Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የተውኔት አውራ –የሀገር ባንዴራ።

$
0
0

ከሥርጉተ ሥላሴ 16.01.2015 /ሲዊዘርላንድ ዙሪክ/

„ወደ ትዕቢተኛና ወደ ሐሰተኛ ሰው ያልተመለከተ ሰው ምስጉን ነው።“
/ መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 40 ቁጥር 4/

እንደ እርእሱ ነው ተፈጥሮው። እንደ እርእሱ ነው ጸጋው። ውድ በጣም ውድ ነው ለሥነ ጥበብ ነፍስ። ክብር ልዩ ክብር ነው – ለታሪክ። ፍቅር ልዩ ፍቅር ነው – ለትውፊት። ጌጥ ልዩ ጌጥ ነው – ለትውልድ። ሩህ ነው ለጥበብ ዓውደ ምህረት – ለመድረክ። የታሪክ ዝማሬ ነው – ለመድረክ ድባብ። – አዛውንቱ የተግባር – ጋሼ ደበበ እሸቱ።
ግን እንሆ እንዲህ ሆነ ————በጦሮ።

ዘመኑ በካቴና፤ ምስጋናው – በእግር ብረት፤ ክብሩ – በስጋት፤ ዬጌጥነቱን – መንፈስ በምስማር – በችካል በመብሳት፤ ውለታው – በግዞት ተወራራደ በዘመነ እሾኽ – በወያኔ።

ታላቁ አርቲስት ጋሼ ደበበ እሸቱ መክሊቱ ቀንድ፤ ቀንድነቱ ደግሞ የአህጉር ሆኖ ሳለ እንደ ትቢያ ታይቶ በትዕቢት – ደቀቀ። ብቃቱ የሰማይ፤ ሥጦታው የመዳህኒተአለም ሆነ ግን በወያኔ አቧራ ለበሰ።

