Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

አስቂኙ የአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ቃለ መጠይቅ! –ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

$
0
0

amsaluየኢሳት ራዲዮና ቴሌቪዥን (ነጋሪተ ወግና ምርዓየ ኩነት) ጋዜጠኞች ከሕዝባዊ ግንባር መሪ አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ተከታተልነው፡፡ ያው አስቀድሜ እንደገመትኩት በአሮጌው ድሪቶ ላይ አሮጌ ጨርቅ ድረታና እብለት ክህደት እንጅ የነበረውን አሮጌውንና ያላዋጣውን በመተው በአዲስና በተመከረ በተማረ ልብ አዲስ ሐሳብ አዲስ መንገድ ለመቀየስ አልተፈለገም፡፡ የሚጠበቀውና አስፈላጊው ግን ይሄኛው ነበር፡፡ ለነገሩ ከአንባገነን ሥርዓት ባለሥልጣናት ይሄ የሚጠበቅ አይደለም እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች እንኳን በአንድ ሰው ዕድሜ ሽህ ዓመታት የመኖር ዕድል ቢሰጣቸው እንኳን እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ሱሪያቸውን በአንገት ለማጥለቅ እንደታገሉ ያልፋሉ እንጅ አይ ሐሳቤ መንገዴ ይሄንን ያህል ዘመን ብታገልም ሊሠራ አልቻለም፡፡ ሊሠራ ያልቻለበትም የራሱ ምክንያት ችግር ስላለበት ሳይሆን አይቀርምና እስኪ ወይ ለሌላው ዕድሉን ልስጥ ወይ አስተሳሰቤን ቀየር ላድረገው አይሉም፡፡ ተፈጥሯቸው አይፈቅድላቸውምና ግትሮች ናቸው፡፡ ሰውየውን አላያቹህትም?  ጓደኞቹን ሰጥ ለበጥ አድርጎ እንቢ ያለውን አጥፍቶ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ ብቻውን ገኖ መግዛት በመቻሉ የሚነበብበትን የእርካታ ስሜት አልታያቹህትም? የተሳካላት የሞላላት ሀገር መሪ እንጅ በተወሳሰበ ችግር ውስጥ ያለች ከዕለት ወደ ዕለት እየተመሰቃቀለች የሕዝቧ ኑሮም እየከፋ ያለች ሀገር መሪ ይመስል ነበር?

እናም ከቃለ ምልልሱ አንድም እንኳን ፍሬ አላገኘሁበትም፡፡ እንዲህ ይባላል እንዲህ ይባላል ስለሚባሉ ነገሮች ተወራ እንጅ በፖለቲካዊ (በእምነተ አሥተዳደራዊ) ጉዳዮች ላይ ግብራዊ (ቴክኒካል) የሆኑ ጥያቄዎች ለምሳሌ በአሰብ ወደብ ዙሪያ ያለውና የመሳሰሉ ዋና ዋና ጉዳዮች ስላልተዳሰሱበት በግሌ ቅር ብሎኛል፡፡ ሲጀመር ቃለ መጠይቁ የቃለ መጠይቅ አሠራርናንና ሒደትን የተከተለ አይደለም፡፡ ጋዜጠኞቹ ትግርኛን ባለማወቃቸው ጥያቄዎችን መጠየቃቸውን እንጅ የጠየቁት ጥያቄ በአግባቡ ስለመመለሱና አለመመለሱ ማረጋገጥ እንዳይችሉ አድርጓል፡፡ ሰውየው ማውራት የምፈልገው በትግርኛ ነው ካሉ መብታቸው ነው ነገር ግን የሚመልሱትን ለጋዜጠኞቹ የሚተረጉም አስተርጓሚ በመሀል መኖር ነበረበት፡፡ ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ እንዴት ቃለ ምልልሱን ለማድረግ እንደፈቀዱ አልገባኝም፡፡ አስተርጓሚ ከሌለም ጠያቂዎቹና ተጠያቂው በጋራ በሚያውቁት ቋንቋ መደረግ ነበረበት፡፡ ወደ ኋላ ላይ አቶ ኢሳይያስ ከትግርኛ ወደ እንግሊዝኛ በመሔዳቸው ለጋዜጠኞቹ ሰውየው የሚሉትን ነገር ምንነት ለመረዳት የተሻለ ዕድል የሰጣቸው ቢሆንም የተጠቀሙበት ግን አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ጥያቄው ይጠየቃል ሰውየው የፈለገውን ሰዓት ያህል ወስዶ ሌላ ነገር ሲቀበጣጥር ቆይቶ ሲጨርስ ሌላ ጥያቄ ደሞ ይጠይቃሉ እንጅ ከጭብጥና ከነጥቡ ውጭ ሲወጣባቸው መመለስ፣ በአግባቡ ያልተመለሰውን እንዲመልስ ማድረግ፣ በዋሸባቸው ወይም በካዳቸው ባበለባቸው ጉዳዮች መሞገት የተባሉ የጋዜጠኛ ሥራዎች ሲሠሩ ባለማየቴ ከፍቶኛል፡፡ ኢሳት ኢሳትን እንጅ ኢቴቪን መሆን አልነበረበትን፡፡ በእርግጥ እነዚህ የኢሳት ጋዜጠኞች ከብቃት ማነስ ሳይሆን ከአቶ ኢሳይያስ ጋራ በገለጽኩት መልኩ ቃለ መጠይቅ ማድረግ እንደ ሌሎቹ ሁሉ እነሱንም እንዳይመለሱ አድርጎ ወኅኒ ሊያስወርዳቸውም ይችላልና ይሄንን ከመፍራት ሳያደርጉት ቀርተው ከሆነ ልንረዳላቸው ይገባል፡፡ አስቀድሞ እንዲህ ዓይነት ሥጋት ከነበራቸው ደግሞ ቃለመጠይቁን ማድረጉ አስፈላጊ አልነበረም፡፡

አንዴ ብቻ አቶ ኢሳይያስ 90ሽህ የደርግ ወታደሮችና ባለሥልጣናት ከባሕረምድር ተሸንፈው በሚወጡበት ወቅት “እንኳን የበቀል እርምጃ ስድብ እንኳን የተናገራቸው አንድ ሰው እንኳን የለም” በማለት የሰውየውን የውሸታምነት ደረጃ የሚያሳይ አስቂኝ ቃል በተናገሩ ጊዜ ፋሲል ምንም እንኳን ሰውየው ተናግረው ጨርሰው ሌላ ጥያቄ ለመቀበል በተዘጋጁበት ሰዓት ቢሆንም “እዚህ ላይ ይቅርታ ላቋርጥዎት” በማለት እነዚህ አቶ ኢሳይያስ 90 ሽህ ናቸው ያሏቸው የደርግ ወታደሮችና ባለሥልጣናት ጥርሳቸውን ሳይቀር እንዲወልቅ እንደተደረገ የእጅ ሰዓት የአንገት ሀብልና ሌሎች ንብረቶች ሁሉ እንደተዘረፉ በታሪክ እንደሰማ አሁን እሳቸው ያሉት ደግሞ ከዚህጋር እንደተለየበት ጠይቋቸው ነበር፡፡ ምንም እንኳን አቶ ኢሳይያስ ለዚህ ጥያቄ ምን እንደመለሱ ኢሳት ባያስደምጠንም ቅሉ፡፡ ለመሆኑ የዚህን ጥያቄ መልስ እንዳንሰማው የተደረገው ለምንድን ነው?

