ደም /Blood/
የሰው ልጅ ከተለገሰው ስጦታ አንዱና ዋነኛው ደሙ ነው፡፡ ከሙቅ የቀጠነው፣ ከውሃ የወፈረው ደማችንን ወገቡ ላይ ብንከፍለው ሁለት ዓበይት ቡድኖች ይፈለፈላሉ፡፡ እነዚህም ፈሳሽ ክፍሉና ህዋስ ክፍሉ ናቸው፡፡ 55% እና 45% እንደየቅደም ተከተላቸው ይይዛሉ፡፡
ፈሳሽ ክፍሉ የተለያዩ ኤሌክትሮላይቶችን ለምሳሌ ሶዲየም፣ ፖታሲየም፣ ክሎሪን ወዘተ ፕሮቲኖችን ኢንዛይሞችን የመሳሰሉትን ሲይዝ የህዋስ ክፍሉ ደግሞ ሶስት አይነት ህዋሳትን ይይዛሉ፡፡ እነዚህም፡-
1. ቀይ ደም ሕዋሳት /Red blood cells/
2. ነጭ የደም ሕዋሳት /White blood cells/
3. ፕላቶሌቶች /Platlets/ ናቸው፡፡
ድርሻቸውን ብንመለከት በአንድ ማይክሮ ሊትር ደም ውስጥ (የአንድ ሊትር አንድ ሚሊዮንኛ እንደማለት ነው) ከ4-6 ሚሊዮን የሚቆጠሩ ቀይ የደም ህዋሶች፣ ከ4,000-10,000-450,000 የሚቆጠሩ ፕላትሌቶችን ይይዛል፡፡
በአጠቃላይ ሰውነታችን ከተሰራበት 100 ትሪሊዮን ሴሎች ውስጥ 25 ትሪሊዮን ቀይ የደም ህዋሳት ናቸው፡፡ ስለዚህ ደም ማነስ ሲባል በደምሳሳው ይሄ ቀይ ሆኖ የምናየው የደማችን ማነስ ሳይሆን የቀይ ደም ህዋሳት ቁጥር መመናመንን ያመለክታል፡፡ ሌሎቹ ግን ሰላም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን የደም ማነስ ቢኖርም ነጭ የደም ህዋሳት የመከላከል ስራቸውን ይቀጥላሉ፣ ፕላትሌቶች ደግሞ የደም መፍሰስ እንዳይኖር ደምን በማርጋት ስራቸው ይወጠራሉ፡፡
– የደም ህዋሳትን ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉ ጥሬ ዕቃዎችና ቅድመ ሁኔታዎች
1. ጤነኛ የሆነ መቅን /Healthly bone marrow/
ጤነኛ የቀይ ደም ህዋሳትን የሚያመርተው መቅን ከተለያዩ እክሎች የፀዳ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ የመቅን ስንፈት /Boon marrow Aplasia/ ወይም መቅኑ በሌላ ጎጂ ህዋስ ከተወረረ ለምሳሌ በደም ካንሰር ህዋሳት ከተወረረ እንደ ጥንቱ በሰላም የማምረቱ ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡
2. ጤነኛ የሆነ ኩላሊት
ኩላሊትን የአጥንታችን መቅን ቀይ የደም ህዋሳትን እንዲያመርት ትዕዛዝ በመስጠቱ ረገድ ከ90% በላይ ስልጣን ተሰጥቷታል፡፡ ይህን ዓላማዋን ኢሪትሮፓዮቲን በተሰኘው የፕሮቲን አይነት ትፈፅማዋለች፡፡ ኩላሊት ላይ ችግር ካለ ይህም ፕሮቲን አብሮ ችግር ውስጥ ይገባል፡፡ ስለዚህ ስር የሰደደ የኩላሊት በሽተኞች ለደም ማነስ ችግር የሚጋለጡት ከዚህ የተነሳ ነው፡፡
3. በቂ የሆነ ፎሊክ አሲድና ቫይታሚን B12
