Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ሃይለማርያም ደሳለኝ የመለስን ሌጋሲ ክደው ከባላንጣቸው ከአቶ አርከበ ጋር ሽር ጉድ ማለታቸው የት ያደርሳቸው ይሆን? (ሪፖርታዥ)

$
0
0

HaileMariam
ምርጫ እና ድርጅታዊ ጉባኤ -አሁን ያለው አመራር ይቀጥላል

አቶ መለስ ያለሰብሳቢ በትነዋቸው የሄዱትና በዓይነ ቁራኛ የሚጠበባቁት የኢህአዴግ ባለሥልጣናት የሚተማመኑበት ድርጅት ሳያውቁት ፈርሷልና መክቶ የሚያድናቸው አይመስልም። ለምሳሌ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲፈጠር ተቃዋሚዎቻቸውን ማራገፍ የሚችሉበት የፓርቲው መዋቅር አካል የሆነው አንዱ መሣሪያ ድርጅታዊ ጉባኤና ምርጫ ነው። በዚህ ወቅት መተማመን ስለጠፋና ከመበላላት መሰንበት ስለተመረጠ በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ድርጅታዊ ጉባኤያቸው ከምርጫው በኋላ እንዲደረግ ተወስኗል። ባለፈው ከተደረገው 9ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ በኋላ 10ኛው መደረግ የነበረበት ከምርጫው በፊት ነበር። አሁን ግን መች እንደሚደረግ የት እንደሚደረግ ሳይገለጽ በእንጥልጥል እንዲቀጥሉ ተደርጓል።

የኢህአዴግ ጉባኤ በየሁለት ዓመቱ ይደረጋል። ሁልጊዜ የሚደረገው ከምርጫው በፊት ነው። ድሮ ቢሆን አቶ መለስ ስላሉ በፊት ይሁን በኋላ ምንም ችግር አልነበረውም። ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆኑት እሳቸው መሆናቸው ግልጽ ነበረ። አሁን ግን የኢህአዴግ ጉባኤ ከምርጫው በኋላ መደረጉ ከወዲሁ የሚገልጸው ነገር አለ። ይሄ ማለት አሁን ያለው አመራር እንዳለ ይቀጥላል ማለት ነው። ኃ/ማርያም ባሉበት ይጸናሉ። በርግጥ ፓርቲው ከፈለገ በጉባኤው የድርጅቱን ሊቀመንበር መቀየር ይችላል። ለጠቅላይ ሚንስትርነት ግን የሚወሰነው በምርጫ ውጤት ላይ ተመርኩዞ ነው። ኃ/ማርያም ምናልባት የፓርቲው ሊቀመንበር ላይሆኑ ይችላሉ። ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ግን እሳቸው ሆነው የመቀጠላቸው ሁኔታ በግልጽ እየታየ ነው። አቶ ኃ/ማርያም (ወይም በሳቸው የተጠለሉት) አሁን ሊቀመበርነቱንም ጠቅላይ ሚኒስትርነቱንም ተጠቅመው እየሠሩ ነው።

ይህ ማለት ግን ሥልጣን ወደ ድርጅቱ ሊሄድ አይችልም ማለት አይደለም። ለምሳሌ በአቶ መለስ ጊዜ ከክፍፍሉ በፊት ድርጅቱን ይመሩ የነበሩት አቶ ተወልደ ነበሩ። መንግሥቱን መለስ፣ ድርጅቱን ተወልደ ሲመሩ ድርጅቱ ከፍተኛ ሥልጣን እንደነበረው ይታወቃል። ወደ ኋላው ላይ ግን በክፍፍሉ ጊዜ፣ ያ ችግር ማምጣቱን የተገነዘቡት አቶ መለስ፣ የድርጅቱን አቅም አሽመድምደው፣ የመንግሥቱን መዋቅር ለማጠናከር ሁለቱንም ጠቅልሎ መያዛቸው ይታወሳል። መለስ ያ አደጋ በትክክል ገብቶታቸው አስተካክለዋል። አሁን ግን ኃ/ማርያም መለስን አይደሉም። ስለዚህ ኃ/ ማርያምን ወይም በሳቸው የተጠለሉትን ለመካለከል የተገደበ ሥልጣን የመስጠት ሙከራ ሊኖር ይችላል።

ህወሓት ምን ያስባል?

