የታቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆነው በፖለቲካ አቋማቸው ብቻ ሁለቱ ልጆቻቸው ያላንዳች ጥፋት እስርቤት መወርወራቸውን አይተው በቅርቡ ለኢትዮጵያ ህዝብ “ይግባኝ” ያሉት አቶ አስገደ ገ/ስላሴ ታመው ለህክምና አሜሪካ ገብተዋል።
አቶ አስገደ በአሁኑ ጊዜ በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል እየታከሙ ይገኛሉ። አሕፈሮም አስገደ የተባለው ልጃቸው ደግሞ መቀሌ በሚገኘው ቀዳማይ ወያኔ ፖሊስ ጣብያ ታስሮ ይገኛል። ወጣቱ አሕፈሮም “ዳኛው የሉም” እየተባለ የዋስ መብቱን አስጠብቆ ሊወጣ ባለመቻሉ እዛው ፖሊስ ጣቢያ እንደታሰረ 54 ቀናትን ቆጥሯል።
በእስር ቤት ሲማቅቅ ቆይቶ ያላንዳች ክስ የተለቀቀው የማነ አስገደ ደግሞ እስርቤት ባደረበት ህመም 22 ቀን ሆስፒታል ከተኛ በኋላ በአሁኑ ጊዜ በቤቱ የአልጋ ቁራኛ ሆኖ ይገኛል።
አቶ አስገደ ሆስፒታል መግባታቸውን ያወቁ ኢትዮጵያውያን ገሚሶቹ በአካል፣ ሌሎቹም በኢሜይልና በስልክ በጎ ምኞታቸውን እና የትግል አጋርነታቸውን ገልጸውላቸዋል።