ማህበረ ቅዱሳን እንዘገበው: በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ላይ በመጋቢት ወር መጨረሻ የኢሬቻ በዓል እንደሚከበር መስከረም 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬሽን በኦሮምኛና በአማርኛ ቋንቋ መተላለፉ ተገቢ እንዳልሆነና ችግር ሊፈጥር የሚችል መሆኑን በመግለጽ የተላለፈው መረጃ እርማት እንዲደረግበት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ለኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ለአቶ ሙክታር ከድር በጻፉት ደብዳቤ ጠየቁ፡፡
የሃይማኖቶች እኩልነት በታወጀበት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕግ መንግሥት አንዱ ቤተ እምነት የሌላውን እምነት መንቀፍም ሆነ መንካት እንደሌለበት ተደንግጓል” ያሉት ፓትርያርኩ በሚዲያ ሽፋን የተሰጠው ጉዳይ ሕገ መንግሥቱን የሚተላለፍ፤ የገዳሙን መናንያን መነኮሳትና በአካባቢው የሚኖሩ ሕዝበ ክርስቲያኖችን የሚያስቆጣ በመሆኑ የክልሉ መንግሥት ለተዘገበው ጉዳይ እርማት እንዲሰጥበት ለኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳደር ለአቶ ሙክታር ከድር በጻፉት ደብዳቤ አሳስበዋል፡፡
በሌላ በኩል ጉዳያችን የጡመራ መድረክ የሚከተለውን ዘገባ አሰራጭቷል:-
ባለፈው መስከረም 15/2007 ዓም በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (በቀድሞ ስሙ ኢቲቪ) በአማርኛ እና በኦሮምኛ እንደተለቀው ዜና ከሆነ ”በመጪው መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ የእሬቻ በዓል በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ውስጥ ይከበራል ”ይላል።ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከተከበሩት እና ከታፈሩት ገዳማት ውስጥ አንዱ ነው።ገዳሙ ፃድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለኢትዮጵያ እና ለመላው የሰው ዘር የፀለዩበት ቅዱስ ስፍራ ነው።
ይህንን ከ800 ዓመታት በላይ ፀንቶ የኖረ ገዳም ”እሬቻ” እንዲከበርበት የተደረገበት ዋና ምክንያት እምነትን ከእምነት ለማጋጨት በስርዓቱ የተሸረበ ተንኮል ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው።ከእዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ መሰረተ እምነትን የጣሱ ተግባራት ሲፈፀሙ እና ሙስና የሚፈፅሙ የስርዓቱ አጎብዳጆች (በቤተ ክህነቱ ዙርያ ‘የጨለማው ቡድን አባላት’ በመባል የሚታወቁት) የቤተ ክርስቲያኒቱን ንብረት እና ገንዘብ መተዳደርያቸው ሲያደርጉት አመታት መቆጠራቸው ይታወሳል።
በቅርቡም በርዕሰ አድባራት እንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሙዚየም የወርቅ መስቀልን ጨምሮ ሌሎች በቅርስነት የተመዘገቡ ንብረቶች መጥፋታቸው ይታወሳል።ከእዚሁ ጋር ተያይዞ የደብሩ አስተዳዳሪ ቀደም ብለው ሰራተኞችን ሰብስበው ”በሙዚየሙ የሚገኙ ቅርሶች ተሸጠው ለአባይ ቦንድ መግዣ ይዋሉ” የሚል ሃሳብ አቅርበው በደብሩ አገልጋዮች እና ሰረተኞች ”ታሪክ አጥፍተን ታሪክ አንሰራም” የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው የገለፀው የሪፖርተር ጋዜጣ ባለፈው ሮብ የካቲት11/2007 ዓም በዘገባው ”የቤተ ክርስቲያኗ ካህናት፣ ሠራተኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች የደብሩን አስተዳዳሪና ሌሎች ኃላፊዎች ተባብረው ወርቆቹን ማጥፋታቸውን፣ በቤተ ክርስቲያኗ ሠራተኞች ላይ በደልና ብልሹ አሠራር እንዲደርስ ማድረጋቸውን በመግለጽ ተቃውሟቸውን በፊርማ በተደገፈ አቤቱታ ለሚመለከታቸው ሁሉ መላካቸውን” ይገልጣል።
The post አቡነ ማትያስ የእሬቻ በዓል በዝቋላ ገዳም ሊከበር ነው የሚለውን ዜና ኢቢሲ እንዲያስተካክል ጠየቁ appeared first on Zehabesha Amharic.