ከ ኆኅተበርሃን ጌጡ /ጀርመን
አጠገቡ ሆኖ ሲያወሩት ጨዋታዉ ለዛለው። ተፈጥሮዉ ሆኖ የ…….. ጠንጋራ ሳይቀር ለይቶ ያዉቃል። በጨዋታ መካከልም ሁለት አይነት ሳቆች አሉት። የዘወትርና የክት። ወደ ደም ስር ዘልቆ የሚገባ ቀልድና ቁምነገር ከገጠመዉ ደግሞ ከልቡ ይፍነቀነቃል። ካልጣመዉም በዘወትሩ የለበጣ ሳቅ ያልፈዋል። የሳቁ ዓይነት ሲነግረንም በረዥሙ ልንቀድ ያሰብነዉን ጉዳይ ባጭሩ እንቀጨዋለን። ሳቁ ለእኛ ምልከታ ወይም ርችት ነዉ። ለጨዋታዉ ዉበት የሚሰጠዉ ደግሞ አማርኛ የአፍ መፍቻ ቑንቑዉ አለመሆኑ ነዉ። ለምንም ለማንም ሳይል ደፋር ተናጋሪነቱ ደግሞ የብዙዎቻችንን ቀልብ ለመሳብ አስቸሎታል። በእርግጥ ለዚሀ አይነቱ አቑሙ ሰዎች የተለያየ ትርጉም ይሰጡታል። ግራና ቀኝ ተሽክመነዉ የምንዞረዉ ጆሮ ባእዳቸን ስለሆነ እሱም እራሱ እስካሁን ጉዳዩን ያልሰማዉ ሊሆን ይችላል። የሚባለዉን እኔም ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ አደባባይ ማዉጣቴ ነዉ። የእሱ ደፋርነት ከሌሎች የተለየ ወንድ ሆኖ አይደለም። ደሙም እንደ የሁላችንም ደም ቀይ ነዉ። ልዩነቱ ከአፋር ክልል ዉጭ በከተማ የሚኑሩ ዘላኖች ስላሉ የዚያ አይነቱ ዘላኔያዊ ባሕርይ ብልጭ እያለበት ነዉ በማለት፤ ሊሞግቱን ይሞክራሉ። ነገርን ነገር እያነሳዉ ተወራጨሁ ወይም ዙሪያ ጥምጥም እየሄድኩ ለአንባቢ አስቸገርኩ መሰል እንጅ፣ ዓላማዬ የሰዉየዉን ባሕርይ ማተት አይደለም። እኔን በግል የሚያስደስተኝና የምመካበት ምንጊዜም የማይበገር ኢትዮዽያዊነት አቁኣሙ እንጅ ግላዊ ባሕርዩ ስላልሆነ፣ ይህን ይህን ለባለቤቱ ለሓዋ ሙሳ ትቼ ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ባመራ ከአንባቢም ጋር የምስማማ ይመስለኛል።
አሰባሳቢ ማንነት ባንድ ሃገር ልጅነት፣ የኢትዮጵያ ዕጣ ፋንታ በሚል ርዕስ የተከተበ መጽሓፍ ሰሞኑን ለንባብ መብቃቱን የተለያዩ ድረ ገጾች አብሥረዉናል። ደራሲዉ በሚኖርበት የኖርዌይ መዲና ኦስሎ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያንም በደመቀ ሥነ ሥርዓት ኖቬምበር 22 ቀን 2014 መፅሐፉን በይፋ መርቀዉታል፤ ከመፅሃፉ የዉጭ ሽፋን እስከ ጀርባ ድጉሥ፤ ከአርትኦት ሥራ እስከ ሥርአተ ነቁጥ (ነጥብ)፣ ከጎላ ግምገማም አልፈዉ ቀመረ ሰዋስዉ የተከተለ መሆኑንና አለመሆኑንም ጭምር አበራይተዉታል። ደራሲዉንም በጥያቄ አፋጠዉታል። እታዲያ ከዚህ የመፅሃፍ ግምገማ ነክ ምረቃ ሥነ ሥርዓት በዓል፤ ወደ ጀርመን ይዤዉ የተመለስኩት ትዝታ ቢኖር፤ የኖርዌይን ብርድና ስሙን የማላስታዉሰው የዋሽራዉ ተወላጅ፣ የሉሲዉ (ድንቅነሽ) አገር የአፋሩ ተወላጅ መፅሃፍ የአማርኛ ቑንቑ አጠቃቀም እንደከበደዉ ጥያቄ ማቅረቡና እንደዚህ ዓይነት ችግር ላለባቸዉ ሌሎችም ተመሳሳዮች፤ በኦስሎ ከተማ በቅርቡ የአማርኛ መማሪያ ጣቢያ እንደሚከፈት የደራሲዉ ባለቤት ስላቅን ያዘለ፤ ፈጣን መልስ መስጠታቸዉና ቃል መግባታቸዉ ተስብሳቢዉን በእጁጉ ማስደመሙ ነዉ። በእርግጥ መፅሃፉና የደራሲዉ የተጸዉኦ ሥም አደባባይ ወጣ እንጅ፤ ሰዉየዉ ለብዙ ኢትዮጵያዉያን አዲስ አይደለም። በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ ልሳን፣ አይንና ጆሮ ሆና ስትታገል የነበረችዋ ጦቢያ መፅሄት ቑሚ አምደኛ በመሆን መጽሃቷን በእግሯ ካቆሙዋትና ተነባቢ እንድትሆን ካበቁአት ጸሐፍት መካከል (እንደነ ጸጋዪ ገብረመድሕን አርአያ፣ ስንሻው ተገኝ…….ወዘተ) በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት አንደኛዉ ነዉ። ሐሰን ኡመር አብደላ በሚለዉ ተናዳፊ የብዕር ሥሙ። ለአራት አመት ያህል ነጻዉን ፕሬስ ተቀላቅላ በአቅም እጥረት ምክንያት የከሰመችዉ የራዕይ መፅሄትም (ፍራንክፈርት ጀርመን ትታም የነበረችዉ) መሥራች የቦርድ አባልና አምደኛም ነበረ። ካረሳሁት በወቅቱ የመፅሄቷ የሥራ መርሆ ምን መሆን እንዳለበት የተለያዩ ሃሳቦች ቀርበዉ ስንነጋገር፣ <ለሁሉም መድረክ ነን፣ የማንም ልሳን ግን አይደለንም>፣ የሚል እንዲሆን፤ ሁሉንም የቦርድ አባላት በአንድ ድምፅ ያሳመነ ሀሳብ አፍላቂዉ እሱ ነበረ። ይህ ብቻም አይደለም፤ ተዘዉትሮ በጀርመን ድምፅ ራዲዮ የምሥራቅ አፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ ተንታኝነቱም የሬዲዮ ጣቢያዉ አድማጮች ጆሯቸዉን ቀስረው የሚያዳምጡት ነዉ። ዛሬም የቀድሞ የጦቢያ ደንበኞች በተለያዩ አጋጣሚዎች በአካል ስንገናኝ ያ፣ አፋሩ የጦቢያ መጽሄት የነፍስ አባት ደኅና ነዉ? ሳንባባል አናልፍም። ይኽዉ አሁን ደግሞ በእዉነተኛ ሥሙ ሁላችን ስንጠብቀዉ የነበረዉን እምቅ ችሎታዉን ያሳየበትን፣ የወደፊቷን ኢትዮጵያን ዕጣ ፋንታ እንደ መስታወት ወለል አድርጎ የሚያሳየዉን መጽሃፍ ይዞ ብቅ ብሏል።
ኮብላዩ ሚኒስትር ኤርምያስ ለገሰ ስለባለቤት አልባዋ ከተማ አዲስ አበባ በወዶ ገብ የኢሕአዴግ ካድሬነቱ ለአሥራ ሁለት አመታት ያለፈበትን ጉዞ፣ ሥርአቱ ምን ያህል የተግማማ እንደሆነና ከቀዳማዊት እመቤት ጀምሮ እስከ አዉራ ካድሬዎቹ በከተማ ቦታ ዝርፊያና በሙስና የነቀዙ መሆናችዉን የጆሮ ሳይሆን የአይን ምሥክርነቱን ሰጥቶበታል። <አሰባሳቢ ማንነት ባንድ ሃገር ልጅነት> የተሰኘዉ ይህ መጽሃፍ ደግሞ ስለባለቤት አልባዋ፣ የእነሱ? ወይንስ የእኛ የሁላችን የዜጎቿ? መሆኗ ገና በዉል ስላልታወቀችዉ ኢትዮጵያ ስለምትባለዋ ሀገራችን ነዉ። እስኪ እራሳችሁን ጠይቁ፣ በአሁኑ ጊዜ ማነዉ የኢትዮጵያ ባለቤትዋ? እነሱና እኛ ተባብለን ሳንቧደን እኛ ኢትዮጵያዉያን የምንላት የሁላችን የሆነች፤ እኛም ዜጎቿ የእሷ የሆንላት፤ የጋራ ሀገር እንዴት መፍጠር እንደሚቻል በአመክንዮ አስረግጦ፣ የአብሮነት ቀመርን አስፈላጊነት ከነመፍትሄዉ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጧል። ከማንነቶች መራኮት ይልቅ ወደ ኢትዮጵያዊነት አሰባሳቢ ማንነት፤ ፍለጋ የመኹተን አስፈላጊነትን በአጽንኦት ለማሳዬት