አሁን ያሉት ህወሓቶች ምን እንደሚያስቡ ለማወቅ በዚያ ደረጃ ማሰብ የሚችል ሰው ከመካከላቸው አለ ብሎ ማመንን ይጠይቃል። አሁን ቀላል የሚሆነው አንድ ለናቱ ጭንቅላታቸው የሆኑት አቶ መለስ ዜናዊ ምን አስበው ነበር ማለቱ ይሻላል። ምክንያቱም አሁን ያለውን ህወሓት እንደገና ጠፍጥፈው የሠሩት እሳቸው ናቸው። ስለዚህ ስላሁኑ ህወሃቶች ስናወራ ስለ አቶ መለስ እያወራን መሆኑን እያሰብን ነው። ህወሓቶች አሁን ያላቸው ሥልጣን እንዳይጠፋ ይሰጋሉ። እንደ አስተሳሰባቸው በቁጥርም ጠባብ በመሆናቸው የባለብዙ ቁጥር ህዝብና ድርጅት ውክልና ሁሌም ያባንናቸዋል። ስለዚህ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ቦታ የሚሰጡት ሰው ከኦሮሞው ወይም ከአማራው እንዲሆን አይፈልጉም። ኦህዴድ ያው ኦነግነት አለበት ብለው ይጠረጥራሉ። አማራውም ላይ ግልጽ የሆነ የጥርጣሬና የጠላትነት ስሜት አላቸው። ሌሎቹም የድርጅት ቢሆኑ አንዳቸው ላንዳቸው ይጠባበቃሉ። ስለዚህ ማንም ሰው ከደቡብ የመጣ ሰው ላይ የጠነከረ ፍቅርም ሆነ የመረረ ጥላቻ እንደሌለው ያውቃሉ። ደቡብ የመገንጠል ጥያቄ የለውም። በኢትዮጵያዊነቱም ላይ ጥያቄ አያነሳም። በዚያ ላይ 53 የተለያዩ ብሔረሰቦች የሚኖሩበት ጥሩ የፌደራሊዝም አስኳል ነው። የክልሉ ቋንቋም አማርኛ ስለሆነ ጥሩ ነው። አቶ መለስ ይህን በማሰብ ነው ከደቡብ የተወሰኑ ሰዎች መርጠው ከዚያ ውስጥ ነው ኃ/ለማርያን ያሰለጠኑት። እንደሚባለው በሚኒስትርነት ሥልጣን አንድ አስር ሰዎች ከደቡብ ለአቶ መለስ ቀርበው ነበር። ከእነዚያ ውስጥ ነው ኃ/ማርያም የተመረጡት። ችሎታ ያለው ታማኝ የሆነ አምጡልኝና ላሰልጥን ብለው አሰልጠነዋቸዋል ይባላል። አቶ መለስ ከሥጣልን ወርደርው በኃ/ማርያም አማካይነት ሊመሩ ህልም ነበራቸው። ሞት ቀደማቸው። አቶ ኃ/ማርያምም መቸም ሰው ከሆኑ ያቺን ቂም ሳይቋጥሩ አይቀሩም። የመለስን ሌጋሲን ክደው ከባላንጣቸው ከአቶ አርከበ ጋር ሽር ጉድ ማለታቸው የት እንደሚያደርሳቸው ግን ይታያል።

ሁለተኛውን የትራንስፎርሜሽን እቅድ የመቅረጽ ሽኩቻ

በሚኒስትሮች ም/ቤት በኩል ያለው ዝግጅት የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ም/ቤት ከመነጋገሩ በፊት አስቀድሞ የተጀመረ ነው። ካለፈው ጁላይ 2013 ጀምሮ ዝግጅት ሲደረግበት እንደነበር ይታወቃል። ለምሳሌ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት በጁላይ 2013 ላይ ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፍሮሜሽን እቅድ እንዲቀርጽ መታዘዙ በወቅቱ ተዘግቧል።

ይሄ ማምን ማለት ነው?

