Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይጠብ ጥንቃቄ ይደረግ!

$
0
0

የአንድ አገር ሉዓላዊነት ባለቤት ሕዝብ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ከምንም ነገር በላይ የአገር የሥልጣን ባለቤት ሕዝብ ነው ማለት ነው፡፡ እንደ እኛ ባለ አገር መቼም ቢሆን ምርጫ ሲከናወን የሥልጣን ባለቤት ሕዝብ መሆኑ ተክዶ አያውቅም፡፡

9f82c54a890bb560467ea1718ee4a9e5_Lነገር ግን ሕዝብ ወሳኝ ሊሆንባቸው በሚገባ የምርጫ ሒደቶች ውስጥ ከሕዝቡ ይልቅ ጎልተው የሚታዩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ምንም እንኳ የሕዝብ ድጋፍ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መሆናቸው ቢታመንም፣ በትንሽ በትልቁ በሚደረጉ ክርክሮችና ውዝግቦች የሕዝቡ ድምፅ ዝቅተኛ ሆኖ በጉልህ የሚሰማው የፓርቲዎች ድምፅ ነው፡፡ ሕዝብ ዳር ቆሞ ተመልካች ሳይሆን ወሳኝ መሆኑ አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል፡፡

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሁሌም ወሳኝ የሆነው የፖለቲካ ምኅዳሩ ጉዳይ ነው፡፡ ምኅዳሩ ሲሰፋና ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት ሲንቀሳቀሱ ለመራጩ ሕዝብ ይበጃል፡፡ በአንፃሩ ምኅዳሩ ጠቦ አማራጭ ሳይኖር ሲቀር ምርጫ ጣዕም አልባ ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰፍቶ ፓርቲዎች በነፃነት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ፣ ምርጫ በእውነትም ትክክለኛው የውሳኔ መስጫ ሒደት ይሆናል፡፡ ሕዝብም የፈለገውን ፓርቲ ያለምንም መሸማቀቅ በነፃነት የመምረጥ መብቱ ይከበርለታል፡፡

አገሪቱ ባለፉት ሃያ ዓመታት አራት በውዝግብ የተቋጩ ምርጫዎችን አካሂዳ አሁን ለአምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በዝግጅት ላይ ናት፡፡ ምርጫ በመጣ ቁጥር የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ፣ ከዕጩዎች ምዝገባ፣ ከመራጮች ምዝገባ፣ ከምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ እስከ ድምፅ መስጠት ቀንና ውጤት ይፋ መሆን ድረስ ለወራት በተለያዩ ሥራዎች ይጠመዳሉ፡፡ በእነዚህ ሒደቶች ውስጥ በርካታ ጭቅጭቆችና ውዝግቦች ይከሰታሉ፡፡ ግጭቶች ይካሄዳሉ፡፡ የሰው ሕይወትም ይጠፋል፡፡ እነዚህ አሳዛኝ ድርጊቶች በተደጋጋሚ ተከስተዋል፡፡

በአገራችን በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ላይ ከሚነሱ ጥያቄዎች ጀምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ገዥው ፓርቲ ጭቅጭቃቸው አሁንም እንዳለ ነው፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ምኅዳሩ ጠቦ ጠቦ በፍፁም የማይላወሱበት ደረጃ ላይ መሆናቸውን በስፋት እየገለጹ ነው፡፡ በአንድ በኩል ከገዥው ፓርቲ፣ በሌላ በኩል ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጫና እየደረሰብን ነው እያሉ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲና ምርጫ ቦርድ ይህንን አቤቱታ እያጣጣሉ ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ፈፅሞ የማይጣጣም ቅራኔ ባለበት ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ በጣም ከባድ ነው፡፡ የከበደውን ለማቅለል ከተፈለገ ዴሞክራሲ ሒደቶችን ለመተግበር ምን ያቅታል?

