ከቦጋለ አበበ
ልክ የዛሬ ዓመት ነው ገንዘቤ ዲባባ በሦስት ሺ ሜትር የቤት ውስጥ የዓለም ክብረወሰንን በማሻሻል ዓለምን ማስደመም የጀመረችው። ዘንድሮም ልክ በዓመቱ ገንዘቤ የውድድር ዓመቱን በክብረወሰን ታጅባ ታሪክ በመሥራቷ ቀጥላለች።
የታላላቅ እህቶቿን ፈለግ ተከትላ በአትሌቲክሱ ዓለም አዲስ ታሪክ እየሠራች የምትገኘው ገንዘቤ ባለፈው ዓመት በስዊድን ስቶክሆልም ኤሪክሰን ግሎብ አሬና የቤት ውስጥ ውድድር በሦስት ሺ ሜትር የዓለምን ክብረወሰን አስመዝግባ ዘንድሮ በተመሳሳይ ውድድር በአምስት ሺ ሜትር ያንኑ ታሪክ መድገም ችላለች።
ገንዘቤ ወደ ውድድሩ እንደምትመለስ ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ ያለፈውን የሦስት ሺ ሜትር ታሪክ በአምስት ሺ ሜትር እንደምትደግም በርካታ ወገኖች ተስፋ አሳድረው ነበር። እርሷም በስቴዲየም የታደሙትን አሥር ሺ ደጋፊዎቿን አላሳፈረችም። የስፖርቱ ተንታኞች የሰጧትን ግምትም አሳክታለች። አሁን አሁን ገንዘቤ ውድድሯ ከአትሌቶች ጋር ሳይሆን ከሰዓት ጋር እየሆነ ነው። በቤት ውስጥ ውድድሮች ገንዘቤ ውድ ገንዘብ መሆኗን በርካታ የስፖርቱ ቤተሰቦች አፋቸውን ሞልተው ይናገሩላታል።
ገንዘቤ ይህን ታሪክ ያስመዘገበችበት ሰዓት 14፡18፡86 ሲሆን፤ ከቀድሞው ክብረወሰን በአምስት ሰከንድ የተሻለ ነው። የርቀቱ ክብረወሰን ከስድስት ዓመት በፊት እዚያው ስቶክሆልም በመሠረት ደፋር የተያዘ ነው። ገንዘቤ የዛሬ ዓመት በሦስት ሺ ሜትር ያስመዘገበችው የዓለም ክብረወሰንም ቀደም ሲል በመሠረት ደፋር ተይዞ የነበረ ነው።
ገንዘቤ የውድድሩን የዓለም ክብረወሰን ለማሻሻል አሯሯጩ ቢያንስ እስከ ውድድሩ ግማሽ ድረስ ሊያሯሩጣት ይገባ ነበር። ይሁን እንጂ ገንዘቤ አሯሯጭ ያስፈለጋት እስከ ሁለት ኪሎ ሜትር ድረስ ብቻ ሆኗል። ከአሥራ ሁለት ወራት በፊት ገንዘቤ ዲባባ አዲስ ታሪክ መሥራት እንደምትችል ያሳየችበት ወቅት ነበር። ከሦስት ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰኗ በኋላ በሁለት ሳምንታት ውስጥ የአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትርና የሁለት ማይል የቤት ውስጥ የዓለምን ክብረወሰን በእጇ ማስገባቷ አይዘነጋም። በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮናም ከሁለት ዓመት በፊት በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ያስመዘገበችውን የወርቅ ሜዳሊያ በሦስት ሺ ሜትር መድገም ችላለች።
ገንዘቤ የቤት ውስጥ ውድድሮች እንቁ መሆኗን ቀጥላለች። የዘንድሮው የውድድር ዓመት የመጀመሪያ የውድድር ምዕራፏ ብሩህ ሆኗል። ከእዚህ በኋላ በሚኖራት ውድድርም ገንዘቤ ሌላ ታሪክ አትሠራም ብሎ መገመት አይቻልም። አሁን ያስመዘገበችው ክብረወሰንና አስደናቂ ብቃት የአትሌቲክስ አፍቃሪው ብዙ እንዲጠብቅባት አድርጓል።
ገንዘቤ ከትናንት በስቲያ ያሳየችው ድንቅ ብቃት ኢትዮጵያ በመጪው ክረምት ቤጂንግ ላይ በሚካሄደው የዓለም ሻምፒዮና ተስፋ እንድትጥልባት አድርጓል። በተለይም ታሪካዊቷ የረጅም ርቀት ንግስት ጥሩነሽ ዲባባ በእርግዝና ምክንያት በዘንድሮው የዓለም ሻምፒዮና አለመካፈሏ ለኢትዮጵያ ስጋት ቢሆንም ታናሽ እህቷ ገንዘቤ ዲባባ በምትኩ የወርቅ ሜዳሊያ እንደምታመጣ ተስፋ ሆናለች።
The post Sport: እንቁዋ አትሌታችን ገንዘቤ ዲባባ ፉክክሯ ከሰዓት ጋር እየሆነ መጥቷል appeared first on Zehabesha Amharic.