ማንነቱ
የህክምና ሰዎች ኤፒስታክሲስ (Epistaxis) እያሉ የሚጠሩትን የሀገራችን ሰዎች ደግሞ ነስር ይሉታል፡፡ ቋንቋ ቢያለያያቸውም የምስጢር ጽንሳቸው ከአንድ ማህፀን የተገኘ ነው፡፡ ስለዚህ ነስር የሚለውን ቃል ስንፈታው ምንጩ አፍንጫን መሰረት ያደረገ ድንገተኛ መድማት ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያትቱት በህይወት ዘመናቸው ከ10 ሰዎች መካከል ስድስቱ ነስር አጋጥሟቸው ያውቃል ወይም ያጋጥማቸዋል፡፡ እንኳንም ይሄ ቁጥር ለካንሰር ወይም ለሌሎች በሽታዎች አልሆነ፡፡ መቼም ሳይደግስ አይጣላምና ይህ ቁጥር ለነስር ሆነ፡፡ ይህ ማለት ይህን ያህል ጊዜ ነሰረኝ ተብሎ የሚይዙትን የሚጨብጡትን የሚያጡበት ምክንያት የለም፡፡ ቢሆንም ግን በነስር ላይ ያለንን ግንዛቤ ከፍ በማድረግ እንዲሁም የተሳሳተ አመለካከት ካለ ወደኋላ ትተን የሚረባንን ነገር ይዘን ወደፊት መሄድ የምንችልበትን አቅም ማጎናፀፍ የፅሑፍ ቀዳሚ አላማ ይሆናል፡፡
መንስዬዎቹ
የነስር ምክንያቶች ለማስረዳት አንድ ምሳሌ ልስጥ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ አፍንጫን በመንደር፤ ሙሉ አካላችንን ደግሞ በሀገር እንመስለው፡፡ ስለዚህ የነስር ምክንያቶች መንደራዊና ሀገራዊ ችግሮች ተብለው በሁለት አበይት ክፍሎች ልንመድባቸው እችላለን፡፡ እንግዲህ መንደራዊ ችግሮች ስል እዛው አፍንጫ አካባቢ የሚርመሰመሱትን ተግዳሮቶችን ሲያመላክት፤ ሀገራዊ ችግሮች ያልኩት በሌላ በኩል ጠቅላላ ሰውነታችን ላይ ተፅዕኖ በማሳደር ነስርን ከምልክቶቻቸው እንደ አንዱ አድርገው ያቀፉትን በሽታዎች ወይም የሰውነት ቀውሶችን ነው፡፡
መንደራዊ ችግሮች (Local Causes)
1. አፍንጫ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች
– አፍንጫን በጥፍር አብዝቶ መጎርጎር
– ባዕድ አካላት (በተለይ ያገኙትን ነገር ወደ አፋቸውና አፍንጫቸው መስደድ የሚቀናቸው ህፃናት ለዚህ አይነቱ የነስር ምክንያት ተጋላጮች ናቸው)
– ደረቅ የአየር ንብረት
– የአፍንጫ አጥንት መሰበር
2. ኢንፌክሽንና አለርጂ
– ጉንፋን፣ ሳይናስይትና ሌሎች አፍንጫ አካባቢ ያሉትን ህዋሳት መጎብኘት የሚወዱ በሽታዎች ለነስር የማይነጥፉ ምንጮች ይሆናሉ፡፡
3. አፍንጫ ውስጥ የሚበቅሉ ዕጢዎችና ስርዓት ያጣ የአፍንጫ ቅርፅ አወቃቀር
4. አንዳንድ መድሃኒቶች
– የአፍንጫ ውስጠና አካል ውስጥ የሚቀቡ መድሃኒቶችና በአፍንጫ በመሳብ የሚወሰዱ ለምሳሌ ኮኬይን (Cocaine) የተባለውን አደንዛዥ ዕፅ እንደ አብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ሀገራዊ ችግሮች (Systemic Causes)
1. የደም ግፊት መጨመር
በዚህ ዙሪያ ላይ ውዝግብ አልጠፋም፡፡ ገሚሶቹ በነስር መንስኤነቱ ሲፈርጁት የተቀሩት ደግሞ አይ መንስኤ ሳይሆን የደም ግፊት መጨመር በሚያሳዩ በሽተኞች ላይ ነስር ቢከሰት ቶሎ ለማቆም አዳጋች ነው ባዮች ናቸው፡፡ እንግዲህ ወደፊት የሚሰሩ እና በመሰራት ላይ የሚገኙ ጥናቶች ወደፊት እውነቱን ፍንትው አድርገው መግለጣቸው አይቀሬ ነው፡፡ እኛም በትዕግስት እንጠብቃቸዋለን፡፡
2. ደምን የሚያቀጥኑ መድሃኒቶች (ለምሳሌ አስፕሪን፣ ዋርፋሪን)
3. በዘር የሚተላለፍና የደም መርጋት ስርዓት የማይዋጥላቸው በሽታዎች
4. የደም ካንሰር (‹‹ውሳኔ›› የሚለው ፊልማችንን የዚህ ምሳሌ ነው)
5. ስር የሰደዱ የጉበትና የኩላሊት በሽታዎች
እንግዲህ ነስር ሲነሳ እነዚህ ችግሮችም አብረው መነሳትና መታየት አለባቸው፡፡ በሌላ አገላለፅ ‹ነስር መጣ› ብቻ ሳይሆን ለምን መጣ? ብሎ መጠየቅ ጠቢብነት ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ግን ከሀገራዊ ችግሮች ይልቅ መንደራዊ ችግር በነስር መንስኤነት ጎልተው ይጠቀሳሉ፡፡ እዚህ ጋር አንድ ጥያቄ ሊነሳ ይገባል፡፡ ነስር የመጨረሻ ደሙ የሚወጣበት ቦታ ወይም መገለጫ ለምን አፍንጫ ሆነ? ስሙ ስለሚጣፍጥ ወይስ ከዓይን፣ ከእጅ፣ ከእግርና ከመሳሰሉት ከተቀሩት የአካል ክፍሎቻችን ይልቅ በልጦ? ነገሩ ወዲህ ነው፡-
ለምን ነስር ከአፍንጫ ሆነ
(Why always me?)
