በየሳምንቱ በመላው ዓለም የሚገኙ ስፖርት አፍቃሪያን በጉጉት የሚጠብቁት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በዚህ ሳምንት በኤፍ ኤ ካፕ 6ኛ ዙር ውድድር ተተክቷል፡፡ በእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር (ኤፍ ኤ) አዘጋጅነት ከሚደረጉ የሀገር ውስጥ ውድድሮች ከፕሪሚየር ሊጉ ቀጥሎ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው የኤፍ ኤ ካፕ ውድድር በርካታ ክለቦችን ጥሎ ስድስተኛ ዙር ላይ ደርሷል፡፡ በስድስተኛው ዙር የኤፍ ኤ ካፕ ውድድር አራት ጨዋታዎች በተለያዩ የእንግሊዝ ከተሞች ይካሄዳሉ፡፡
የመጀመሪያው ጨዋታ ቅዳሜ በእንግሊዞች የምሳ ሰዓት ጨዋታ 9፡45 ላይ የሊግ አንዱ ተወዳዳሪ ብራድፎርድ ሲቲ የሻምፒዮንሺፑን ሬዲንግ በሜዳውና በደጋፊው ፊት በሚፋለምበት መርሐ ግብር ይጀመራል፡፡
ብራድፎርድ ሲቲ በሊግ አንድ ውስጥ በ48 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ተጋጣሚው ሬዲንግ በበኩሉ በሻምፒዮንሺፑ በ41 ነጥብ በአሥራ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ የሊግ አንድ የደረጃ ሰንጠረዥን ብሪስቶል ሲቲ በ73 ነጥብ፣ ፕሪስተን በ63 ነጥብ እና ማክዶንስ በ62 ነጥብ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ይዘዋል። የሻምፒ ዮንሺፑን የደረጃ ሰንጠረዥ ደግሞ ሚድል ስቦሮው በ66 ነጥብ፣ ደርቢ ካውንቲ በ65 ነጥብ እንዲሁም ዋትፎርድ በግብ ተቀድሞ በተመሳሳይ 65 ነጥብ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለማደግ የሚደረገውን ሩጫ እያገባደዱ ይገኛሉ፡፡ ሁለቱ ክለቦች ለስድስተኛ ዙር ጨዋታ የደረሱት ብራድፎርድ ሲቲ ቼልሲና ሰንደርላንድ ጥለው ሲሆን፤ ሬዲንግ በበኩሉ ካርዲፍ ሲቲንና ደርቢ ካውንቲን በጥሎ ማለፍ አሸንፎ መሆኑ ይታወሳል፡፡
ጨዋታው ቀጥሎ ምሽት 2፡30 ላይ አስቶንቪላ በሜዳው ቪላ ፓርክ ላይ ዌስትብሮሚች አልቪዮንን ይገጥማል፡፡ ይህ ጨዋታ ሁለቱ ክለቦች ባለፈው ማክሰኞ በቪላ ፓርክ በ28ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር በተገናኙ ሳምንት ሳይሞላቸው ለሁለተኛ ጊዜ የሚገናኙበት ጨዋታ ይሆናል፡፡ አስቶንቪላዎች የቀድሞ አሠልጣኛቸውን ፖል ላምበርትን አባረው በምትኩ የቶትንሃም ሆትስፐር ዋና አሠልጣኝ የነበሩትን ቲም ሽሩድን በአሠልጣኝነት ከቀጠሩ በኋላ መጠነኛ የሚባል ለውጥ ያመጡ ሲሆን፤ ሽሩድም የመጀመሪያ ሦስት ነጥባቸውን አግኘተዋል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ የቶኒ ፑሊሱን ዌስትብሮሚች አልቪዮን አስተናግደው ምስጋና ለዳኛው ይግባውና በባከነ ሰዓት በተሰጣቸው የፍጹም ቅጣት ምት ማሸነፋቸው እና የመጀመሪያ ሦስት ነጥባቸውን ማግኘታቸው ከፍተኛ መነሳሳት ፈጥሮላቸዋል፡፡ ዌስትብሮሚች አልቪዮኖች በበኩላቸው በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪያቸው በራሂኖ ታግዘው ከፍተኛ የፕሪሜር ሊጉን ሽንፈታቸውን ለመበቀል ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡
መርሐ ግብሩ ዕሁድ ቀጥሎ ምሽት 1፡00 ላይ የመርሲሳይዱ ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ሮድ ስታዲየም የሻምፒዮን ሺፑን ብላክበረን ሮቨርስን ያስተናግዳል፡፡ ሊቨርፑሎች በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጓቸው ተከታታይ ጨዋታዎች በማሸነፍ ከነበሩበት የ12ኛ ደረጃ ወደ አምስተኛ ደረጃ መምጣታቸው እና ይህንን ጨዋታ በሜዳቸው የሚያደርጉ መሆኑ ከፍተኛ የማሸነፍ ዕድል ተሰጥቶታል፡፡ ብላክበርን በበኩሉ አሁን ያለበት ደረጃ ሊቨርፑልን ሙሉ ለሙሉ ማቆም የሚያስችል ባይሆንም ለጨዋታው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው በመግባት ለሊቨርፑል ከፍተኛ ፈተና እንደሚሆኑባቸው ይጠበቃል፡፡
አራተኛውና በጉጉት የሚጠበቀው የመጨረሻው ጨዋታ ሰኞ ምሽት 4፡45 ማንቸስተር ዩናይትድንና አርሰናልን ያገናኘው ጨዋታ ነው፡፡ ሁለቱ ክለቦች በተገናኙ ቁጥር ከጨዋታው በላይ በአሠልጣኞችና በተጫዋቾች መካከል የሚደረገው እሰጥ አገባ ሁሌም የሚናፈቅ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ደግሞ አርሰናል ከተፋላሚው ማንችስተር ዩናይትድ በፕሪሚየር ሊጉ በአንድ ነጥብ ከፍ ብሎ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ሲሆን፤ ማንችስተር ዩናይትድ በበኩሉ ከአርሰናል በመቀጠል በአራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ እንደሚታወሳው ሁለቱም ክለቦች ባለፈው ረቡዕ በፕሪሚየር ሊጉ ከሜዳቸው ውጪ ያደረጓቸውን ጨዋታዎች በድል ተወጥተዋል፡፡ ማንችስተር ወደ ጄምስ ፓርክ ስታዲየም አቅንቶ ኒውካስል ዩናይትድን ገጥሞ በ89ኛው ደቂቃ በኒውካስትሉ ግብ ጠባቂ ቲም ክሩል ስህተት ተጠቅሞ አሽሊ ያንግ ባስቆጠራት ግብ 1ለ0 ሲያሸንፍ አርሰናል በበኩሉ ወደ ሎፍተስ ሮድ በማቅናት ኪውፒአርን ገጥሞ ኦሊቬ ጅሩድና አሌክሲስ ሳንቼዝ ባስቆጠሯቸው ሁለት ተከታታይ ግቦች 2ለ1 አሸንፎ መመለሱ አይዘነጋም፡፡
በአራት የተለያዩ ጨዋታዎች ቀጥሎ የሚውለው የእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ 6ኛ ዙር ውድድር አራት ክለቦችን ወደ ግማሽ ፍጻሜ ሲያሳልፍ አራት ክለቦችን በማሰናበት ይቋጫል፡፡ የፍጻሜው ውድድር በመጪው ግንቦት መጀመሪያ አካባቢ በታላቁ ዌምብሌይ ስታዲየም የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል፡፡
The post Sport: ኤፍ ኤ ካፕ 6ኛው ዙር: ማን.ዩናይትድ ከአርሰናል (ልዩ ትንታኔ ስለ ፍልሚያው) appeared first on Zehabesha Amharic.