∙በቃል የቀረበው አቤቱታ ከድምጽ ክምችት ክፍል ጠፍቷል ተብሏል
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች እና ሌሎች በተመሳሳይ መዝገብ ያሉ የሽብር ተከሳሾች በቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር መካከል ያለው አቤቱታ እስካሁን እልባት ሊያገኝ አልቻለም፡፡
ዛሬ ጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰማያዊ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና አቶ አብርሃ ደስታ እንዲሁም አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቅአገኘሁን ጨምሮ ሌሎች ተከሳሾች ማረሚያ ቤቱ የመብት ጥሰት እየፈጸመባቸው እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ አቤት ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በዛሬ ዕለት በጉዳዩ ላይ የማረሚያ ቤቱ አስተዳዳሪ ችሎት ቀርበው መልስ ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ቀደም ባለው ቀጠሮ ወቅት አቤቱታው በቃል ተሰምቶ በመቅረጸ ድምጽ ተቀድቶ እንደገና በጽሑፍ ተገልብጦ ከመልስ ጋር እንዲቀርብ ታዝዞ የነበር ቢሆንም ድምጹ ከፍርድ በቱ ድምጽ ክምችት ክፍል ሊገኝ ስላልቻለ በወረቀት ተገልብጦ መልስ እንዲሰጥበት ለማረሚያ ቤቱ አለመድረሱ ተገልጹዋል፡፡
በዚህ የተነሳም ፍርድ ቤቱ ለጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ችሎት ቀርቦ መልስ እንዲሰጥ ለማስቻል፣ በቀጣዩቹ ቀናት ውስጥ አቤቱታው እንደገና በጽሑፍ ለፍርድ ቤቱ እንዲቀርብ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
በተመሳሳይ በቀድሞው የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦኬሎ አኳይ የክስ መዝገብ በተከሰሱ ሰዎች ላይ የአቃቤ ህግ ምስክሮች የሰጡት ምስክርነት ከድምጽ ክምችት ክፍል ስለጠፋ እንደገና በሌላ ተለዋጭ ቀጠሮ ድጋሜ ምስክሮቹ እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