ይህ ጥያቄ ከሁለት አቅጣጫ ሊታይ ይችላል፡፡ የመጀመሪያው የደም ቧንቧዎቹ የሰፈሩበት ቦታ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የደም ቧንቧዎቹ የአወቃቀር ሁኔታ ነው፡፡
ቦታ፣ አፍንጫ ውስጥ የደም ቧንቧዎቹ የሰፈሩበትን ቦታ ስናጤነው ለአደጋ በሚያጋልጣቸው ቅርብ ቦታ ላይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የደም ቧንቧዎቹ ጥቃት እንዳይደርስባቸው አስበው ራሳቸውን ጠለቅ ባለ ቦታ ላይ አለመሰረቱም፡፡ ይልቁንም የአፍንጫ መግቢያ ቀዳዳ ላይ ባለውና አፍንጫን ለሁለት በሚከፍለው ቋሚ ግድግዳ ላይ እንደ መረብ ተጠላልፈውና ተሰናስለው ይገኛሉ፡፡ በህክምናው ቋንቋ ‹‹ኪስልባች ፕሌክስስ›› ወይም የኪስልባች መረብ ይባላል፡፡ በጽሑፉ መግቢያ ላያ ያያችሁት ይሄንን ነው፡፡ ታዲያ ይህ ግድግዳ ቀደም ሲል በተጠቀሱት ችግሮች ሳቢያ በቀላሉ ደርቆ መላላጥ እና መሰነጣጠቅ ሲጀምር የእነዚህም የደም ቧንቧ ህልውና ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይገባል፡፡ ያኔ ቅሬታቸውን በነስር መልክ ይገልፁታል፡፡
አወቃቀር፡- የደም ቧንቧዎቹ አወቃቀርን ስንመለከት ደግሞ አፍንጫን አሁንም ከሌሎች ለየት የሚያደርገው አመል አላጣውም፡፡ ይኸውም ከ4-5 የሚደርሱ የደም ቧንቧዎች ተገናኝተው የተጠላለፈ መረብ የሚፈጥሩት የደም ቧንቧ አወቃቀር ስርዓት አለው፡፡ ከዚህ የተነሳ የደም ጎርፍ ፀጋ በዛላቸው ከሚባሉት የአካል ክፍሎቻችን ውስጥ አስመድቦታል፡፡ ስለዚህ ከዚህ ቦታ መድማት ሲከሰት ገኖ የመታየት ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡
ነስር ሲከፈል…
ነስር ከሚነሳበት ቦታ አንፃር በሁለት ወገን መመደብ ይቻላል፡፡ የፊትና የኋላ ተብሎ፡፡ የፊት ነስር በአፍንጫችን ፊት በኩል ባለው ቀዳዳ መውጣትን ሲያዘወትር የኋላ ነስር ደግሞ በስተኋላ በኩል በመፍሰስ ወደ አፍ የመምጣት ጠባይ አለው፡፡ ከነሰረን አይቀር በፊት በኩል ቢሆን ይመረጣል፡፡ የኋላ ነስር የሚያባክነው ደም ብዙ ከመሆኑ በተጨማሪ ለማቆምም ቢሆን ቀላል የማይባል ጥረት ሊፈልግ ይችላል፡፡ ደግነቱ አብዛኛውን ጊዜ ነስር ከፊት በኩል ስለሆነ ያን ያህል ስጋት ውስጥ አይከትም፡፡
ሲነስረን ምን ብናደርግ ይሻላል?