አቶ ኢሳይያስ የገረሙኝ ነገር ቢኖር ፖለቲካዊ ጉዳዮችንስ እሽ መደበቅ የሚፈልጉት ጉዳይ ስለሚኖር ለመሸሽ ሌላ ሌላ ነገር ቀበጣጥረው አለፉ እንበል እሳቸው እኮ ቢናገሩት አድማጩን ምንም የማይጠቅመውንና የሚያውቀውን ጉዳይ ሁሉ እኮ ነበር ሊናገሩ ያልቻሉት፡፡ ለምሳሌ ስለ ራሳቸው ስለ ልጆቻቸው ተጠየቁና ሲመልሱ ይሄም ቁም ነገር ሆኖባቸው ልጆቻቸው ማን ማን እንደሚባሉና ስንት እንደሆኑ ምን እንደተማሩ አንድም ነገር ሳይናገሩ ተፈላሰፍኩ አሉና “ዘለው የባለ ሥልጣን ልጆች ስለሆኑ ከሌላው በተለየ ሊታዩ አይገባም እነሱም ሰው ናቸው ሁለት ዐይኖች እንጅ አራት ዐይኖች የላቸውም ሁለት ጆሮዎች እንጅ አራት ጆሮዎች የላቸውም ሁለት እግር እንጅ ሁለት እጅ እንጅ አንድ አፍንጫ እንጅ አንድ ምንትስ ሁለት ቅብርጥስ” እያሉ በመዛዛት ስንት ነገር ሊሠራበት የሚችለውን ወርቃማ ጊዜ እንዲያው በከንቱ አባከኑብን፡፡ ከሰው ልጅ ከተወለዱ ሁለት አንድ እያሉ የዘረዘሯቸውን የሰውነት አካላት እንደሚይዙ ማን ያጣዋል ብለው ነው አቶ ኢሳይያስ? መጀመሪያ እነማን እንደሆኑ መች አስተዋወቁንና? ስለነሱ ልናወራ የምንችለው መጀመሪያ ልጆች እንዳሏቸው ሲያሳውቁን አልነበረም እንዴ? ያሉት ነገር እውነት በሆነ በእውነት ከፍልስፍና በቆጠርኩልዎት ነበር እርስዎንም ለሕዝብ እንደሚያስብ ቅን አሳቢ ቡቡ መሪ በቆጠርኩዎት ነበር፡፡ አቶ ኢሳይያስ እንዲያው ግን ሰው ይታዘበኛል የሚባል ኅሊናም የለዎት? አሁን ማን ይሙትና እርስዎን ጨምሮ ልጆችዎ የእርስዎ ልጆች ኑሮ ከተራው ዜጋ ኑሮ ምንም ያልተለየ ነው? እርስዎና የእርስዎ ልጆች አብዛኛውን ጊዜ የሚበላውን አጥቶ በቀን አንዴ እንደሚበላው ባስ ሲልም ጦም እንደሚያድረው እንደአብዛኛው የገጠር ሕዝብዎና እንደከፊሉ የከተማ ሕዝብዎ ጦም አድራቹህ ወይም በቀን አንዴ ብቻ ተመግባቹህ ታውቃላቹህ? የምትቀይሩት ልብስ አጥታቹህ በአንድ ልብስ ላይ ተጣብቃቹህ ታውቃላቹህ? መኝታቹህን ትኋን ቁንጫና ቅማል ይዘልበታል? ባለው ከፍተኛ የውኃ ችግር እንደሌላው ሁሉ ልብሶቻቹህ ሳይታጠቡ ንጽሕናቹህ ሳይጠበቅ በክታቹህ ትሰነብታላቹህ? የማይመስል ነገር እየቀባጠሩ ሲወሸክቱ ምን ያህል ግብዝና አስመሳይ አታላይ መሆንዎ ነው ቁልጭ ብሎ የታየኝ፡፡

የጥያቄዎችን ጭብጥና ነጥብ ሳይጠብቁ የሰውነት አካላትን ሁሉ አንድ ሁለት እያሉ እርባና የሌለውን ዝባዝንኬና የባጥ የቆጡን ወሬ እየቀበጣጠሩ ረጅም ሰዓት ማውራት ችሎታና ብቃት መስሎዎት ነው አቶ ኢሳይያስ? ለዛ ነው እንዴ “በዚህ ጉዳይ ላይ ለሰዓታት ላወራ እችላለሁ!” ሲሉ ደረትዎን ነፍተው የተናገሩት? አየ አቶ ኢሳይያስ! እንደ ማን የሆኑ መስሎዎት ነው? እንደ ኩባው ፊደል ካስትሮ? ነው ወይስ እንደ ሊቢያው ጋዳፊ? እንዲህ ጊዜ ወርቅ በሆነበት ከወርቅም አልማዝ ከአልማዝም ዩራኒየም በሆነበት ዘመን በዝባዝንኬ ወሬ እርስዎም ሥራ ፈተው እኛንም ቁምነገር ያወራሉ መስሎን ሥራ አስፈትተው ይሆናል ብለው ነው? ነው ወይስ “ጊዜ ወርቅ ነው” የሚለው ብሂል ገና እርስዎ ላይ አልደረሰም? አዎ በሥራዎ በአስተሳሰብዎ ሁሉ እያየነው አይደል? አሁን ሌላ ጊዜ አቶ ኢሳይያስ ቃለ መጠይቅ አላቸው ቢባል ማን ነው ቁጭ ብሎ የሚሰማልዎት? አየ አቶ ኢሳይያስ! ለሌላው ጊዜ ግን ሲጠየቁ በነጥቡ ላይ ብቻ አተኩረው ከጭብጥ ሳይወጡ ጥያቄውን መመለስ ነው እንጅ ያልተጠየቁትን የሰውነት አካላት በመዘርዘር የሰው ውድ ጊዜ አያባክኑ እሽ? መመለስ የማይፈልጉት ጥያቄ ካጋጠመዎት ደግሞ እንደሌሎቹ መዝለል ነው እንጅ የማይረባ ዝባዝንኬ መቀበጣጠር ያስገምትዎታል፡፡

አቶ ኢሳይያስ በጣም አስገራሚ ሰው ነዎት፡፡ ፍልስፍናው እንደሱ አይደለም፡፡ ቅዠት በሆነና የትም ቦታ ባልታየ ሊታይ ሊተገበር ባልቻለ የኮሚውኒዝምና (መደባዊ ያልሆነ ሥርዓተ ማኅበር) የሶሻሊዝም (የኅብረተሰባዊነት) ፍንስፍና እየዳከሩ ጊዜዎን በከንቱ ባያቃጥሉ ሕዝቡንም ባያደክሙ ባያንገላቱት መልካም ነው፡፡ ምክንያቱም ይሄ ፍልስፍና ሲበዛ ተምኔታዊ (Ideal) በመሆኑና ማንም ሀገር በትክክል ሊተገብረው ስላልቻለ ሊተገበርም ስለማይቻል፡፡ ሲሰሙት ደስ ይላል አማላይም ነው ተግባራዊ ማድረግ ግን ፈጽሞ የሚቻል አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ትንሽ የጭንቅላት እጥበት (brain wash) ላደርግዎት እፈልጋለሁ፡፡ ይሄውልዎት አቶ ኢሳይያስ እያንዳንዱ ሰው የልፋቱን ያህል ማግኘት ካልቻለና ጠንካራውም ደካማውም ምሁሩም መሀይሙም እኩልና ተመሳሳይ የኑሮ ደረጃ እንዲኖረው ከተደረገ ውጤቱ ሰውን ከአቅም በታች እንዲሠራ እንዲለግም ያደርጉታል በዚህም ሀገር ትጎዳለች እንጅ እንዲተጋ፣ አቅሙን አሟጦ እንዲፈጋ፣ እራሱን በሥራ እንዲጠምድ፣ ለጥራት ትኩረት እንዲሰጥ ሊያደርጉት አይችሉም ንግድን ጨምሮ ሌሎች እንቅስቃሴዎች ሁሉ አይነቃቁም፣ ኑሮ ፉክክር የሌለበትና አሰልች ይሆናል ፈጠራ ግኝትና ፍልሰፋን የመሰሉ የንቁ ጭንቅላት ፍሬዎችማ ጨርሶ የሚታሰቡ አይሆንም፡፡ ሰው አዳዲስ ነገር ሊፈጥር ሊያገኝ ሊፈለስፍ የሚችለው የሚበረታታው የድካሙን የልፋቱን የጥረቱን ያህል ሲከፈለው ዕውቅናና አክብሮት ሲቸረው እንጅ ያንን ያህል ደክሞ ለፍቶ ጥሮና ግሮ ከተራው ዜጋ ጋር በተመሳሳይ የኑሮ ደረጃ እንዲኖር ሲደረግ አይደለም፡፡ ይሄ የሥራ መነቃቃት ስሜትን ይገላል፡፡ ለብርቱው ለታታሪው ለጠንካራው የየጥረቱን ያህል ዳጎስ ዳጎስ ያለ ክፍያ ሲከፈለው ግን መነቃቃት ይፈጠራል፡፡