አቶ መለስ ከሞቱ በኋላ ከአማካሪዎቻቸው ጋር ካቢኔያቸውን የመሰረቱት ወይም “የተመሠረተላቸው” ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ፣ ሹመት ከሰጧቸው ሰዎች መካከል አቶ መኮንን ማንያዘዋል ይገኙበታል። አቶ መኮንን በአቶ መለስ ጊዜ ለረዥም ዓመታት በከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ላይ ቆይተዋል። የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ሆነው ከማገልገላቸውም በላይ የመጀመሪያውን የልማትና ትራንስፎርሜሽን እቅድን ማሰናዳታቸው ተነግሯል። እንደ መለስ ራዕይ ተደርጎ የተገለጸው እቅድ እሳቸው ያዘጋጁት መሆኑ ነው። አቶ መኮንን በቀድሞ የደርግ መንግሥት አንስቶ በፕላን ጽ/ቤት….የቆየ የረጅም ጊዜ የሥራ ልምድ አላቸው። የገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ አባል ባለመሆናቸው ከፓርቲው ይልቅ ከመንግሥት አካላት ጋር ግንኙነታቸው የጠበቀ ነው። የድርጅት አባል ሳይሆኑ በሥልጣን ላይ ከቀሩት ጥቂት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል እንደ አቶ ተቀዳ ዓለሙ፣ ኃይሌ አሰግዴ ከመሳሰሉት ውስጥ አሁን ሥልጣን ላይ የሚገኙት እሳቸው ብቻ ናቸው። ሌሎቹ ከአቶ መለስ ሞት ጋር ሄደዋል። ስለሆነም አቶ መኮንን የፓርቲና የመንግሥት ሥልጣንን በማራራቅ የተካኑት አቶ መለስ ዜናዊ ካቀረቧቸው ሰዎች አንዱ ነበሩ። አሁንም በፓርቲውና በመንግሥት መካከል ልዩነት ፈጣሪ ሆኖ በተገኘው የልማትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ላይ ከፍተኛውን ድርሻ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ኃላፊነት ተመልሶ የተሰጣቸው ይመስላል። ከአቶ መለስ ሞት በኋላ አዲስ የተቋቋመው ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው እንዲሰሩ ተሹመዋል። ኮሚሽኑ ደግሞ ቀጣዩን የዕድትና ትራንስሮሜሽን እቅድን እንዲቀርጽ በጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት ታዟል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ለራሱ ተጠሪ የሆነ የፕላን ኮሚሽን እንዲያቋቋም መደረጉ በፖሊሲ አማካሪነት ኃ/ማርያምን የከበቧቸውን የአቶ መለስ ቱባ ቱባ ባለሥልጣናት ለመከላከል ይሆን የሚል ግምት ማሳደሩ አይቀርም። ምክንያቱም አማካሪዎቹ የፓርቲ እንጂ የመንግሥትነት ሥልጣን የላቸውም።

ለመሆኑ የ5 ዓመት የልማትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሀሳብ እንዴት መጣ?

የእቅዱ ሀሳብ ተጸንሶ የተወለደው በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ሲሆን ዘመኑ 2010 ነው። በ2010 የተደረገውን ምርጫ ማሸነፉን ከልቡ ያመነው ወይም በፈለገው ሁኔታ በመጠናቀቁ የተደሰተው ኢህዴግ መሪ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ያመጡት ሀሳብ ነው። አቶ መለስ የውስጥም ሆነ የውጭ ጠላቶቻቸውን ድል ነስተው ሲደላደሉ ካሁን በኋላ እዚህም እዚያም ቁጥ ቁጥ የሆነ ፕላን ሳይሆን ሁለገብና አብይ (ግራንድ) የሆነ ፕላን ያስፈልገናል ብለው ተነሱ። ለዚህም ኃላፊነት አቶ መኮንን ማን ያዘዋልንን መርጠው የአምስት ዓመት የልማትና የትራንስፎርሜሽን ፕላን እንዲዘጋጅ አዘዟቸው። አቶ መኮንን ቢሯቸውን ዘግተው ሶስት ወር ያህል ከቀመጡ በኋላ የአገሪቱ መነጋገሪያ የሆነውን ፕላን ይዘው ወጡ። አቶ መለስ ዜናዊ እሱን ተቀብለውና ቀባብተው የአገሪቱ ፕላን አድርገው በይፋ አወጁ። ባለ ራዕይ ያሰኛቸው ይህ ፕላን መሆኑ ይገመታል። መቸም የአቶ መኮንን ማንያዘዋል ራዕይ አይባልም።
አቶ መኮንን በቀድሞው የፕላንና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርና በኢኮኖሚ ልማትና ትብብር ሚኒስቴር በተለያዩ ኃላፊነቶችና በሚኒስቴር ዴኤታ ማዕረግ አገልግለዋል፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በዴቨሎፕመንት ማኔጅመንት ሲያገኙ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የተቀበሉት ደግሞ በዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ ነው፡፡

ስለትራንስፍሮሜሽኑ አወጣጥ ሌሎች ደግሞ የተለየ አመለካከት አላቸው። የአቶ ኤርምያስን አስተያየት ያንብቡት።

አሁን ታዲይ ሁለተኛውን ልማትና ትራንስፎርሜሽን ለመቅረጽ ምን እየተደረገ ነው?