አብዛኛውን ጊዜ ነስርን ቤት እያሉ ማስቆም ይቻላል፡፡ እንዴት ካሉ፤
– ተቀምጠውም ሆነ ቁጭ ብለው ከሽንጦት ወደፊት ዘንበል ይበሉና በአውራ ጣትና በጠቋሚ ጣትዎ የአፍንጫዎትን ጫፍ ከ5-10 ደቂቃ ያህል ጭምቅ አድርገው ይያዙ፡፡ በእነዚህ ጊዜ ውስጥ እጅዎትን ያለማቋረጥ ይጫኑ፡፡ በየመሀሉ እየለቀቁ ማየት አይመከርም፡፡ ህዝባችን የሚያደርገው ግን ተቃራኒውን ነው፡፡ ነስር ከመጣ ወደኋላ መንጋለል ወይም አንገትን ወደኋላ መላክ ደምን ወደላይ ይመልሰዋል የሚል ፈሊጥ አለን፡፡ ይህ ግን ስህተት ነው፡፡ ይልቁንም ደም ወደ ጨጓራችን በመግባት ለትውከትና አላስፈላጊ ላልሆኑ ምልክቶች ራስን ማጋለጥ ነው፡፡ ስለዚህ በስዕሉ ላይ እንደሚታየው አፍንጫዎትን ይዘው ነስሮትን ያስቁሙ፡፡
– ከዚህ በተጨማሪ ደስ ካለዎት አፍንጫዎትን ከተጫኑበት ቦታ ከፍ ብለው በረዶ ሊያኖሩበት ይችላሉ፡፡ ይህ በረዶ የደም ቧንቧዎቹን እንዲያኮማትሩና እንዲሸበሽቡ ስለሚያደርግ ነስሮትን ሊያግድ ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ በረዶን ማባከን ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሰውን ዘዴ ብቻ በመተግበር ነስርን በመጣበት እግሩ ሊመልሱት ይችላሉ፡፡
ለነስር ብለው ሆስፒታላችን መቼ ይምጡ?
– የሚፈሰው ደም መጠን ከፍተኛ ከሆነና ለመቆም አሻፈረኝ የሚል ከሆነ፤
– ነስሩን ተከትሎ የእጅ መዳፍና የእግር ውስጠኛ ክፍል መንጣት፣ ድካም ወይም ራስን የማዞር ስሜት ከተሰማዎት፤
– በቅርቡ አፍንጫዎ አካባቢ ቀዶ ጥገና አድርገው ከሆነ፤
– የታወቀ የአፍንጫ ዕጢ ካለቦት፤
– ነስሩ ከዚህ ቀደም ወይም በቅርቡ ለሌሎች ተያያዥ ምልክት ካጀቡት ለምሳሌ የአጥንት ህመም፣ ትኩሳት፣ ቆዎት ላይ ወደቀይ የሚያደሉ ነጠብጣቦች ካስተዋሉ፤
– ነስሩ አደጋን ተከትሎ የመጣ ከሆነ፤
– እንደዚሁም ደምን የሚያቀጥን መድሃኒቶች የሚጠቀሙ ከሆነ ለምሳሌ አስፕሪን፣ ዋርፋሪን፣ ክሎፒዴግሮል፤
– ነስሩ በተለያየ ጊዜ እየደጋገመ የሚመጣ ከሆነ በህክምና ባለሙያ ታይቶ መሰረታዊ ችግሩ ከስር መሰረቱ ሊፈታ ይገባል፡፡
መከላከያ አለው ወይ?
– ውሃ በጨው አፍልተው አፍንጫዎትን ማጠብ፡፡ ለማዘጋጀት ከፈለጉ አንድ የሻይ ማንኪያ ጨው በአንድ ሊትር ውሃ ለሃያ ደቂቃ አፍልተው ለስ እስኪል ድረስ ያቆዩት፡፡ ከዚያ ይታጠብበት ይህ የአፍንጫዎ ህዋሳት እርጥበታቸውን እንዲጠብቁ ያደርጋል፡፡
– ከላይ የተጠቀሰውን ማድረግ ካልቻሉ ቫዝሊን መቀባት ይችላሉ፡፡
– ሲያስነጥስዎት በአፍዎ ለማስነጠስ ይሞክሩ፡፡
– አፍንጫዎት ውስጥ የሚያስቀምጡት ነገር ካለ ያስወግዱ፡፡
– ማጨስን እርግፍ አድርገው ይተዉ፡፡
– አፍንጫዎ አካባቢ አለርጂ የሚያስቸግሮት ከሆነ ሐኪምዎን ያማክሩ፡፡
– በጥቅሉ ነስር ከብዙ በጥቂቱ ይህንን ይመስላል፡፡ ምናልባትም ለአንዳንዶቻችን ነስር የሚያስጨንቀን አጀንዳ ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለሮማ ለመንግስት ትልቅ የሆነ ቁርጠት ሆኖ ወረራ ላደረሰባት የሀን ንጉስ አትለ ግን በሠርጉ ዕለት ምሽት ነበር በነስር ምክንያት ወደ መቃብር የወረደው፡፡ ኦ ነስር ሆይ እንዲህም ታደርጋለህ እንዴ?! መጠንቀቅ ነው፡፡