Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Sport: የዢሩ ‹‹ኑዛዜ››

$
0
0

የኦሊቪዮ ዢሩ ግምገማ ግልፅነት ይታይበታል፡፡ ከስቶክ ሲቲ ጋር ሲጫወቱ የፈፀሙትን ስህተት ለመናገር አላመነታም፡፡ የጨዋታውን እንቅስቃሴ በቪዲዮ ደግሞ ከተመለከተ በኋላ ማመንታት አላስፈለገውም፡፡ ‹‹ተሰጥኦ በቂ አይደለም፡፡ ተወዳዳሪ መሆን ያስፈልጋል፡፡ በዕለቱ የቁርጠኝነት ችግር ነበረብን፡፡ ስህተቶችን ስንፈፅም የነበረው እንደ ወጣት ተጨዋቾች ነው፡፡ ያንን በደንብ ተመልክተናል፡፡ መፈፀምም አይገባንም፡፡ ጠንካራ መሆናችንን እናውቃለን፡፡ ጥሩ ስብስብ አለን፡፡ ነገር ግን አልፎ አልፎ የቁርጠኝነት ችግር ይከሰታል፡፡ 100% ለጨዋታ ብቁ ሳትሆን የምትጫወትባቸው ጊዜያትም አሉ›› ፈረንሳዊው አጥቂ ሃሳቡን ማካፈል የሚጀምረው ይህን በመሰለው አስተያት ነው፡፡
Oliver Arsenal
የተሸነፈው ቡድን አካል የነበረው ተጨዋች የሰጠው መደምደሚያ ጥሩ መሰረት ያለው ነው፡፡ በሜዳ ውስጥ የነበረው መንትያ ወንድሜ ነው ሲልም ይቀልዳል፡፡ ከዚያን ዕለቱ ጨዋታ በኋላ ቡድኑ ጋላታሳራይን 4-1 አሸንፏል፡፡ የቼልሲን ያለመሸነፍ ጉዞ መቋጫ ያበጀለትን ኒውካስል ዩናይትድን ረትቷል፡፡

ነገር ግን የስቶኩ ሽንፈት ደስ የማይሉ ትዝታዎችን ጥሎ አልፏል፡፡ ተጨዋቾች ወደ ለንሰን ለመመለስ ባቡር በሚሳፈሩበት ወቅት በገዛ ደጋፊዎቻቸው ተጮሆባቸዋል፡፡ አርሰን ቬንገርም ከጥቃት አላመለጡም፡፡ እንዲያውም አጋጣሚው እጅግ የከፋ ስለነበር ብዙዎችን አስደንግጧል፡፡ ጋሪ ሲኒከር ‹‹አሳፋሪ እና ክብረ ነክ›› ሲል ድርጊቱን አውግዞታል፡፡

‹‹ሰዎቹን ሰምተናቸዋለ፡፡ የአርሰናል ደጋፊ እንደሆኑ የሚታሰቡ ሰዎች ተችተውናል፡፡ በተለይ አሰልጣኙን አንጓጠዋል›› ይላል ዤሩ፡፡ አባባሉ በአርሰን ቬንገር ላይ ያንን መሰል ያልተገባ ጥቃት  የሰነዘሩት ቡድናቸውን ለመደገፍ ከተጓዙ ደጋፊዎች መካከል አነስተኛ ድርሻ የሚይዙ መሆናቸውን ይጠቁማል፡፡ ‹‹አሳዛኝ ነበር፡፡ ያንን መሰሉ ውርጅብኝ ለእርሱ ይገባዋል ብዬ አላስብም፡፡ ጨዋታዎችን ስትሸነፍ እንዲህ ያለው ነገር ያጋጥማል፡፡ በእርግጥ እራስህን መፈተሽ ይጠበቅብሃል፡፡ ነገር ግን ሁሉንም ነገር መቀየር አለባችሁ አይባልም፡፡ እንዲህ አይነቱን አጋጣሚ እንዴት መቋቋም እንዳለበት የሚያውቅ ሰው በመሆኑ እኛን ብዙ አያስጨንቀንም››

ዢሩ የደጋፊዎቹን ቁጣ ይረዳል፡፡ ‹‹ያንን የሚያደርጉት ጨዋታዎችን እንድናሸንፍ ነው፡፡ የምንጫወተው ለአርሰናል ነው፡፡ ቡድኑ ትልቅ ነው፡፡ ደጋፊዎች ብዙ ይጠብቃሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በውጤቱ እንደተከፉ እንገነዘባለን፡፡ ጥንካሬያችንን እና አፀፋችንን ለማሳየት የምንፈልገው ለዚያ ነው››