ውሰጡ ሻማ፤ ስጦታው የዘለዓለም – ማሾ፤ ህሊናው እራስ እግሩ ፍሬ ሆኖ፤ ነገር ግን በደፋሩ ወያኔ ታምሩ በዱላ ተቀጠቀጠ። ጋሼ ጸጋዬ የተውኔት አውራ ብቻ አልነበረም – የዘመንም እንጂ። ጋሼ ደበበ አውራነቱ ለሥነ ጥበብ ብቻ ሳይሆን ለሰብዕዊ መብት መከበርም ጭምር አንጂ። የሰብዕዊ መብት ተሟጋችነት ጸጋው በቁሙ ጻድቅ ነው። መከራን ለብዙኃን ፍቅር ሲል ፈቅዶ አብዝቶ የተቀበለ።
„የዕውቀት ከንፈር ግን የከበረች ናት“ / ምሳሌ ምዕራፍ 20 ቁጥር 15/ የሰብዕዊ መብት ተሟጋቹ ሞገዳማ ድምጹ የምህረት መሰላል ነበር። ያ ውስጥን ዳሳሽ ድምጹ የብሥራት ነጋሪ ነበር። ተናፋቂው ድምጹ የፈውስ ደወል ነበር። የማይጠገበው ድምጹ የምሽት ማህሌት ነበር። ድምጹ ከጸጋው ጋር ለኢትዮጵያ የኤዶም ሽልማት ነበር። ጋሼ ደበበና መድረክ፤ መድረክና ጋሼ ደበበ ደግሞ ሌሊኛ የቅኔ ግጥሞች – የመንፈስ ልዑቅ ቋንቋዎች ነበሩ። ለመደረክ ጋሼ ደበበ – ጋሼ ደበበን ደግሞ ለመደረክ ፈጣሪ መርቆና ቀድሶ ፈጣራቸው – ግን በፋሽስት ወያኔ የሰማይ ስጦታ ዕሴት አልባ ሆኖ እንሆ ጨለማ ተገመደለበት።
አዲስ አበባ ውስጥ ሰፊ ዬአማተር ከያንያን ክበቦች ነበሩ። እንዲያውም የታላቁ የሥነ ተውኔት ጸሐይ የጋሼ ወጋዬሁ ንጋቱ የሙት ዓመት 5ኛ ዓመት ሲከበር እኔ „እሱ ማነው“ በሚለው ግጥሜ አሸንፌ ብሄራዊ ቲያትር የግጥሜን አቮል አቅርቤ ነበር። አዘጋጁ „የወጋዬሁ አማተር የተዋናይ ክበብ ነበር“ የውድድሩን ዕድሉ አቀናባሪው ደግሞ የአዲስ አበባ የባህልና ስፖርት ቢሮ ነበር። ዝግጅቱ እጅግ ማራኪና ውብ ነበር። በዛ በማይጠገበው የብሄራዊ ቲያትር አዳራሽ ታዳሚው ሙሉዑ ነበር። አዛውንት የጥበቡ አባና እማ ወራዎች በክብር ተገኝተውበትም ነበር። ታዲያ ያን ጊዜ ያን የመሰለ ተግባር ይፈጽሙ የነበሩ ክበቦች ዛሬ ምን በላቸው? ለመሆኑ አንድ ቀን ሰብሰብ ብለው ሄደው ግንዱን – ዋርካውን የሥነ ጥበብ ዋርካ አይተውት ያውቁ ይሆን? የጋሼ ደበበ ቀንን ለማክበርስ ምን አድርገው ያውቁ ይሆን? ጋሼ ደበበ አይደገመም። ኮፒ የለውም። ሥጦታ ነው የእኛ። በከፋው ቀን፤ ቀን በተደፋበት ጊዜ ከጎኑ ለመሆን ቀጣይ ከያንያን ምን ያስቡ ይሆን? የጥበብ ቤተኞች ቱግ ብለው የሚፈሉት ለእነሱ ሲቀርባቸው ሳይሆን ሥነ ጥበብ ከነ ሙሉአካሉ ሲታሰር፣ ሲንገላታ፣ ሲገደል፣ ሲሳደድ፣ ሲሞት፣ ሲቀበር፣ መራራን ዘመን ሲጠጣ መሆን አለበት ባይም ነኝ – እኔው። ጸሐፍትም የጥበብ ቤተኛ ናቸው። እግር ብረቱ እነሱንም ዕለት – ተዕለት ሲለቅማቸው አደቡ እስከመቼ ይሆን? ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ጥበብ የሚባለው ነገርም ወይነ?! መገላበጥ መቼስ ዘመን ሰጥቶት ዬለ …
ዛሬ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ከያንያን – ህዝብ ለሚሳጣቸው አቻ የለሽ ፍቅር ውለታው እኮ ፈጣሪያቸው ለሰጣቸው ጸጋ መንገድ ጠራጊዎቻቸውን ዕንባ ሲጋሩ ነበር። ግን ኮሽ የሚል ነገር የለም። በቃ ጭር ጸጥ ረጭ። ጦሩ ለእኔ ካልተመዘዘ በማለት ዘግቶ – መቀመጥን የመረጡ ይመስላል። አልፍ ብሎም ገዳይን ማወደስ ማድነቅ ማቆለበባስ ….ሥራዬ ብለው ተያይዘውታል። ይህ እውነት ለመናገር ኢትዮጵያዊነት ተረግጦ ጎጠኛን ማሞጋገስ ለእኔ ኢትዮጵያን የመጠቅጠቅ ያህል ነው። ለዛውም ፍርፋሪ ለማይገኝበት – በጎሬጥ ለሚታይበት ዘመን። በአይመለከተኝም መስመርስ ተሂዶ የጥበብ ቤተኝነት አባልነት ወይንስ ደባልነት – ለሆድነት?

