የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አሁንም ደጋፊዎቹን በደስታ ያሳበደ ውጤትን በአዲስ አበባ ስታዲየም አስመዝግቧል። እሁድ እለት የደቡብ አፍሪካ አቻውን 2ለ1 በማሸነፍ ለብራዚሉ የአለም ዋንጫ የመጨረሻ ምዕራፍ ማለፉ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ከመጠን በላይ አስፈንጥዟል። ለብዙዎችም ውጤቱ ለማመን የሚከብድ ስለነበር ደስታውና ፈንጠዝያው ልክ አልነበረውም። ዋልያዎቹን ለመደገፍ በአዲስ አበባ ስታዲየም ዙሪያ ተሰልፎ ያነጋው ተመልካች አንገቱን ደፍቶ አለመመለሱ ራሱ እጅግ የሚያስደስት ነው።
በዋልያዎቹ የተመዘገበው ውጤት የፈጠረው ፈንጠዝያ የቆየው ለጥቂት ሰዓታት ብቻ ነበር። የአለም እግር ኳስን በበላይነት የሚመራው አለምአቀፉ የእግር ኳስ ማህበር በዋልያዎቹ የደስታ ቀን ማምሻውን ያወጣው መረጃ የጋለውን የኢትዮጵያውያንን የደስታ ስሜት የሚያቀዘቅዝ ነበር። የነገሮችንም ሒደት ፍጹም እንዲቀያየር አድርጓል። ፊፋ በድረገጹ ላይ ይፋ ባደረገው መረጃ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሶስት የአፍሪካ ሃገራት የነጥብና ገንዘብ ቅጣት የሚያስከትል ምርመራ እንደሚያደርግ ነው ያስታወቀው።
በኢትዮጵያ በኩል ችግሩ የኢትዮጵያ ቡድን ከሳምንት በፊት ከሜዳው ውጪ ቦትስዋናን 2ለ1 በአሸነፈበት ጨዋታ ያልተገባ ተጫዋች ማሰለፉ ነው። ኢትዮጵያ በሁለት ጨዋታዎች ላይ ሁለት ቢጫ የተመለከተ ተጫዋች ማሰለፏ በፊፋ ድረገጽ ላይ ቀርቧል። ይህ ተጫዋችም ምንያህል ተሾመ እንደሆነ በድረገጽ ላይ ከሰፈረው የሃገራት የአለም ዋንጫ ማጣሪያዎች አጠቃላይ ውጤትና ተያያዝ መረጃዎች ላይ ለማወቅ ተችሏል። ምንያህል ዋልያዎቹ ረስተንበርግ ላይ ከባፋና ባፋናዎቹ ጋር 1ለ1 በተለያዩበት ጨዋታ ላይና አዲስ አበባ ላይ ቦትስዋናን 1ለ0 በአሸነፉበት ጨዋታ ላይ የቢጫ ካርድ ተመልክቷል።
በፊፋ በሚካሔዱ የማጣሪያም ሆነ የነጥብ ጨዋታዎች ላይ ሁለት ቢጫ የተመለከተ ተጫዋች በቀጣዩ አንድ ጨዋታ ላይ እንዳይሰለፍ በቀጥታ የሚታገድ ይሆናል ሲል ፊፋ በስነምግባር ህጉ ላይ ግልጽ የሆነ አርፍተ ነገር አስፍሯል። (If a player receives a caution in two separate matches of the same FIFA competition, he is automatically suspended from the next match in that competition.)
