Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

መኢአድ በወያኔ ሚዲያዎች በኢቢሲ በፋና በዛሚ እንዳያቀርበዉ የተከለከለዉ ጽሑፍ

$
0
0

የተወደድክና የተከበርከው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!

aeupከዘመናት በፊት የሥልጣኔ ችቦ ከተቀጣጠለባቸው ጥቂት አገሮች መካከል አገራችን ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡ በዚህ ረጅም የሥልጣኔና
የታሪክ ዘመን ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያዩ መንገዶችና በማንኛውም ሁኔታ ነፃነቱን ለማስከበር ከውጭ ወራሪ ሐይሎች
ጋር ሲታገል መኖሩ የዓለምን ሕዝብ ቀልብ ከመሳቡ ባሻገር ለአፍሪካውያንና በዓለም ላይ ላሉ ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት አርአያና
ተመሳሌት በመሆን የጥቁርን ዘር ክንድ ብርታትና ፅኑነቱን አስመስክሯል፡፡ ይህ አስደናቂና ወደር የማይገኝለት ድል ዘወትር
የሚከነክናቸው ባእዳን የሀገር ውስጥ ባንዳዎችን በማዘጋጀትና ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን ብዙና ከባድ የችግር ቀንበር
ሊጭኑበት ሞክረዋል በዚህ ምክንያት ህዝባችን ዘርፈ ብዙ መስዋዕትነትን እንዳከፍልም ሆኗል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱን፣ ታሪኩን፣ ሉዓላዊነቱንና ባህሉን ለሦስት ሺህ ዓመታት ጠብቆ የኖረ መሆኑን ዓለም ይመሰክራል፡፡
ሕዝባችን በውስጥ አስተዳድር የደላውና የተመቸው ባይሆንም ቅሉ ብሶቱን አቻችሎ የአገሩን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ለማስከበር
ዘር፣ ጐሳ፣ ቀለምና መንደር ሳይለየው በደሙ እየዋጀ መተኪያ የሌላት ሕይወቱንም ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
የኢህአዴግ መንግሥት ሥልጣን ከያዘበት ቀን ጀምሮ ይህን በደምና በአጥንት የተገነባ ዳር ድንበር እንዲጣስ በማድረግ
ለባእድ ፈቅዶ በመሥጠት ወደብ አልባ አድርጐናል፡፡ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም እንዲሁም የሕዝቧን ግለሰባዊና ቡድናዊ
ነጻነትና ደህንነት በተገቢው መንገድ ማስጠበቅ ስላልቻለ ድርጊቱን በመቃወም ለመታገል የመላው ኢትዮጵያ አንድነት
ድርጅት /መኢአድ/ በሕብረ ብሔራዊና አገር አቀፍ ፓርቲነት በቁርጥ ቀን ልጆች ተመሰረተ፡፡
ኢህአዴግ የደርግን መንግሥት ተክቶ ሥልጣን ከያዘበት ቀን ጀምሮ ይመጣል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረውን የአገር አንድነት፣
ሰብአዊ መብት መከበር፣ የዲሞክራሲ መጎልበት ሒደት ቀልብሶ የኢትዮጵያን ሕዝብ ዘርና ቋንቋን መስፈርት ባደረገ የክፍፍል
ቀለበት ውስጥ አስገብቶ እርስ በእርሱ እንዲናቆር የሚአደረግ ሥልት ዘረጋ፡፡ ሕዝባችንም በተወለደባት አገር ከቦታ ቦታ
በመዘዋወር በነጻነት መሥራት እንዳይችል በተደረገበት ወቅት መኢአድ ይህን ለአገርና ለትውልድ የማይበጅ ድርጊት በመቃወም
የኢትዮጵያን ሕዝብ አስተባብሮ ሉአላዊነቷ የተጠበቀ፣ እድገቷ የተፋጠነና የህግ የበላይነት የሰፈነባት ዲሞከራሲያዊት ኢትዮጵያን
ለመገንባት የተቋቋመ አንጋፋ ድርጅት ነው፡፡ መኢአድ የህን ለአገርና ለትውልድ የማይበጅ ሥርዓት ሲታገል
ቆይቷል፤ በመታገል ላይም ይገኛል፡፡ መኢአድ ይህን እንቅስቃሴ ሲያደርግ በነበረበት ወቅትም ትግሉ አልጋ በአልጋ አልነበረምና
የገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና አመራሮች በፓርቲው መሪዎች፣ አባላቶችና ደጋፊዎች ላይ ከፍተኛ የሆነና ግፍ የተሞላበት
ድብደባ፣ መሳደድና፣ የመታሰርና የመገደል ዕጣ ሲደርሱባቸው ቆይተዋል፡፡
እጅግ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሚቀየር ቢሆንም የሕዝብ ጥያቄ የሆነውን የነፃነት፣ የሕግ የበላይነት መስፈን፣ የሰብዓዊና
ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ለሚደረገው ትግል የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመምራት በግንባር ቀደምትነት ብቸኛውና ጥንካሬውን
ያስመሰከረው የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ የሆነው መኢአድ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያደረገው ሕዝባዊ
ትግል የኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን የዓለምን ሕብረተሰብ ትኩረት በመሳብ ላይ ይገኛል፡፡ መኢአድ ከስሙ መረዳት
እንደሚቻለው ሕዝባችን በአንድነት በእኩልነትና በመፈቃቀር እንደኖር አስተማማኝ ፖሊሲዎችን ነድፎ ተግባራዊ ለማድረግ
በመላ አገሪቱ በመንቀሳቀስ ላይ ያለ ሀቀኛ የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡
መኢአድ ይህንን ታሪካዊና ህዝባዊ ሃላፊነት ለመወጣት ሲል በሚያደርገው ሁሉንተናዊ የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ የገዥው
ፓርቲ ኢህአዴግ ከቅድመ ምርጫ 97 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በፓርቲው አባላት ላይ ከፍተኛ እንቅፋት መፍጠሩ የቀን ከቀን
ትዕይንት ሆኖ ቀጥሎአል፡፡ ኢህአዴግ ይህን ሁሉ ቢፈጽምም ሚስማር ሲመታ ይጠብቃል እንደሚባለው ሁሉ መኢአድ በአባላቱ
ላይ የሚደርስበትን ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖ፣ ችግርና ሰቆቃ በመቋቋም ለሕዝብና ለሀገር የሚጠቅም ሥራ በመስራት የኢትዮጰያን ትንሳኤ
ለማየት ህዝባዊና ሀገራዊ ሀላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡ አሁን በሀገራችን ኢትዮጵያ የሚታዩት ከዚህ ቀደም ያለፉት የገዥ
መደቦች የሕዝብ ምርጫና ሰላማዊ መንገድ የሥልጣን ሽግግር ባለመከናወናቸው ኢህአደግም ያንን በመከተል ከማንወጣው
ችግር ውስጥ እንድንገባ ተደርገናል ያለፉት የገዢው መደቦች ሰላማዊ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዳይኖር ሕዝቡን በአንድ
ወጥ የአገዛዝ ቀንበር ከሥረው ያቆዩትን ጨቋኝ ልማድ ኢህአዴግ በመረከብ ከህዝባዊ ምርጫ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር
እንዳይኖር በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከብዙ ሺህ አመታት የነፃነት ታሪካችን ባለተናነሰ ሁኔታ በዘር በቋንቋና በጉሳ ሳይለያይ በፍፁም ወንድማማችነት፣
መከባበር፣ መፈቃቀርና መቻቻል አብሮ መኖሩን ታሪክ ይመሰክራል፡፡ ዛሬ የሕዝባችን ችግር ኢህአዴግ እንደሚያራግበው
የክልል፣ የቋንቅ፣ የሀይማኖትና የዘር ልዩነት አይደለም፣ ችግሩ ዳር ድንበራችንን አስጠብቆና አንድነታችንን አጠናክሮ የተለመደ አብሮ
የመኖር የፍቅርና የአንድነት ባህሉን አስጠብቆ ከድህነት ማጥ ውስጥ በማውጣት ለተሻለ ሕይወት ሊያበቃን የሚችል ሐዝብ
የመረጠውና የሕዝብን አመኔታ ያገኘ መንግሥት አለማግኘት ነው፡፡ የኢህአዴግ መንግሥት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአያት ቅድመ አያቱ
ጀምሮ የያዘውንና እትብቱ የተቀበረቡትን መሬት በሀይል ነጥቆ ሕዝባችንን እንደፈለገ የሚነቅለውና የሚተክለው አዲስ አይነት
የመንግሠት ጭሰኛ አድርጎታል፡፡ በገጠርም ሆነ በከተማ የሚገኘው መሬት የኢትዮጵያ ሕዝብ ደሙን ያፈሰሰበት ህይወት
የገበረበት አንጡራ ሀብት ሆኖ እያለ የገዥው ፓርቲ መሬት የመንግሥት እንጂ የሕዝብ የግል ሀብት መሆን አይችልም በሚል
ፈሊጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአባቶቹ የወረሰውን መሬት በኪራይ እንጂ /በጭሰኝነት/ በባለቤትነት በመያዝ ለልጁ እንዳያወርስ፣
እንዳይሸጥና እንዳይለውጥ በአዋጅ ከልክሏል፡፡ በዚህም የተነሳ የኢህአዴግ መንግሥት የመሬትን ፖሊሲ የፖለቲካ ትርፍ
