የቴዲ አፍሮ ዝግጅት በፋራንክፈርት ሲደረግ በቦታው ተገኝቼ ነበር ። ብዙ ጊዜ ዘፋኝ ሲመጣ አልገኝም ። ዘንድሮ ግን ወያኔ በእሱ ላይ ያደረገውን ተንኮል መቃወም የሚቻለው በዝግጅቱ በመገኘት በመሆኑ ሰብሰብ ብለን ተገኝተን ነበር። ሰልፉ ሳይጠነክር ቀደም ብለን ለመግባት በጊዜ ነበር የደረስነው። ሰዓቱን ጠብቀን ከፍለን ገባንና ጥግ ላይ ወንበር ፈልገን መጠበቅ ጀመርን ። እሱ ወደ መድረክ እስከሚወጣ በልዩ ልዩ ዘፈን እየተዝናናን ቆየን ። ወጣት ይጎርፋል፣ አለባበስ ይታያል፣ ዓመት በዓሉን ዓመት በዓል አስመስለውታል። የአዲስ ዓመት ዋዜማ . . . ለቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ዝግጅቱ ተጠናቋል። አዳራሹ እኩለ ሌሊት ላይ እየሞላ መጣ።
የሚጠበቀው ቴዲ አፍሮ ወደ መድረክ ሲወጣ ወጣቶች ያብዱ ጀመር። እሱ “ፍቅር ያሸንፋል“ ይላል። ወጣቶቹ ይጮኻሉ። “እወዳችኋለሁ“ ሌላ ጩኸት። አዳራሹ ድብልቅልቅ አለ ! ደስታና ጩኸት ይፈራረቁ ጀመር። ለአንድ ጊዜ እንኳን ቢሆን ይህንን ዓይነት አቀባበል የኢትዮጵያ ገዥዎች መቼ ይሆን የሚያገኙት ? ብዬ አሰብኩ። በ2015 ይኽንን ብመኝ የተጋነነ ይሆናል?
በተከታታይ አራት ዘፈን ተዘፈነ ። ልዩ ልዩ ዓይነት ጭፈራ ታየ ፣ ውስጥ ሙዚቃ ፣ ደጅ ርችት ፣ መድረኩ ላይ ጭፈራ ቀለጠ ። 2015 በደስታ ተጀመረ ። ለዛሬም ቢሆን ችግራችንን ሁሉ ልንረሳ የተስማማን ይመስላል። ተስፋችንን አንግበን ለፍቅር የተነሳን ሆንን። ፍቅር ያሸንፋል ቴዲ ፣ እኛም ያሸንፋል . . . ። አጠገቤ የነበረው ጓደኛዬ ግን ዘመን መቀየሩን ረስቶት ያሸንፋል እያለ ግራ እጁን ቡጢ ጨብጦ መፈክር ያሰማል። ሌላው አውርድ እጅህን እዚህ ቡጢ አያስፈልግም ይለዋል። የፍቅር ጠላቶችን አደቅበታለሁ ሲል ተሳሳቅን። ወጣቱ መድረኩ አካባቢ እኛ ጥግ ጥጉን ይዘን እስክስታውን ወረድነው።በቴዲ ዘፈን ምንጃርኛም ይሞከራል። ያልተሞከረ አልነበረም። ፍራንክፈርት ቀለጠች . . . ቤት የቀረም ሰው ያለ አይመስልም . . . አዳራሹ ምንም ትልቅ ቢሆን ተጨናንቋል። አዲስ ዘመን በአዲስ ተስፋ ተጀመረ።
እንደ ድንገት አንድ ወጣት ከጭፈራው ብዛት ደክሞት አጠገቤ ተቀመጠ።
ደከመህ ? ብዬ ጠየቅሁት ።
ጭንቅላቱን በማወዛወዝ አዎን አለኝ።
ትንሽ ትንፋሽ እሲከያገኝ ጠበቅሁና ቴዲን ትወደዋለህ ? መልሱን በአማርኛ ስጠብቅ በትግርኛ ቀጠለ። በንግግር ልንግባባ አልቻልንም። አማርኛ አይችልም። ቴዲ አዲስ ዘፈን ሲጀምር ወጣቱ አብሮት ይዘፍናል። ወጣቱ የቴዲን ዘፈን በቃሉ ያወርደዋል። ከቴዲ አፍሮ ጋር በዘፈን ይግባባሉ። ከእኔ ጋር ግን በቋንቋ ልንግባባ አልቻልንም። ለዘመናት የቆየው ጦርነት ምክንያት የወጣቱን ቋንቋ አለመናገራችን ይሆን?? ሃሳብ መጣ ። አሁን ስለ ወጣቱ የማወቅ ፍላጎቴ ጨመረ ።
ሁሉን ዘፈን ታውቀዋለህ ?