እነዚህ የምግብ አይነቶች ለቀይ ደም ህዋሳት ቶሎ በስሎ መውጣት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ፡፡ እነሱም ከሌሉ በአጥንት መቅን ውስጥ የሚኖረው የቀይ ደም ህዋሳት እርባታ ፍጥነቱ ይዘገያል፡፡ ይሄን ለማካካስ እያንዳንዱ ህዋስ በግሉ ያብጣል፡፡ እውነተኛ ቅርፃቸውን ያጣሉ፡፡ ቶሎ ህዋሱ ፈንድቶ እንዲሞት በማድረግ ሰውዬውን ለደም ማነስ ሊያጋልጡ ይችላሉ፡፡
4. በቂ የሆነ የብረት ማዕድን
ሰውነታችን ብረትን እጅጉን አጥብቆ ይፈልገዋል፡፡ የሚፈልገው ደግሞ ባሌስትራ ለመስራት ሳይሆን የቀይ ደም ህዋሳትን ለመቀሸር ነው፡፡ የቀይ ደም ህዋሳትን የኦክስጅን ማኅፀን ያደረጋቸው ሔሞግሎቢን የተሰኘው ንጥረ ነገር ነው፡፡ ሄሞግሎቢን ደግሞ ማነው ብለን ብንጠይቅ የፕሮቲን የፓይሮልና የብረት ውህደት ነው፡፡ በሰውነታችን ውስጥ አለ ተብሎ ከሚታመነው ከ4-5 ግራም የሚደርሰው የብረት መጠን 65 ፐርሰንቱ የተከማቸው ቀይ ደም ህዋሳት ውስጥ ነው፡፡ ሳንባ ጋር የደረሰው ኦክስጅን በቀጥታ የሚያያዘው ሔሞግሎቢን ውስጥ ካለው የብረት አተም ጋር ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ብረት የኦክስጅንን እጅ ይዞ ከእያንዳንዱ የሰውነታችን ህዋሳት ጋር በሰላም ያደርሰዋል፡፡ ደምን ያከበረው ትልቁ ጉዳይ እስትንፋሳችንን ማጓጓዙ ነው፡፡ ኦክስጅንን የማይሸከም ደም ካለ ገደል መግባት ይችላል፡፡ ይሄንን ስል ደም ኦክስጅንን ከመጠግረር ውጪ ሌላ ስራ የለውም ማለቴ አይደለም፡፡ ነገር ግን የሰውነታችን ህዋሳት አፍንና አፍንጫን አፍኖ ሌላን ስራ መስራት በአንድ እጅ ማጨብጨብ ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ብረት አጠረን ማለት ኦክስጅን አጠረን ማለት ነው፡፡ በአማካኝ በ100 ሚሊ ሊትር ቀይ ደም ህዋሳት ውስጥ 15 ግራም የሚደርስ ሔሞግሎቢን በወንዶች ሲኖር፤ በሴቶች ደግሞ 14 ግራም ይደርሳል፡፡ እያንዳንዱ ግራም ሔሞግሎቢን 1.34 ሚሊ ሊትር ኦክስጅንን ይሸከማል፡፡ ጠቅለል አድርገን ብናሰላው 100 ሚሊ ሊትር ቀይ ደም ሀዋሳት 20 ሚሊ ሊትር ኦክስጅን በወንዶች፣ 19 ሚሊ ሊትር ኦክስጅን በሴቶች ይዞ ይዞራል ማለት ነው፡፡ በዚሁ አጋጣሚ የአንዱ ጎልማሳ የደም መጠን ከ5-6 ሊትር ይደርሳል፡፡
5. ጤነኛ የሆነ ዘረመል
የደም ማነስ መንስኤዎች፡-