እንደሚታወቀው ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በሥራ ላይ ያለው ዘመናዊው የውክልና ዲሞክራሲ ገቢራዊ መሆን የጀመረው በምርጫዎች አማካይነት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሒደት ደግሞ የሚሠራው መንግሥት ለመመሥረት ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ የግል የቢዝነስ ተቋማት፣ ለተለያዩ ዓላማዎች ለሚመሠረቱ ማኅበራት፣ ለበጎ ፈቃደኞች ስብስቦችና ለትላልቅ ኮርፖሬሽኖች ጭምር ነው፡፡ ለዚህም ነው ምርጫ የብዙኃኑን ሕዝብ ወኪሎች ለመምረጥ እንደ ሁነኛ መሣሪያ የሚታየው፡፡ ምርጫም ነፃ፣ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ የሚሆነው በተወዳዳሪዎች መካከል እኩል የመፎካከሪያ ሜዳ ሲኖር ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ምርጫ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምርጫ ቦርድና ዋነኛ በሚባሉት የተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል እየታየ ያለው ውጥረት የተሞላበት ግንኙነት መርገብ ይኖርበታል፡፡ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ነፃና ፍትሐዊ አድርጌ አስፈጽማለሁ ሲል ቢያንስ ቢያንስ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን በቅርበት ማነጋገር አለበት፡፡ አለ የሚሉትን ችግር መስማት ይኖርበታል፡፡ የገለልተኝነቱ ጥያቄ እንዳለ ሆኖም የምርጫው ተዋናዮች እስከሆኑ ድረስ ሊደመጡ ይገባል፡፡ ከሕጋዊና ከሰላማዊ ጥያቄዎቻቸው በተጨማሪ በምርጫ እንቅስቃሴያቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ መሰናክሎች እንዳይጋረጡባቸው መከላከል አለበት፡፡ ለምርጫው ሰላማዊነት፣ ነፃነት፣ ፍትሐዊነትና ተዓማኒነት የሚጠቅመው ይህ ዓይነቱ መንገድ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ሕጎችን አስከብራለሁ ሲል ሁለገብ የሆኑ ጥያቄዎችን በብቃት ሊመልስ የግድ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ‹‹በሆደ ሰፊነት…›› እያለ የሚገልጻቸው አባባሎች ግራ ያጋባሉ፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ መንግሥት እንደመምራቱ መጠን ለምርጫው ስኬት ከልቡ ካልተነሳ ለዓመታት የዘለቁ ችግሮች ተባብሰው ይቀጥላሉ፡፡ በምርጫ ተሳታፊነቱ ራሱን እንደ አንድ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲ ማየት ከተሳነው ችግር አለ፡፡ ሠራዊቱንና የፀጥታ ኃይሎችን በሕገ መንግሥቱ መሠረት ገለልተኝነታቸውን መጠበቅ፣ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት በምንም ዓይነት ሁኔታ ለምርጫ ቅስቀሳ እንዳይውል ማድረግ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከመድፈቅ መታቀብና ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የበኩሉን ሚና መጫወት አለበት፡፡ በርካታ የተለያዩ ፍላጎቶችና ስሜቶች ባሉበት አገር ውስጥ አንድ ፓርቲ ሁሉንም ጠቅልሎ ወሰደ ሲባል ያስነቅፋል፡፡ ምርጫ ትርጉም ከማጣቱም በላይ ባይኖርስ ያስብላል፡፡ ይህ ዓይነቱ መንፈስ ደግሞ በዚህ ዘመን ተፈላጊ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የኋላ ቀርነት ምልክትም ነው፡፡

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲሰፋ ሲፈለግ የአገሪቱ ዴሞክራቲክ ተቋማት በሙሉ ከምንም ነገር ነፃ መሆን አለባቸው፡፡ ምንም እንኳ ነፃነት በምሉዕነት ተሟልቶ ሊገኝ ይችላል ተብሎ ባይታመንም፣ ቢያንስ ቢያንስ እነዚህ ተቋማት የገለልተኝነት ሚናቸውን እንዲወጡ መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ ሚዲያውም ከወገንተኝነት ነፃ ሆኖ የምርጫውን እንቅስቃሴ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው እንዲዘግብ የማመቻቸት ትልቁ ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ ይህ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የሚታመንበት እንደሆነ ተደጋግሞ ቢነገርም፣ በተግባር ባለመረጋገጡ ለምርጫ ሒደት እንቅፋት ሆኗል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ መስፋት የሚፈለገውም ለዚህ ነው፡፡

ለምርጫ እንደ ፈተና ከሚታዩ ችግሮች መካከል አንዱ የሕግ የበላይነት ደካማ መሆን ነው፡፡ በብዙ ታዳጊ አገሮች ምርጫዎች ዓለም አቀፍ ደረጃን ያልጠበቁ ናቸው የሚባለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ምርጫ ነፃና ፍትሐዊ እንዲሆን ሲፈለግ ከምንም ነገር በላይ የሕግ የበላይነት ክብደት ሊሰጠው ይገባል፡፡ የሕግ የበላይነት ሲኖር የፖለቲካ ምኅዳሩ ይሰፋል፡፡ ምርጫም ነፃና ዴሞክራሲያዊ ይሆናል፡፡ ተወዳዳሪ ፓርቲዎችም ለሕግ ተገዥ ይሆናሉ፡፡ መንግሥት የአገሪቱ ሕገ መንግሥትና ሌሎች ተያያዥ ሕጎችን ማክበርና ማስከበር አለበት፡፡ ሕጎች ባልተከበሩት ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓትም ሆነ ስለምርጫ መነጋገር ፋይዳ የለውም፡፡ የሕግ የበላይነት መኖር ወሳኝ ነው፡፡