አንድ ቀላል ምሳሌ ልስጥዎት አቶ ኢሳይያስ፡- በአንድ ክፍል ውስጥ ተማሪዎች ብቃታቸውና ችሎታቸው የተለያየ ሆኖ እያለ እኩል ነጥብ ልስጥ ይላሉ እንዴ? ሁሉም ተማሪዎች እኩል የመቀበልና የመረዳት አቅም ችሎታ ሊኖራቸው አይችልምና ወይም አንደኛው ከሌላኛው ሊጎብዝና ሊሰንፍ ይችላልና እኩል ነጥብ ልንሰጥ አንችልም አይገባምም ካደረግነውም አሠራራችን ፍትሐዊና አመክንዮአዊ አይሆንም፡፡ የተፈጥሮ ጉዳይ ነውና ሁሉንም እኩል ማጎበዝ እኩል እንዲያስቡ ማድረግም አይቻልም፡፡ ልናደርግ የምንችለው ሁኔታዎችን በማመቻቸትና በመርዳት የሚሰንፍ ሰው እንዳይኖር ምርጥ ብቃቱን ችሎታውን እንዲጠቀም ማድረግ፡፡ እንዲህ አድርገን ከረዳናቸው በኋላ ችሎታቸው ብቃታቸው በፈቀደላቸው መጠን የሚያመጡትን ውጤት ግን የየችሎታቸውንና ውጤታቸውን ያህል ነው ሊሆን የሚገባው፡፡ ይሄ ካልሆነና ለሁሉም እኩል ነጥብ የሚሰጥ ከሆነ ግን የሚጎብዝ ተማሪ ሊወጣ አይችልም፡፡ ምን አለፋውና? በሥራም ዘርፍ ያለው ነገር እንዲሁ ነው፡፡ ስለሆነም ጠንክሮ በርትቶ የሠራ ሀብታም የሚሆንበት የተሰጠውን ዕድልና ድጋፍ መጠቀም ሳይችል ቀርቶ የወደቀው ደግሞ ደህይቶ በድህነት የሚቀጣበት ሁኔታ ክፍት መሆን አለበት፡፡ ባለፀጋው በድካሙ በጥረቱ በልፋቱ አግኝቷልና የድካም ፍሬውንም እንዲበላ ሊፈቀድለት ይገባል፡፡ ሰው የሚደኸየው በስንፍናው ብቻ አይደለምና ባለጸጋው በሰብአዊነት በራሱ ፈቃድ ድሆችን መርዳት ከፈለገ ግን የፈቀደውን ያህል ያለውን ማካፈል መብቱ ነው፡፡ የሞራል (የቅስም) ግዴታም አለበት፡፡ በግድ ግን ያለህን አምጣ ከሌላው የተለየ የላቀ ኑሮ ልትኖር አትችልም ሊባል አይገባም፡፡ በዚህ ዓይነት አሥተዳደር ሀገር ልትገነባ ዜጎች ሊለወጡ አይችሉም፡፡

የሀገራት መሪዎች ሊጠነቀቁ የሚገባው ነገር ቢኖር ለሁሉም ዜጋ ሠርቶ ሊለወጥ ሊበለጽግ የሚችልበት እኩል ዕድል የመኖሩን ጉዳይና ሕግ ከፈቀደው መንገድ ውጪ ሊበለጸግ የሚቻልበትን ሙስናን የመሰለ አግባብ ያልሆነና ሕገ ወጥ አሠራር ኖሮ ዜጎች ሠርተው መለወጥ የሚችሉበትን ዕድል አጥተው ጥቂቶች ወንጀለኞች ብቻ ደግሞ የሚበለጽጉበት ሁኔታ እንዳይፈጠር እንጅ በነጻና ፍትሐዊ ፉክክር የጠነከሩት የበረቱት ሠርተው ማግኘት መለወጥ የሚችሉት ዜጎች መኖራቸው አይደደለም ሊያሳስባቸው የሚገባው፡፡ ይሄማ ሥጋት ነው ሊሆን የሚችለው የአንባ ገነን መሪዎች ሥጋት፡፡ በበረቱ በበለጸጉ በነቁ በበቁ ሰዎች እንዋጣለን ጥቅማችን ይጎዳል ሥልጣናችንን ሁሉ ልናጣ እንችላለን የሚል የሀገርን ጥቅም ሳይሆን የግል ጥቅማቸውን ማዕከል ያደረገ ሥጋት፡፡ ሲመስለኝ የእርስዎም ሥጋት ይሔው ነው ምክንያቱም ከላይ እንደገለጽኩት እርስዎ የተናገሩትን እርስዎም ሆኑ ልጆችዎ አትኖሩትምና ነው፡፡ ጉርድ ሸሚዝና ክፍት ጫማ አድርገው መታየትዎ ወደ ኋላ ላይ ተስቶዎት እውነቷን እንደተናገሩት ቀለል ያለ የኑሮ ዘይቤ ስለሚወዱ እንጅ መግቢያዎ ላይ ለማወናበድ ይታሰብልኛል ብለው እንደገመቱትና እንደተናገሩት ከተራው ሕዝብ የተለየ ኑሮ እንዲኖርዎት የማይፈልጉ ስለሆኑ አይደለም፡፡ ባሰኘዎት ጊዜና ቦታ ደግሞ እንዴት እንደሚዘንጡ በሚገባ እናውቃለንና፡፡ በእርግጥ አንዳንድ የዋሀንን ሊያታልሉ ይችሉ ይሆናል የሆነ ሆኖ ግን እውነት ያልሆነና የማስመሰል ነገር መሠረታዊ የሆነ ለውጥ አያመጣምና እንዲህ ዓይነቱን ነገር ቁም ነገሬ ብለው ባይይዙት መልካም ነው፡፡ እርስዎንም ማንንም አይጠቅምምና፡፡

በተመሳሳይ ስለ የትጥቅ ትግል ለማድረግ እናንተጋ ስላሉት የተቃውሞ ኃይሎች “ሸአቢያ አንድ እንዳይሆኑ ያደርጋል፣ በዘር ወይም በብሔር እየከፋፈለ በማደራጀት የተለያየ ዓላማ ያላቸውን የተለያዩ ብሔር ተኮር የፖለቲካ ድርጅቶችን ይፈጥራል ይባላልና ለዚህ ምላሽዎ ምንድን ነው?” ተብለው ለተጠየቁት በመቀበጣጠር “ኦነግን፣ ኢሕአፓን፣ ምንትስን እያሉ እኛ ከመመሥረታችን በፊት የተመሠረቱ በመሆናቸው እኛ ልናደራጃቸው አንችልም” አሉ ታደራጃላቹህ የተባላቹህት መቸ እነሱን ሆነና? በደንብ ካላዳመጡ ጥያቄው እንዲብራራልዎት መጠየቅ ነው እነማንን ማለትህ ነው ቢሉ ይዘረዘርልዎት ነበር እነሱንስ ቢሆን እንዳይግባቡና አንድነት እንዳይፈጥሩ እንደሚያደርጉ የማናውቅ ይመስልዎታል? አዳዲሶቹን በሀገሪቱ ያለው የወያኔ የዘር ፖለቲካ የፈጠራቸው እንጅ እኛ አልፈጠርናቸውም አሉ “ለማያውቅሽ ታጠኝ” አለ ያገሬ ሰው እነ መለስ ሕገመንግሥቱን ሲያሳዩኝ የኢትዮጵያን ሕዝብ በዘር የሚከፋፍልና የማይጠቅም ነው ብለው ወያኔን የመከሩ ሰው ከሆኑ በወያኔ የዘር ፖለቲካ ተሳስተው በሀገርዎ የተደራጁ ወገኖችን መክረውና እንደማይጠቅም አስረድተው በአንድ እንዲደራጁ ማድረግ ምን ነው ተሳነውትሳ ታዲያ አቶ ኢሳይያስ?