ያም ቢሆን ደጋፊዎቹ ቬንገር ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ በእጃዙር ቡድኑን እንደሚጎዱ ያምናል፡፡ ‹‹በሜዳ ውስጥ አንድነታችንን እና ጥንካሬያችንን እናሳያለን፡፡ በህብረት ለመፋለም ተጨማሪ ጉልበት ይሆነናል፡፡ እኛ ቡድን ነን፡፡ ከመካከላችን በአንዱ ላይ ጥቃት ቢሰነዘር ሁሉም የቡድኑ አባላት በጋረ በመሆን ይከላከላሉ፡፡ ይህ አሰልጣኙንም ይጨምራል፡፡ በስቶክ ያጋጠመን መጥፎ አጋጣሚ ነው፡፡ በተቻለን ፍጥነት ወደ ጥሩ አቋማችን እንመለሳለን›› ሲል የመድፈኞቹ አጥቂ ለአሰልጣኙ ጥብቅና ይቆማል፡፡ በቻምፒዮንስ ሊጉ ተሳታፊ የሚያደርጋቸውን ደረጃ ይዘው ለማጠናቀቅ እንደሚጥሩም ይጠቁማል፡፡

በአርሰናል ያሉ ተጨዋቾች በሙሉ የቬንገር ውለታ አለባቸው፡፡ ከፊሎቹን ከሌሎች ክለቦች አዘዋውረዋቸዋል፡፡ የተወሰኑትን ከታችኛው ቡድን አሳድገው የመሰለፍ ዕድል ሰጥተዋቸዋል፡፡ በመሆኑም ከቬንገር ጎን የማይቆም የለም፡፡ ነገር ግን ዢሩ የተጨዋቾቹ ታማኝነት ምንጭ ከዚያም በላይ ስር የሰደደ ምክንያት እንዳለው ይናገራል፡፡ ‹‹ለእኔ መልካም የሚሆነው ስላስፈረመኝ ብቻ አይደለም፡፡ በጥሩ ሁኔታ ስጫወት ያሞግሰኛል፡፡ በመጥፎ ሁኔታ ስንቀሳቀስ ጉድለቴን ይጥቁመኛል፡፡ እርሱ ስላስፈረመኝ  ብቻ የተለየ እንክብካቤ አያደርግልኝም››

ዢሩ ተስፋ አልቆረጠም፡፡ በውድድሩ ረዥም ርቀት መጓዝ እንደሚችሉ ያምናል፡፡ ነገር ግን የአርሰናል ደጋፊዎች እና የውጪ ታዛቢዎች ይህንን ሁሉ ጉድለቶች ይዞ እና ገና ከአሁኑ ከመሪው ቼልሲ በ13 ነጥብ ርቆ ፕሪሚየር ሊጉን ማሸነፍ መቻሉን ይጠራጠራሉ፡፡

‹‹አልረፈደም፡፡ የውድድር ዘመኑ ገና አልተጋመሰም፡፡ በእርግጥ የቼልሲ አጀማመር ድንቅ ነው፡፡ ማንቸስተር ሲቲም ጥሩ ጊዜያት አሳልፏል፡፡ ነገር ግን ረዥም ጉዞ ይቀራል፡፡  የተወሰኑ መሻሻሎችን ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ለጨዋታዎች ሙሉ ትኩረት መስጠት ያስፈልገናል፡፡ በቀጣዮቹ ጨዋታዎች ይህንን ማድረጋችንን ከቀጠለን ከመሪዎቹ ተርታ መሰለፍ እንችላለን፡፡ እኔ ቡድኑን ከተቀላቀልኩ ወዲህ ባለፉት ሁለት እና ሶት ዓመታት ምርጦቹን ተጨዋቾቻችንን በቡድኑ ውስጥ ማቆየት ችለናል፡፡ ሆኖም ደጋፊዎች ሌሎች ታላላቅ ተጨዋቾች ቡድኑን እንዲቀላቀሉ ፈለጉ፡፡ አሰልጣኙም ሃሳባቸውን አደመጠ፡፡ ሜሱት ኦዚል፣ አሌክሲስ ሳንቼዝ እና ሌሎች ተጨዋቾችን ወደ ቡድኑ ቀላቀለ፡፡ በብቃታችን ጫፍ ላይ መድረስ እንፈልጋለን፡፡ ተጨማሪ ዋንጫዎችንም ማንሳት እንሻለን፡፡

