Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የግልና የ«ብሄር» ነፃነት በኣቶ ገብሩ ኣስራት እይታ

$
0
0

ኣምሃ ኣስፋው

«ሉኣላዊነትትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ» የተሰኘው የኣቶ ገብሩ መፅሃፍ ከፍተኛ ተቀባይነትና ኣድናቆት እንዳተረፈ በየድረ ገፁ ተወስቷል። መፅሃፉ በኣማርኛው ጥራትም ሆነ በይዘቱ ጥልቀት ሊደነቅ የሚገባው ይመስለኛል። እርግጥ ብዙ የፊደል ግድፈቶች ኣሉበት። ይህ ግን፣ የኣርታኢዎች ስህተት ብቻ ሳይሆን፣ መቀምሮች (Computers) ማንም ሳያዛቸው በራሳቸው ፊደሎችን የመቀያየር ጠባይ ስላላቸውም ጭምር ነው። ይህ መፅሃፍ የደረሰን ከወያኔ/ህወሃት ኣባል እይታ ቢሆንም የዘመኑን ታሪክ ለማወቅ እጅግ ጠቃሚ ይመስለኛል። ሁኔታው ሲፈቅድ፣ ኢትዮጵያዊያን ልጆች ከሚማሩባቸው መፃህፍት ኣንዱ ቢሆን ከተለያዩ ኣቅጣጫዎች በሚመጡ ሃሳቦች የታነፁ ዜጎችን ለማፍራት ይጠቅማል የሚል እምነት ኣለኝ።
የኣቶ ገብሩን መፅሃፍ በኣማርኛው ጥራትና በይዘቱ ጥልቀት ባደንቀውም፣ የኣንድምታውን ትክክለኛነትም ሆነ የጭብጡን እውንነት እቀበላለሁ ማለቴ ኣይደለም። የዛሬው ፅሁፌም ምክንያት ከማይስማሙኝ ኣስተሳሰባቸው ኣንዱን ለመተቸት ነው፤ በንግግር ነፃነት ስለሚያምኑ ትችቴ ቅር እንደማያሰኛቸው በማመን።
Gebru Asrat
ኣቶ ገብሩ ባለማለት፣ የማለትን ጥበብ የተካኑ ፖለቲከኛ ይመስላሉ። የኣፄ ቴዎድሮስን የጀግንነት ኣሟሟት ሲተርኩ፣ ጠላቶቻቸውን፣ እንግሊዞችን፣ እየመሩ ያመጡት ኣፄ ዮሃንስ መሆናቸውን ይዘሉታል። የኣፄ ምኒልክንና የጣሊያኖችን ውል ደጋግመው ሲያትቱ፣ ጣሊያኖች ኤርትራን በኣፄ ዮሃንስ ዘመን ያልያዟት ለማስመሰል ይሞክራሉ። በሻብያና በኢትዮጵያ ህዝብ መሃከል በተደረገው የመጨረሻ ጦርነት፣ ከምእራብ እስከምስራቅ፣ ከሰሜን እስከደቡብ ያለውን ህዝብ ጀግንነት ሲያሞግሱ፣ ሸዋን እንዳልነበረ ሁሉ ይዘሉታል። በምርጫ 97 የቅንጅትን ኣባል ማህበሮች እንቅስቃሴ ሲገልፁ፣ የመኢኣድ ኣስተዋፅኦ እንዳልነበር፣ እነ ኣቶ ሃይሉ ሻውል ደግሞ እንዳልተፈጠሩ ለማድረግ ሞክረዋል። በደፈናው «ነባር ፖለቲከኞች» ይሏቸዋል። ኣድሃሪ፣ ፊውዳል፣ ነፍጠኛ፣ ትምክህተኛ፣ ምናልባትም እንደ ቀስተ ደመና የምሁራን ሳይሆን የደንቆሮዎች ስብስብ ከሚል ኣስተሳሰብ ብዙም የራቁ ኣይመስለኝም።

እነዚህ የቀድሞ ባለስልጣኖች ስልጣናቸውን ሲነጠቁና ጥቅማቸውን ሲነፈጉ የሚያሰሙት የ«ተሳስተን ነበር» ጩኸት ይገርመኛል። እንዲያውም የጥላሁንን ዘፈን ያስታውሰኛል።