አሁን ገባው መሰለኝ አዎ ሁ.. ሉ ን አለኝ በአማርኛ በትግርኛ አነጋገር ። ገና ዘፈኑ ከማለቁ በፊት ልጁ እየሮጠ ወደ ዳንሱ ገባ ። እኔን ጥሎ ከቴዲ ጋር በሙዚቃ ሊግባባ ከነፈ . . . ።
ከጎኔ የነበረው ለጭፈራ የሄደው የጓደኛዬ ትርፍ ቦታ ለወጣቶች መተዋወቂያ ጠቀመኝ ። አንዲት በረጅም ጫማ ላይ የቆመች ወጣት መጣች ።
“መቀመጥ ይቻላል?“ እየተቅለሰለሰች ጠየቀችን ። ባለቤቱ እስከሚመጣ ፈቀድኩ ።
“ይህ ጫማ እግርሽን አያደክመውም?“ ወሬ መጀመሪያዬ ሆነ ።
“ትለምደዋለህ ፤ ከዚያ ብዙም አይሰማህም።“ ስለ ጫማው አስረዳችኝ።
“እዚህ ሃገር ቆይተሻል?“ የሚቀጥለው ጥያቄ ነበር ።
“ ገና አራት ወሬ ነው ?“
“ገና አዲስ ነሻ ? ”
” አዎ ነኝ።”
“የት ነው የተመደብሽ ? ” ከፍራንክፈርት ራቅ ያለ ቦታ ጠራችልኝ ።
“እና ለቴዲ አፍሮ ብለሽ ነው ከዛ ድረስ የመጣሽው ? ”
“ታዲያስ!” አለችኝ በመደነቅ ። አመላለስዋ ለቴዲ ያልተመጣ ለማን ይመጣል? የሚል ጥያቄ ያዘለ ይመስላል።
ቴዲ አዲስ ዘፈን ጀመረ ። ጥያቄዬን ሳልጨርስ ጥላኝ ነጎደች። ጫማዋን ግን እዛው ጥላው በረረች።
እኔም በተራዬ መድረኩ ጋር ብቃ አልኩ። ከዘፈኖቹ ማህል ቴዲ መፈክሩን ያሰማል። “ ፍቅር ያሰኝፋል“ ወጣቶቹ በሞላ በአንደነት እንደ መፈክር ይደግሙታል ። ሲዘፍን ይከተሉታል ፣ ቴዲ አውቆ ማሕል ላይ ሲያቆም እነርሱ ይሰማሉ ። በዚህ ምሽት ሁሉም ደናሽ ፣ ሁሉም ዘፋኝ ሆኗል ። ጩኸቱ ስለበዛ ለዕረፍት ወደ ውጭ ወጣ አልኩ ። አዳራሹ ውስጥ አንድ ሺህ የሚሆን ሰው አለ ። ደጅ ከ200 -300 የሚሆን ሰው ለመግባት ቆሟል። ይህ ሁሉ ሰው እንዴት ሊሆን ነው ራሴን ጠየቅሁ ። ሕዝብ እንደ ጉድ ይጎርፋል። ይዘፈናል ይጨፈራል፣ ይፈከራል ፣ ቴዲ እውዳቸኋለሁ ይላል፣ ወጣቶቹም በጩኸት ፍቅራቸውን ይገልጹለታል።
ተመልሼ ቦታዬ ተቀመጥኩ ። አሁን ከብዙ ወጣቶች ጋር ተዋወቅሁ። ቦርሳና ጫማ እኔጋ እያስቀመጡ መሄድ ተጀመረ ። ለዚህ የታማኝነት ሥራ በመብቃቴ አልከፋኝም ። ወጣት ሲደሰት ከማየት በላይ ምን የሚያስደስት ነገር አለ ። ኢትዮጵያ ፣ ኤርትራ የሚለው ነገር ቦታ አልነበረውም ። ቴዲም ያውቅበታል፣ ፍቅር ያሸንፋል ! እያለ ፍቅርን ይዘራዋል። ወጣት በቡድን ሆኖ አብሮ ይጨፍራል። የመግባቢያ ቋንቋ የቴዲ ዘፈን ሆኗል። እኔም ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ የጫማና የቦርሳ ጥበቃዬን በሰፊው ይዠዋለሁ። ተስማምቶኛል። አይሆንም ብዬ በዘመኑ ቋንቋ አላካብድም ።
ሌላ መጣ ቦታ ጠየቀኝ ። የተለመደው መልስ ተሰጠው ። ኤርትራዊ እንደሆነ ገብቶኛል። ቀስ በቀስ ተግባባን። ለምንድነው ቴዲን የምትወዱት ?