ከአንድ ህመምተኛ ደም ማነስን መርምሮ ማግኘት ጀግና ተብዬ የአንበሳ ቆዳ ካለበስኩ አያስብልም፡፡ ዋናው ጥያቄ ለምን ደሙ አነሰ ነው፡፡ ለምሳሌ እያለቀሰ ያለን ሰውዬ ተከፍቶ ነው የሚያለቅሰው ብሎ መናገር ነቢይ አያሰኝም፡፡ ይልቁንም ጥያቄው ለምን ተከፋ ነው፡፡ ሰው ሞቶበት ነው? ፍሬንዱ ዳምፕ አድርጋው ነው? አርሰናል ተሸንፎ? ወዘተ… የሚለውን ጥያቄ መለየቱ ነው መፍትሄ የሚያመጣው፡፡ ደም ማነስ የቀይ ደም ህዋሳት ለቅሶ ነው፡፡ ለምን አለቀሱ? ለደም ማነስ ድንኳን ተክለናል ያሉ የደም ምሁራን /Hematologists/ ብዙ ምክንያቶችን አንብተዋል፡፡ እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. የቀይ ደም ህዋሳት ምርት መቀነስ
ይህ አይነቱ ምክንያት የሚከሰተው የሚመረቱት የቀይ ደም ህዋሳት ቁጥር ከሚሞቱት የቀይ ደም ህዋሳት በታች ሲሆን ነው፡፡ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት እንደ መንስኤነት ሊወቀሱ ይችላሉ፡፡
– የብረት፣ ፎሊክ አሲድና ቫይታሚን B12 እጥረት
– የአጥንት መቅን ችግር
ይሄ ደግሞ ዋናው አምራቹ ክፍል ሲታመም ነው፡፡ ለምሳሌ በካንሰር ህዋሳት ሲወረር፣ እንዲሁም እሱን ሊጎዱ የሚችሉ አንዳድ መድሃኒቶች፣ ጨረሮች ወዘተ…
– የቀይ ደም ህዋሳት እንዲመረቱ የሚያበረታቱ ሆርሞኖች እጥረት ለምሳሌ፡- አነስተኛ የሆነ የታይሮይድ ሆርሞን፣ ስር የሰደደ የኩላሊት በሽታ፤
– ስር የሰደዱ በሽታዎች ለምሳሌ ካንሰር፣ ቲቢ
2. የቀይ ደም ህዋሳት ጥፋት መጨመር
ጤነኛ በሆነ ሰውነት የቀይ ደም ህዋሳት በህይወት የሚቆዩት ለ120 ቀናት ነው፡፡ የቀይ ደም ህዋሳት ጥፋት መጨመር ማለት በሰውነታችን ውስጥ ከ100 ቀናት በታች ሲኖሩ ነው፡፡ የሆነ ሰው በወጣትነቱ ዕድሜ ቢሞት በአጭሩ ተቀጨ እንደምንለው እነዚህም ህዋሳት ኦክስጅንን በሚገባ ተሸክመው ሳይጠግቡ በአጭሩ ይቀጫሉ፡፡ ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ የወባ በሽታ እንዲህ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ሾተላይም ሽሉን ወይም ህፃኑን የሚገለው በዚህ መልኩ ነው፡፡
3. የደም መፍሰስ
ይህ አይነቱ የደም ማነስ የሚከሰተው ከሰውነታችን ያለ አግባብ በሚያመልጥ የደም መፍሰስ ምክንያት ነው፡፡ እነዚህ የደም መፍሰሶች ምንጫቸው የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡
– ከመጠን በላይ የሆነ የወር አበባ (በአንድ ዑደት ከ80 ሚሊ ሊትር በላይ ወይም ከ7 ቀን በላይ የሚፈሳት ከሆነ)
– ከጨጓራና አንጀት በሽታ የተነሳ የሚፈጠሩ መድማቶች
– በወሊድ፣ በውርጃ፣ በአደጋ ምክንያት የሚፈጠር መድማት
– አንዳንድ ጥገኛ ህዋሳት ለምሳሌ ቅድም ያየነው የደም ማነስ በሽተኛ የነበረበት የመንጠቆ ትል ለዚህ ማስረጃ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ አንድ የመንጠቆ ትል በቀን 0.3-0.5 ሚሊ ሊትር ደም ከአንጀት ላይ ሊጠባ ይችላል፡፡ እንግዲህ አስቡት! በቀላሉ እንኳን ለሁለት ዓመት ከመንጠቆ ትሎች ጋር አብሮ የኖረ ሰው ደም ማነስ ቢይዘው ከብቶቹንም ጥሎ ሆስፒታል ቢመጣ የሚገርም አይሆንም፡፡
