Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የጠለምትና የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ የጎንደሬዎች . . .(አንዱዓለም ተፈራ)

$
0
0

አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ

ታህሣሥ ፳ ፭ ቀን ፳ ፻ ፯ ዓመተ ምህረት ( 01/03/2015 )

welkaiyt

በጠለምት፣ በበየዳ፣ በጃናሞራ፣ በወልቃይት፣ በጠገዴ፣ በአርማጨኾ ነዋሪው እየተባረረ፣ ሀብቱ እየተዘረፈ፣ ያንገራገረው እየተገደለ፤ ሰው በምሬትና በሰቀቀን ኑሮውን መግፋት አቅቶት አጣብቂኝ ላይ ገብቷል። ትናንት ቡያ ነበር ክልሉ። ትናንት በሀከር ነበር ክልሉ። ቀጥሎ ራስ ደጀንን ወደነሱ አካተቱት። ጠገዴን ጠቀለሉት። ገፍተው ስሜን አውራጃን በሙሉ ጠቀለሉ። ወገራ አውራጃን ሽራርፈው ወሰዱና ጎንደር አውራጃን ተጠጉ። አሁን ዘለው የጎንደር ከተማውን ገነት ተራራ፤ የትግራይ መሬት እያሉ ለትግራይ ልጆቻቸው እያሰተማሩ ነው። ጎንደር ከምድረ ገጽ እንድትጠፋ እየተገፋ ነው። ይህ የመኖርና ያለመኖር፤ ውሎ የማደርና በወጡበት የመቅረት፤ ተገፍቶ ተገፍቶ የገደል ጫፍ ላይ የተንጠለጠለ ሕይወት ሕዝቡን ሰቅዞ ይዞታል። ይህ ጉዳይ የጎንደሬዎች ብቻ ጉዳይ አይደለም። አዎ! በዋግም ተመሳሳይ ተግባር እየተፈጸመ ነው። የዋግ ጉዳይ የወሎዬዎች ብቻ ጉዳይ አይደለም። በመተከል ተመሳሳይ ተግባር እየተፈጸመ ነው። ይህ ጉዳይ የጎጃሜዎች ብቻ ጉዳይ አይደለም። በሐረርና በአርሲም ሲጀምር በግልጽ ይህ ጉዳይ ተተግብሯል። በጉራፈርዳና በደቡብ ክልል የተደረገው ኢትዮጵያዊያንን በያለንበት ሰቅጥጦናል። ይህ ጉዳይ የአንድ አካባቢ ወይንም የተወሰኑ ሰዎች ጉዳይ አይደለም። ይህን ካልተገነዘብንና መልስ ካላዘጋጀን፤ ለተከታዩ ሂደት ተጠያቂዎች፤ እኛው ጆሯችንን ደፍነን፣ ዓይኖቻችንን ጨፍነን፣ ዝም ያልነው በሙሉ ነን። የአካባቢው ሰው ብቻ ተቆርቋሪና እርምጃ ወሳጅ ነው የሚል እምነት ካለን፤ ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በምንም መንገድ ያልተለየን ነን። ለምን ይኼን ጉዳይ ክብደት ሠጥቼ የጽሑፌ ማጠንጠኛ እንዳደረግሁት ላስረዳ፤

ጉዳዩ፤ ጠለምት፣ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ አርማጨኾ፣ በየዳ፤ ብራ ዋስያ፣ ሻግኔና ላሄን፣ ድብ ባሕር፣ አብደራፊና ሁመራ፤ከጎንደር ተነጥቀው ለትግራይ ተሠጥተዋል። በጠቅላላው የስሜንና የወገራ አውራጃዎች ወደ ትግራይ ገብተዋል። ይህ በጎንደር ሲሆን፤ በተመሳሳይ መልኩ የወሎው ዋግ ተነጥቆ ለትግራይ ተሠጥቷል።

ጉዳዩ፤  በነዚህ ቦታዎች የነበረው ነዋሪ፤ በደቡብ ኢትዮጵያ የሚኖረው አማራ፤ ሀገርህ አይደለም ተብሎ እንደተፈናቀለው፣ እንደተገደለው፣ ሀብቱ እንደተነጠቀበትና እንደተባረረው ሁሉ፤ እኒህም ለዚሁ ዕጣ ተዳርገዋል። መሬታቸው ብቻ ሳይሆን፤ ሀብታቸው ተዘርፏል። ከብቶቻቸው ተነድተዋል። እህላቸውን ተነጥቀዋል። ያንገራገሩት ተገድለዋል። እሽ ያሉት በወባና በተላላፊ በሽታ እንዲያልቁ ባልሆነ ቦታ ሰፍረዋል።

ጉዳዩ፣  በነዚህ በተነጠቁ ቦታዎች አጎራባች ሆነው የሚገኙት ነዋሪዎች፤ የተነጠቁትን ወገኖቻችንን በማስጠጋት ለወደፊት የባለቤትነት ጥያቄ እንዳያነሱና ሰላም እንዳያገኙ፤ ጎንደሬዎችን እርስ በርስ በማፋጀት ለማጥፋት፤ ሌላ አጀንዳ አውጥቶ፤ በአርማጨኾና በጭልጋ አካባቢ ያሉትን፤ ቅማንትና አማራ በማለት ከፋፍሎ፤ ጥልቅ ግጭት በመፍጠር ለማተላለቅ ቁስቆሳውን እያጧጧፈው ነው።

እንግዲህ ነጥቡ ይህ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሠጠው የሚገባው ሀገራዊ አጀንዳ ነው። ያካባቢው ወገናችን ለብቻው ጥቃቱን እስከዛሬ ችለውታል። በዝርዝር ላስቀምጥ፤

  • ከሌሎች የሀገራችን ክፍሎች በባሰ መንገድ በጎንደር በኩል የኢትዮጵያ ደንበር በስፋት ተደፍሯል። መሬቱ ለሱዳን ተሠጥቷል። ከሌሎች የሀገራችን ክፍሎች በባሰ መንገድ የጎንደር ለም መሬት ወደ ትግራይ ተወስዷል።
  • በነዚህ አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩት ወገኖቻችን፤ ተለቅመው በመባረር በቦታቸው የትግራይ ሰዋች እንዲሰፍሩ ተደርገዋል። ሕዝቡ ማንነቱን ሳይጠየቅ የተደረገው ነጠቃ፤ ከውጭ የመጣ ወራሪ ከሚያደርገው ግፍና በደል ያልተለየ ነው።
  • በጎንደር ከተማ ውስጥ ሥልጣኑንና ሀብቱን አሟጠው የያዙት የትግራይ ተወላጆች ናቸው። ይህ የከተማውን ወገናችን በጣም ከማማረሩ በላይ፤ የቂም መርዝ እየተከለ ነው።

ይህ ያካባቢውን ወገናችን ወደየት ይገፋዋል?

  • ቀሪው ኢትዮጵያዊ ስላልደረሰልኝ፤ ዝም ብዬ መጠበቄ አያዛልቀኝም። እናም ራሴን ላድን ወደሚል፤
  • የራሴን ዕድል ራሴ ልወስን ወደሚል፤
  • የኔ አጀንዳ የሌሎች አጀንዳ ስላልሆነ፤ የራሴን አጀንዳ ራሴ ብቻ ማንገብ አለብኝ ወደሚል፤

እና ምን መደረግ አለበት?

ሀ)       ታሪኩን መርምረን ማጥናት የያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው። በተለይ በትግሉ ዙሪያ የምንገኝ በሙሉ፤ ይህ ግዴታ፤ ከራሳችን አልፎ ሌሎችን በዚህ ለማጠቃለል ኃላፊነቱ አለብን። ለዚህ በጉዳዩ የጠለቀ እውቀት ያላቸውና አካባቢውን ጠንቅቀው የሚያውቁት ይምሩ።

ለ)       የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በአሁኑ ሰዓት፤ ትግሬዎችና አማራዎች በቦታ ባለቤትነት ሳቢያ፤ በመካከላቸው የዕልቂት ጦርነት እንዲኖር እያራገበ ነው። አለመታደል ሆኖ መተላለቁ ተጀምሯል። የመለስ የኢንተራሐምዌ ምኞት የሚተገበርበት በር እየተከፈተ ነው። የርሱ ምኞት የራሱን ሥልጣን ለማራዘም ማማካኛ ነበር፤ ሀቅ ሲሆን ደግሞ የራሱን ደጋፊዎችና ወገኖች አደጋ ላይ ሊጥል ነው። እናም ይህ ሁላችንን ሊያሳስበን ይገባል። ክብደት እንሥጠው።

ሐ)      ዋናው መፍትሔ አንድ የትግል ማዕከል ባስቸኳይ መፍጠሩ ነው። በየቦታው የተኮለኮለው የየራስ ድርጅትና የየአካባቢ መሰባሰብ፤ ለኢትዮጵያ መጥፋት ምክንያት ይሆናል። በየድርጅቶቻቸው ተሸጉጠው እኔ እንዲህ፣ እነሱ እንዲያ የሚባለው ፉገራ ያቁም። ለነገዋ ኢትዮጵያ፤ ተወቃሹ የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባር ሳይሆን እኛው ራሳችን ነን። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርማ የኢትዮጵያ ጠላት ነው። ማን ለኢትዮጵያ አልተውቆረቆርክም ብሎ ያማዋል! ይህ ድርጅት እኮ፤ “እኛ” እና “እነሱ” በማለት፤ የኢትዮጵያን ህዝብ ጠላት ብሎ ፈርጆ፤ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የቆመና የራሱን አዲስ ሀገር ለመመሥረት ካልሆነለት ደግሞ ትግራይን ገንጥሎ የራሱ ሀገር ለማድረግ ቆርጦ የተነሳ ጠላት ነው። እናም ሁሉን የየአካባቢ አጀንዳ ባንድነት ያቀፈ የትግል ማዕከል ባስቸኳይ ካልተፈጠረ፤ እንዲህ የባሳቸውንና በመኖርና በመጥፋት መካከል ያሉትን መቆጣጠር አይቻልም። ብሶታቸው ትክክል ነውና የሚወስዱትም እርምጃ ትክክለኛ ይሆናል። በሚያውቁትና በጃቸው ባለ እንጂ በምኞት በኛ አጀንዳ አይታገሉም።

መ)      በተጨማሪ ደግሞ፤ እስላሞች ለብቻቸው፣ በደቡብ የተፈናቀሉት ለብቻቸው፣ መምህራን ለብቻቸው፣ ነጋዴዎች ለብቻቸው፣ ቤት ያጡ ለብቻቸው እየተባለ የሚደረገው ተከላካይነት በተናጠል ለመመታት መዘጋጀት ነው። ለየብቻ እስከቆምን ድረስ ደግሞ፤ በያንዳንዱ ለየብቻ በቆመ ተከላካይ ስብስብ ውስጥ ያሉ ጠንካራ አባላት፤ ወደፊት በመግፋት ብቻቸውን ለማደጋቸው ጥርጣሬ ሊኖረን አይገባም። ደግሞም የቴክኖሎጅው አመቺነትና የወጣቶቻችን ቀልጣፋነት፤ ባጭር ጊዜ ውስጥ ለመሰብሰብና ለማደግ እንደሚያስችል የማይረዳ የለም። ስለዚህ ልንሰጋ ይገባናል። ስለዚህ፤ እያንዳንዳችን የያዝነውን አጀንዳ፤ ከዚህ ሀገራዊ ጉዳይ አንጻር ክብደትና ቅለቱን በማነጻጸር፤ ባስቸኳይ አንድ የትግል ማዕከል መፍጠር አለብን። ለዚህ መፈጠርና አለመፈጠር ተጠያቂዎቹ እኛውና እኛው ብቻ ነን።

የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በጎንደር የሚያደርገው ተግባር፤ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ከሚያደርገው ግስገሳ የተከተለ ነው።  በቀጥታ ሲታይ ለሙን መሬት በቋሚነት ለመውሰድ፤ ግጭቱን ምክንያት ለማድረግና ወታደሮቹን ለማስፈር ያቀደው ሲሆን፤ በተዘዋዋሪ መንገድ ደግሞ፤ ትግራይን ገንጥሎ ለመውሰድ ካለው ዕቅዱ አኳያ፤ የትግራይን የመሬት ይዘት ዓለም አቀፋዊ ድንበር ለማድረግ፤ የአካባቢውን ነዋሪ ለማጥፈት ያዘጋጀው ነው። ቁጭ ብለን ሞት እንዲወስደን እንጠብቅም ያሉት፤ ራሳቸውን መከላከል ጀምረዋል።

ይህ ጉዳይ፤ በሐረር፣ በአርሲ፣ በጉራፈርዳና በሌሎች አካባቢ በአማራው ወገናችን ላይ የደረሰው ቀጣይ እርምጃ ነው። ብዙዎቹ በደረሰባቸው ግፍ ምክንያት፤ ከፍተኛ የንብረትና የሕይወት መስዋዕትነትን እየከፈሉ ናቸው። ጀግንነቱ፣ ቆራጥነቱ፣ ለወገን ያላቸው ፍቅር የማያጠያይቀው የአካባቢው ተወላጆች፤ ዝም ብሎ ማየቱ በቅቷቸዋል። ሌሎች ኢትዮጵያዊ ወገናቸው፤ ጭንቀታችሁ ጭንቀታችን ነው፤ ቁስላችሁ ቁስላችን ነው፤ ብለው አብረዋቸው ካልቆሙ፤ ያናንተ ጉዳይ የኛም ጉዳይ ነው ብለው አብረው ካልተባበሩና የአካባቢው ተወላጆች ብቻውን ከቆሙ፤ የብቻቸውን አጀንዳና የብቻቸውን እርምጃ እንዲወስዱ መንገዱን እየቀደድንላቸው ነው። ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳይ ነው። ለብቻቸው መቆም የለባቸውም ብሎ ከሩቅ መደንፋት ይቻላል። ይህ ግን አፍራሽ እንጂ ገንቢ አይደለም። ለብቻቸው እንዳይቆሙ አብሯቸው መሰለፍ ያስፈልጋል።

ለአካባቢው ተወላጆች፤

ላላችሁባቸውና ለምታምኑባቸው ድርጅቶች ንቁ ተሳታፊዎች በመሆን፤ የናንተ ጉዳይ የየድርጅቶቹ ጉዳይ እንዲሆን ጣሩ። በመሠረቱ ደግሞ በአንድነት ታግለን ይሄን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ማስወገድ ካልቻልን፤ ወዳልታወቀ የወደፊት እየተጓዝን ነው። እናም ትኩረታችን ይሄን መንግሥት ለማስወገድና በሂደቱ ጉዳያችን ቅድሚያ የሚሠጥበት እንዲሆን መጣር አለብን። አሁንም ዋናው መፍትሔ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መውደቅና የኢትዮጵያ ሕዝብ መንግሥት መቋቋም ስለሆነ፤ ይሄን መግፋት አለባችሁ። በሂደቱ ይህ የጎንደር ጉዳይ ሀገራዊ አጀንዳ ሆኖ እንዲቀርብ መጣር የሁላችን ኃላፊነት ነው። ይህ ኢትዮጵያዊነትን መቀበል ማለት ነው። ይህ ጉዳይ የኔ ብሎ መነሳት፤ ከፍተኛ ትኩረት ሊሠጠው ይገባል። eske.meche@yahoo.com


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>