ኢሳት ዜና :-የህወሀትን 40ኛ ዓመት አክብረው ሲመለሱ እግረ መንገዳቸውን በ አማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎችን እየጎበኙ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ፤የካቲተ 16 ቀን በወልቃይት ሊያደርጉት የነበረውን ጉብኝት የህዝቡን ተቃውሞ በመፍራት መሰረዛቸው ነዋሪውን ክፉኛ አስቆጥቷል።
የወልቃይት ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቲት 16 ቀን ወልቃይትን እንዲጎበኙ በአካባቢው ሹመኞች መነገሩን ተከትሎ በየገጠር የሚኖረው ህዝብ ሳይቀር በመሰባሰብ እና ምሳ በማሰናዳት ሲጠባበቃቸው ቢውልም የውሀ ሽታ ሆነው ቀርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩን በአካል አግኝቶ የአስተዳደራዊ በደል ጥያቄውን ለማቅረብ ከ8 ሺህ በላይ ህዝብ ተሰባስቦ እንደነበር የገለጹት የነዋሪዎቹ አስተባባሪዎች፤ ህዝቡ ተቃውሞውን ለመግለጽና ጥያቄ ለማቅረብ እንደተዘጋጀ የተረዱት የአካባቢው ሹመኞች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ወልቃይት እንዳይገቡ አድርገው ቅጠታ ወደ ደጀና እንደወሰዷቸው ተናግረዋል።
ይህ በመሆኑም ተሰባስቦ ሲጠባበቅ የነበረው ህዝብ በቁጣና በብስጭት ወደ ቤቱ መመለሱን የገለጹት አስተባባሪዎቹ፤ ንዴታቸውን መቆጣጠር የተሳናቸው የአካባቢው ወጣቶችም በአደባባይ የህወሀትን ባንዲራ በማቃጠል የዚያኑ እለት ለትግል ወደ በረሀ መውጣታቸውን ተናግረዋል።
ቀርቦ በማናገር እንጂ ከህዝብ በመደበቅ ወይም በመሸሽ ከችግር መሸሽ እንደማይቻል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊረዱት ይገባል ያሉት ነዋሪዎቹ፤ አንድ የሀገር መሪ- ከህዝብ ጋር የዚህ ዓይነት ድብብቆሽ ጨዋታ ውስጥ መግባቱ እጅግ እንዳሳፈራቸውም ገልጸዋል።
<<አማራዎች ሆነን ሳለን ያለፍላጎታችን ወደ ትግራይ ክልል እንድንጠቃለል ተገደናል፣ የማንነት ጥያቄያቸን ምላሽ እንዲያገኝ ጥያቄ በማቅረባችን ለበርካታ ዓመታት ተነግረው የማያለቁ በደሎችና ግፎች እየተፈጸሙብን ነው>> የሚሉት ወልቃይቶች፤ << በቅርቡ በተደራጀ ሁኔታ በደብዳቤ ላቀረብነው አቤቱታም እስካሁን ከመንግስት ምላሽ አላገኘንም፤ መንግስት መልስ የማይሰጠን ከሆነ፤ ራሳችን መልስ ለመስጠት እንገደዳለን>፡>በማለት አስጠንቅቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የወልቃይት ህዝብ ላለማየት ተራምደውት ያለፉት አቶ ሀይለማርያም ትናንት ምሽት ከ አቶ አርከበ እቁባይና ከአማራ ክልል ርእሰ-መስተዳድር ከ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር በመሆን ኮምቦልቻ ከተማ መግባታቸው ታውቋል።
ዛሬ ጧት የኮምቦልቻ ከተማ ተማሪዎች – ለአቶ ሀይለማርያም አቀባበል ለማድረግ በሚል ከትምህርት ገበታቸው በግዳጅ መወሰዳቸውን የገለጹት ምንጮችን የከተማውም ነዋሪ በተመሳሳይ መንገድ ለ አቀባበል ተብሎ በግዳጅ እንዲወጣ መደረጉን ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማለዳ ላይ የዛሬ ዓመት የተመረቀውን የ ኮምቦልቻ አውሮፕላን ማረፊያ እንደ አዲስ እንዲመርቁ ከተደረገ በሁዋላ ለአዋሽ-ኮምቦልቻ የባቡር ሀዲድ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጣቸውን የገለጹት ምንጮቹ፤ የመሰረት ድንጋይ የማኖር ፕሮግራሙ የተካሄደውም የሽህ መሀመድ ሁሴን አል አሙዲ የቆርቆሮ ፋብሪካ አጠገብ በተጣለ ዳስ ውስጥ እንደነበር አመልክተዋል።
ወደ ዳሱ እንዲገቡ የታደሙት << አዋሽ -ኮምቦልቻ ሀራ ገበያ>> የሚል መግቢያ ባጅ የተሰጣቸው የኢህአዴግ ካድሬዎች ብቻ መሆናቸውን የጠቀሱት ምንጮቹ፤ ይሁንና ከነበረው እጅግ ጥብቅ ፍተሻ አኳያ፤ ተጋባዦቹ የኢህአዴግ አባላት ሳይሆን አደገኛ ጠላት ነበር የሚመስሉት ብለዋል።
አቶ ሀይለማርያም የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጣቸውን ተከትሎ “ኢህአዴግን ምረጡ” የሚል ቅስቀሳ መደረጉን የጠቀሱት ምንጮች፤ የመሰረት ድንጋይ ሊጥሉ መጡ የተባለውም ሆነ ከአመት በፊት የተመረቀን አውሮፕላን ማረፊያ እንደ አዲስ እንዲመርቁ የተደረገውም ለምርጫው ህዝቡን ለማታለል እንደሆነ በደንብ ገብቶናል”ብለዋል።
የምንልሰውና የምንቀምሰው ባጣንበት ወቅት በባቡር ፕሮፓጋንዳ ሊያታልሉን አይችሉም ያሉት ነዋሪዎቹ፤ በትራንስፖርትም ረገድ ቀደም ሲል 1 ብር የነበረው የታክሲ ታሪፍ እስከ 3 ብር፣ 2 ብር የነበረው እስከ 6 ብር ደርሶ ህዝቡ እየተማረረ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
The post ሀይለማርያም ደሳለኝ የወልቃይትን ህዝብ ለማነጋገር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ appeared first on Zehabesha Amharic.