ለማግኘት እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ መሬት ከሀብትም ሁሉ በላይ የሆነ የገበሬው የደምና የአጥንት መስዋዕትነት የተከፈለበት ምትክ
የሌለው ህይወቱ ነው፡፡ ገበሬውም ሆነ ከተሜው ከመኢአድ ጋር ከተጓዝክ የገጠር መሬት በግል ባለበትነት እንዲያዝ ትታገላለህ
ለድልም ትበቃለህ፣ የከተማ ቦታን ከሊዝ ነፃ በማድረግ የምታዝበት አንጡራ ሀብትህ ታደርጋለህ፣
ሕዝብ በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ወድቆ እያለ በነጻነት እንደፈለገው በመንቀሳቀስ ለአገሩ እድገትና ለሕዝቡም ብልጽግና ይሰራል
ማለት አይቻልም መንግሥትም ያምናል ማለት የሕዝብን እውቀት፣ ጉልበትና ሀብት አስተባብሮ ለአገር ልማት ለማዋል በመጀመሪያ
ደረጃ አንዱን ልጅ ሌላውን የእንጀራ ልጅ አድርጎ የሚገዛ መንግሥት ሳይሆን የአገሪቱን ሕዝብ ያሳተፈ፣ ፍትሀዊ የሆነና
ከሙስናና ከአድልኦ የጸዳ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲ በአስተማማኝ ሁኔታ መመሥረት ሲቻል ነው፡፡
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ይህን ክፍተት በመሙላት የኢትዮጵያን ሕዝብ በአንድነት፣ በእኩልነትና ፍትህ
በተሞላበት ሁኔታ በመምራት ለነጻነት ለማብቃት በመታገል ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም መኢአድ በ1997 በቅንጅት ከሌሎች
ኃይሎች ጋር በተሰለፈበት ወቅት በደረሰበት በደልና ግፍ ተስፋ ሳይቆርጥ ባለው ከፍተኛ ህዝባዊ ተቀባይነት የተነሳ በአሁኑ ሰዓት
በመላው ሀገሪቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቢሮዎችን በመክፈት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በዕኩልነት በማሳተፍ ላይ ነው፡፡ በዚህ
የአንድነትና የነጻነት ትግል እንቅስቃሴ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን መብት ለማስከበር ከሁሉም ጋር ጥብቅ የሆነ ግንኙነት ፈጥሮ
ተስፋ የተጣለበት ሥራ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ በመላ ሀገሪቱ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፣
ከርዕሰ ከተማ እስከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ ህብረተሰቡን በማደራጀትና በማንቃት፣ ህዝቡ ስለሀገሩ አንድነት፣ ነፃነትና
የዲሞክራሲ ፅንሰ ሀሳብ ግንዛቤ እንዲያዳብር በማድግ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ የፓርቲው እንቅስቃሴ በሀገር
ውስጥ ብቻ የተወሰነ ባለመሆኑ በተለያዩ ምክንያቶችና መንገድ ሀገራቸውን ጥለው በባዕድ ሀገር በስደት የሚኖሩትን
ኢትዮጵያውያን ጭምር ስለሀገራቸውና ህዝባቸው ማድረግ ያለባቸውን ሁሉ ሀላፊነት በመፈጸም የነፃነት ትግሉ ተሳታፊዎች
ከመሆን አልፈው ባለቤት ጭምር እንዲሆኑ አድርጓል፤ በማድግ ላይም ይገኛል፡፡
መኢአድ በዓለም ላይ ባሉ በርካታ ሀገሮች ተሞክሮ ውጤታማነቱ በተረጋገጠው የሌቨራል ዲሞክራሲ ጽንሰ ሀሳብ ላይ የተመሰረተ
የፖለቲካ ፍልስፍና የሚከተል ፓርቲ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት መኢአድ ዋና ግቡ በአገራችን ስልጣን በህዝብ እጅ እንዲገባና ባጭር ጊዜ
ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በመገንባት፣ ፍትህና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ ለህዝባችን ደህንነትና ልማት ዋስትና
ሊሰጥ የሚችል፤ ባጠቃላይ ለህዝብ መብት መከበር የቆመ መንግሥት መመስረት ነው፡፡ የመኢአድ ተልኮ የኢትዮጵያን ሕዝብ
በነፃዊ ዲሞክራሲ መርህ መሰረት በመምራት የስልጣን አመንጭነቱን፤ ባለቤትነቱንና ተቆጣጣሪነቱን በማረጋገጥ
የበለፀገች ጠንካራ ኢትዮጵያን መገንባት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!
