት ነች። ከዚህ መከራ ለመገላገል ጋሬጣው ቢበዛም የጋራ ድርጅት ፈጥሮ ለጋራ ስርዓት መታገል ነው።
ኣረጋዊ በርሀ
11 ማርች 2015
The post ጄኔራል ፃድቃንና ጤዛዋ ማሌሊት …በ40ኛው – ከአረጋዊ በርሀ appeared first on Zehabesha Amharic.