Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Health: ብጉር መንስኤው እና መፍትሄው ምንድን ነው?

$
0
0

በተለይ ከአፍላ ወጣትነት ዕድሜ ጋር ተያይዞ ከሚከሰቱ እና የቆዳ ውበትን በመቀነስ የስነ ልቦና ጫና ከሚፈጥሩ ነገሮች መካከል አንዱ ብጉር ነው፡፡ በተለያዩ የቆዳ ህክምና መስጫዎች ሳጠና የታዘብኩት ነገር ለህክምና ከሚመጡ ሰዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ወጣቶች ከብጉር ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ብዙዎቹ ቆዳቸው በብጉር ምክንያት በተከሰቱ ጠባሳዎች እና መጥቆሮች ከተጎዳ በኋላ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ላይ ደግሞ ህክምና ያን ያህል መፍትሄ የማይሰጥ በመሆኑ አጥጋቢ መፍትሄ ሳያገኙ ይመለሳሉ፡፡ በአገራችን በአጠቃላይ በብጉር የተጠቁ ሰዎችን ቁጥር የሚያሳይ መረጃ ማግኘት ባልችልም አንድ ማህበረሰብን መሰረት ባደረገ ጥናት ከ14 እስከ 16 ዓመት 55% ወንዶች እና 45% ሴቶች በብጉር የተጠቁ ናቸው፡፡ ከአሜሪካ ህዝብ ከ40 እስከ 50 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑት የብጉር ሰለባ ናቸው፡፡

acne ethiopian girl

ብጉር በብዛት የሚታየው በፊት፣ ትከሻ፣ የላይኛው የደረት ክፍል እና ጀርባ ላይ ሲሆን በሁለት የዕድሜ ክልል ውስጥ በብዛት ይገኛል፡፡ የመጀመሪያው በጨቅላነት ወይም የህፃንነት ጊዜ ሲሆን በዚህ ወቅት 20% በሚሆኑት ላይ ይከሰታል፡፡ ይህም የሚከሰተው ከእናትየዋ በእርግዝና ወቅት ወደ ህፃኑ በሚተላለፍ ሆርሞን አማካኝነት ነው፡፡

ሌላኛው ወቅት ደግሞ አፍላ ወጣትነት ሲሆን አንዳንዴ ብጉር የዚህ ዕድሜ ክልል መግቢያ ማሳያ እየተደረገ ይወሰዳል፡፡ በዚህ ወቅት በወንዶች ከ16 እስከ 19 ዓመት እና በሴቶች ደግሞ ከ14 እስከ 17 ዓመት ባሉ ላይ በብዛት ይወጣል፡፡

ብጉር ከ20 እስከ 25 ዓመት የዕድሜ ክልል (90%) በሚሆኑት ሰዎች ላይ ቀስ እያለ በመቀነስ በመጨረሻ የመጥፋት አዝማሚያ የሚያሳይ ሲሆን በጥቂት ሰዎች ላይ ግን ከ25 ዓመት በኋላ በተለይም ሴቶች ላይ እስከ ሰላሳዎቹ እና ከዚያም በላይ ሊቆይ ይችላል፡፡

ብጉር እንዴት ይፈጠራል?

ብዙ ጊዜ የሚከሰተው የዘረ መል ተጋላጭነት ከእናት ወይም ከአባት ወይም ከሁለቱም ባለ ጊዜ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ሁሌም ይከሰታል ማለት ግን አይደለም፡፡ የዘረ መሉ ውርስ ሙሉ ላይሆን እና የተወሰነ ትውልድንም ሊያልፍ (Genetic Skip) ይችላል፡፡

ከዘረ መሉ ተጋላጭነት ጋር ተዳምሮ ብጉር ለመከሰት አራት መሰረታዊ ደረጃዎች አሉት፡፡ እነዚህም፡-

1. በላይኛው የፀጉር መውጫ ህዋሳት በብዛት በመራባት እና አንድ ላይ በመያያዝ የቆዳ ቀዳዳዎችን መድፈን፤

2. ቅባት መሰል ፈሳሽ የሚያመነጩ እጢዎች በብዛት መመረት፤

3. የቆዳ መቆጣት እና

4. በተፈጥሮ በቆዳ ላይ የሚገኝ ባክቴሪያ መኖር እና በብዛት መራባት ናቸው፡፡

የቆዳ ቀዳዳዎቹ በሚራቡት ህዋሳት ምክንያት በመዘጋታቸው በብዛት የተመረተው ቅባት መሰል ፈሳሽሽ ባክቴሪያ እና ሌሎችም በቆዳ ውስጥ በመከማቸት ትንንሽ እብጠቶችን ይፈጥራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባክቴሪያው ትራይግላይስራይድ የሚባል የቅባት አይነት ወደ ቅንጣት ነፃ አይነት ቅባቶች በመቀየር ሰውነት እነዚህ ቅባቶች ላይ ጥቃት በሚያደርስበት ጊዜ የቆዳ መቆጣትን በማስከተል የሚያሙ ብጉሮች ይፈጠራሉ፡፡ በቆዳ ውስጥ ክምችቱ ከመጠን በላይ የሚገባ ሲሆን የሰውነትን መቆጣት በማባባስ ትልልቅ እብጠቶች አንዳንዴም መግል አዘል የሚመስሉ እብጠቶችን በቆዳ ላይ ሊያስከትል ይችላል፡፡

በአጠቃላይ ብጉር ክፍት ትንንሽ እብጠቶችን (ጫፋቸው ጠቆር ያሉ)፣ ዝግ ትንንሽ እብጠቶችን (ጫፋቸው ነጭ የሆኑ)፣ ቀላ ያሉ፣ የሚያሙ እና መግል አዘል የሚመስሉ እብጠቶችን አንዳንዴም በጣም የከፋ ሲሆን ትልልቅ እብጠቶችን ሊያስከትል ይችላል፡፡ የእነዚህም ጦስ ቆዳ ላይ ቋሚ ጠባሳና ጥቁረት መከሰት ነው፡፡

ብጉርን የሚያባብሱ ነገሮች ምንድናቸው?

– ብጉርን ማፍረጥ

ይህ ሁኔታ ብዙ ሰዎች ላይ የሚስተዋል ሲሆን ይኸውም የብጉር መንስኤ የሆነውን ባክቴሪያ ከአንድ የቆዳ ቀዳዳ ወደ ሌላ በማዛመት ብጉሩ እንዲባባስ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም ብጉሩ በሌሎች ቆዳ ላይ በሚገኙ አደገኛ ባክቴሪያዎች እንዲመረዝ በማድረግ እና በቆዳ ላይ ጠባሳና መጥቆር በማስከተል ዘላቂ የሆነ ችግር ይፈጥራል፡፡

– ፊትን በተደጋጋሚ እና ቆዳው እስኪጎዳ ድረስ መታጠብ

– ቆዳን የሚጎዱ የቆዳ ማፅጃዎችን መጠቀም

– ቆዳን በጨርቅ መፈግፈግ

– ቅባት አዘል የሆኑ መዋቢያዎችን መጠቀም

– ፊትን በእጅ መደገፍ ወይም ስልክ ረዘም ላለ ጊዜ ፊት ላይ መያዝ

– ጭንቀት

– ቀዝቃዛ የአየር ጠባይ

– በቅድመ የወር አበባ ወቅት ብጉር 70% የሚሆኑ ሴቶች ላይ የወር አበባ ከ2 እስከ 7 ቀን ባሉ ቀኖች ውስጥ ከመምጣቱ በፊት የመባባስ ምልክት ሊኖር ይችላል፡፡ የሚቀጥለው የወር አበባ ዑደት ሲጀምር ግን ይሻሻላል፡፡

– ለተለያዩ የበሽ አይነት የምንወስዳቸው መድሃኒቶች ብጉርን ሊያባብሱም ይችላሉ፡፡ የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል ኮርቲኮስቴሮይድ (በብዛት ለልዩ ልዩ የቆዳ በሽታ ይሰጣል)፣ የሚጥል በሽታ መድሃኒቶች፣ ፀረ ቲቢ መድሃኒቶች በተለይም አይሶናዚድ የሚባለው በተወሰኑ በሽተኞች ላይ ብጉር ሊያስከትል ይችላል፤ ለአዕምሮ ህሙማን የሚሰጡ መድሃኒቶች ወዘተ… ናቸው፡፡

አንዳንድ ሴቶች ላይ የብጉር መኖር የተወሰኑ በሽታዎች ማሳያ ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ፣ አንዲት ሴት ከብጉር በተጨማሪ የወር አበባ ዑደት መዛባት፣ የወሲብ ፍላጎት መቀየር እና ባልተለመደ ቦታ ላይ ፀጉር ማብቀል ምልክት ካላት የሆርሞን መዛባት ችግር ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡

መፍትሄ

የብጉርን ህክምና በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡

1. መሰረታዊ የቆዳ እንክብካቤ ማድረግ

– የቆዳ ንፅህናን በሚገባ መጠበቅ ብጉርን በመከላከል እና እንዳይባባስ በማድረግ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ ይህም ፊትን በቀን ሁለት ጊዜ ሞቅ ባለ ውሃ እና ቆዳ ላይ ጉዳት በማያደርስ ሳሙና በጣታችን ጫፎች መታጠብ፡፡

– ቆዳ በሚደርቅበት ወቅት ብጉር አምጪ ያልሆኑ የቆዳ ማለስለሻዎችን መጠቀም

– በቅርብ ጊዜ ከቆዳ ብጉር ጋር ተያይዞ የሚመጣ የቆዳ መጥቆርን ለመከላከል የፀሐይ መከላከያ ወይም ‹‹ሰን ስክሪን›› ቅባቶችን መጠቀም እና ከላይ የጠቀስኳቸውን ብጉርን የሚያባብሱ መንስኤዎችን ማስወገድ ናቸው፡፡

2. በመድሃኒት ማከም

የብጉር መድሃኒቶች በሐኪም የሚታዘዙ ሲሆን የመድሃኒቶቹ ምርጫ እንደየብጉሩ አይነት እና አፈጣጠር ምክንያት የተለያየ ነው፡፡ እነዚህም በቆዳ ላይ የሚደረጉ ወይም በአፍ የሚወሰዱ ሲሆን ተግባራቸውም አንዳንዶቹ የተደፈውን የቆዳ ቀዳዳ የሚከፍቱ፣ የቆዳ መቆጣትን የሚቀንሱ እና ሌሎቹ ደግሞ የፀረ ባክቴሪያ መድሃኒቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

በመጨረሻም በብጉር ምክንያት በቆዳ ላይ ቋሚ የሆነ ምልክት ከመፈጠሩ በፊት ወደ ጤና ተቋማት በተለይም የቆዳ ሐኪሞች ወደሚገኙበት በመሄድ ተገቢውን የሆነ ምክር እና ህክምና ማግኘት አስፈላጊ ነው፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>