‹‹የባለፈው ዓመቱ የኤፍኤካፕ ድል የአስደናቂው ታሪክ መጀመሪያ ነው፡፡ ታላቅ ቡድን ለመገንባት ጊዜ ያስፈልገናል፡፡ በስኳዱ ውስጥ ድንቅ ብቃት ያላቸው በቂ ተጨዋቾች አሉ፡፡ ወደ ቀድሞ ብቃታችን መመለስ መቻላችን የሚያስጨንቀን ለዚያ ነው›› በማለት የቀድሞው የሞንፒዬሌ ተጨዋች ልበ ሙሉነቱን ይገልጻል፡፡

ዢሩ ከዚህ ቀደም ወደ ጎን የተገፋበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ተስፋ ተጥሎበት እየተወደሰ ያደገ ተጨዋች አይደለም፡፡ በፈረንሳይ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ይጫወት ለነበረው ግሬኖብል እንደማይመጥን ተነግሮት ወደ ኤስትሬስ እና ቱርስ በውሰት ተሰጥቶ ነበር፡፡ ሁለቱም ክለቦች የታችኛው ሊግ ቡድኖች ናቸው፡፡ በግሬኖብል አሰልጣኙ የነበሩት መሐመድ ቤዝዳሬቪች በአንድ ወቅት ዢሩ በከፍተኛ ደረጃ ለመጫወት የማይመጥን አጥቂ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡ እርሳቸው ከፍተኛ ብለው የገለፁት የፈረንሳይን ሁለተኛ የሊግ እርከን መሆኑን ልብ በሉ፡፡

ተጨዋቹ አርሰናልን የተቀላቀለው ከሞንፔሲዮ ጋር የፈረንሳይ ሊግ ሻምፒዮን ከሆነ በኋላ ነው፡፡ ከመድፈኞቹ ጋር የኤፍ.ኤ ካፕ ዋንጫን አነሳ፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን 23 ጎሎችን አስቆጠረ፡፡ በዓለም ዋንጫው እንደ ጎል በስሙ አስመዝገበ፡፡ እነዚህ ስኬቶቹ የቀድሞውን አሰልጣኙን አስተያየት ስህተት መሆን ጠቋሚዎች ናቸው፡፡ የቤዝዳሬቪችን አስተያየት ሲያስታውሱት ይስቃል፡፡ ‹‹የበለጠ የመጫወቻ ጊዜ ማግኘት ስለፈለግኩ ግሬኖብልን ለመልቀቅ ወሰንኩ፡፡ በውሳኔዬ ትንሽ ተበሳጭቶ ስለነበር መልቀቅ ፈለግኩ፡፡ ችግር የለውም ሂድ፡፡ ነገር ግን በፈረንሳይ ሊግ 1 ቀርቶ በሁለተኛው ዲቪዥን እንኳን የሚያቅፍህ ብቃት እንደሌለህ ልታወቅ ይገባል አለኝ፡፡ ሆኖም ወጣት እንደመሆኔ በሜዳ ውስጥ የማሳልፈው ጊዜ ፈለግኩ፡፡ በመሆኑም ክለቡን ለመልቀቅ ወሰንኩ፡፡ ከሞንፔሊዬ ጋር ሊጉን ሳሸንፍ እርሱ የሶቮ አሰልጣኝ ነበር፡፡ ከእርሱ ቡድን ጋር ያደረግነውን ጨዋታ 3-1 አሸነፍን፡፡

ሶስቱንም ጎሎች ያስቆጠርኩት እኔ ነኝ፡፡ ከጨዋታው በፊት ሰላም ብዬዋለሁ፡፡ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ግን ላገኘው አልቻልኩም፡፡ እንደዚህ ያሉ አጋጣሚዎች ያነቃቁሃል፡፡ ሜዳ ውስጥ ጠንካራ የአእምሮ ዝግጅት እንዳለህ ማስመስከር አለብህ›› በማለት አጋጣሚውን መለስ ብሎ ያስታውሳል፡፡