የደም ማነስ ምልክቶች
የደም ማነስ ምልክቶች የሚወሰኑት በሽተኛው ላይ በተከሰተበት ፍጥነት፣ መጠንና ደም ማነሱ ያመጣው መንስኤ አማካኝነት ነው፡፡ አንዳንዱ ህመምተኛ የደም ማነሱ አነስተኛ ከሆነ ምንም ላይሰማው ይችላል፡፡ የደም ማነሱ ከፍተኛ ከሆነ ግን እሱን ተከትሎ የሚመጡ ብዙ ምልክቶች ይኖራሉ፡፡
ድካም፣ ራስ ምታት፣ ማዞር፣ ድቀት፣ ለስራ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ የአየር ማጠር ወይም ቁና ቁማ መተንፈስ፣ የራስን የልብ ምት ማድመጥ የተለመዱት የደም ማነስ ምልክቶች ናቸው፡፡ በተለይ የቀደመ የልብ በሽተኞች የሆኑ ሰዎች ለደም ማነስ በሚጋለጡበት ጊዜ የተፈጠረውን የኦክስጅን እጥረት ለመቅረፍ ብላ ልብ ከመጠን በላይ ስለምትሰራ ምልክቶቹ የገዘፉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሌሎችም እንደ ደም ማነሱ አይነት ተያያዥ ምልክቶች ደም ማነሱን ሊያጅቡት ይችላሉ፡፡
ምን እናድርግ?
- አመጋገባችንን በተመለከተ
1. በብረት (Iron) የበለፀጉ ምግቦች መመገብ
ከዓለም ህዝብ 30% የሚሆነው በደም ማነስ ተጠቅቷል፡፡ ከዚሁ ውስጥ ግማሽ ያህሉ የብረት እጥረት ነው የተጫወተበት፡፡ ከላይ እንደተገለፀው ሔሞግሎቢን የተሰኘው የቀይ ደም ህዋሳት ክፍል የተሰራበት ንጥረ ነገር አንዱ ብረት ነው፡፡ ደማችን በዚህ ምክንያት ቀይ ሆኗል፡፡ ለምሳሌ ኮፕር(መዳብ) ይህን ቦታ በሚሸፍንላቸው እንደነሎብስተር አይነት አሳዎች ደማቸው ሰማያዊ ሆኗል፡፡ ስለዚህ የብረት ማዕድን የበዛባቸው ምግቦችን መመገብ ደምን ቀይ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን ቁጥራቸውንም ደህና አድርጎ ይሰቅልልናል፡፡ እነማናቸው ካላችሁ ቀይ ሥጋ፣ ጉበት፣ የዕንቁላል አስኳል፣ ሽንብራ፣ ባቄላ መብላት ይችላሉ፡፡
2. በፎሊክ አሲድና በቫይታሚን B12 የከበሩ ምግቦች መመገብ
ለሰውነታችን በቀን የሚያስፈልገው የፎሊክ አሲድ መጠን ከ0.4 ሚ.ግ አይበልጥም፡፡ ታዲያ 100 ግራ የሚመዝን ቅጠላ ቅጠል የተመገበ ሰው ከ1 ሚ.ግ የበለጠ ፎሊክ አሲድ ማግኘት ይችላል፡፡ ጠቅላላ የሰውነታችን የፎሊክ አሲድ ጎተራ 5 ሚ.ግ ነው፡፡ ታዲያ አነስተኛ የሆነ ፎሊክ አሲድ በየቀኑ የሚመገብ ሰው ካለ በ4 ወር ውስጥ የደም ማነስ ተጠቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ለምን ጠላት ደስ ይበለው? ቆስጣ፣ ሰላጣ፣ ባቄላ፣ ሎሚ፣ ብርቱካን፣ ሃብሃብ፣ ጉበት፣ ኩላሊት፣ እንጉዳይ እንክት አድርገው ቢበሉ በዚህ ምክንያት የሚመጣ የደም ማነስን አስቀሩ ማለት ነው፡፡
ቫይታሚን B12ን ቢሆን ሰውነታችን እንዲሁ ይፈልገዋል፡፡ ከፎሊክ አሲድ የሚለየው የሚያስፈልገን የቀን ቀለብ ከፎሌት የሚያንስ በመሆኑ ብዙ እንኳን ባንመገብ ደም ማነሱ ሊከሰትብን የሚችለው ከ3-5 ዓመታት ባሉት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ሌላው ቁም ነገር ደግሞ ቫይታሚን B12 ከእፅዋት እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህ ከስጋ ተዋፅኦዎች ከዓሣና ከወተት ውጤቶች ላይ መፈለግ ግድ ነው፡፡
– ስር ለሰደዱ በሽታዎች መፍትሄ መፈለግ
ለምሳሌ የቲቢ በሽታ ከሆነ ቶሎ መታከም፡፡ የደም ካንሰርም ከሆነ በተለይ ልጆች ላይ አመርቂ የሆነ ውጤት ስላለው በጊዜው መፍትሄ መፈለግ ደም ማነሱንም ሆነ ዋናውን በሽታ ቶሎ ማስወገድ ይቻላል፡፡
– የሚሰጠንን የደም ማነስ መድሃኒቶች በአግባቡ መውሰድ
በተለይ ከፍተኛ የሆነ የብረት፣ የፎሊክ አሲድና ቫይታሚን B12 ፍላጎት የሚንርበት የእርግዝና ወቅት ላይ የሚሰጥ መድሃኒት አለ፡፡ መድሃኒቱ ትንሽ ጨጓራን የመንካት ጠባይ ስላለው፣ በተጨማሪም ዘለግ ላለ ጊዜ ስለሚወሰድ ለምሳሌ ለሶስት ወር ያህል ተጠቃሚው መድሃኒቱን የማቋረጥ ነገር ይታይበታል፡፡ ነገር ግን ለጨጓራው ከሐኪም ሌላ መፍትሄ መፈለግ ይሻላል እንጂ መድሃኒቱን ባያቋርጡት መልካም ነው፡፡
ደም
ለሰው መድሃኒቱ ሰው ነው እንደሚባለው ሁሉ ለደም ማነስም መድሃኒቱ ደም የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ ለምሳሌ ብዙ ደም ፈሶት ሔሞግሎቢኑ በጣም የወረደ ሰው ጉበት ብላና ዳን ማለት እኔ የምሞተው ዛሬ ማታ ላሜ የምትወልደው ለፍልሰታ እንዳለችው ሴት ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም በእንደዚህ አይነት ሁኔታ የፈሰሰ ደም ቶሎ መተካት ስላለበት ጉበቱን ለጊዜው ፍሪጅ ውስጥ ማስቀመጥ ይሻላል፡፡ ይልቁንም የሚመሳሰለውን ደም ፈልጎ መለገስ ህመምተኛውን ከሞት በእጅጉ ይታደገዋል፡፡
- ከኢንፌክሽንና ከአንዳንድ ጥገኛ ራስን መጠበቅ
ለምሳሌ ወባ ደምን ከማሳነስ ጀምሮ እስከ መግደል ታደርሳለች፡፡ ስለዚህ ራስን ከወባ ትንኝ መጠበቅ ብልህነት ነው፡፡ የራስን የግል ንፅህና መጠበቅም ቅድም መግቢያችን ላይ እንዳየነው ህመምተኛ በጥገኛ ህዋሳት ከመጠቃት ያርቃል፡፡
መቅንን መተካት
ይህ አይነቱ ህክምና የመቅን ስንፈተ ስጋ ጠማቸው ህመምተኞች የሚከናወንና እጅግ ውስብስብ ቴክኖሎጂን የሚፈልግ ነው፡፡
መልካም ጊዜ፡፡
The post Health: ደም ማነስ! (የቀይ ደም ህዋሳት ለቅሶ) appeared first on Zehabesha Amharic.