ዬት ይሆን ያሉት – አነዚህ ተተኪ የጥበብ ዕንቡጦች? ከቶ ዬት ይሆን አድራሻቸው? ለነገሩ ዝንቅንቅ ብሎ ጸጋ ሳይሆን ቅመሙ መለያው – መስፈሪያው – ማንዘርዘሪያው – ዘመንተኝነት ሆኗል። የሆኖ ሁኖ ግን አምልጠው የወጡት ግን ፊት ለፊት ወጥተው በሚገባም ተደራጅትው ገዢውን ስንክሳር – ሊሟገቱት ይገባል። ሰንደቃችን – ምሳሌያችን አባት ደበበን ሊያስቡት፤ ሊያስታውሱት፤ አውዳዓመት ሲደርስ ሄደው ሊጠይቁትና የተቀነባበረ ተግባር ሊከውኑ ይገባል። በተጨማሪም ማን ጌታ አለባቸው አካውንታቸው ላይ ፎቶውን ቢለጥፉት – ቤታቸው ውስጥ በፍሬም ቢያስቀምጡት ክብር ነው – ረድኤት ነው- አደራንም መወጣት – ምርቃትም።

ከሰሞናቱ ፈረንሳይ ውስጥ አንድ አስቃቂ ሀዘን ተፈጸመ – ለሶስት ተከታታይ ቀናት። በአንድ የህዝብ ልሳን በሆነ ላይ „አሸባሪዎች“ ወንጀል ፈጸሙ። በተከታታይ ሶስት ቀናት ፈረንሳይ በሃዘን – በምጥ ላይ ነበረች ከጥር 7 – 9። በ11.01.02 ከ50 በላይ የሚሆኑ የሌላ ሀገር ጠቅላይ ሚ/ሮች የመንግሥት ተወካዮች 100000 ታዳሚዎች ብሄራዊ ዓለምዐቀፋዊ የሶሊዳሪቲ ስልፍ ነበር „እኔም ሻርሊ ነኝ፤ እኔም ይሁዳዊ ነኝ፤ የሃሳብ ነፃነት ይከበር፤ የፕሬስ ነፃነት ይከበር፤ የሃይማኖት መቻቻል ይበልጽግ“ በማለት ከሁለኛው ዓለም ጦርነት ፍጻሜ በኋላ የታዬ መጠነ ሰፊ የህዝብ ቁጣና የሀዘን ቀን ነበር። በህንድ፣ በጀርምን በተለዬ ሁኔታ፤ በእንግሊዚም ተማሳሳይ የወዳጅነት ሰልፍ ነበር … ይህን ጥቃት የደረሰበትን መጋዚን ለማጋዝም ሚሊዮኖች ተሰልፈዋል። እኛ ጋር ሲመጣ ሌላ ነው። በ2012 „ፍትህ“ ጋዜጣ 30000 ህትምት ስትቃጠል በጎኑ ዬመቆም አቅሙ ምን ያህል ነበር? የብዕር ውጤት ምርቶች ሲታገዱ አምራች ህሊናዎች ሲንገላቱ፤ ሲታሰሩ፤ ሲሰቃዩ ህዝቡም ሆነ ዋና የጥበብ ቤተኛው ታዳሚው ኮሽ አይልም። 30 ሺህ የፍትህ እትም መቃጠል ማለት በአማካኝ በስሌት አንድ ህትምት ቢያንስ በመዋዋስ 5 ሰው ያነበዋል። በማዕካለዊ ግምት ሲሰላ 150000 ሰው መንፈስ አብሮ ተቃጥሏል። ለዛውም የሆነውን እውነት ነገር በመጻፉ። ከዛም የተለያዩ ሙከራዎች አድርጎ ታታሪ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ መንፈሱ – ብቃቱ እግር ብርት ሆነ። ጭራሽ ስንቅ እንዳይገባለት ከቤተሰብ እንዳይገናኝ ተወሰነ። እውነት በቲያትር፤ በፊልም፤ በሙዚቃ፤ በሥነ ጹሑፍ በጸሐፊነት፤ በገጣሚነት፤ የተሰማራው ቤተኛ ሁሉ ጥበብ ቀብር ላይ ሆኖ እንዴት እንቅልፍ ወስዶት እንደሚያድር ሳስበው መተንፈስ ያቅተኛል – የእውነት። የጥበብን ጽኑ ጣር መስማት ያልቻለ ጆሮ ምን ይሁን ትላላችሁ – ክብሮቼ?