ሁለት ቢጫ ካርዶችን የተመለከተው ምንያህል ተሾመ ግን ቦትስዋና በሜዳዋ የኢትዮጵያ ቡድንን በአስተናገደችበት ጨዋታ ላይ ለዋልያዎቹ ተሰልፎ ተጫውቷል።
በአለም ዋንጫ የማጣሪያና የነጥብ ጨዋታዎች ላይ ሁለት ቢጫ ካርዶች የተመዘዙበት ተጫዋች በቀጣይ አንድ ጨዋታ ላይ መሰለፍ አይገባውም የሚለውን የፊፋን ህግ መጣስ ተጫዋቹን ከአሰለፈው ቡድን የሶስት ነጥብ ቅነሳ እና የ6 ሺ ዶላር ቅጣት ይጣልበታል።
ይህ የኢትዮጵያ ቡድንን ውጤት የሚያስቀንስ የፊፋ ህግ ፈንጠዝያውን ላልጨረሰው የኢትዮጵያ ህዝብ አስደንጋጭና መራር ዜና ነው። አንድ ጨዋታ እየቀረው ምድቡን በበላይነት በመምራት አዲስ ታሪክ የሰራው የዋልያዎቹ ቡድንንም ለሌላ ፈተና የዳረገ እውነታ ነው።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምንያህል ተሾመ ሁለት ቢጫ ካርዶች አለመመልከቱን የሚያሳይ ማስረጃ እስካአላቀረበ ድረስ ፊፋ ህግ መጣሱን ጠቅሶ ቅጣት ማስተላለፉ የማይቀር ነው። ከገንዘብ ቅጣቱም በላይ ደግሞ የሶስት ነጥብ ቅነሳው ከምንም በላይ ዋልያዎቹን ይጎዳል። እሁድ እለት ጨርሰውት የነበረውን የአለም ዋንጫ የመጀመሪያ ምዕራፍ ጉዞን እንደገና እንዲገፉ እና በቀጣይ መስከረም ወር ከሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር ከሜዳቸው ውጪ የሚያደርጉትን ጨዋታ በማሸነፍ ግዴታ ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል። በስነልቦናም የሚደርስባቸው ጉዳት ቀላል የሚባል አይደለም።
ከተጠያቂነት የማያመልጡ አካላት
ዋልያዎቹ ለብራዚሉ የአለም ዋንጫ ማጣሪያ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሳቸውን ያረጋገጡበት ውጤት እንደ ዋዛ የሚታይ አይደለም። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የማይገባ ተጫዋች ማሰለፍ በፊፋ የተከሰሰበት ጥፋቱን ውድቅ የሚያደርግበት ማስረጃ ይኖረዋል ተብሎም አይታመንም። ፊፋም የዋልያዎቹን ሶስት ነጥብ መቀነሱ የማይቀር ነው። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ አዲስ ተብሎ የሚጠቀሰው የዋልያዎቹ ውጤት ጥቂት በሚባል ጥፋት ማጣት እንዲሁ መቅረቱ ያስቆጫልም። ለዚህ ጥፋት መፈጸም ሚና የነበረው አካልም ተጠያቂ ሊሆን ይገባል።
ብዙዎች ኢትዮጵያ የማይገባ ተጫዋች በማሰለፍ ለመከሰሷ ጣታቸውን የሚጠቁሙት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ላይ ነው። ከተጫዋቹ ጀምሮ አሰልጣኞች፣ ጋዜጠኞችና የስፖርት አመራር አካላትን ተጠያቂ አድርገዋል። በእርግጥም የሁሉም አካላት ድርሻ እንዳለበት ማመን ይገባል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ተጫዋቹና እግር ኳሱን በኃላፊነት የሚመራው አካል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የላቀውን ድርሻ ይወስዳል።
ተጫዋቹ ምንያህል ተሾመ ከማንም በላይ የሁለት ቢጫ ካርዶች ሰለባ እንደሆነ ራሱ ያውቃል ተብሎ ይታመናል። ምናልባት ሁለት ካርድ የተመለከተ ተጫዋች በቀጣዩ ጨዋታ እንደማይሰለፍ ስለማላውቅ ነው የተጫወትኩት የሚል ከሆነ ጉዳዩ በጣም አሳፋሪ ነው የሚሆነው። በርካታ አመታትን በኢትዮጵያ ታላላቅ ክለቦች በጨዋታ ከአሳለፈ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የማይጠበቅ ትልቅ ስህተት ይሆንበታል። በዚያ ላይ ደግሞ በቀን ውስጥ ረጅም ሰአታትን በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ ከሚያሳልፉ ተጫዋቾች አንዱ መሆኑ ሲታሰብ “እንዴት ይህን የፊፋን ህግና መረጃ ለማንበብ ጊዜ አጣ” ያስብላል።
የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኞችም እንዲሁ የፊፋን እግር ኳስ ህግና መመሪያ ያውቃሉ ተብሎ ይታመናል። ብሔራዊ ቡድንን ያህል ትልቅ ኃላፊነት ይዘው በአለም ዋንጫ እየተጓዙ ሁለት ቢጫ ካርድ የተመለከቱ ተጫዋቾች ማሰለፍ እንደሚያስቀጣ አለማወቅ እጅጉን ያስወቅሳል። አሰልጣኞቹ በእያንዳንዳንዱ ጨዋታ ተጫዋቾች የነበራቸውን ብቃትና ሚና በመመዘን ዋጋ እንደሚሰጡ ይታመናል። ድክመትና ጥንካሬያቸውን በአጠቃላይም በየጨዋታው ያሳዩትን አቋም ነጥብ እየሰጡ በማስታወሻቸው ላይ ያሰፍራሉ ተብሎ ይታሰባል። የእኛ አሰልጣኞች ይህን ካደረጉ ደግሞ ምንያህል ተሾመ በየጨዋታዎቹ የነበረውን አጠቃላይ አቋም ያውቃሉ፣ የሁለት ቢጫ ካርድ ሰለባ መሆኑንም በቀላሉ ይገነዘባሉ። ይህንን አላስታወስንም ወይንም አላወቅንም የሚሉን ከሆነ ግን ቡድኑን የሚመሩት በደመነፍስ ነው ብለን እንድናስብ ያስገድዱናል።
የብሔራዊ ቡድኑ የቡድን መሪዎችም ከተጠያቂነት የሚድኑ አይደሉም። ቡድኑን በመምራት በተጓዙባቸው ቦታዎችና በአደረጓቸው ጨዋታዎች ላይ ሁሉንም ክስተቶች ይከታላሉ፣ ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑም ሪፖርት ያደርጋሉ። ከተጫዋቾች፣ አሰልጣኞችና የፌዴሬሽን አመራር አካላት ጋር የጠበቀ ትስስር ይኖራቸዋል። ስለ ቡድኑ በቂ የሆነ መረጃ ያላቸውና ሲጠየቁም ለመስጠት የሚችሉ ናቸው። ቡድኑ ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊው ነገር ሁሉ መሟላቱን ያረጋግጣሉ፣ ለቡድኑ ስጋትና ችግር የሆኑ ነገሮች እንዳይከሰቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ።
ከዚህ የብሔራዊ ቡድን የቡድን መሪ ኃላፊነት በመነሳትም አንጻር የዋልያዎቹ ቡድን መሪ የምንያህልን ሁለት ቢጫ ካርድ መመልከትን ማወቅ ይጠበቅባቸዋል። ለቡድኑ ውጤት ማጣት ችግር እንደሚሆን በመረዳትም በቦትስዋናው ጨዋታ እንዳይሰለፍ መረጃውን ለአሰልጣኙ ማሳወቅ ይጠበቅባቸው ነበር። ይህን ኃላፊነት ያልተወጣ የቡድን መሪ ሃገር ለመጎብኘት ከቡድኑ ጋር እንዲጓዝ የተመደበ እንጂ የቡድን መሪ አያስብለውም። ፌዴሬሽኑም ሰዎችን በመቀያየር የቡድን መሪ አድርጎ የሚመድበው ምናልባት ሁሉም አመራር ሃገር የመጎብኘት ተራው ይድረሰው ብሎ ይሆን?
የስፖርት ጋዜጠኞች፣ አሰልጣኞችና ባለሞያዎች እንዲሁም ለስፖርቱ ቅርብ የሆኑ አካላት በአጠቃላይ የበኩላቸውን የተጠያቂነት ድርሻ መውሰድ ይኖርባቸዋል። በእግር ኳስ ስፖርት ትንተና የራዲዮውን ሰዓትና ጋዜጣዎችን የተቆጣጠርን ነን የሚሉ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችም ለዚህ ውድቀት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ። የአውሮፓ ተጫዋቾችን የሜዳ ውስጥ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን ግላዊ ህይወቱንና የየእለት እንቅስቃሴውን ሳይቀር ስራዬ ብለው ፈትሸው የሚያቀርቡ የስፖርት ጋዜጠኞች ምንያህል ተሾመ የሁለት ቢጫ ካርድ ሰለባ መሆኑ እንዴት ማወቅ ተሳናቸው? ይህን ማወቅ ካልቻሉ አንዳንድ ተቺዎች እንደሚሉት የስፖርት ጋጠኞች ሳይሆኑ ተርጓሚዎች ብቻ ናችው ልንላቸው እንገደዳለን። የድረ ገጽ ጥገኞች እንጂ ጋዜጠኞች ለመባል የሚያስችል ብቃት እንደሌላቸውም ለመናገር እንደፍራለን።