አቶ ኃ/ርያም የተሰየሙበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ ቤት አቶ መኮንን ማንያዘዋልን ከሾመ በኋላ አዲስ የተቋቋመው ብሔራዊ የፕላን ኮሚሽን ራሱን በተቋም ደረጃ እንዲያዋቅር ተደርጓል። በተለይ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ እንዳለ ወደ ብሔራዊው ፕላን ኮሚሽን በመውሰድ በመደራጀት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መንደፍ መጀመሩም ተመልክቷል። እቅዱ ገና ሳይጠናቀቅ ግን በፓርቲው ባለሥልጣናት በኩል እክል የገጠመው መስሏል።

በፓርቲው ውስጥ ያሉት ሰዎች በመንግሥትነት ያስቀመጧቸው ጓዶቻቸው የሚወስኗቸው ውሳኔዎች ከፓርቲው መርህ ውጭ እየሆነ ነው በማለት ጭቅጭቅ ማሰማት ጀምረዋል። ፖሊሲውን ማን ይቅረጽ የሚል ጥያቄው የሥልጣን መገለጫ እየመሰለ ሲያነታርክም ሰንብቷል። ለዚህ ንትርክ እልባት ለመስጠት ይመስላል የሁለተኛውን የትንራንስፎርሜሽን እቅድ በሚመለከት መንግሥት ያቋቋመው የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን አልበቃ ብሎ ሌላ ተደራቢ ኮሚቴ መቋቋሙን ሰሞኑን ሰምተናል። ሪፖርተር ጋዜጣ ባለፈው ጃንዋሪ1 8/2015 እትሙ የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገውን ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በማዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ዘግቧል።

እንደጋዜጣው ዘገባ የአምስት ዓመቱ ዕቅድ በስምንት ዘርፎችና ኮሚቴዎች ተከፍሎ እየተዘጋጀ ነው። እቅዱ እንደ ቀድሞው በጠቅላይ ሚኒስትሩ (አቶ መለስ) ራዕይና ትእዛዝ ብቻ መቀረጹና መዘጋጀቱ ቀርቶ አሁን ሁሉም ባለስልጣናት የየራሳቸውን ራዕይ የሚያኖሩበት እየመሰለ ነው። በተቋም ደረጃ በብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን ደረጃ እንኳ እንዲዘጋጅ አልተፈለገም። በመሆኑም ፕላኑ በሚቀጥሉት ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሆኖ የኮሚቴ ሰብሳቢዎች ተመድበውለታል።

• የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮች፣ የዕቃዎችና የአገልግሎቶች ኤክስፖርት-የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን አህመድ
• የግብርናና የገጠር ትራንስፎርሜሽን- የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ በረከት ሰምዖን-
• የኢንዱስትሪ ልማትና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ- በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ
• ዘመናዊ የከተማ ልማትና የኮንስትራክሽን ዘርፍ አቅም ግንባታን- በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ዓባይ ፀሐዬ
• የሰው ሀብት ካፒታል ማሳደግና የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታን – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን
• ወሳኝ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና የማስፈጸም አቅም ግንባታ- በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል
* ልማታዊ መልካም አስተዳደር፣ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ከምንጩ በማድረቅ ተወዳዳሪነትን ማጎልበት – ወ/ሮ አስቴር ማሞ
ዴሞክራሲን ማስፈን፣ ብሔራዊ መግባባት መፍጠርና የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ሥራን የመተለከተ- አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ

በእነዚህ ኮሚቴዎች የታቀደው አገራዊ ዕቅድ ውይይት ከተደረገበት በኋላ አገሪቱ ለአምስት ዓመታት የምትመራበት ብሔራዊ ሰነድ እንደሚሆን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከሁለተኛው የልማትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ የሚጠበቀው ምንድነው?