እኔማ የሚጠየቁት ሌላ የሚመልሱት ሌላ ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ አራንባና ቆቦ እየሆነ ሲያስቸግረኝ ይቅርታ ይደረግልኝና ሰውየው ጤነኛ መሆናቸውን ሁሉ ለመጠራጠር ነው የተገደድኩት፡፡ ዝም ብሎ ይቀዳል ሰውየው እውነት ተናገረ ውሸት የሚለውን ለጊዜው እንተወውና እንደ ፖለቲከኛ እንኳን ምን ብል ይታመንልኛል? ምንስ ብል አይታመንልኝም? የሚለውን ነገር ጨርሶ መለየት የሚችል ሰው ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ጤነኛ ሰው እኮ ሲጠይቁት ምን እንደጠየቁት አውቆ ተረድቶ የተጠየቀውን በአግባቡ ሲመልስ እንጅ የተጠየቀውን ትቶ ጨርሶ የማይገናኝ ነገር ከቀበጣጠረ እንዴት ነው ጤነኛ ነው ልንል የምንችለው? ባጠቃላይ ሰውየው አውርቶ የሄደው ሊያወራው ሲዘጋጅበት የሰነበተውንና የሸመደደውን ነገር ነው አውርቶ የሄደው ጥያቄ የተባሉት ባይሰነዘሩና ቪዲዮ ካሜራ (መቅረጸ ትዕይንት) ደቅነው ቢተውለት ራሱ ይሄንኑ ራሱን አንዳችም ሳይቀንስ ሳይጨምር ሊያወራላቸው ይችል ነበር፡፡

ሲያወራው የነበረው በጠቅላላ ሐሰት ነበር፡፡ ምን እንደሚዋሽም አላወቀም ለምሳሌ እነዚያ 90 ሽህ የተባሉ የደርግ ወታደሮችና ባለሥልጣናት ሁሉም ባይሆኑ በአብዛኛው በሕይዎት ባሉበትና የተፈጸመባቸውን ግፍ በሚገባ ሊናገሩ ሊመሰክሩ ሊያረጋግጡ በሚችሉበት ሁኔታ ሽምጥጥ አድርጎ ክዶ “እንኳን የበቀል እርምጃ ስድብ እንኳን የተናገራቸው አንድ ሰው የለም” ባለበት ሁኔታ ሰውየው ምን እንደሚያስተባብል ምን እንደማያስተባብል ለይቶ ያውቃል ማለት እንዴት ነው የሚቻለው? አቶ ኢሳይያስ ያ የሠሩት ግፍ ከባድነት ታወቃቸው እንዴ? ነው ወይስ ካደረሱባቸውም ግፍ በላይ ሳይፈጇቸው በመልቀቃቸው ቆጫቸው?

ለነገሩ ሰውየው ይሄ ጠፍቶት አይመስለኝም ሰውየው ከገመትኩት በላይ የተዋጣለት አሽሙረኛ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ አቶ ኢሳይያስ በወቅቱ 90 ሽህ ናቸው ባሏቸው የደርግ ወታደሮችና ባለሥልጣናት  ላይ ምን ምን ዓይነት ግፍ እንደተፈጸመባቸው በምን መልኩ ሰብአዊ ክብራቸው ተዋርዶና ንብረታቸው ተዘርፎ የወርቅ ጌጣጌጥ እንደ ቀለበትና ሀብል ደብቃቹሀል እየተባሉ እያስጎነበሱ ፍንጢጣቸው ሳይቀር እየተፈተሸ ከለበሱት ልብስ አቅም እንኳን እያስወለቁ ድሪቶ እያለበሱ ወይም እርቃናቸውን እየሆኑ እንዲወጡ እንደተደረጉ አቶ ኢሳይያስ አትተውት ወይም ሳያውቁ ቀርተው አይደለም፡፡ ነገር ግን የደርግ ወታደሮችና ባለሥልጣናት የነበሩት በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ሆነው አሁንም ድረስ በተቃውሞው ጎራ ተሰልፈው ሀገራቸውን ለማገልገል በሚያደርጉት ጥረት ሸአቢያ ጥቅሙ እየተጎዳበት ማንነቱ እየተጋለጠበትና በ1990ዓ.ም. ላይ በተደረገው ጦርነትም ጉልህ ሚና መጫወታቸው እነዚህን ወገኖች በሕይዎታቸው የማይረሱትን ክፉ የሕይዎት አጋጣሚ እንዲያስታውሱት አድረገው አቁስለው ሲያበቁ እንደገና ደሞ ያኔ ከተፈጸመባቸው ግፍ በላይ የተፈጸመባቸውን ግፍ ፈጽሞ እንዳልተፈጸመባቸው ተደርጎ ተሸምጥጦ በመካዱ እንደገና እንዲቆስሉ እንዲያሩ እንዲበግኑ ማድረግ ፈልጎ ነው ሰውየው ሀገር ያወቀውን ፀሐይ የሞቀውን የአደባባይ ምሥጢር ሸምጥጦ ለመካድ የሞከረው፡፡

እናም ብቻ በእነዚህ በእነዚህ ምክንያቶች ይሄ ቃለ መጠይቅ እርባና ቢስ የሚነሣ ነገር አንድ እንኳ የሌለው ነው የሆነብኝ፡፡ ነገር ግን እንዲያው አንዳንድ የገረሙኝንና የሰውየውን የዋህነት አጉልተው ያሳዩኝን አንዳንድ ነገሮች ሰውየውንም ሀገራችንንም ሕዝባችንንም እጅግ የሚጎዱ ሆነው ስላገኘኋቸው በእነሱ ጉዳዮች ላይ ማውራት ግድ ብሎኛል፡፡

አንደኛው አቶ ኢሳይያስ ፈርጠም ብለው ሲናገሩ ምን አሉ? “የሁለቱም ሀገሮች ግንኙነት 1997 (1989ዓም.) በፊት ወደ ነበረው ሰላማዊ ግንኙነት መመለስ አለበት” አሉ፡፡ ይህች አነጋገር እንዲህ ቀላል አነጋገር እንዳትመስላቹህ፡፡ አቶ ኢሳይያስ እንዲህ ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ ለብዙዎቻችን ግልጽ እንዳልሆነ እገምታለሁ፡፡ አቶ ኢሳይያስ እንዲህ ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? እንደምታስታውሱት ወያኔና ሸአቢያ ግፍን የሚመለከተው የመድኃኔዓለም እጅ ገብቶበት ግንኙነታቸው ሻክሮ ከመጣላታቸው በፊት ሸአቢያ በሀገራችን የኢኮኖሚ (የምጣኔ ሀብት) እንቅስቃሴ ከፍተኛ ጫና ይፈጥር ነበር፡፡ አንድ ምሳሌ ብሰጥ ኤርትራ አንድ እንኳን የቡና ችግኝ የማይገኝባት ሆና እያለ በዓለም ካሉ ታዋቂ ቡና ላኪ ሀገራት ውስጥ አንዷ ሆና የተመዘገበችበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ቡናችንን ብቻ ይደለም እንደ ሰሊጥና ጥጥም የመሳሰሉ የግብርና ምርቶቻችንንም እንጅ፡፡ በዚያ ወቅት ሸአቢያ ያለ አንዳች ከልካይ በሀገራች ገበያ ላይ እንደፈለገ እየዋኘ ምርቶችን እየጫነ እየወሰደ ነበር ለውጭ ገበያ ያቀርብ የነበረው፡፡ አቶ ኢሳይያስ 1989ዓም. በፊት ወደ ነበረው ግንኙነት መመለስ አለበት ሲሉ አሁንም እንደያኔው ገብቸ የምዘርፍበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ማለታቸው ነው፡፡ ለጦርነቱ መፈጠር መንስኤ የሆነውም ይሄው ነው ወያኔም በመንቃቱና ሸአቢያ የሚያገኘውን ጥቅም በንግድ ድርጅቶቹ በኩል ለራሱ ሊበላ ስለፈለገና ሸአቢያን በመከልከሉ በተፈጠረው ውዝግብ ሸአቢያ እነዚህንና ሌሎች ምርቶችንም ከሀገራችን እየዘረፈ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የማይችልበት ሁኔታ መፈጠሩ ነው የጦርነቱ መንስኤ፡፡ ባድመ ሰበብ እንጅ ትክክለኛው መንስኤ እሱ አልነበረም፡፡ እናም አቶ ኢሳይያስ ያ ወርቃማ ዘመናቸው ዛሬም ድረስ በዐይናቸው እንደዞረ አለ ደግመው ሊያገኙትም እጅግ ይመኛሉ ይቋምጣሉም፡፡

