Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Sport: በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ 10ሩ አክሳሪ ተጫዋቾች

$
0
0

FBL-EUR-C3-TOTTENHAM-PANATHINAIKOS
ከይርጋ አበበ
እለታዊው የእንግሊዙ ዘሰን ጋዜጣ በስፖርት አምዱ ላይ ባለፉት አሥር ዓመታት ቀጣሪዎቻቸውን ለከባድ ኪሳራ ያጋለጡ አሥር ከዋክብት ብሎ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ተጫዋቾች አቅርቧቸዋል። ተጫዋቾቹ ክለቦቹን ሊያከስሩ የቻሉት ከተገዙ በኋላ ጥሩ መጫወት ባለመቻላቸው እንደገና ለገበያ ሲቀርቡ የተሸጡበት ዋጋ መጀመሪያ ከተገዙበት በእጅጉ ያነሰ በመሆኑ ነው ሲል ዘገባው ይገልጻል። ከአስሩ አክሳሪ ተጫዋቾች በተጨማሪ በቅርቡ የቼልሲው ስፔናዊ ኮከብ ፈርናንዶ ቶሬዝ ወደ ባርሴሎና ዝውውር ካደረገ የመጀመሪያውን ቦታ የሚይዝ ይሆናል። ለጊዜው ግን ዘሰን አክሳሪ ብሎ የሰየማቸውን ለአንባቢያን በሚመች መልኩ ከዚህ በታች አቅርበናቸዋል።
10. ሽዋን ራይት ፍሊፕስ
እንግሊዛዊው ፈጣን የመስመር ተጫዋች የሮማን አብራሞቪችን ካዝና ሃያ አንድ ሚሊዮን ፓውንድ ካስወጣ በኋላ ለሦስት ዓመታት በስታንፎርድ ብሪጅ የመጫወት እድል ቢያገኝም የተጠበቀውን ያህል ለክለቡ መጥቀም ባለመቻሉ በጆዜ ሞሪንሆ የመውጫ በር ተከፍቶለት ወደ ቀድሞ ክለቡ ማንቸስተር ሲቲ በስምንት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ፓውንድ ተዘዋውሯል።
9. አልቤርቶ አኩይላኒ
ዣቪ አሎንሶን ለሪያል ማድሪድ አሳልፈው የሰጡት ራፋኤል ቤኔቴዝ ቦታውን ለመድፈን ዓይናቸው ያረፈበት የሮማው መልከ መልካም ወጣት አልቤርቶ አኩይላኒ ነበር። ለእዚህ ጥበበኛ ጣሊያናዊ ሃያ ሚሊዮን ፓውንድ ከፍለው የኮፕሶቹ ቢያደርጉትም ከእንግሊዝ ጋር መላመድ አለመቻሉ ለድጋሚ ሽያጭ እንዲቀርብ ሆነ። በጁቬንቱስ ለአንድ ዓመት በውሰት ከቆየ በኋላ ወደ ፍዮሬነቲና በሰባት ሚሊዮን ፓውንድ በቋሚነት ፈርሟል።
8. ሮቢንሆ
የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ባለሀብቶች ማንቸስተር ሲቲን እንደተረከቡ በ32ሚሊዮን ፓውንድ ከሪያል ማድሪድ በ2008 አስፈረሙት። ወጣቱ ላቲን አሜሪካዊ ለሰማያዊ ለባሾቹ ብዙ አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉ ወደ ሳንቶስ ለውሰት በመሄድ ለአንድ ዓመት ተጫወተ። የውሰት ውሉ ተጠናቅቆ ወደ እንግሊዝ ቢመለስም የታሰበውን ያህል መጥቀም ባለመቻሉ አስራ አራት ሚሊዮን ፓውንድ ከስረው በ18ሚሊዮን ፓውንድ ለኤሲ ሚላን ለመሸጥ ተገደዋል
7. ሔርናን ክሬስፖ
አርጄንቲናዊው ጸጉረ ሉጫ አጥቂ በ2003 የክረምት የተጫዋቾች ዝውውር ሲከፈት አስራ ስድስት ሚሊዮን ፓውንድ ተከፍሎበት በክላውዲዮ ራኒየሪ ዘመን ለቼልሲ ፈረመ። ራኒየሪ ተነስተው ጆዜ ሞሪንሆ ክለቡን ማሰልጠን ሲጀምሩ ላንተ የሚሆን ቦታ የለኝም ብለው ወደ ኤሲ ሚላን በውሰት ሸኙት። ሁለት ዓመታትን በሳንሲሮ ከቆየ በኋላ በነጻ የዝውውር ሂሳብ ለሌላው የሚላን ክለብ ኢንተር ሚላን በነፃ ፈረመ።
6. ማይክል ኦውን
የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ማሸነፍ እፈልጋለሁ ብሎ ከሊቨርፑል ወደ ሪያል ማድሪድ ላቀናው አጭሩ እንግሊዛዊ አጥቂ በስፔኑ ክለብ የሮናልዶና ራኡል ጎንዛሌዝን ክፍያ የከፈለው ኒውካስትል ዩናይትድ ነበር። ነገር ግን ተደጋጋሚ ጉዳቶች ከሜዳ ያራቁት ኦውን ከአራት ዓመታት ቆይታ በኋላ ሴንት ጀምስ ፓርክን በነጻ ተሰናብቶ ኦልድ ትራፎርድ ደረሰ።
5. ኦውን ሃርግሬቭስ
ትውልደ ካናዳዊ የሆነው እንግሊዛዊው የቀድሞ የባየር ሙኒክ አማካይ በ17 ሚሊዮን ፓውንድ ክፍያ ኦልድትራፎርድ የደረሰው በ2006 የውድድር ዘመን ነበር። ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ክፍተቴን በደንብ ይሸፍንልኛል ያሉት ይህ አማካይ ተከላካይ ለጉዳት ቅርብ መሆኑ ብዙውን ጊዜውን በማገገሚያ ክፍል ማሳለፉ ነበር ለከተማ ተቀናቃኛቸው በነፃ ዝውውር አሳልፈው እንዲሰጡት ያስገደዳቸው። የግሌዘር ቤተሰቦችም በልጁ አስራ ሰባት ሚሊዮን ፓውንድ ከስረዋል።
4. ጆ
የስሙ ሆሄያት አጭር የሆነው መለሎው ብራዚላዊ ሲኤስ ሲ ሞስኮን ለቆ ለማንቸስተር ሲቲ የፈረመው በ2008 የውድድር ዘመን በ18 ሚሊዮን ፓውንድ ክፍያ ነበር። ነገር ግን እንደተጠበቀው ክለቡን ማገልገል ባለመቻሉ ለሃገሩ ክለብ ኢንተር ናሲዮናል በነፃ ዝውውር ሊፈርም ችሏል። አስራ ስምንት ሚሊዮን ፓውንድ ያከሰረው ብራዚላዊ አራተኛ ደረጃ ላይ ሊቀመጥ ተገዷል።
3. ኢማኑኤል አዲባዮር
ዌለሳዊው የቀድሞ የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ማርክ ሂውዝ በአርሴናል የተገፋውን አፍሪካዊ ግዙፍ አጥቂ በሃያ አምስት ሚሊዮን ፓውንድ የዝውውር ሂሳብ ወደ ክለባቸው ያዘዋወሩት በ2009 ነበር። ግዙፉ አጥቂ በኢቲሃድ ጅማሮው ጥሩ ቢሆንም ማርክ ሂውዝን ተክተው ክለቡን የተረከቡት ሮቤርቶ «ማንቺኒ አልፈልግም »ስላሉት በተለያዩ ክለቦች በውሰት ሲንከራተት ቆይቶ በመጨረሻም ለሰሜን ለንደኑ ቶተንሃም በአምስት ሚሊዮን ፓውንድ ክፍያ በቋሚነት ፈረመ። ሃያ ሚሊዮን ፓውንድ በማክሰሩ የሶስተኛነት ደረጃን በብቸኝነት ተቆናጠጠ።
2. ዲሚታር ቤርባቶቭ
ቡልጋሪያዊው አጥቂ ካረሎሰ ቴቬዝ ትቶት የሄደውን የማንቸስተር ዩናይትድ አጥቂ ክፍል ሊደፍን 31 ሚሊዮን ፓውንድ ተከፍሎበት ኦልድትራፎርድ ደረሰ። ለኦልድትራፎርዱ ክለብ በአራት ዓመት ቆይታው ሁለት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ጨምሮ የተለያዩ ክብሮችን ቢጎናጸፍም የሮቢን ቫንፔርሲን ለማንቸስተር መፈረም ተከትሎ ከክለቡ እንዲለቅ ሲደረግ በቶተንሃም ቆይታው የሚያወቁት ሆላንዳዊ አሰልጣኝ ማርቲን ዮል በአምስት ሚሊዮን ፓውንድ ለፉልሃም አስፈረሙት። ሃያ ስድስት ሚሊዮን ፓውንድ ክለቡን ለኪሳራ ዳረገ ብሎ ዘሰን ጋዜጣ ሁለተኛው አክሳሪ ሲል ሰይሞታል።
1. አንድሪ ሸቪቼንኮ
ዩክሬናዊው አጥቂ በኤሲ ሚላን ቆይታው የባሎን ዶር ሽልማትንና ተደጋጋሚ የሴሪአው ኮከብ ግብ አስቆጣሪነት ክብርን ተጎናጽፎ ነበር። ሩሲያዊው የቼልሲ ባለቤት የጎረቤት ሀገራቸውን ልጅ ወደ ክለባቸው እንዲመጣላቸው የሳንሲሮ አቻዎቻቸውን በተደጋጋሚ ደጅ መጥናታቸው በ30 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ፓውንድ ይሸጡላቸዋል ። ነገር ግን በክለቡ አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ ስላልተፈለገ የተጠባባቂ ወንበር አሟቂ ሆነ። «የመጫወት እንጂ ወንበር ላይ የመቀመጥ ልክፍት የለብኝም » እያለ ምሬቱን ደጋግሞ ሲገልጽ የቆየው አጥቂ ፣ለቀድሞ ክለቡ ኤሲ ሚላን በውሰት ሲጫወት ቆይቶ በመጨረሻም የሮማን አብራሞቪችን 30 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ፓውንድ እንደ ጉም ብን አድርጎ ወደ አሳዳጊ ክለቡ ዳይናሞ ኬቭ በነጻ ዝውውር ሄደ ። የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የአስር መቱ ቁጥር አንድ አክሳሪ ተጫዋች ለመባልም ተዳረገ ።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>