-የአቶ መለስ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የታሰበውን መዋቅራዊ ለውጥ አላማምጣቱ በግልጽ እየተነገረ መሆኑ ይታወቃል። ሪፖተር ቀደም ሲል ስለ እቅዱ አፈጻጸም ጥናት ያደረጉና በጉዳዩ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊና አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ጋር ጭምር የተወያዩና በአማካሪነት የሠሩ ሁለት ጃፓናዊ ባለሙያዎችን ፕሮፌሰር ኪኒቺ ኦህኖ እና ፕሮፌሰር ኢዙሚ ኦህኖን ጠቅሶ እንደዘገበው በትራንስፎርሜሽኑ ይፋ የተደረገው የኢንዱስትሪ ፖሊሲ የሚፈለገውን ለውጥ አላመጣም። ለኢንዱስትሪ የሚመች ምንም መዋቅር ቀድሞ ባለመዘርጋቱ ነው። ዕቅዶቹን ሊያስተገበሩ የሚችሉ ተቋማትና ባለሙያዎች በሚያስፈልገው መጠን አልተሟሉም። በወዲህም በኩል ብቁ የሆኑ ኢንዱስትሪዎች ባለመኖራቸው የታቀዱት የወጪ ንግድ ግቦች አልተሳኩም።
መንግሥት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ለውጥ ይመጣል ብሎ ተስፋ ካደረገባቸው መካከል ትልልቅ የውጭ ኩባንያዎች መምጣታቸው ዋናው ነው፡፡ የቻይና፣ የህንድ፣ የቱርክና የኮሪያ አምራቾችን ጨምሮ ከቅርብ ጊዜ በኋላ የጃፓን ትልልቅ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ኢንቨስት ሊያደርጉ ማሰባቸው ለለውጡ ታሳቢ የተደረጉ ተስፋዎች ናቸው፡፡

ያለፈው እቅድ ተሳክቷል?

አቶ መለስ የአገሪቱን አጠቃላይ ገቢ በእጥፍ እናሳድጋለን ብለው ነበር። አልተሳካም። ያኔ 37 ቢሊዮን አካባቢ ነበር አሁን 40 ቢሊዮን ነው- አላጠፈም።
እንደ ኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የአዲስ ዓመት ንግግር ከሆነ አልተሳካም። ፕሬዚዳንቱ በሰፕቴምበር 2014 በአራተኛው የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አምስተኛ የሥራ ዘመን የመጀመሪያ የጋራ ስብሰባ ላይ ያደረጉት የመክፈቻ ንግግር ይህን አያረጋግጥም። የ እቅዱ መለያ ባህርያት ተደርገው ከተወሰዱት ግዙፍ ሜጋ ፕሮጀከቶች መካከል ብቸኛው ተቀዋሚ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት (ፓርላማ) አባል ግርማ ሰይፉ ይህንን የ እቅዱን አለመሳካት ለፓርላማው አባላት የደረሰውን ሪፖርት አጣቅሰው ጽፈዋል። የጽሑፋቸው ፍሬ ነገር የአምስት ዓመቱን የልማትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ያወጣው ኢህ አዴግ እቅዱን ማሳካት አልቻለም። ምክንያቱም ራሱ ያወጣውን እቅድ እንኳ ማሳካት የሚችል ድርጅት አይደለም በማለት የእቅዱን ውጤት አብጠልጥለውታል።

የእቅዱን ዋና ዋና ትልሞች ለምሳሌ የአስፋልት መንገድ ሳይጨምር የገጠር ቀበሌዎችን ከዋና መንገድ ጋር የሚያገናኙ ከ71 ሺ ኪሎ ሜትር ክረምት ከበጋ የሚያገለግሉ መንገዶች ግንባታ አለመሳካቱን፣ 10 ሺ ሜጋ ዋት የሚደርስ የኢነርጂ ልማት ተግባራዊ አለመደረጉን፣ በማዳበሪያ ምርት ከፊል የሀገር ውስጥ ፍጆታን ይሸፈናል የተባለው አለመፈጸሙን ወዘተ እየጠቀሱ ነቅፈዋል። የ እቅዱ ዋነኛ ማጠንጠኛ የሆነው የኢንደስትሪ ሴክተሩንም አንስተው “የማኑፋክቸሪንግ ሴክተሩ የተጣለወን ሃያ በመቶ እድገት ለማሳካት የሚያስችል የግል ሴክተር ተነሳሽነት አይታይም፤ ቢመጣም ማነቆ ብዙ ነው፡፡” ብለዋል።

ይህ ጽሑፍ በዘ-ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ ታትሞ ወጥቷል:: ርዕሱን ግን ለድረገጽ አንባቢዎች በሚስማማ መልኩ ቀይረነዋል::

The post ሃይለማርያም ደሳለኝ የመለስን ሌጋሲ ክደው ከባላንጣቸው ከአቶ አርከበ ጋር ሽር ጉድ ማለታቸው የት ያደርሳቸው ይሆን? (ሪፖርታዥ) appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>