የፖለቲካ ምኅዳሩን በማጥበብ በኩል ከገዥው ፓርቲ በተጨማሪ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡ ገዥው ፓርቲ ችግሮች አሉበት ሲባል የተገዳዳሪዎቹም መጠቀስ አለበት፡፡ ይህ የሚጠቅመው ደግሞ ጉድለቶቻቸውን አርመው ወደ ምርጫ እንዲገቡ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ከአደረጃጀታቸው፣ ከአቻ ፓርቲዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት፣ ዓላማቸውን በበቂ ሁኔታ ለሕዝብ በማሳወቃቸው፣ ውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲን ተግባራዊ በማድረጋቸው፣ እርስ በርስ በመጠላለፋቸው፣ ወዘተ ያላቸው ይዞታ መመርመር አለበት፡፡ ሕዝቡን ግራ የሚያጋቡ ብዙ ችግሮች አሉባቸውም፡፡ ውጫዊ ችግሮችን ከሚፈቱባቸው ሥልታዊ አካሄዶች ድክመት አንስቶ የተለያዩ ተግዳሮቶች ይታዩባቸዋል፡፡ በመተባበር፣ በመቀናጀት፣ ግንባር በመፍጠርና በመዋሀድ ሒደቶች ውስጥ በሚፈጥሯቸው ችግሮች ምክንያት ሲጠላለፉ ይታያሉ፡፡ ለችግሮች መፍትሔ በማፈላለግ በኩልም አዝጋሚ ናቸው፡፡ የገዥውን ፓርቲ ጫና ብቻ እየተረኩ ሌሎችን ድክመቶች ያድበሰብሳሉ፡፡ የዳያስፖራው ተፅዕኖ እግር ተወርች ሲያስራቸው በፅናት ሲታገሉ አይታዩም፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ለፖለቲካ ምኅዳሩ መስፋት ጥርሳቸውን ነክሰው መታገል ሲችሉ ይብረከረካሉ፡፡ አንዳንድ ወገኖች የተቃዋሚዎች ችግር ለምን ይነሳል ይላሉ፡፡ በዚህ ዓለም ፍፁምነት የለምና ለሰላማዊ ፖለቲካ ትግሉ መሳካት ራሳቸውን በቅጡ ቢያዩ ይበጃቸዋል፡፡ አንድ ነገር ላይ ብቻ በማተኮር ጊዜያቸውን በማጥፋት የፖለቲካውን መንገድ መሳት የለባቸውም፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲሰፋ ሲፈልጉ ማንኛውንም ችግር ችለው መልፋት አለባቸው፡፡

የመጪው ግንቦት ምርጫ ከወዲሁ ሲገመገም ካሁኑ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መፍትሔ ያሻዋል እንላለን፡፡ በተደጋጋሚ ምርጫው ነፃ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ ይሆናል ሲባል በተግባር መረጋገጥ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን የአብሮ የመኖርና የመቻቻል ተምሳሌት በመሆኗ ወሳኙ ሕዝብ ሊከበር ይገባዋል፡፡ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች አንዱ ሕጋዊ ምርጫ ሲሆን፣ ይህ ምርጫ የሕዝባችንን ፍላጎት የሚያማክል መሆን አለበት፡፡ ሕዝብ የሥልጣን ምንጭ እስከሆነ ድረስ ድምፁ ሊከበር እንደሚገባ ሁሉ፣ የምርጫ ሒደቱም ከእንከን የፀዳ እንዲሆን የሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ መረባረብ አለባቸው፡፡ ዳር ሆኖ ግለት መፍጠር ሳይሆን እውነተኛ ምርጫ እንዲኖር አስተዋጽኦ ማድረግ የአገር ወዳድ ዜጎች ኃላፊነት ነው፡፡ ለዚህም ነው የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይጠብ ጥንቃቄ ይደረግ የሚባለው!

Source:: Ethiopian Reporter


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>