የሁሉም አካላት ተጠያቂ መሆን እንዳለ ሆኖ አጠቃላይ መንስኤው ግን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ላይ መውደቁ አይቀርም። ፌዴሬሽኑ በስፖርቱ እውቀት ባላቸው ሰዎች ቢመራ ወይም አማካሪዎችን ቢያስጠጋ ምናልባት ችግሩ ላይከሰት ይችል ነበር። አመራሩ የእግር ኳስ ጥልቅ እውቀት እንዲኖረው ባይጠበቅም ብሔራዊ ቡድኑ ለኢንተርናሽናል ጨዋታዎች በሚዘጋጅበት ጊዜ እንኳን የእግር ኳስ ባለሞያዎችን ጋብዞ በፈቃደኝነት ቡድኑን በእውቀታቸው እንዲያግዙ ቢያደርግ ለእንዲህ ያለ ችግር አይጋለጥም ነበር። ሁሉንም ነገር በአሰልጣኞቹ ትከሻ ላይ ጥሎ መተኛት ለወደፊቱም ቢሆን የሚበጅ አይደለም።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሰራን ዘመናዊና የፊፋ ደረጃን የጠበቀ እንደሆነ ፕሬዝዳንቱ ከዚህ በፊት ከሰንደቅ ጋዜ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ መናገራቸው ይታወሳል። ይህ የፊፋን ደረጃን የጠበቀ አሰራርን የተከተለ ፌዴሽን ግን ሁለት ቢጫ ያለበት ተጫዋች በማሰለፍ ሃገርን ዋጋ ያስከፈለ፣ የዋልያዎቹንም ልፋት ከንቱ ያደረገ ጥፋት ፈጽሟል። ፕሬዝዳንቱ የብሔራዊ ቡድኑን በዳታ የተደገፈ አጠቃላይ መረጃ የሚሰበስብ ባለሞያ የሌለው ፌዴሬሽንን የሚመሩት ፕሬዝዳንቱ አቶ ሳህሉ ገብረወልድ በባለሞያዎች የተደራጀ የሰው ሃይልን እንዳሟሉ ነግረውን ነበር። አሁን ብሔራዊ ቡድኑንና ሃገርን የሚጎዳ ስህተት ተፈጽሞ ሲታይ ግን ፌዴሽኑ በባለያዎች የተደራጀ እንዳልሆነ እንረዳለን።
የዋልያዎቹን ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ስኬት የአመራሩ ስራ እንደሆነ ሲነግሩን የከረሙት የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ አመራሮች አሁንስ ጥፋቱን በማን ላይ ያላክኩ ይሆን?
በማሸነፍ ላይ የተመሰረተ የዋልያዎቹ እድል
ፊፋ በኢትዮጵያ ላይ የጀመረውን ክስ አጣርቶ ጥፋት መፈጸሙን አረጋግጫለሁ ካለ ከዋልያዎቹ ሶስት ነጥብ መቀነሱ የግድ ነው። ይኸውም በ13 ነጥብ ምድቡን ይመራ የነበረው ቡድናችን 10 ነጥብ ይኖረዋል ማለት ነው። መልካሙ ነገር ቡድኑ ነጥብም ተቀንሶበት የምድቡ መሪ ሆኖ የመጨረሻ ጨዋታውን ውጤት መጠበቁ ነው። ደቡብ አፍሪካ ስምንት፣ ቦትስዋና ደግሞ ሰባት ነጥብ በመያዝ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ይከተሉታል። ሶስቱም ሀገሮች ምድቡን በበላይነት ለመጨረስ እድል ያላቸው ሲሆን፣ በመጪው መስከረም ወር ላይ በሚያደርጉት የመጨረሻ ጨዋታ ውጤታቸው የሚታወቅ ይሆናል።
ኢትዮጵያ ከምድቡ መውደቋን ያረጋገጠችውን ሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክን ስትገጥም፣ ደቡብ አፍሪካ በሜዳዋ ቦትስዋናን ታስተናግዳለች። ከደቡብ አፍሪካና ቦትስዋና በተሻለም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተሻለ እድል አለው። ጨዋታውን ማሸነፍ ከቻለ የሌሎቹን ውጤት ሳይጠብቅ የምድቡ አላፊ መሆኑን ያረጋግጣል። ደቡብ አፍሪካና ቦትስዋና ግን አሸንፈውም ቢሆን የኢትዮጵያን መሸነፍ በመጠበቅ ላይ የተመሰረተ እድል ነው ያላቸው። ሁለቱም በአቻ ውጤት የሚለያዩ ከሆነ ደግሞ የኢትዮጵያ ቡድን አቻ ቢለያይ ወይም ቢሸነፍም እንኳ የማለፍ እድል አለው።
