• በሶስት ከተሞች ረብሻዎች ተነስተዋል
(ነገረ ኢትዮጵያ) በምስራቅ ጎጃም ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል መሰናዶ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቁመው እንዲወስዱ የተደረገውን የ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ስልጠና ላይ ተቃውሞ ማሰማታቸውን ምንጮን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
በስልጠናው ወቅት የህዝቡ አስተሳሰብ፣ የግል ሚዲያ፣ ተቃዋሚዎች ለኢትዮጵያ እድገት ጠንቅ ተደርገው የቀረቡ ሲሆን ተማሪዎች ይህንን አቀራረብ ተቃውመውታል፡፡ በአንጻሩ ከወራት በፊት ስልጠናውን የወሰዱት መምህራንም ዳግመኛ ስልጠናውን እየወሰዱ ቢሆንም ዝምታን መምረጣቸው ተገልጾአል፡፡
ተማሪዎቹ ‹‹የምርጫ ቅስቀሳ ከሆነ ለተቃዋሚዎችም ይፈቀድ፣ ለምን ለግጭት የሚጋብዙ ቅስቀሳ ትቀሰቅሳላችሁ፣ የኢህአዴግ ፖሊሲ ምሁራንንም ጭምር ለስደት የዳረገ ነው፣ ከቻይና እና ከኮሪያ የሚያስተሳስረን የታሪክም ሆነ የባህል መሰረት የለንም፣ ኢህአዴግ 23 አመት ያልተገበረውን ዴሞክራሲ ሊያስተምረን አይችልም›› የሚሉ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አንስተዋል፡፡
በስልጠናው ወቅት ተቃውሞዎች እየተነሱ ሲሆን በተለይም ደብረማርቆስ፣ ባሶ ሊበንና ሞጣ ላይ ተማሪዎቹ ‹‹ኢህአዴግ ሌላ፣ ኢህአዴግ ሌባ›› የሚል ጩኸት በማሰማታቸው ሲሰለጥኑበት ከነበረው ሰፊ አዳራሽ 20፣ 20 ሆነው በየክፍሉ እንዲሰለጥኑ ተደርገዋል፡፡ በተለይ በደብረማርቆስ ከተማ በሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቹ የካድሬ ስልጠና አንሰለጥንም በማለት መረር ያለ ተቃውሞ እያሰሙ እንደሚገኙ ከአካባቢው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