Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የእቴጌ ጣይቱ ሆቴል ቃጠሎ ውዝግብ ፈጥሯል

$
0
0

bee392ccb91b968f78a29a035271c5d5_L

‹‹የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች እንደደረሱ ቢያጠፉ ሆቴሉን ማትረፍ ይቻል ነበር›› የእቴጌ ጣይቱ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ

‹‹በተደወለልን በሁለት ደቂቃ ውስጥ ደርሰናል›› የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ባለሥልጣን

አዲስ አበባ ከተማ በተቆረቆረች በ19ኛ ዓመቷ በአሁኑ አጠራር በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ፒያሳ በ1898 ዓ.ም. በተገነባውና 109ኛ ዓመቱን ባስቆጠረው እቴጌ ጣይቱ ሆቴል ላይ፣ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ከማለዳው 2፡15 ሰዓት አካባቢ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ እያወዛገበ ነው፡፡

ለእሳቱ መነሻ ቦታና ምክንያቱ እስካሁን ያልተደረሰበትና በቃጠሎው ምን ያህል ንብረት እንደወደመ የሆቴሉን ባለቤቶች ጨምሮ መግለጽ የሚችል አካል ባይገኝም፣ ከሆቴሉ ሕንፃ ጋር ተያይዞ በተሠራው ‹‹ጃዝ አምባ ላውንጅ›› መዝናኛ የመጀመሪያው እሳት የታየ ከመሆኑ አንፃር፣ የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን ፈጥኖ ደርሶ ቢሆን፣ እሳቱን እዚያው የታየበት ቦታ ማስቀረት (ማጥፋት) ይቻል እንደነበር በአካባቢው የተገኙ ሰዎች እየገለጹ ነው፡፡

በዕለተ ሰንበት (እሑድ) ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ከማለዳው 2፡15 ሰዓት አካባቢ የእሳት አደጋው እንደተነሳ እንደሰሙና መኖሪያቸው ከሆቴሉ ብዙም ያልራቀ በመሆኑ፣ በአሥር ደቂቃ ውስጥ መድረሳቸውን የሚናገሩት የእቴጌ ጣይቱ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ አቶ አያሌው ታደሰም፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና በቃጠሎው ወቅት በሥፍራው የነበሩ ሰዎች በሚሉት ይስማማሉ፡፡

የስልክ ጥሪ በደረሰው በሁለት ደቂቃ ውስጥ በአደጋው ቦታ መድረሱንና ያለውን ኃይል ሁሉ በመጠቀም፣ አደጋው ወደ ሌላ አካባቢ ሳይዛመት ሊቆጣጠር እንደቻለ እየገለጸ የሚገኘውን የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣንን የሚቃወሙት ሥራ አስኪያጁ፣ የባለሥልጣኑ ሠራተኞች ‹‹በሁለት ደቂቃ ደርሻለሁ›› ማለታቸውን ‹‹በፍፁም አልደረሱም›› በማለት ተቃውመዋል፡፡

እንደ አቶ አያሌው ገለጻ፣ በሁለት ደቂቃ ወይም በሌላ ማለቱን ትተው በደረሱበት ወቅት ማጥፋት ቢጀምሩ ኖሮ፣ እሳቱ ወደ ሆቴሉ ሕንፃ ሳይዛመት ጃዝ አምባ ላውንጅ ላይ እያለ ማጥፋት ይችሉ ነበር፡፡ ስልካቸው አልሠራ በማለቱ በመኪና እዚያው ድረስ ተሄዶ እንደተነገራቸውና ነጋሪው መጥቶ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደደረሱም ይዘውት የመጡት የእሳት ማጥፊያ ተሽከርካሪ ማጥፋት የሚችል ባለመሆኑ እሳቱ ወደ ሆቴሉ ሊዛመት መቻሉን አስረድተው፣ ‹‹ስለ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ፍጥነትና መዘግየት በወቅቱ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ይናገሩ፤›› ብለዋል፡፡

