ቶኮላ
ኢሳት ወደ ኤርትራ ተጉዞ የኤርትራውን ፕሬዝዳንት ማናገሩ ከተሰማ ወዲህና በተለይም የቃለመጠይቁ ቅንጣቢ ከቀረበ ቦኋላ እየበገኑ ያሉት ወያኔዎች ብቻ ሳይሆኑ በወያኔ የብሄር ፖለቲካ እናተርፋለን ብለው ሲዳክሩ አመታት ያስቆጠሩ ብሄርተኞች ጭምር መሆናቸውን ጭፍሮቻቸው በሶሻል ሚዲያ ላይ ለማስተጋባት ከሚሞክሩ አስተያየቶች ለማየት እየቻልን ነው:: “በሚንልኪ ዘመን የደነቆረ በሚንልክ እየማለ ይኖራል” እንደተባለው እነዚ ሰዎች ከመንደርተኝነት ተላቀው አለማችን ከቀዝቃዛው ጦርነት ፍጻሜ ወዲህ የደረሰቺበትን እድገት ምነው መረዳት ተሳናቸው? የሚል ጥያቄ ያስጨንቀኝ ጀምሮአል:: በኤኮኖሚ የበለጸጉት የአውሮጳ አገሮች ብንዋሃድ ነው በአለም ውስጥ ተገቢ ስፍራችንን ይዘን መቀጠል የምንችለው በማለት አንድ ለመሆን ሲጣደፉ የኛዎቹ በቋንቋ ተካለን የየራሳችንን የፖለቲካ ጎጆ ብንቀልስ ነው የሚበጀን ማለታቸው የጤና ነው?
ከሁሉም የሚገርመው ሰው በሰውነቱ በተከበረበት አለም እየኖሩ ለአገራቸውና ለህዝባቸው ግን የሚመኙት ሰው በቋንቋ ማንነቱ እርስ በርሱ የሚጠፋፋበትን የጥንትዮሽ ዘመን አይነት አስተዳደር መሆኑ የሰው ደም የሚያስጠማቸው ምን አይነት መንፈስ ብጠናወታቸው ነው? ያስብላል:: ቋንቋና ባህል ሰው በተወለደበት ህብረተሰብ ውስጥ የሚማረውና ይዞት የሚያድገው ትርጉምና ጥቅም የሚሰጠውም በዚያው ህብረተሰብ ውስጥ እስከተኖረ ድረስ ብቻ ሆኖ ሳለ ሌላው ቀርቶ አሜሪካና አውሮፓ ውስጥ ከአብራካቸው የሚወለዱት ወይም የተወለዱት ሳይቀሩ እነርሱ የኛ ነው የሚሉትን የማይወርሱ መሆናቸውን እያወቁ ለምንድነው አመለካከታቸውን መቀየር የተሳናቸው?
እኔን የሚያሳዝነኝ የመልካም አስተዳደር እጦት ለምድራዊ ጉስቁልና የዳረገው መከረኛ ህዝብ በቋንቋና በባህል ልዩነት ምክንያት እርስ በርሱ ቢገዳደል ምንድነው ጥቅሙ? የምሥራቅ አውሮፓዎን የቅርብ ጊዜ ትዝታ ትተን አይናችን ፊት በሩዋንዳ፤ በቡሩንድ፤ በሱማሌ ወዘተ ህዝብ እርስ በርስ መጠፋፋት ማን ተጠቀመ? እንዴት ከዚህ መማር ይሳነናል?
አያት ቅድሜ አያቶቻችን በመሰዋዕትነት ባስረከቡን ነጻ አገር ውስጥ ተወልደንና አድገን የአስተዳደር በደል ያስከተለውን ኢፍትሃዊነት ከመዋጋትና የጋራ ቤታችንን ከድህነትና ከመብት ረገጣ የጸዳ ከማድረግ ይልቅ እራሳችንን የሚያሳንስ ለሌላው ግን የሌለ ኩራትና ክብር የሚፈጥር ” የጥቁር ቅኝ ገዥ” ታሪክ በራሳችን ላይ መፍጠር ለምን አስፈለገ?