አሁን ላይ ፈረንሳዊው አጥቂ በቋሚነት ለመሰለፍ ከአሌክሲስ ሳንቼዝ እና ዳኒ ዌልቤክ ጋር ብርቱ ፉክክር ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ እርሱም ቢሆን ዝግጁ ነው፡፡ ሁለቱም ተጨዋቾች የአርሰናልን የአጥቂ መስመር የተቀላቀሉት ባለፈው ክረምት ነው፡፡ ዢሩ ያለፉትን ሶስት ወራት በጉዳት ከሜዳ ርቆ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ደግሞ ሳንቼዝ እና ዌልቤክ በእርሱ እግር ተተክተው ድንቅ ብቃት አሳይተዋል፡፡ ፈተናውን ያከብዱበታል ተብሎ የተሰጋው ለዚያ ነው፡፡ የተጫወቹ ምላሽ ግን ፍፁም የተለየ ነው፡፡ ‹‹መሰለፍ አለመሰለፌ አያስጨንቀኝም፡፡ ዋናው ነገር የእኔ ቦታ አይደለም፡፡ ወሳኙ እያንዳንዱ ተጨዋች ለቡድኑ የሚሰጠው ግልጋሎት ነው፡፡ በጥሩ ብቃት ላይ ከሆንኩ እጫወታለሁ፡፡ ለዚህ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ችግሮች ሲኖሩብኝ ደግሞ ወደ ተጠባባቂ ወንበር እወርዳለሁ፡፡ ወሳኙ ለቡድኑ የምትሰጠው ነገር ነው፡፡ እንደምንደጋገፍ አስባለሁ፡፡ በዚህ የውድድር ዘመን የተሻለ ነገር እናሳያለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ችግሮቻችንን በጋራ በመቆም መጋፈጥ ይኖርብናል፡፡››

ዢሩ ያደገው በግሬኖብል አቅራቢያ ነው፡፡ ይህንን ቃለ መጠይቅ በሚሰጥበት ቀን የተማሪነት ጊዜውን የሚያስታውሰው አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ከኤምሬትስ ስታዲየም ብዙም በማይርቅ ስፍራ ላይ በሚገኘው ሴንት ማርክ ትምህርት ቤት ልምምድ በመስራት ላይ የነበሩ ተማሪዎችን ዢሩ ተቀላቀላቸው፡፡ አጋጣሚው የአርሰናል ፋወንዴሽን እያከናወነ ያለውን ስራ ጠቋሚ ነው፡፡ በትምህርት ቤቱ የሚገኘው የ3G  የእግርኳስ መጫወቻ ሜዳ በክለቡ በከፊል ከሚደጉሙ 13 ተቋሞች መካከል አንዱ ነው፡፡ ፈረንሳዊው አጥቂ ከታዳጊዎቹ ጋር ያሳለፈውን ጊዜ የወደደው ይመስላል፡፡ ያለበትን አካባቢ እንደወደደውም ፍንጭ ይሰጣል፡፡

‹‹ተማሪ ሳለሁ ይህንን በመሰለ ሜዳ አልተጫወትኩም፡፡ ያደግነው በአሸዋ ላይ እየተጨዋወትን ነው›› ይላል ዢሩ፡፡ በዚያን ወቅት የማርሴይ ደጋፊ ነበር፡፡ ነገር ግን ዕድሜው 10 ሲደርስ እርሱ እና የክፍል ጓደኞቹ ለሰሜን ለንደኑ ክለብ ፍቅር ማሳየት ጀመሩ፡፡ ‹‹በፕሪሚየር ሊጉ የምወደድደው ቡድን አርሰናል ነበር›› ሲል ቬንገር የተሾመበትን መንገድ እና ኢማኑኤል  ፐቲ እና ፓትሪክ ቪዬራ ፈጥረውት የነበረውን ጥምረት በማስታወስ ዢሩ ምላሽ ይሰጣል፡፡ ‹‹ታዳጊ ሳለሁ በአርሰናል ያሉ ፈረንሳውያንን እመለከት ነበር፡፡ አርሰናልን መቀላቀሌ ትልቅ ስሜት የፈጠረብኝ ለዚያ ነው፡፡ በፈረንሳይ የአሰልጣኙ ገድል ትልቅ ክብር ይሰጠዋል፡፡ ለአርሰናል መፈረም ምን ያህል ተጨዋቾችን እንደሚያሻሽልም ተመልክቼያለሁ››

አንዳንድ ጊዜ ቬንገር ምን ያህል የተከበሩ እንደሆኑ ይዘነጋል፡፡ ነገር ግን ሥራቸው ዘብ ቆሞ ይከራከርላቸዋል፡፡

The post Sport: የዢሩ ‹‹ኑዛዜ›› appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>