እሳቱ ከማብሰያ ክፍል ስለመነሳቱ የተጠየቁት ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹እሳቱ መቶ በመቶ ከማብሰያ ክፍል (ኪችን) አልተነሳም፡፡ መነሻው የሚሆነው ጃዝ አምባ እንደሚሆንና ምክንያቱ ደግሞ ቀድሞ የተቀጣጠለውና ሙሉ በሙሉ የወደመውም እሱ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ ጃዝ አምባ እየነደደ የሆቴሉ ማብሰያ ክፍል በሥራ ላይ እንደነበረና በማብሰያ ክፍል ውስጥ የነበሩትን እሳት አባባሽ ነገሮችን ቀድመው ማስወገድ መቻላቸውንም ገልጸዋል፡፡ በጃዝ አምባ ላውንጅ ውስጥ እሳት ሊያስነሳ የሚችል ነገር ስለመኖሩ ተጠይቀው፣ በጃዝ አምባ ውስጥ ሊቀጣጠል ወይም እሳት ሊያስነሳ የሚችል ነገር እሳቸው እንደማያውቁ ገልጸው፣ በወቅቱ ምን እንደነበርም ማወቅ እንዳልቻሉ አስረድተዋል፡፡ ጃዝ አምባ ላውንጅ አብዛኛውን ጊዜ የሚሠራው በምሽት ከመሆኑ አንፃር እሳቱ በተነሳበት ወቅት ሥራ ስለመኖሩ የተጠየቁት ሥራ አስኪያጁ፣ እሳቸው ጠዋት ባይኖሩም የላውንጁ ሠራተኛ የሆነ አንድ ሰው ከጠዋቱ አንድ ሰዓት አካባቢ ገብቶ መውጣቱን እንደሰሙ ጠቁመዋል፡፡ ጃዝ አምባ ላውንጅ መሥራት ከጀመረ ከሦስት ዓመታት በላይ እንደሆነውም ተናግረዋል፡፡

እቴጌ ጣይቱ ሆቴል ባለአንድ ፎቅ ሲሆን፣ አሥር የመኝታ ክፍሎች እንዳሉትና በእያንዳንዱ ክፍል ሁለት ሁለት አልጋዎች በመኖራቸው፣ በጠቅላላው 20 አልጋዎች እንዳነበሩ ሆነው ሙሉ በሙሉ መቃጠላቸውንም ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ደንበኞቻቸው የውጭ አገር ዜጐች መሆናቸውንም አክለዋል፡፡ በሆቴሉ ውስጥ የነበሩ ቁም ሳጥኖች ከእነዕቃዎቻቸው፣ የተለያዩ ታሪካዊ ምሥሎች፣ ቅርፃ ቅርፆችና ሌሎች ብዙ ዕቃዎች መውደማቸውንም ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን ግን፣ በአካባቢው ነበርን የሚሉትንም ሰዎች ሆነ ሌላ አካል የሚለውን አይቀበልም፡፡ የባለሥልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ደጋፊ የሥራ ሒደት መሪ አቶ ሰለሞን መኰንን ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ እቴጌ ጣይቱ ሆቴል ላይ ቃጠሎ እንደተነሳ መረጃ የደረሳቸው ከማለዳው 3፡08 ሰዓት ነው፡፡ የእሳት አደጋ መከላከል ቡድኑ ወዲያው ተሰማርቶ በሁለት ደቂቃ ውስጥ በቦታው ደርሷል፡፡ ‹‹አደጋው ከባድ ነበር፡፡ የባለሥልጣኑ ሰባት ቅርንጫፍ ጣቢያዎች ከባለሙያዎችና ከማሽኖች ጋር ተሰማርተው በመረባረባቸው እሳቱን መቆጣጠር ተችሏል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

የባለሥልጣኑ ሠራተኞች ከነማሽኖቻቸው ደርሰው በተለያዩ አቅጣጫዎች እሳቱን እየቆረጡ ማጥፋት ባይችሉ ኖሮ፣ በአካባቢው የሚገኙ መሥሪያ ቤቶችንና መኖሪያ ቤቶችን ሊያዳርስና ሊያጠፋ ይችል እንደነበር የተናገሩት የሥራ ሒደት መሪው፣ ‹‹በስንት ሰዓት እሳቱ ተነሳ? በስንት ሰዓት እናንተ ደረሳችሁ? የሚለው ጥያቄ ለእኛ አይጠቅምም፡፡ እኛ የምንሠራው የእሳት ቃጠሎ ተነሳ ተብሎ የተደወለበትን አስበን ነው፡፡ ወዲያው ስላልተደወለ እሳቱ ሊስፋፋ ችሏል፤›› ብለዋል፡፡

በሆቴሉና በባለሥልጣኑ መካከል ያለው ርቀት አጭር ከመሆኑ አንፃር የደረሱበት ሰዓት መዘግየቱን በተመለከተ ተጠይቀው፣ ጥሪው በደረሳቸው በሁለት ደቂቃ መድረሳቸውን የተናገሩት አቶ ሰለሞን፣ እንደተባለው እቴጌ ጣይቱ ሆቴል ለባለሥልጣኑ ቅርብ ከመሆኑ አንፃር የዘገዩት እነሱ ሳይሆኑ፣ ጥሪው የደረሰበት ጊዜ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ባይዘገይ ኖሮ ብዙ ንብረት ማትረፍ ይቻል እንደነበርም አስረድተዋል፡፡