እኔ ከዚህ ቃለ መጠይቅ የተረዳሁት ነገር ቢኖር ሸአቢያ ከሚገመተው በላይ አደገኛ የሆነ የጥገኝነት ተፈጥሮና አስተሳሰብ እንዳለበት ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ ነው አቶ ኢሳይያስ “የኛ ፍላጎት የነበረው ከኢትዮጵያ ጋር በአንድ ገንዘብ፣ በአንድ የቁጥጥር (monitory) እና የመንግሥት ገቢ (fiscal) መመሪያ (policy) እንድንተዳደር ነበር” አሉ፡፡ ይታያቹህ! አቶ ኢሳይያስ ለመሆኑ ተገንጥለናል ራሳችንን የቻልን ሉዓላዊ ሀገር ሆነናል ካሉ በኋላ እንዴትና ለምንድን ነው እሱ በአንድ ገንዘብ፣ በአንድ የቁጥጥር (monitory) እና የባጀት (fiscal) መመሪያ (policy) እንድንተዳደር የተፈለገው? በጣም የሚገርም እኮነው! እንደ አቶ ኢሳይያስ ያለ የድንጋይ ዳቦ ዘመን ብልጥ ሰው አጋጥሟቹህ ያውቃል? ለመሆኑ እንዲህ ዓይነት ግንኙነት ተጎዳኝተን ስናበቃ ሀገራችንን ማን እንድንላት ነበር ያሰቡት አቶ ኢሳይያስ? የተባበረችው ኢትዮጵያ ነው ወይስ ሌላ ስም ነበረዎት? ለካ የአፍሪካ ሲንጋፖርን የመፍጠር ሕልምዎን እውን ሊያደርጉት ያሰቡት በሀገራችን ሀብት ኖሯል? ባይሆንማ ኖሮ እነሆ ሲንጋፖር ሲሆኑ እናይዎት አልነበር! ለነገሩ እርስዎ ምን ያድርጉ ይሄንን እንዲያስቡ ያስገደደዎት ባሕረ ምድርን ከገነጠሉ በኋላ ባሕረ ምድርን እንደሀገር ህልውናዋን ለማስቀጠል ብሎም ለእድገት ብልጽግና ለማብቃት የሚያበቃ የተፈጥሮ ሀብት አልባ ሀገር ሆነችብዎት አይደል? ማጣፊያው አጠረብዎት አይደል? ሲጨንቅዎት ምን ያድርጉ? ያለዎት አማራጭ ሀገራችንን እየቦጠቦጡ የአፍሪካን ሲንጋፖር ማለም ነው፡፡

“የምን ዐይነ ደረቅ” የሚባለው ነገር ነው የሆነብን፡፡ አዩት አይደል የእርስዎን (የሕዝባዊ ግንባርን) ስሕተት? ሀገር እንደ ገበሬ ጓሮ ለብቻየ ተብሎ የሚፈጠር ነገር አለመሆኑን ተረዱት አይደል? ሀገር ሲታሰብ ብዙ ነገር ያስፈልጋል፡፡ ይሄንን ሁሉ ነገር ቀድሞ ለማየት ለመገመት የሚችል ጭንቅላት ስላልነበረዎት ይህ የገጠመዎት ችግር በፊት አልታየዎትም ነበር፡፡ በእርስዎ እውቀትና እምነት አንድ የሆነ መሬትን ቆርሶ ወይም ገንጥሎ መውሰድ ከተቻለ ሀገር የሚሆን ይመስልዎት ነበር፡፡ የሚያሳዝነኝ ነገር እንዲህ እንደእርስዎ ባሉ ሰዎች የሕዝብ ዕጣ ፋንታ መወሰኑ ብቻ ሳይሆን ድርጊታቹህ የተሳሳተ እንደነበር ብታውቁም ተሳሳቱ ላለመባል ብቻ አምናቹህ አለመቀበላቹህና ለመታረም ባለመፈለግ ሕዝብን ተጨማሪ ዋጋ እንዲከፍል ማድረጋቹህ ነው፡፡ ስሕተትን ለመሸፈን መፍትሔ አድርጋቹህ ለመውሰድ የምትፈልጉት ጉዳይ ደግሞ ነገሩን ይባስ ከድጡ ወደ ማጡ የሚወስድ መሆኑ ነው ሌላው የሚገርመው ነገር፡፡ አሁንም ይህን መፍትሔ አድርጋቹህ ያያቹህትን ነገር ለዘለቄታው ማርድረግ ይቻላል ወይ? ብላቹህ ለማሰብ አለመቻላቹህ አሁንም ደካማ የማሰብ ችሎታቹህን የሚያሳይ ነው፡፡ አቶ ኢሳይያስ ፈጽሞ የፖለቲከኛ ጭንቅላት የለዎትም ሌላ ሊሠሩ የሚችሉት ነገር ካለ ትተውት ቢሄዱ መልካም ነው፡፡ እንዴ! እርስዎና ወያኔ የምትገርሙኝ ነገር ቢኖር እናንተ ያልቻላቹህበት እንደሆነ በእናንተ ስሕተቶች እኛ መሰቃየት አለብን እንዴ? ምናለ ሐፍረት ቢሰማቹህ? ምን ዓይነት ሰብእና ቢኖራቹህ ነው ሐፍረት የሚባል ነገር ጨርሶ ሊሰማቹህ የማይችለው? ለማንኛውም ሲያምርዎት ይቅር እርስዎና ቢጤዎችዎ ከድንቁርና ቅዠታቹህ ጋር ገሀነም ትወርዳላቹህ እንጅ ኢትዮጵያን በመቦጥቦጥ ሲንጋፖርን መሆን አይቻልም፡፡

ሌላው ደግሞ አቶ ኢሳይያስ ምን አሉ? “እኔ ስለ 3ሽህ ወይም ከዚያ በላይ ዓመታት ስላለው ታሪክ ማውራት አልፈልግም ማውራት የምፈልገው ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወዲህ ያለውን ነው፡፡ ብዙ ጊዜ 20ኛው መቶ ክ/ዘ ታሪክ የአፍሪካ ሀገሮች ታሪክ ብለን ስንል የ 19ኛው መቶ ክ/ዘ መጨረሻ ታሪክ ማለታችን ነው፡፡ ምክንያቱም የቅኝ ግዛት ድንበር የሚባለው ነገር የሚመጣው ያኔ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ግን የአጋንንት ሳጥን (Pandora’s box) ምናልባት 19ኛው ወይም 18ኛው መቶ ክ/ዘ ቅኝ ግዛት ከመምጣቱ በፊት ይሄ አካባቢ ምን ይመስል ነበር? ብሎ መነጋገር ይቻል ይሆናል ይሄ ግን ሌላ ርእስ ነው እኛ አሁን ያለንበት ከአፍሪካ በቅኝ ግዛት መከፋፈል በኋላ የተፈጠረ ስለሆነ የኛ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው” በማለት ስለ እሳቸው እኔ ያፈርኩላቸውን ነገር ተናገሩ፡፡ አቶ ኢሳይያስ በእርስዎ ቤት መሳደብዎ ነው አይደል?

አቶ ኢሳይያስ ይሄንን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን አዋጅ እየደጋገሙ የሚያነሡበት ምክንያት ቅኝ ገዣቸው ባሕረ ምርድ የሚለውን ኢትዮጵያን ሰሜናዊ ክፍል በኃይል ቆርጠው ስም ቀይረው ኤርትራ በማለት አዲስ ባወጡላት ስም የሚጠሯት ሀገራቸው ህልውና ከመቸ እንደሚጀምርና በአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአፍሪካ ኅብረት) አዋጅ መሠረትም የሀገር ህልውና እንደሚኖራት ለመሟገት ነው፡፡ ወደዚህ ዝርዝር ከመግባቴ በፊት ግን አቶ ኢሳይያስ የግሪኮችን ተረት (myth) አውቃለሁ ለማለት የአጋንንት ሳጥን (Pandora’s Box) “ላስተካክልላቸውና የፓንዶራ የአጋንንት ሳጥን ነው የሚባለው” ስለሱ ጥቂት ልበል፡፡ ይገርማል አቶ ኢሳይያስ ቅድመ 19ኛው መቶ ክ/ዘ ያለውን ታሪካችንን በፓንዶራ የአጋንንት ሳጥን (Pandora’s Box) መስለውታል፡፡ ይሄ ሰውየው ለሀገራችን ታሪክ ያላቸውን ከባድና ጤነኛ ያልሆነ ጥላቻ ያሳያል፡፡ ለመሆኑ የአጋንንት ሳጥን መባል ካለበት መባል ያለበት የትኛው ዘመን ነው አቶ ኢሳይያስ? እንዲያው ምን ዓይነት ጭንቅላት ቢኖርዎ እንዴትስ ቢያስቡ ነው ከነጻነቱ የአገርዎ ባለቤት ከነበሩበት ሕዝቡ በነጻነት የሀገሩ ባለቤት ሆኖ ይኖር የነበረበት ዘመን የአጋንንት ሳጥን ሆኖ በቅኝ ገዥ ተጠፍንጎ በገዛ ሀገሩ ባዕድ ሆኖ እንደ መገልገያ ዕቃ ተቆጥሮ በባርነት በግዞት በጭቆና የኖረበት ደግኖ የመላእክት ሳጥን የሚሆንበት በምን ሒሳብ በምን መመዘኛ ነው አቶ ኢሳይያስ? ግን ጤነኛ ነዎት ለመሆኑ?

አቶ ኢሳይያስን ልጠይቅ የምሻው ነገር ፍጹም እንከን ወይም የእርስ በእርስ ግጭት የሌለበት በተለይ ደግሞ እኛን በመሰለ የረጅም ዘመን ታሪክ ባላቸው ሀገራት ምንም ኮሽታ ያልነበረበት ሀገር አንድ እንኳን ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ? ከእነዚህ ሀገራት ውስጥም በአንፃራዊ መልኩ ሲታይ ከእኛ የተሻለ ሰብአዊነት የነበረበት ሀገር አንድ እንኳን ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ? ይሄንን ለማለት የሚያስችልዎት እርስዎ ባሉበት አካባቢና በተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል መካከል የተፈጠረ ይሄንን ያህል አማረው ሊያወሩት የሚችሉት ነገር ምንድን ነው? ተብለው ቢጠየቁ ምን ብለው ሊመልሱ ነው በፓንዶራ የአጋንንት ሳጥን እስከመመሰል ያደረሰዎት? ትንሽ እንኳን ይታዘቡኛል ምን ይሉኛል አይሉም? እስኪ በሞቴ ይሄ ይሄ ይሄ ብለው ቆጥረው ይንገሩን? አሁን ምንም ማለት አልፈልግም ይሄ ይሄ ብለው የተናገሩ ዕለት ግን በሚገባ የምልዎት ነገር ይኖራል፡፡ ምንም ነገር ሳይናገሩ በደፈናው አጨፍግገው አከፋፍተው በመናገር በዜጎችዎ ጭንቅላት ውስጥ ስለ ኢትዮጵያና ሕዝቧ መጥፎ ሥዕል በመሳል ያንን ዘመን እንዲጠሉ ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረት ግን ቢተውት ይሻላል፡፡ አለዛ ግን ከፆታ ልዩነት በስተቀር ፓንዶራን እራሷን ሆነው እየተወኑ እንደሆን ልብ ሊሉት ይገባል፡፡

በጣም የሚገርመው አቶ ኢሳይያስን የሚያኮራቸው ሲያወሩትም ደስ የሚላቸው ዋጋ የሚሰጡትና የሚወዱት ከ19ኛው መቶ ክ/ዘ በፊት የነበረውን የነጻነቱን የአንድነቱንና ብርቅየውን የፍቅሩን አኩሪውን የሚያስቀናውን ታሪክ ሳይሆን ከ19ኛው መቶ ከ/ዘ ወዲህ ያለው የባርነቱን፣ እንደ ሰው ሳይሆን እንደ እንስሳ ተቆጥረው የተገጠቡበትን፣ ሰብአዊ ክብራቸው ተገፎ እንደ ዕቃ የተቆጠሩበትን፣ የሰቆቃውን የውርደቱን ዘመን መሆኑ ሰውየው ያለበትን የሞራል (የቅስም) ደረጃ ዝቅጠት ውድቀትና ኪሳራ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ እጅግ ይገርማል የሚያሳፍረው ያኮራዋል ሲያወራውም ያስደስተዋል የሚያኮራው ግን ያሳፍረዋል ጨርሶም ሊያወራው አይፈልግም፡፡ አይገርምም? “ለምን ምን አይጥማትም” ነበር ያለው ያገሬ ሰው? ይህ አስተሳሰብ የአጠቃላይ የሕዝቡ እንዳልሆነ ተስፋ ላድርግ ይሆን? እኔ የምልዎ አቶ ኢሳይያስ እርስዎና መሰሎችዎ እንዲያው ከቅኝ ግዛት ምን ብትጠቀሙ ነው ለቅኝ ግዛት ያላቹህ ፍቅር ይሄንን ያህል የቅኝ ግዛትን ውርስ ለማስጠበቅ መሥዋዕትነት እስከመክፈል ድረስ ያደረሳቹህ? ባንዳነት እኮ ያሳፍራል! አያሳፍርም እንዴ አቶ ኢሳይያስ? ለእናንተ እንጃ ለኛ ለነጻነት ታላቅ ቦታና ዋጋ ለምንሰጠው ለሱም ምንም የምስሰስተው ነገር ለሌለን ኢትዮጵያዊያን ግን እጅግ አሳፋሪ አስነዋሪ አዋራጅ ርካሽ ወራዳ ማንነት ነው፡፡

አቶ ኢሳይያስ ቅኝ ገዢዎች ኢትዮጵያን ከሦስት ሊከፍሏት ፈልገው የነበሩት ለምን ይመስልዎታል? የባርነትዎን ውርስ እንደታላቅ ቅርስ እስከ መጨረሻው ለመጠበቅ ቁርጠኛ በመሆንዎ ሕዝብዎ ካላፈረብዎት በሌላ በምንም የሚያፍር አይሆንም፡፡ ከሽዎች ዓመታቱ የአንድነት የከበረ ታሪካችን ይልቅ ለ60 ዓመታቱ የባርነት የጭቆና ታሪክ ይንሰፈሰፉለታል ይንገበገቡለታል ያስቡለታል ይሄ በፍጹም የጤና አይደለም፡፡ ጤነኛ ሰው እንዴት ከወንድሙ ይልቅ በመረረ ግፍና ጭቆና እንደ አሕያ ሲገጥበው የኖረውን ጠላት ይወዳል? ምን እያልኩዎት እንደሆነ ይገባዎታል አቶ ኢሳይያስ? የባርነትን ውርስ በመጠበቅ በመንከባከብ እያስፈጸሙ ያሉት የነዚያን ግፈኞች አረመኔዎች የቅኝ ገዥዎችን ዕቅድና ዓላማ ነው ይሄ ደግሞ ባንዳነት ነው ባርነት ነው ነጻ ወጥቻለሁ ነጻ ነኝ ብለው እንዳያስቡ፡፡ ጭንቅላት ቢኖርዎት ማሰብ ቢችሉ በዚህ እጅግ ሊያፍሩ ሊሸማቀቁ እንጂ እያየንዎት እንዳለው ሊኮሩ ሊኮፈሱ አይገባም ነው እያልኩዎት ያለሁት፡፡ ይሄ ይገባዎት ይሆን አቶ ኢሳይያስ? ሕዝብዎንስ ይገባው ይሆን? እርግጠኛ ባልሆንም ታፍነው ተይዘው እንጅ የሚገባቸው ይኖራሉ ብየ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ግፈኞቹ ቅኝ ገዥዎች ባሕረ ምድርን ከኢትዮጵያ ቆርጠው ይዘው ነበር ዛሬ እነሱ የሉም፡፡ እነሱ በሌሉበት ሁኔታ የግፈኞችን ሕልምና ዓላማ ውርስ በማስቀጠል ባሕረ ምድርን ከኢትዮጵያ እንደተቆረጠች ለማስቀረት መጣር የፋሽስት ዝግንትል ተሸካሚነት (አህያነት) አይደለም ወይ? የሄስ አያሳፍርም ወይ? ያውም እኮ የሚያዋጣ በሆነ ምንም ባልነበር ነገር ግን ጨርሶ የማያዋጣ በሆነበት ሁሌታ እንዲህ መሆን ከአህያም አህያነት አይደለም ወይ? እኔ ምንም አልገባ አለኝ እንዴት ነው የምታስቡት?

እናንተ ብዙ ጊዜ የምታነሡት ነገር አለ “ዐፄ ምንሊክ ሸጠውናል ተከድተናል” የሚል ስለ እውነት ለመናገር ታሪክ ያነበበ በወቅቱ የሆነውን በሚገባ የተረዳ ሰው የሚያስብና የሚያገናዝብ ጭንቅላት ያለው ሰው በእርግጠኝነት ይሄንን አይልም፡፡ የእናንተ ችግር ሲጀመር ታሪኩን የነበረውን ሁኔታ በንጹሕ ሕሊና ለማየት አለመሞከራቹህ አለመፈለጋቹህ ነው፡፡ ይሄንን ለማለት የሚያስደፍረኝ ነገር ከአድዋ ጦርነት ዋዜማ በኢትዮጵያ ምን ተከስቶ እንደነበር ያውቃሉ? “ክፉ ቀን” በመባል የሚታወቀው በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የድርቅ ሳይሆን የረሀብ ወቅት ነበር፡፡ ድርቅ ሳይኖር እንዴት ያውም ከባድ ረሀብ ሊኖር ቻለ ይሉ ይሆናል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ረሀቡ የተፈጠረው በሰው ሰራሽ ችግር እንጅ በተፈጥሮ አለመሆኑ ነው፡፡ ረሀቡ የተፈጠረው ጣሊያን ከጦርነቱ ከዓመታት በፊት ሀገሪቱንና ሕዝቧን ለቅኝ ግዛት እጅ እንዲሰጡ ለማድረግ የከብት በሽታ ከህንድ አስገብቶ ከብቶችን በመውጋት ከብቱ ሁሉ እንዲያል ስላደረገ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው እጅግ አስከፊው “ክፉ ቀን” የሚባለው ረሀብ ሊከሰት የቻለው፡፡ የግብርናው አከርካሪ በመሰበሩ ምክንያት፡፡ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ሕዝባችን በዚህ መከራ ላይ እያለ ነበር የአድዋ ጦርነት የመጣው ሀበሻ ከነጻነቱ የሚያደርሰውና ለነጻነቱ የማይከፍለው የመሥዋዕትነት ዓይነት ባለመኖሩ በረሀብ የደከመ የኮሰመነ ጉልበቱን ይዞ ነገር ግን እንደ አሳተጎመራ የሚፋጅ የሚገነፍል ወኔውንና የሀገር ፍቅሩን ይዞ ነበር ወደ አድዋ የዘመተው፡፡ ከድሉ በሏላ ገፍቶ በመሔድ ባሕረ ምድርንም ማስለቀቅ ጠፍቶት አልነበረም በመቶ ዐሥር ሽህ ከሚቆጠረው ዘማች (በእርግጥ ጣሊያኖች ቁጥሩን እስከ 160 ሽህ ድረስ ያደርሱታል በቁጥር ብልጫ ስለተወሰደብን ነው የተሸነፍነው ለማለት ነው እንጅ ሐሰት ነው) ከዚህ ሠራዊት ከፊሉ ለአርበኞች ምግብ የሚያበስሉ ሲቆስሉ የሚንከባከቡና የተለያየ አገልግሎት የሚሰጡ ሴቶችና የሚቆዩበት ባለመኖሩ ከወላጆቻቸው ጋር የሔዱ ሕፃናት ናቸው፣ ከሃያ ሽህ በላይ የሚሆነው በጦርነቱ የተሠዋና ቁስለኛ ነበር፣ ሠራዊቱ ስንቅ ጨርሷል ለመሰንበቻ ያህል ከአካባቢው ሰው ለመሸመት ቢፈለግም አንዲት እፍኝ እንኳን ሊገኝ አልቻለም፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ የነበረ ሠራዊት እንዴት ብሎ ነው ገፍቶ በመሔድ ምናልባትም ከአድዋ የከበደ ጦርነትን ሊያደርግ የሚችለው? ነው ወይስ ተሸንፎ መላዋ ኢትዮጵያ በባርነት ሥር መውደቅ ነበረባት ማለታቹህ ነው?

በዚህ ላይ ደግሞ በጣም የሚገርመውና ሳልነግርዎት ማለፍ የማልፈልገው ነገር ከጣሊያን ወራሪ ሠራዊት ውስጥ ከዓረቦችና ከጣሊያኖች በላቀ ቁጥር በባንዳነት ከጣሊያን ጋር ተሰልፎ የገዛ ሀገሩንና ወገኑን ይወጋ የነበረው የእርስዎ ወገኖች እንደነበሩ ያውቁ ይሆን? ይሄንንም ግንዛቤ ውስጥ ብታስገቡ መልካም ነው፡፡ እናንተ የምታግዙ ቢሆን ነገሩ ምንኛ ቀላል በነበረ ነበር የሆነው ግን ሌላ ነው እናንተም እራሳቹህ ከጣሊያን ጋር ተሰልፋቹህ ሀገር ወገናቹህን የምትወጉበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ ይሄ ይሄ ሁሉ እያለ አይከብድም አቶ ኢሳይያስ? ስለዚህ ያለው አማራጭ መመለስና ጣሊያንን በውልና በአንዳንድ ነገሮች እዛው ባለበት አስሮ ለማቆየት ጥረት በማድረግ ዕረፍት ወስዶና ጊዜ ወስዶ ተጠናክሮ መመለሱ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ስለሆነባቸው ነው የተመለሱት፡፡

አቶ ኢሳይያስ እስኪ አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት አምላክ ታደገን እንጅ ፋሽስት ጣሊያንን የ1928ቱ ወረራው ወደ ቅኝ ግዛት አሸጋግሮት መላዋን ኢትዮጵያን ቅኝ መግዛት ችሎ ቢሆንና ሀገራችን እንደሌሎቹ ሀገራት ከጊዜ በኋላ ነጻ ወጥታ ቢሆን ኖሮ ይሄንን የጠቀሱትን የአፍሪክ አንድነት ድርጅት አዋጅ ያነሡ ወይም ማንሣት ይችሉ ነበር? አዩ አይደል ለዚህ ነው የባርነትን ውርስ ለመጠበቅ ለመንከባከብ ህያው ለማድረግ የሚሠሩ ባሪያ ነዎት የምልዎት፡፡ እያልኩዎት ያለሁት ነገር ይገባዎታል? እያልኩ ያለሁት እርስዎ የሚሉትን ነገር ሁሉ ፋሽስት ጣሊያን ከ40 ዓመታት በኋላ በ1928 ባደረገው ወረራ እንዳይሠራ አድርጎታል ነው እያልኩዎት ያለሁት፡፡ ሰው እንዴት ከባርነት ጋር ፍቅር ይወድቃል? ኧረ እባካቹህ ንቁ በእናንተ ይብቃ ልጆቻቹህንም የባርነት አስተሳሰብ ሰለባ አታድርጓቸው ነጻ ይውጡ ሰዎች እንጅ ጣሊያን ሲገጥባቸው እንደነበሩት አያቶቻቸው ባሪያዎችና የቅኝ ገዥ አጋሰሶች አታድርጓቸው፡፡