የልብን ሰርቶ ይቅር በሉኝ፣
ምንስ ኣጠፋሁ ምን በደልኩኝ፣

የሚለውን። በስልጣን ላይ እያሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ስቃይ ካልታያቸው፣ ስልጣኑን እንደገና ቢያገኙ የህዝቡ በደል ተመልሶ እንደማይሰወርባቸው ምን ዋስትና ኣለን? ኣሁንም ቢሆን፣ የኣቶ ገብሩ ኩራታቸው፣ ጭንቀታቸውም ሆነ ተስፋቸው ለትግሬና ለኤርትራ ህዝብ ብቻ ነው። ይህንን ለመረዳት በመፅሃፉ ሽፋን ላይ ያለውን ካርታ መመልከቱ ብቻ ይበቃል። የመፅሃፉ እኩሌታ የሚነግረን የትግሬን ህዝብ ታላቅነትና ጀግንነት ነው። ካንድ ቦታ፣ ኣንዱን የደርግ መኮንን «ሻብያን ማሸነፍ ለኛ ቀላል ነበር። ሞራላችንን የሰበራችሁትና፣ ድል ያደረጋችሁን እናንተ(ወያኔዎች) ናችሁ።» ብሎ እንዲናገር ያደርጉታል። ከእውነተኛ ሰው ይልቅ የመድረክ ገፀ ባህሪ ነው የመሰለኝ። የትረካቸውን እውነትነት በቦታው ለነበሩና ለታሪክ ኣዋቂዎች ትቼ ወደ ተነሳሁበት ኣላማ ልመለስ። በመፅሃፋቸው ማጠቃለያ ላይ፣ ስለብሄር ነፃነት፣ ስለግል ነፃነትና ስለኢትዮጵያዊነት ያትታሉ።

በመጀመርያ ሌሎችም እንዲያስቡበት ኣንድ ኣንድ ጥያቄዎችን እና የኣቶ ገብሩን ሃሳቦች ላቅርብ።

1. ብሄር ማለት ምን ማለት ነው? ኣቶ ገብሩ ይህንን ጥያቄ ኣይነኩትም፤ ብቻ ትርጉሙ ኣከራካሪ እንዳልሆነ ሁሉ «የብሄር ነፃነት» የሚለውን ሃሳብ እንደልብ ይጠቀሙበታል። መዝገበ ቃላቱ፣ መንደር፣ ኣውራጃ፣ ምድር፣ ኣለም፣ ኩል (Universe) ፣ ባንድ ቋንቋ የሚናገሩ፣ ወገን፣ ነገድ፣ ህዝብ፣ ኣገር፣ ባንድ መንግስት ስር የሚተዳደሩ፣ ባንድ መድበል ስር የተጠቃለሉ ሙሉ መፅሃፎች እያሉ እጅግ ሰፊ የሆነ ትርጉም ይሰጡታል። ሆኖም ኣቶ ገብሩ መፅሃፋቸውን የፃፉት በኣማርኛ ስለሆነ የብሄር ትርጉም ኣማርኛ የተቀበለው ብቻ መሆን ይገባው ነበር። ትርጉሙን በመቀየር ኣዲስ የኣማርኛ ቃል መፍጠራቸው ከሆነም፣ ከመጠቀማቸው በፊት ቃሉን መደንገግ(Define) ነበረባቸው። ዘመናዊ ኣማርኛ የተቀበለው የብሄር ትርጉም «በኣንድ መንግስት ስር የሚተዳደር ህዝብ» የሚለውን ነው። ለዚህም ነው «የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ» እንጂ «የትግሬ ብሄራዊ ቡድን፣ የኣማራ ብሄራዊ ባንክ» የማንለው። ኣቶ ገብሩ ጎሳ የሚለውን ቃል ኣይወዱትም እንጂ የሚፈልጉትን ሃሳብ «ጎሳ» ወይም «ነገድ» የሚሉት ቃሎች የተሻለ ይገልፁላቸው ነበር። ግን፣ ወያኔዎች ሁሌም ድብቅ ኣላማ ስላላቸው «ብሄር» ሲሉ «ኣስፈላጊ በሆነ ጊዜ ነፃነቱን የሚያውጅ የህዝብ ስብስብ» ማለታቸው ይሆናል። ለዛሬው ግን የብሄር ትርጉም ልፅፈው የፈለግሁት ጉዳይ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ስለሌ፣ ባላምንበትም የኣማራ ብሄር፣ የትግሬ ብሄር፣ የኦሮሞ ብሄር፣ የደቡብ ብሄር … እየተባሉ የሚጠሩ ህዝቦች ኣሉ፣ የሚለውን ሃሳብ ተቀብየ ልቀጥል።

2. «ፍፁማዊ የግል ነፃነት» በሚል ሃረግ የግል ነፃነት ደጋፊዎችን ለማጣጣል ይሞክራሉ። ፍፁማዊ የሚባል ነገር ኣለ? እንኳንስ በህብረተሰባዊ ስይንስ ይቅርና በሂሳብና በፊዚካ ኣለምም ፍፁማዊነት እንደሌለ ሳያውቁት ቀርተው ኣይመስለኝም። ሆኖም ፍፁማዊነት የለም ተብሎ ኣላስፈላጊ የሆኑ ኣምባገነናዊ ስርኣቶች በህዝብ ላይ ኣይጫኑም።

3. የብሄር ነፃነት ማለት መዝፈንና መጨፈር ብቻ ኣይደለም ብለው ይነግሩናል። የብሄር ነፃነት የሚሰጠን፣ ግን የግል ነፃነት ሊያሟላው የማይችል ምሳሌ ሊሰጡን ይችላሉ? ብየ ጥያቄየን ሳልጨርስ መልሱን ይሰጡናል። የብሄር ነፃነት ልጆችህን በራስህ ቋንቋ ማስተማር፣ ቋንቋህን ማሳደግና ማበልፀግን ያካትታል ብለው።

ሶስተኛዋን ጥያቄ ልውሰድና ሃሳቤን ላጠቃል።
ቋንቋ ሊያድግ የሚችልባቸው መንገዶች ሁለት ናቸው።
1. ሀ. ልጆችን በሚፈልጉት ቋንቋ ማስተማር። ለ. በሚፈልጉት ቋንቋ መፃፍ። መ. በሚፈልጉት ቋንቋ ላይ ምርምር ማካሄድ። ሰ. የሚፈልጉትን ቋንቋ በመገናኛ ብዙሃን ማሰራጨት።

2. ሌሎች ቋንቋዎች እንዳያድጉ በመከልከል የሚፈልጉት ቋንቋ ብቸኛ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ። ኣማርኛ ኣድርጓል ተብሎ እንደሚታማው ማለት ነው።
እውነተኛ ዴሞክራሲ ካለ… ግን፣ እውነተኛ ዴሞክራሲ ማለት ምን ማለት ነው? ለኔ ዴሞክራሲ ማለት የግለ ሰብን መብት የሚያከብር እንጂ የኣብዛኝውን ህዝብ ፍላጎት የሚያስፈፅም ስርኣት ኣይደለም። ኣብዛኛው የኣሜሪካ ህዝብ ባርነትን ይደግፍ ነበር። የባሮቹን የግል መብት ይፃረራልና እንድያ ኣይነቱ ስርኣት እውነተኛ ዴሞክራሲ ሊሆን ኣይችልም።
እውነተኛ ዴሞክራሲ ካለ፡
geberu asrat new book
ማንኛውም ሰው በሚወደው ወይም ያተርፈኛል በሚለው ቋንቋ የሚያስተምር ትምህርት ቤት መክፈት ይችላል። ማንኛውም ሰው ልጁን የፈለገው ትምህርት ቤት ሰዶ ማስተማር ይችላል። የዚህም ምንጩ የግለሰብ ነፃነት እንጂ የብሄር «ነፃነት» ኣይደለም። የራዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያ ማቋቋም፣ ጋዜጣና መፃህፍትን ኣትሞ ማሰራጨትም የግል እንጂ የብሄር «ነፃነት» ኣይደለም። እርግጥ ሰዎች ተሰብስበው ከላይ
የተገለፁትን ሁሉ በቡድን ማድረግ ይችላሉ። ይህም ቢሆን ግለሰቦች መብታቸውን ሰብስበው የፈጠሩት ቡድን እንጂ፣ ቡድኑ የቸራቸው ነፃነት ኣይደለም። እነዚህ ተቋሞች በመንግስት ደረጃም ሊመሰረቱ ይችላሉ። ኣሁንም ቢሆን ግለሰቦች ነፃነታቸውን በምርጫ ላቆሙት መንግስት ኣካፍለውት እንጂ መንግስት ለግለሰቦች የሚታደል ነፃነት የለውም።

ታድያ የብሄር ወይም የቡድን «ነፃነት» ጥቅሙ ምን ላይ ነው? ትሉኝ ይሆናል። በመጀመርያ የብሄር ወይም የቡድን ነፃነት የሚሉት ነገር የለም፣ የብሄር ኣምባገነንነት እንጂ። ኮሚኒስቶች እውነቱን ግልፅ ኣድርገው ሲናገሩ «የላብ ኣደሩ ኣምባገነንነት» እንደሚሉት ማለት ነው። የቡድን ወይም የብሄር «ነፃነት» በቁጥር ሁለት የተገለፀውን ኣይነት፣ የሌሎችን የግል ነፃነት መግፈፊያ መሳሪያ ነው። ከኢትዮጵያዊነት ጋርም ጨርሶ ኣይጣጣምም።
ምሳሌ ልስጥ፡፡ የብሄር «ነፃነት» የሚፈጥራቸው ህጎች የሚከተሉትን ይመስላሉ።

• ትግሬ ውስጥ ትግሬ ላልሆነ ሰው የንግድ ፈቃድ ኣይሰጥም።
• ኦሮሞ ክልል ውስጥ ጉራጌኛ መናገርም ሆን መፃፍ ክልክል ነው።
• ሃረር ውስጥ ኣማራ መምረጥም ሆነ መመረጥ ኣይችልም።
የብሄር «ነፃነት» (ትክክለኛው ስሙ ግን የብሄር ኣምባገነንነት ሊሆን ይገባዋል) ጥቅሙ ኢትዮጵያዊነትን መወሰን ብቻ ነው። ስለዚህ ከኢትዮጵያዊነት ጋር ሊታረቅ የሚችል ባህርይ የለውም።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>