መለስ ዜናዊና የበታቸኝነ ስሜት የፈጠራቸው ጥቂት የትግራይ ጉጂሌዎች ከፋፍሎ ለመግዛት በሸረቡት ሤራ ተተብትበን እስከመቼ እንታለላለን? በኔ አስተያየት በብሄርተኝነት ዙሪያ ጫፍ የረገጥ ፖለቲካ የሚያቀነቅኑ ሰዎች በተለያየ ምክንያት በግለሰብ ደረጃ የበታቸኝነት ስሜት ውስጥ የተዘፈቁ ናቸው:: ምናልባት ዘመናዊ ትምህርት ችግሩን ሳያባብሰው አልቀረም:: የሥነልቦና ሙያተኛም ባልሆን የበታቸኝነት ስሜት የሚጠፋው ከውስጥ ተኮትኩቶ በሚወጣ የራስ መተማመን ብቻ ነው ብየ አምናለሁ:: እራስን ማከም ለሚቻል የስነልቦና ችግር አንድ ሚስኪን ከሌላው ሚስኪን የአገሩ ዜጋ ጋር እንዲገዳደል ማነሳሳት ወንጀል ነው::
ስለዚህ ለአገርና ለወገን የማይበጅ የኦሮሞ፡ የትግሬ፡ የሱማሌ ፡የሲዳማ፡የአማራ ወዘተ ብሄርተኝነት ከማቀንቀን እኔ በቋንቋዬ ፡ በሃይማኖቴ ፡በባህሌ ወይም በመልኬ ምክንያት ከማንም በታች አይደለሁም:: ያነስኩ ሆኘ እራሴን አይቼ ቢሆን እንኳ ያለፉት ኋላ ቀር አገዛዞች ጭነውብኝ ያለፉት ስለሆነ የዚያ ሠለባ ለመሆን እራሴን አሳልፌ አልሰጥም የሚል በራስ መተማመን ከውስጥ ሊመነጭ ይገባል:: በሠለጠነው 21ኛው ክፍለ ዘመን እኔን ከራሱ አሳንሶ የሚያየኝ ካለ በድንጋይ ዘመን ከነበሩት እነዚያ አገዛዞች የባሰ ኋላቀር ነው ብሎ የሰው መሳቂያ መሳለቂያም ማድረግ ይቻላል:: ኢሳያስ አፈወርቂ አሉም አላሉም የብሄር ፖለቲካው ምን ያህል እንደጎዳንና እንዳዳከመን ስላወቅን ነው የብሄር ፖለቲካው ላይ የትግል ክንዳችንን ለማንሳት የተገደድነው:: የብሄር ብሄረሰቦች ቀን እንድናከብር አድርጎን በሌላ በኩል ግን በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ለብሄር ጭቆና የዳረገንና የኢትዮጵያ እስር ቤቶች ኦሮሚኛ ተናጋሪ ሆኖአል እስከመባል ያደረሰንን ሥርዓት የምንዋጋው ያለምክንያት አለመሆኑን ወያኔ ራሱ ተረድቶታል:: በብሄራችን ምክንያት ብቻ ከሥራ መፈናቀል፡ለእሥር፡ ለስደትና ለሞት የተዳረገን ሁሉ ሳንለያይና ሳንከፋፈል ዘረኛውን አገዛዝ ከጫንቃችን ለማውረድ ጊዜው አሁን ነው:: አገራችንን የዘረፈ፡ የመጭውን ትውልድ ሳይቀር ዕድል ለማጨለም አገራችንን ለም መሬት እየሸነሸነ ለባዕድ እየቸበቸበ ያለውን ወያኔን በምንም መስፈርት ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር አናወዳድርም :: ምንም እንኳ ኢሳያስ የዛሬዎቹን ጨቋኞቻችንን ለድል ለማብቃት አስተዋጽ ቢኖራቸውም ዋናው ለአገራችንና ለሁለቱ ህዝቦች ቅን እንደሚያስቡ ከአንደበታቸው መስማታችን ለኔ በቂ ነው:: ደግሞ ሰው ይሳሳታል ዋናው ከስህተቱ ለመማርና ስህተቱን ለማረም ዝግጁ መሆኑ ነው:: ፕረዝዳንት ኢሳያስን የወደድኩት ይህንን ስላረጋገጡልኝ ነው ::
እናንተስ ምን ትላላችሁ?
The post የኢሳያስ ቃለመጠየቅና የብሔርተኞች ጫጫታ appeared first on Zehabesha Amharic.