በተለይ ደግሞ ሊያስቡ የሚገባው ነገር በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትና በቅኝ ገዥዎቻቸው መሀከል የነበረው ሁኔታና ግንኙነት በኢትዮጵያና በጣሊያን መሀከል ከነበረው ሁኔታና ግንኙነት ፍጹም የተለያየና ምንም የሚያገናኘው ነገር ስለሌለ “የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አዋጅ” እያሉ የሚጠቅሱት ድንጋጌ እኛን አይገዛንም በእኛ ላይ አይሠራም፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ለአንድ ሀገር ብሎ የተለየ አዋጅ ማውጣት ስለሌለበት ሁኔታው በግልጽ ስለሚታወቅ ማንም ሊገነዘበው ስለሚችል ነው የተለየ ሕግ ለኢትዮጵያ ያላወጡት፡፡ በእኛና በጣሊያን መሀከል የነበረው ነባራዊ ሁኔታ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች የተለየ በመሆኑ፡፡ ስለሆነም ይሄንን አዋጅ እንደመተማመኛ ሰነድ አድርገው መቁጠርዎን ያቆማሉ፡፡ እስኪ ሌላ ጥያቄ ልጠይቅዎት ይህ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አዋጅ በሶማሊያ ላይ ለምን ያልሠራ ይመስልዎታል? እንደ እርስዎ እምነት ቢሆን ኖሮ እኮ ሶማሊያ ሁለት ሀገር መሆን ነበረባት፡፡ የእንግሊዝ ሶማሌ (ሶማሌ ላንድ) እና የጣሊያን ሶማሌ ተብለው የተለያዩ ሀገራት መሆን ነበረባቸው፡፡ ነገር ግን ያ አልሆነም፡፡ አሁን ሶማሊያ ከፈራረሰች በኋላ ሶማሌ ላንድ “እኔ ሰላም ነኝ እራሴን ችየ ተነጥያለሁ እራሴንም እያሥተዳደርኩ ነኝ እባካቹህ ዕውቅና ይገባኛል እውቅና ስጡኝ?” እያለች ስትጮህ የአፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ ምዕራባዊያን የተቀረውም የዓለም ክፍል ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ዕውቅናውን የነፈጋት ለምን ይመስልዎታል? ስለሆነም ዐሥሬ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አዋጅ እያሉ አያላዝኑብን እንኳንና በኛ በነጻዋ ሀገር በሱማሌም አልሠራም፡፡ ለዚህም ነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባሕረ ምድርን ወደ እናት ሀገሯ እንድትቀላቀል የወሰነው፡፡

እኛ እኮ እንዲያው የአባቶቻችንን አዳራ ለመጠበቅ የሀገራችንን የግዛት አንድነት ላለማስደፈር ያስረከቡንን እንደተረከብን አድርገን ለተከታይ ትውልድ ለማስረከብ  በሚል ነው እንጅ እኮ እንዲህ የምንንገበገበው አንዳች ጥቅም ኖሯቹህ እኮ አይደለም፡፡ እንኳን ለኛ እራሳቹህ ለራሳቹህ እንኳን እንዳልጠቀማቹህ እያያቹህት ነው፡፡ እናም አደራ ለመጠበቅ ስንል ብቻ በሕገ ወጥ መንገድ ከእናት ሀገሯ የተቆረጠችውን ባሕረ ምድርን ወደ እናት ሀገሯ እንመልሳታለን፡፡ በክህደት የተመረዛቹህና ኢትዮጵያዊያን አይደለንም ኢትዮጵያዊ መሆን አንፈልግም የምትሉ ካላቹህ ተጠራርጋቹህ ቀይ ባሕር ልትገቡ ትችላላቹህ፡፡ መሬታችንን ግን እናት አባቶቻችን ደምና አጥንታቸውን ያፈሰሱ የከሰከሱበትን ምድር ግን እንመልሳለን፡፡ ካዘንንላቹህ ደግሞ አላግባብ በወያኔ የክህደት ሥራ በልግስና የተሰጣቹህን አሰብን ወደ ሀገሩ መልሰን “መንገዱን ጨርቅ ያርግላቹህ” ብለን መርቀን እንሸኛቹሀለን የት እንደምትደርሱ እናያለን፡፡ ከዚያ በኋላ ግን “ኧረ ኢትዮጵያዊያን ነን መልሱን እሪ ያገር ያለህ” ብትሉም እንኳ አንፈልግም ይህ የናንተ ትውልድ ለመገንጠል ብረት እንዳነሣ ሁሉ ቀጣዩ ትውልዳቹህ ደግሞ ለመዋሐድ ብረት የሚያነሣ ይሆናል፡፡

እንግዲህ አቶ ኢሳይያስ በቃለመጠይቃቸው የቀበጣጠሩት የባጥ የቆጡንና የተንዛዛም ስለነበር ተንዛዝተው ሲያበቁ እኔንም አንዛዙኝ፡፡ በሌላው ጉዳይም ሁሉ መልስ ልስጥ ብል እሳቸውን መሆን ስለሚሆን በዚሁ ይብቃኝ፡፡ ከመቋጨቴ በፊት ግን በትጥቅ ትግል እዚያ ላሉ ወገኖቻችን የማስተላልፈው መልዕክት አለኝ፡- ወገኖቸ ሸአቢያ ሸአቢያ ነው፡፡ መቸም ቢሆን ከሸአቢያነቱ ሊለወጥ አይችልም፡፡ ሸአቢያን ከሸአቢያነቱ ወያኔንንም ከወያኔነቱ መለወጥ ማለት ሰይጣንን ወደ መልአክነት መለወጥ መቻል ማለት ነው ፈጽሞ የማይቻል የማይሆን ነገር ነው፡፡ ስለሆነም በምንም ተአምር ቢሆን በሸአቢያ ላይ እምነት እንዳትጥሉ፡፡ አማራጭ የለምና የትጥቅ ትግሉን እዚያው ማድረግ ግድ ነው፡፡ ሸአቢያ ይሄንን ዕድል በመስጠቱ ውለታ እንደሠራልን እንዳትቆጥሩት፡፡ እሱ ሊያደርገው የማይችለውንና መቸም የማያገኘውን ዕድል ነው በእናንተ ምክንያት ያገኘው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ልብና ድጋፍ ከእናንተ ጋር ነው ይሄ ማለት በወያኔና በሸአቢያ መሀከል ጦርነት ቢነሣ እንደ ባለፈው ሁሉ ሕዝቡ ሆ ብሎ ከወያኔ ጋራ ተሰልፎ ሸአቢያን አይወጋም እንኳንና ሕዝቡ ወታደሩም እንኳን ቢሆን ይሄንን አያደርግም ይሄንን የሚያደርገው ለሸአቢያ በማዘን ሳይሆን ለእሱ ስትሉ በረሀ ስለገባቹህት ስለእናንተ ሲል ነው፡፡ ሸአቢያ ለእናንተ ቦታ በመስጠቱ ወይም በመርዳቱ ምክንያት ይሄንን ታላቅ ጥቅምና አጋጣሚ ማግኘት ችሏል በዚህም ምክንያት ከወያኔ ጋራ ጦርነት ቢገጥም በቀላሉ ሊያሸንፍ የሚችልበትን ዕድል አግኝቷል፡፡ ይሄ ነው የውለታው ክፍያ፡፡ ያደረገው ለራሱ ጥቅም ሲል እንጅ ለኛ ወይም ለኢትዮጵያ አይደለም፡፡ መችም መቸም ሊያገኘው የማይችለውን ጠላቱን እንዲበቀል የማድረግ ዕድሉን እንዲያገኝ አድርገናልና ውለታው በዚህ ተመልሷል፡፡ ሌላ ክፍያ ሊጠብቅ አይደለም ሊያስብ እንኳን አይገባም፡፡ ነገር ግን ሸአቢያ ልብና ማስተዋል ጭንቅላት የለውምና እንዲህ ስላደረኩላቹህ ወይም ስለማደርግላቹህ እንዲህ ታደርጉልኛላቹህ እያለ አስጨንቆ ቢይዛቹህ አሽ በሉት ፈርሙም ካላቹህ በዐሥር ጣቶቻቹህ ፈርሙለት ይሄንን ባለማድረጋቹህ እናንተን ማጣት አንፈልግምና፡፡ ልባቹህን እናውቀዋለንና ተገዳቹህ የውሸት የፈረማቹህለትን ፊርማ በመፈረማቹህ ክህደት እንደፈጸማቹህ አንቆጥርም፡፡ ታደርጉልኛላቹህ ያላቹህ ነገር ሊከፈለው የሚችለው እዚህ ሀገራቹህ ገብታቹህ በምድራቹህ ሆናቹህ ወያኔን አስወግዳቹህ ነውና ሊሆን የሚችለው ከሕገ ወጥና ከከሀዲ ጋር የተደረገ ውል አይጸናምና ያኔ አፍንጫህን ላስ ብንለው በሀገራቹህ በምድራቹህ ከወገናቹህ ጋር ሆናቹህ ነውና ምንም ሊያመጣ አይችልም፡፡ በጅብ ሀገር እንደ ጅብ መጮህ ግድ ይላል፡፡ መድኃኔዓለም ከናንተ ጋር ይሁን!!!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

 

The post አስቂኙ የአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ቃለ መጠይቅ! – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>