ሥነ – ጥበብ ዓለምነቷ የራሷመርህ ብቻ ሳይሆን የራሷ ፕላኔት ያላት ከመሆኑ ላይ ነው፤ ሥናዊቱ ሃይማኖት ጥበብ ህገመንግሥት ያላት፤ የሥምረት ማዕዶት ናት። ኪናዊቱ – ማናቸውንም ግርዶሽ ሁሉ ፈነቃቅላ እራሷን የመግለጽ የኤደን አቅም አላት። ልዕልት ጸሐይ ጉምን አሸንፋ ተወዳዳሪ የለሽ የኃይል ምንጭ እንደ ሆነች ሁሉ ጥበብ የአቅም ምጣኔ ባንክ ናት። የብቃት መጠለያ ናት። ኪዳን ናት – ውል። ማተብ ናት – ዕምነት። ሁሉን ለመጋራት የፈቀደች ወላጅ እናት ናት – አናት። ታዲያ አዛውንቱ አንድ ዕጣ ነፍሱን የቀረው ታላቅ ብርሃን – ዬትውልድ በ100 ዓመት ሊተካ የማይችለው የትዕይንት ንጉሥ ጨለማ ውስጥ ሆኖ እንዴት ስለእሱ ተቆርቋሪ ቀንጣ የሥነ – ጥበብ ክበብ፤ ቆራጥና ደፋር አርበኛ በባዕት ይታጣ?! አይጎረብጥም? ትንሺ ብጣቂ ሰለምታ በወል መላክ እንኳን ሳይቻል፤ ለተቋምነትህ እናመሰግንሃለን ሳይባል የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና አንድ ነገር ቢሆን ለወጣት ተዋናይ የህሊና ረመጥ አይሆንም?! ታሪክስ ትውፊትስ አይራገመሙም? አስተውሉ ….. እነ ኮበል እነ ሸበላ እባካችሁ ….. ን። ጥበብን አስቡ – መንፈሳችሁን – አነቃንቁት …. ለጥበብ ነፃነት አደባባይ ውጡ – ደጋፊዎቻችሁን፤ አድናቂዎቻችሁንም አሰልፉ — ዕልፍናችሁና ዕልፍነታችሁን በተግባር እልፍ አድርጉት እንጂ የምን ተኝቶ በለኝ ነው¡