“ቴዲ እንደ ሌሎቹ አያካብድማ ? ኤርትራ ፣ ኢትዮጵያ ገለመሌ ፣ ገለመሌ አይልም ። ይመቻል። ዛሬ እዛ ፍራንክፈርት ሌላም ዘፈን አለ ። “ማህበረኩም“ ያዘጋጀው ነው ። ከአስመራ የመጡ ታዋቂ ዘፋኞች አሉ። እዛ ማንም አልሄደ ፣ እዚህ ነው የመጣነው።” ብዙ ነገር አስረዳኝ ። እኔም “ማህበረኩም“ ምን እነደሆነ ማጣራት ጀመርኩ ። የሻብያ እጅ ያለበት ድርጅት እንደሆነ ሰማሁ። ገረመኝ ሻዕብያን በዘፈን ማሸነፍ ተቻለ ማለት ነው ? “ቦለኛ“ የሚተሰኘ የቀድሞ የኤርትራውያን የዘፈን ዝግጅት ታሰበኝ ። ያኔ ወርቅና ጌጥ ሳይቀር የሚሰጥበት ዘመን ነበር ። የዛን ጊዜ ማነው ከቦለኛ የሚቀር። አሁን ግን ቴዲ በዘፈን አሸነፈ ። የወጣቱን ፍላጎት የወያኔም፣ የሻዕብያም እንዳልሆነ ታዬ . . . የምን ጦርነት ፣ የምን የሕዝብ እልቂት ፍቅር ያሸንፋል ። ወጣት ተሰብስቦ አንድ ላይ ይጨፍራል ፣ ይፋቀራል፣ ይዝናናል . . . የጦርነት ጡሩምባ ለዛሬም ቢሆን ቆሟል . . . የክፍፍል አባዜ ቆሟል ቴዲ የፍቅር ጦሩን ይዞ ዘመቻውን ካለውጊያ ቀጥሏል።
በዚህ ምሽት አንድ ነገር ተመኘሁ በሚቀጥለው ዓመት እነዚህን ወጣቶች የሚያፋቅር ፣ የቴዲ አፍሮን ጥሪ ቀጣይነት ተመኘሁ። ፍቅር የሚያሸንፍበት ቢሆን ብዬ ተመኘሁ። እነዚህ ወጣቶች የሚያፍሩበትን ሳይሆን የሚኮሩበትን ሃገር ተመኘሁ። ቴዲ አፍሮን አሥመራ ንግስት ሳባ ስታዲዩም ውስጥ መድረክ ላይ ሆኖ ፍቅር ያሸንፋል ሲል መስማትን ተመኘሁ። ከሁሉ በላይ ግን ማካበድን የማያውቅ የወጣትነትን ዘመን ተመኘሁ። . . . በወያኔና በሻብዕያ ትምክህት ሊገዳደሉ የሚችሉ ወጣቶች በአንድነት ሲጨፍሩ ማየትን የመሰለ መልካም ስጦታ ከቴዲ አፍሮ 2015 ተሰጠን። እኛም በደስታ ተቀበልነው ።
ስለ ሕዝብ ፍቅር የሚዘፍኑ በሰላም ይክረሙ !
01.01.2015
ፍራንክፈርት