አሳሳቢው የዋልያዎቹ አቋም
ባለፈው እሁድ በአዲስ አበባ ስታዲየም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደቡብ አፍሪካን 2ለ1 ያሸነፈበት ብቃቱን በማስተዋል ላጤነው ቡድኑ እድል ከእርሱ ጋር እንደነበረች መናገሩ አይቀርም። የቡድኑ እድለኛነት በርናንድ ፓርከር በራሱ መረብ ላይ ግብ ስላስቆጠረ ብቻ ሳይሆን በእለቱ ፈጽሞ የወረደ አቋም አሳይቶ በማሸነፉም ነው። ውጤቱ አስደሳች ቢሆንም በሰከነ ስሜት የቡድኑን ድክመቶች ገልጾ መነጋገሩ አይከፋም።
ዋልያዎቹ በሜዳቸውና በደጋፊያቸው ፊት በተጋጣሚያቸው ላይ ጫና ለመፍጠር የቻሉበትን ብቃት ማሳየት አልቻሉም። ከራሳቸው ሜዳ ለመውጣት በጣም ሲቸገሩ ነበር። ኳስን በረጅሙ በማሻገር ተጋጣሚ ግብ ክልል ለመድረስ የተደረገው ሙከራም አላዋጣቸውም። ወደፊት የሚሻገሩ ኳሶች ሁሉ ለባፋና ባፋና ተከላካዮችና ግብ ጠባቂ ሲሳይ ሆነዋል። አጥቂዎቹ ሳላዲን ሰኢድና ጌታነህ ከበደ ኳስ ለማግኘት ብዙ ደቂቃዎችን ሲታገሉ ቆይተዋል። ሳላዲን መሐል ሜዳ ድረስ በመምጣት ኳስ ተቀብሎ ወደፊት ለማለፍ ሲሞክር ታይቷል። አንዳንድ ጊዜ የሚያገኛቸውን ኳሶች ለማን እንደሚሰጥ ቸግሮት ሲያባክናቸው ነበር። ጌታነህ ከበደ እረፍት አጋማሽ ሲቃረብ ለዋልያዎቹ የአቻነት ግብን ከማስቆጠሩ በፊት ኳስ ይዞ ሲጫወት አልታየም ነበር። ከደቡብ አፍሪካ ተከላካዮች ጋር ሲጋፋ ነበር የቆየው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጌታነህ ከበደ አቻ የምታደርገዋን ግብ ያስቆጠረበትን መንገድ ስናስተውል ብዙ ቅብብሎሽ እንደነበሩ እንረዳለን። አስራት መገርሳ፣ አዲስ ህንጻ፣ ሽመልስ በቀለ፣ ምንያህል ተሾመና ጌታነህ ከበደ ኳሷን በአጭር ተቀባብለው በመጫወት ጫና ስለፈጠሩ ግብ ማስገኘት ችለዋል። ይህ አይነቱን የጨዋታ እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ ማሳየት ቢችሉ ኖሮ ግቦችን የማስቆጠር እድላቸው ሰፊ እንደነበር መገመት ይቻላል።
እንግዳው ቡድን ከእረፍት በፊትም ሆነ በኋላ የአሳየው ብቃት እጅግ አስደናቂ ነበር። በተለይም በኳስ ቁጥጥርና በግብ ሙከራዎች ፍጹም የበላይነት ነበረው። ባፋናዎች ኳስን በአግባቡ በመቀባበል ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በተደጋጋሚ ይጠጉ ነበር። የአዲስ አበባ ስታዲየም ደጋፊ ጫና ሳይበግራቸው ጥሩ ፍሰት ያለው የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ማሳየት ችለዋል። እድል ግን ከእነርሱ ጋር አልነበረችምና ውጤት ሳይቀናቸው ቀርቷል።
የዋልያዎቹ ዋና ችግር ተደርጎ የሚጠቀሰው አማካይ ክፍሉ ፍጹም ባዶ እንደነበር እሁድ እለት ከደቡብ አፍሪካ ጋር የነበረው ጨዋታ ላይ ታይቷል። ቡድኑ ኳስን አደራጅቶ ለአጥቂ ክፍል በአግባቡ የሚያሻግር አማካይ ተጫዋች አልነበረውም። ለዚህም ነበር ከሜዳው ወጥቶ ለመጫወት ሲቸገር የታየው።
በቀጣይም ቡድኑ ከፍተኛ ክፍተት የታየበትን አማካይ ክፍሉን መገንባት ካልቻለ በተጋጣሚው ላይ ብልጫ ለመውሰድ የሚያስችለውን የጨዋታ እንቅስቃሴ ለማሳየትና ውጤታማ ለመሆን የሚቸገር ይሆናል።n
(ምንጭ፡- ሰንደቅ ጋዜጣ )