ወያኔ እንደ ሆነ ድልድይ መስበር አመሉ ነው። የተፈጠረውም ሆነ የሰለጠነው መንገድ ለማፈረስ ነው። ይህን ምኞቱን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይፈጽመዋል። ጋሼ ደበበ ባይታሰር ስንት ወጣቶች በብሄራዊ ስሜት ጥበብን አልቀው፤ ጥበብን እንደ ተፈጥሮው አቅልመው መቅረጽ የሚችሉ የነገ ጽጌረዳዎችን ባፈራ ነበር። ይህም ተፈርቶ ነው የታሰረው። ለአንድ ታላቅ ብልጹግ የሥነ ጥበብ አባዎራ – እማወራ አንድ ቀን ብዙ፣ እጅግ ብዙ ምርት የሚታፈስበት ዕለቱ ነው። እንኳንስ —- አስሉት ከ97 ጀምሮ ያሉትን ጊዜያቶች ….. ሥንት ዕንቡጥ የተውኔት ለጋ ኮሽ ብሎ ደርቆ እንደ ረገፈ፤ ተስፋ በግፍ ተነቀለ፤ ፍቅር ከፍቅረኛው ታገደ …. ያቆስላል። መድርክም ደም አማጣች! ይህን ፍሬ ነገር የነገ የተስፋ ተስፋዎች ከልብ ሆናችሁ አስሉት – አንሰላስሉት …. እናም ወስኑ ነገን ለማግኘት እባካችሁን ቁረጡ?! ለጥበብ አደራ ብቁ ወታደር ሁኑ። በራችሁ እሲኪንኳኳ ድረስ አትጠበቁ …. ተንቀሳቀሱ! ፍጠኑ! ትንሽ ተነቃነቁ ጅም ነገር አድርጉ! …. በትንሹ ጀምሩት … ይሄው ሰሞናቱ ዘመነ አስተርዮ ነው። ቃና ዘገሊላ ታምር የተመሰጠረበት። …. እሰኪ ፖስት ካርድ ላይ ፊርማ አሰባስባችሁ እንኳን አደረሰህ አባታችን በሉት። የ5 ወይንም የ10 ወገኖቹ ሊሆን ይችላል። ብጣቂ ቁራሽ ሳቅ እስኪ ውስዱለት። እንወድሃለን፤ እናከብርሃለን ተክሊላችን ነህ እስኪ በሉት አፋችሁን ሞልታችሁ፤ ድፈሩ! መንፈሳችሁን አደላድላችሁ – ፍላጎታችሁን ፈጽሙ። ጨው አይዳላችሁ አትማሙ – እሰኪ ተስፋነታችሁን ጀምሩት፤ እኛም ተስፋ እንዲኖረን አድርጉን። አሉልን – አሉልን – አሉልን እንበል። መታሰር ይኖራል፤ መገፋት ይኖራል፤ መሳደድ ይኖራል። „ከድምጽችን ይሰማም ተማሩ! ለሰማይው ጸጋችሁ ፍትኃት ቁረጡ – ወስኑ – ከድርጊት ጋር ከትሙ። ከመከራ በስተጀርባ ታላቅ ክብር አለ። መከራ በበዛ ቁጥር መጪው ቀን ብሩህ እንዲሚሆን ያበስራል።
ጥበብ ተናገረች – መርሄ ነው ብላ
ልቧነን አውጥቶ ካቴና ሲባላ፤
ጥበብ ታውጃላች – ተከተሉት ብላ
ሥነ ህግን – ገላ።
ጥበብ – ሠራች ባላ
የመሆን – አዝመራ!
እኔም ተቀበልኩኝ
እሺ አልኩኝ፤ እሺ አልኩኝ —-
ለእሱ – ይሁንልኝ
ለመንፈስ ሁነኛ
መገኛ – መዳኛ፤
የሆነልን – ዬእኛ – ለእኛ። /05.01.2015 ሲዊዘርላንድ – ቪንተርቱር/

እንሆ – „የታላቋ ትግራይ ህልም“ ሁለመናን ያሳድዳል፤ ሁለንትናን – ይቀማል። ዘመቻው ጥልቅ ስትራቴጁም ስውር – ነውር። በተከታታይና በትጋት ዬትውልድን ውርርስ ሃብት ለመከተር ዋርካ ይነቀላል፤ የትውፊትን ቀንዱን ይሠበራል – ሴሉም ይገደላል። ድንበር ይጣሳል – ዘረፋም ይጎናል። ስለዚህ ሥር ሰደድ በደል ሥር ነቀል ለውጥን ማለም አለበት – እላለሁ – እኔው። የፍላጎት አቅም ሙያዊ ግዴታን በአግባቡ ከመወጣት ይታፈሳልና። በስተቀር እዬሞቱ መኖር እዬኖሩ መሞት —– ግን ይህ መኖር ወይንስ ምን?!

ጥበብ የእውነት አረበኛ ናት። ጥበብ ለማተቧ ሰማዕት ናት። ጥበብ ዘር ናት። ተከታዮቿ – ቤተኞቿ – አድናቂዎቿም – የዕውነት ሐዋርያ መሆን አለባቸው። ከዚህ ከወጡ ያረጡ ከንቱዎች ናችሁ ብላ ጥበብ እራሷ ትሰርዛቸዋለች። ከሰጠቻቸው እርእስት ሆነ ከጉልማ* መሬታቸውም ትነቅላቸዋለች። ጥበብ ካኮረፈች ወይንም ከተቆጣች ጸጋን እውሃ ሲሄድበት የከረመ አለት የማድረግ አቅሟ ብልህ ነው። ስለምን? ከዕውነት ውጪ ጥበብ አትታሰብም፤ ወይንም ቀና ብላ ጆሮ አትሰጥም። ጥበብ – ታማኝነትን ውጣ፤ ሃቅን አጣጥማ፤ ፈርኃ እግዚአብሄርን የጠበቀች ለ እውነት ያደረች ግማደ መስቀል ናት – ለኑሮ! ኑሮን ፈጥራ – ቀርፃ ጸሐይ ያደረገች የኑሮ ፈርጠ – ጉልላት።