አቶ አያሌው ማብሰያ ክፍሉ ቆይቶ እንደተቃጠለ የተናገሩ ቢሆንም፣ አቶ ሰለሞን ግን ለእሳቱ መባባስ ምክንያቱ በማብሰያ ቦታ አካባቢ የነበሩ ቁሳቁሶች መሆናቸውንና ቃጠሎውንም ከባድ እንዳደረጉት ገልጸዋል፡፡ 113 የባለሥልጣኑ ሠራተኞች በ12 ተሽከርካሪዎችና በአምስት አምቡላንሶች ታግዘው፣ 236,300 ሊትር ውኃና 500 ሊትር ፎም በመርጨት ቃጠሎውን መቆጣጠር መቻላቸውን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡ አደጋውን ለመቆጣጠርም ከሁለት ሰዓት በላይ መፍጀቱን ጠቁመው፣ ምክንያቱ ደግሞ ሆቴሉ ከጥድ እንጨት የተሠራ በመሆኑ በቀላሉ ማጥፋት ስለማይቻል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የጃዝ አምባ ላውንጅ ባለቤቶች ወይም ኃላፊዎችን ለማግኘት ባለመቻሉ በእነሱ በኩል ያለውን መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡

በእቴጌ ጣይቱ ሆቴል ግቢ ውስጥ ሕብረት ባንክ፣ የትኬት መሸጫ ቢሮና ሌሎች ድርጅቶች ተከራይተው ይሠራሉ፡፡ የትኬት መሸጫ ቢሮ ኃላፊዎችና የሌሎቹ ድርጅቶች ባለቤቶች ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ባለሥልጣን በወቅቱ ደርሶ ቢሆን ኖሮ እሳቱን መቆጣጠር ይቻል ነበር፡፡

በተመሳሳይ የሕብረት ባንክ አክሲዮን ማኅበር ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. በፕሬዚዳንቱ አማካይነት መግለጫ የሰጠ ሲሆን መገናኛ ብዙኃንን፣ ኅብረተሰቡንና ሌሎች የሚመለከታቸው አካሎች እሳቱን ለማጥፋትና የደረሰውን አደጋ ለሕዝብ ለማሳወቅ ያደረጉትን አስተዋጽኦ አድንቋል፡፡ በሆቴሉ ግቢ ውስጥ በነበረው ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ላይ ምንም ዓይነት የገንዘብም ሆነ የመረጃ ሰነዶች መቃጠል እንዳልደረሰበት አስታውቋል፡፡

ደንበኞቹ በሞባይል፣ በኢንተርኔት፣ በኤቲኤምና በሌሎቹም አገልግሎቱን እያገኙና የሚያገኙ በመሆናቸው ምንም ዓይነት ሥጋት እንደሌለ ገልጿል፡፡ እሳት ያልበገረው ካዝናውን በግራይንደር በመቁረጥ ገንዘቡ ተቆጥሮ ከመዝገቡ ጋር ተመሳክሮ ትክክለኛነቱ መረጋገጡን አስታውቋል፡፡

እቴጌ ጣይቱ ሆቴል በቀድሞ የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ለአቶ ፍፁም ዘአብ አስገዶም መሸጡ ይታወሳል፡፡ አሁንም የሆቴሉ ባለቤት አቶ ፍፁም ናቸው፡፡ በአፄ በዳግማዊ ምኒልክ ባለቤት እቴጌ ጣይቱ ብጡል በ1898 ዓ.ም. ነው የተገነባው፡፡ የመንበረ ፀሐይ እንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ሊመርቅ የመጣው ሕዝብ ምግብና ማረፊያ አጥቶ ስለነበር፣ አፄ ምኒልክ የሌሎች አገሮች የሆቴል ልምድን ከቀሰሙ በኋላ፣ በ1898 ዓ.ም. ‹‹ሆቴል›› የሚል ስያሜ ሰጥተውት ሥራ መጀመሩን የንጉሠ ነገሥቱ ዜና መዋዕል ፀሐፊ የነበሩት ፀሐፌ ገብረሥላሴ ካሰፈሩት መረጃ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ሆቴሉ ከተሠራ በኋላ ሕዝብ ሊጠቀምበት ባለመቻሉ አፄ ምኒልክ መኳንንቱን እየሰበሰቡ በተደጋጋሚ በመጋበዛቸው፣ የእሳቸውን ብድር ለመመለስ መኳንንቱ ‹‹እቴጌ ውቴል ሄደን እንብላ›› ማለት ስላበዙ ‹‹እቴጌ ሆቴል›› የሚለውን መጠሪያ እንዳገኘም ይታወቃል፡፡

መጠሪያው እስከ 1967 ዓ.ም. የቆየ ቢሆንም፣ ደርግ የንጉሠ ነገሥት ሥርዓቱን ካስወገደ በኋላ ስያሜውን ‹‹አውራሪስ›› ብሎ ነበር፡፡ እስከ ውድቀቱ ድረስ (1983 ዓ.ም.) ሲጠራበት መቆየቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ እቴጌ ሆቴል በይፋ የተመረቀው ከ107 ዓመት በፊት ጥቅምት 25 ቀን 1900 ዓ.ም.ነበር፡፡

Source:: Ethiopian Reporter


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles