[Updated](ዘ-ሐበሻ) የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የሃሰት ዲግሪዎችን ከአሜሪካና አውሮፓ እንዲሁም ከቻይና እየገዙ እንደሚጠቀሙ በተደጋጋሚ እየተጋለጠ መሆኑ የሚታወስ ነው;; አበበ ገላው የዛሬ አንድ ወር ገደማ የዶ/ር ኮንተንጢኖስ በርሀን የሃሰት ዲግሪዎችን ያጋለጠ ሲሆን አሁን ተረኛው አባዱላ ገመዳ ናቸው ብሏል::
“ክቡር አፈጉባኤ አባዱላ ገመዳ አሜሪካ ሴንቸሪ ከሚባል የዲግሪ ወፍጮ ቤት የሃሰት ዲግሪዎች ገዝተው ጥቅም ላይ ማዋላቸው ተረጋገጠ” ሲል በፌስቡክ ገጹ ያስታወቀው አበበ ገላው ማስረጃዎቹን ዛሬ ለቋል::
አባ ዱላ ገመዳ የባችለር ዲግሪያቸውን እና የማስተር ኦፍ አርት ዲግሪያቸው ከአሜሪካው ሴንቸሪ ኮሌጅ በ2001 እና በ204 የገዙ ሲሆን ከ እንግሊዙ ግሪንዊች ዩኒቨርሲቲም ማስተር ዲግሪያቸውን እንዳገኙ ታውቋል::
አባዱላ በውሸት ዲግሪዎች የ80 ሚሊዮኑን የውሸት ፓርላማ ቁጭ ብለው ይመራሉ:: የኦሮሚያን መሬቶች ቸብችበዋል እየተባሉ የሚወገዙት እኚሁ ባለስልጣን በሃብት ደረጃም የሚወዳደራቸው ባለስልጣናት የሕወሓት ሰዎች ብቻ መሆናቸው ይነገራል::
የአበበ ገላው ምስጢራዊ የምርመራ ዘገባ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ
(አዲስ ቮይስ) የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ የሆኑት አባዱላ ገመዳ በኢንተርኔት ያለምንም ትምህርት ዲግሪ በመሸጥ ከሚታወቅ አንድ የዲፕሎማ ወፍጮ ቤት (diploma mill) የሃሰት ዲግሪዎችን ገዝተው መጠቀማቸውን አዲስ ቮይስ አረጋገጠ።
አፈጉባኤው የባችለርስ ዲግሪ እ.ኤ.ኤ በ2001 እንዲሁም የማስተርስ ዲግሪ በ2004 አሜሪካን አገር በሚኖረውና አሊ ሚርዛኢ በሚባል ኢራናዊ ከሚንቀሳቀሰው “አሜሪካን ሴንቸሪ ዩኒቨርሲቲ” (ሴንቸሪ ዩኒቨርሲቲ) ያለምንም ትምህርት መግዛታቸው በመረጃ ተረጋግጧል። አባዱላ ሁለቱንም ዲግሪዎች የህዝብ አስተዳደር ትምህርት ተምረው አንዳገኟቸው ሲገልጹ የቆዩ ሲሆን ይህንንም በፓርላማ ድረገጽ፣በፌስቡክ፣ ዊኪፔድያ፣ በመንግስትና በግል የመገናኛ ተቋማት በይፋ ታትሞ እንዲሰራጭ አድርገዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከቻይና መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በወታደራዊ አመራር የባችለርስ ዲግሪ እንዳገኙ በህይወት ታሪካቸው ላይ በይፋ ያሰፈሩት አባዱላ እንዲህ አይነት ዲግሪም ይሁን ትምህርት ከቻይና የትምህርት ተቋም አለማግኘታቸው ታውቋል።
ሴንቸሪ ዩኒቨርሲቲ ከማንም እውቅና ያልተሰጠው ሲሆን አሊ ሚርዛኢ በዋነኛነት ከቤቱ የዲግሪ ሽያጭ እንደሚያከናውን አዲስ ቮይስ በምርመራው ከማረጋገጡም በላይ ምርመራውን ደንበኛ መስሎ ላካሄደው ጋዜጠኛ አበበ ገላው የማስተርስና የዶክትሬት ዲግሪዎችን በ4000 ዶላር ሊሸጥለት ሞክሯል። ይህንንም ህገወጥ የዲግሪ ሽያጭ የሚያረጋግጡ በርካታ የኢሜይልና የሰነድ መረጃዎች ጋዜጠኛው እጅ ገብተዋል።
ከሁለት ሳምንታት በፊት የህወሃቶች ቁንጮ ምሁራን ተደርገው ይቆጠሩ ከነበሩት አንዱ ቆንስጣንጢኖስ በርሄ የማስተርስና የዶክትሬት ዲግሪ ከሴንቸሪ ዩኒቨርሲቲ ገዝተው እራሳቸው በዶክተርነትና በፕሮፌሰርነት መሾማቸው መጋለጡ ይታወሳል። በኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ የሃሰት ዲግሪና ሰርተፍኬት ተጠቅሞ ለራስም ሆነ ለሌሎች ጥቅም ማግኘትና ማስገኘት በማጭበርበር ወንጀል የሚያስከስ ስና እስከ አንድ አመት እስር የሚያሰቀጣ ድርጊት ነው።
የሴንቸሪ ዩኒቨርሲቲ ባለቤት ከዚህ በፊት የማጭበርበር ወንጀል ሲፈጽም ተደርሶበት በባለቤትነት ሲመራው የነበረው የሃዋይ ቢዝነስ ኮሌጅን እኤአ 2007 እንዲዘጋ ተደርጓል።
በኢፌዲሪ ህገ መንግስት መሰረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛው የስልጣን አካል ሲሆን አፈጉባኤው ዋነኛው ህግ አውጭ ተደርጎ ይቆጠራል። የዛሬ አራት አመት አፈጉባኤ ሆነው የተሾሙት አባዱላ ገመዳ (ሚናሴ ወደጊዮርጊስ) ትምርታቸው ከ8ኛ ክፍል አቋርጠው የደርግ ወታደር ሆነው የነበር ሲሆን በኤርትራ በሻቢያ ተማርከው የነበረ ሲሆን በህወሃትና በሻቢያ መካከል በተደረገ ስምምነት መሰረት ከእነ አቶ ኩማ ደመቅሳ (ታዬ ተክለሃይማኖት) ጋር ለህወሃቶች ተላልፈው ከተሰጡ በሁዋላ የኦህዴድ መሪና መስራች እንዲሆኑ ተደርጓል።
የእነ አባዱላን ዲርጊት አሳፋሪ ሲሉ የገለጹት እውቁ ጋናዊው ምሁር ፕሮፌሰር ጆርጅ አይቴ እንዲህ አይነት እርካሽ የማጭበርበርና የማስመሰል ድርጊት የስርአቱን ንቅዘት ፍንትው አድርጎ አንደሚያሳይ ገልጸዋል። ፕሮፈሰሩ ተጠያቂነት የሌለው ህገውጥነት የአንባገነኖች ባህሪ መሆኑን አስገንዝበው አጭበርባሪ የስልጣን ጥመኞች ለውጥ ፈላጊ በሆነው አዲስ ትውልድ መተካት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል። አይቴ አገር ለመምራት የምያስፈልገው እውቀት እንጂ ዲግሪ አይደለም ብለዋል። “ዲግሪ መግዛት ይቻላል፣ እውቀት ግን ፈጽሞ አይገዛም” በማለት የእነ አባዱላን ድካም ከንቱነት ጠቁመዋል።
የቀድሞው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስቴር ዴታ የነበረው ኤርምያስ ለገሰ በበኩሉ አባዱላ በራስ መተማመን የሌለው የሃሰት ስብእና በህወሃቾች የተፈጠረለት ግለሰብ በመሆኑ ያንን በዲግሪ ጋጋታ ለመሸፈን የሚያደርገው ጥረት አካል ሊሆን እንደሚችል ግምቱን ሰንዝሯል።
በርካታ ዜጎች ያለምንም ወንጀልና ጥፋት ለበርካታ አመታት ያለፍርድ በእስር በሚሰቃዩባት ኢትዮጵያ እነ አባዱላ በሃሰት ዲግሪ አገር ሲመሩ ማየት ህዝቡን የበለጠ ለለውጥ ሊያነሳስው ይገባል ሲል አስተያተቱ ሰጥቷል።
—-
ተያያዥ መረጃዎች:
Abadula Gemeda’s official biography on Ethiopia’s parliament website (screenshot)
http://addisvoice.com/wp-content/uploads/2015/02/Abadula-Gemeda-par.pdf
House of People Representative: Abadula biography
http://www.hopr.gov.et/web/guest/higherofficial
Ethiopia: Abadula Gemeda, Speaker of the Parliament (Addis Fortune)
http://allafrica.com/stories/201309161711.html
Facebook official page: Honorable Abbaaduula Gammadaa
http://addisvoice.com/wp-content/uploads/2015/02/Abadula-facebook-official.pdf
The post አበበ ገላው በአባዱላ ገመዳ 2 የውሸት ዲግሪዎች ግዢ ዙሪያ ማስረጃዎችን ለቀቀ appeared first on Zehabesha Amharic.