„ ለሁሉ ዘመን አለው፤ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው“ /መጸሐፈ መክበብ ምዕርፍ 3 ከቁጥር 1 እስከ 2/
ቅኔያችን – ለእኛ የተከበረው የሰባዕዊ መብት ተሟጋችና ታላቁን የጥበብ ሰው አርቲስት ደበበ እሸቱን አምላካችን ይጠብቅልን። አሜን! ዕድሜውን ሰጥቶት ጸጋውን ይምግበን ዘንድም አምላካችን አዶናይ ይርዳን። አሜን!

በተረፈ ነገ ጥር 17 ቀን ነው። የጀግና ኃይለመድህን አበራ 11ኛ ጀኔባ የገባባት የጀግንነት ወሩ ነው። እሱ የሳሳለት፤ ሁሉን የሰጠው፤ ለነፃነት መንፈስ ሲል ስለሆነ የእሱን ቀን ለተግባሩ ውለታ ለጋሼ ደበብ ይሁን ብዬ ወሰንኩ። ስለ ሀይልዬ ሆነ ቀልብን ሳብ አድርገው በሰነባበቱ ጥቂት ብሄራዊ ጉዳዮች ላይ ያቺው መቼም ቆራጣ ናት አንድ ሰዓት የሚሏት፤ የተቻለውን ያህል ትናንትና በ15.01. 2015 በነበረው ፕሮግራም Tsegaye Radio ያለው ነበር። እሰኪ ገባ ብላችሁ አዳምጡት ከቻላችሁ። የሃይልዬም አምድ የበኩሉን ከውኗልና።

ይቋጭ – የኔዎቹ እንዴት አላችሁልኝ። አልገርምም ግን ስስናበት ሰላምታ። ይሁን። ለስላሳ ትህትና ለጀርጋዳ ስንብት እንሆ።
ውዶቼ አንድ ነገር – እሰኪ ሰንበትን በአካውንታችሁ የዚህን የዘመን አውራ ፎቶ መንበሩ ላይ የምትችሉ አስቀምጡት፤ ውስጡን በመንፈስ ብሌን ትክ ብላችሁ እዬት። በዕዝን ህሊና ከንፍርም በፍቅር ዳስሱት። ክብራችን – ጌጣችን – ግርማ ሞገሳችን – ውባችን – ተቆራቋሪያችን – አድባራችን – አለኝታችን – ትምህርት ቤታችን – ተቋማችን፤ የጥበብ ባዕታችን እስኪ በሉት — እንዲያምርባችሁ —– እንዲያምርብን — ሸበላ ሰንበት እንዲሆን ከመንፈሴ ተመኘሁኝ። ፍቅር ስለሆናቸውም ድንበር አልቦሽ – ነፍስ የሆነ ፍቅሬንም እንሆ! መሸቢያ – ሰሞናት- ኑሩልኝ።

*መፍቻ ጉልማ … ከሰፊው የምርት ማሳ ወላጆች ለልጆቻቸው የሚሰጧቸው ቁራሽ የግል መሬት ሲሆን። ልጆችም ይህን መሬት በራሳቸው መንገድ አልምተው የፈለጉትን ዘርተው የሚያገኙት ገቢ ለራሳቸው የግል ጉዳይ መፈጸሚያ ወይንም ማስፈጸሚያ ያደርጉታል። ጎጆ ሲወጡም ጎጆ መውጫ ይሆናቸዋል። ሥነ ጥበብ ከሰፊው ማሳው ዘርፈ ብዙ የማይቋረጥ በብዙ መስመሮች ሊገለጽ የሚችል ረቂቅ ጥልቅ የሰማይ መክሊት ሲሆን ለሰው ልጆች የሰማይ ስጦታ ነው። እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ የራሱን መክሊት ይዞ ይወለዳልና። እንደ መክሊቱም ህዝብን ዝቅ ብሎ ያገለግልበታል። ግን ችለናልን ወይንስ አደራ በይ ሆነናል ነው ጥያቄው ——

ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>