አሁንም ሆነ ወደፊት በቆራጥነት፣ በሙሉ ልብና ብሩህ ተስፋ በተሞላበት ሁኔታ እጅ ለእጅ ተያይዘን በሀገራችን ላይ በአንድነት
የነፃነት ችቦ እንደናበራ ከፓርቲህ ከመኢአድ ጐን እንድትሰለፍ ሀገራዊ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
1. የመጀመሪያው ምርጫ የአሸናፊነቱን መንግሥት መመሥረት ነው፡፡
2. ለዜጋና ለሀገር ከፍተኛ አገልግሎት የሚሰጡ ምሁራንን ከሌሎች ፓርቲዎችም ሆነ ግለሰቦች በመንግሥት መዋቅር ውስጥ
ተሳታፊ እንዲሆኑ ይጥራል ነው፡፡
የመኢአድ የፖለቲካ ፍልስፍናና የወደፊት ራዕይ እንደሚከተለው ይሆናል፡፡
1. ፓርቲያችን በምርጫ የበላይነት ሲቀናጅ ሐገራችንን በጋራና በሕብረት ለመገንባት እንዲቻል እንዳስፈላጊነቱ ከአንድ ወይም
ከዚህ በላይ ከሆኑ ዲሞራሲያዊ ከሆኑት ፓርቲዎች ጋር የጥምር መንግሥት ያቋቁማል፡፡
2. ወቅቱን ጠብቆ በሚከናወነው ምርጫ አንድ ሰው አንድ ድምጽ በሚል የሊበራል ዲሞክራሲ መርሀ መሠረት በግለጽ፣ በነጻና
በፍትሐዊ ምርጫ የሕዝቡን የሥልጣን አመንጭነት በባለቤትነትና በተቆጣጣሪነት ለማረጋገጥ መኢአድ የበኩሉን ሁሉ ያደርጎል፡፡
3. ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጐች የተለያዩ እምነቶችና የፖለቲካ አመለካከቶች በነጻነት ማራመድና ልዩነቶቻቸውን አቻችለው መኖር
የሚችሉበት አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር መኢአድ የበኩሉን ጥረት ያማርጋል፡፡
4. ሕግ አስፈጻሚ አካል በቀጥታ በሕዝብ በሚመረጥና የሥልጣን ዘመኑ በሕግ በተገደበ ኘሬዝዳንት የሚዋቀርና የመከላከያ ኃይል
ተጠሪነቱ ለኘሬዝዳንቱ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ ይሁን እንጂ የመከላከያ ኃይሉ ለፖለቲካ ጉደይ መጠቀሚያ እንዲውል
አይደረግም፡፡
5. የብሔረሰቦች ክልል ያለ ሕዝብ ጥያቄና ያለ ሕዝቡ ውሳኔ /referendum/ የማይቀየር የማይለወጥ ቢሆንም ማንም
ኢትዮጵያዊ በፈለገበት አካባቢ የመኖር፣ የመስራት፣ ሐብት የማፍራት ወዘተ… መብቱ የተጠበቀና የተከበረ እንዲሆን
ይደረጋል፡፡
6. ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብቱ፣ የአካል ደሕንነቱና ነጻነቱ ፍፁም የማይጣስና የማይገሰስ መሆኑን መኢአድ ያምናል፤
ለተግባራዊነቱም ይታገላል፡፡
7. ማንኛዋም ሰው ከሕግ አግባብ ውጭ አይያዝም፣ አይታሰርም፣ አይቀጣም እንዲሁም ሰውነቱም ሆነ የግል ንብረቱ ከሕግ አግባብ
ውጭ አይፈተሽም፣ አይወሰድም፡፡
8. መኢአድ የሌሎች ድርጅቶችን ሕጋዊ ሕልውና የሚያከብር ሲሆን በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች በትጥቅ ትግልና በስደት ላይ
የሚገኙ የፖለቲካ ቡድኖችና ሌሎች ወገኖቻችንን ሰላማዊና በሕዝባዊ ፖለቲካ መንገድ መሳተፍ እንዲሳተፉ ሐገራዊ የድርድር
መድረክ እንዲመቻች ሁሉን አቀፍ የሆነ የፖለቲካ ሥርአት እንዲሰፍን የማያቋርጥ ጥረት ያደርጋል፡፡
9. ሊብራል ዲሞክራሲ በሰፈነባቸው የበለፀጉ ሐገሮች መገናኛ ብዙሃን እንደ አራተኛ የመንግሥት ዘርፍ ይቆጠራል፡፡ በኢትዮጵያም
ተመሳሳይ ሁኔታ እንዲፈጠር መኢአድ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል፡፡

The post መኢአድ በወያኔ ሚዲያዎች በኢቢሲ በፋና በዛሚ እንዳያቀርበዉ የተከለከለዉ ጽሑፍ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>