ደክሞበታል። አዎ፤ ሁላችን የምንነጋገረዉ፤ ኢትዮጵያ ስለምትባለው ሃገር ከሆነ፣ ኢትዮጵያዊነት ግን ግለሰቡ በምርጫዉና በገዛ ፈቃዱ የሚላበሰዉ ወገንተኝነት በመሆኑ፣ ይህን አሰባሳቢነት ኢትዮጵያዊነት በእያንዳንዱ ተወለድሽኝ ዜጋ ሥነ አዕምሮ እንዴት ማስረጽ እንደሚቻል፣ አትቷል። የመጽሃፉ ምሥጢርና ሰምና ወርቅም በዚህ ዙሪያ የሚያጠነጥን ሆኖ እናገኝዋለን። የመጽሃፉ መዘዉረ ሃሳብ በዚህ ዙሪያ ያቀንቅን እንጅ፣ ደራሲዉ ወደዚህ የማሳረጊያ ነጥቡ ለመድረስ ብዙ የማንነት ፍለጋ ጉዞ እንዳደረገ፣ ያገላበጣቸዉ ዋቢ መረጃዎቹ ያስረዳሉ። ዋቢዎቹም ሀገርኛና የዉጭ ቑንቑዎችን አካተዋል። ከመጽሃፉ ይዘት ጋር ቁርኝት ያላቸዉ የኅብረተሰቡን ገሃድ አለም አቀንቃኞች የሚገልጹባቸዉ የዘፈን ስንኞችም ልብ መሳጭነት ባለዉ መንገድ ሰፍረዋል። የመጽሃፉ ዘይቤያዊ አገላለጽና የአጻጻፍ ሥልት ሲፈተሽ፤ በመንዝኛም፤ በጎንደርኛም፤ በሸበል በረንታም ቅላጼ ባለዉ አማርኛ ሳይሆን፤ እራሱን ዩሱፍ ዩሱፍን በሚሸት የራሱ ዩሱፋዊ ዘይቤና ቃና ባለዉ መንገድ ተክሸኖ የቀረበ ነዉ። የመልዕክቱን ይዘት ለተረዳዉ ደግሞ አፋሩ ለኢትዮጵያዉያን የተቀኘዉ ይበል የሚሰኝ ቅኔ የተቀኘበት መጽሃፍ ነዉ። ብዙአዪሁ የሚባል ዘፋኝ ቅርብ ጊዜ ባወጣዉ አልበሙ፣ አንዷን ኮረዳ ይህ ቀረሽ በማይባል ዉበት መላበሷን ሲግልፅ፣ ፈጣሪ ተራቆብሻል፤ ጥበቡን ማሳያ አርጎሻል። እንዳለዉ፣ የኢትዮጵያዉያንን የአብሮነት የመኖር ጥበብን አስፈላጊነት ጆሮ ያለዉ ከሰማ፣ልብ ያለዉ ካስተዋለ ለአሰባሳቢ ማንነታችን እንደ ፍቱን መሳሪያነት ልንጠቀምበት የሚገባ ሰነዳችን ነዉ።
ከማንነቶች መራኮት ይልቅ ወደ አሰባሳቢ ማንነት ፍለጋ ጉዟችንን እንድናሳምር፣ ጸሐፊዉ የማሳረጊያ ቡራኬ ከመስጠቱ በፊት፤ ለመጽሃፉ አላማ ግብ መምቻ የሚዉሉና በቀጥታ ለመፅሃፉ መደረስም አዉራ አመክንዮነት ያላቸዉን መድበለ ሃሳቦች በአሥራ ሦስት ሞእራፎች (መሪ ርዕሶች) እና በሰማንያ አራት ንኡሳን ክፍሎች (መዘርዝረ ሐተታ) በመፈረጅ፤ ለእያንዳንዱ ተጟዳኝ ርዕስ ጥልቅ ትንተና ሰጥቶባቸዋል። ስለማንነት፤ ማንነትን ስለመለዬት ሂደት፤ በምን፣ በምን፣ እንደምንኮራ፤ ከምን፣ ከምንስ፣ እንደምንሰጋ፤ያለን የመንግሥትነት ታሪክ? ወይንስ ረዥም የሥልጣኔ ታሪክ? በማለት ከራሱና ካለፈ ታሪካችን ጋር ይሟገትና ከዚሁ ርዕስ ጋር ተቆራኝቶ፤ ያለን የረዥም ጊዜ የሥልጣኔ ታሪክ ነዉ ወደሚል መደምደሚያ የምናመራም ከሆነ፤ ሌሎቹ ለምን ጥለዉን ሄዱ? ለምን እኛ ጭራ ሆነን ቀረን? ብለን እራሳችንን በቁጭት እንድንጠይቅ ያደርግና፤ በቁስላችን ላይ እንጨት ሰድዶ ሆዳችንን ያባብሰዋል። የመንግሥት ጣልቃ ገብነትንና የሃይማኖት ተቑማትን ነጻነት ስለመለዬት አስፍላጊነት፤ በታሪካችን ስለተከናወነዉ የግዛተ አፄን የማስፋፋትና የማዕከላዊ መንግሥትን መደላደል ዘመቻ፤ ይህ የጥንት ዘመቻም በአሁኑ አብሮነታችን ላይ ያሳረፈዉ አሉታዊና አወንታዊ ገጽታዉ ምን እንደሆነ፤ ይህን ርዕስም ያጎዳኝና፤ የኦሮሞ ብሔረተኛነት፣ የማንነት ፖለቲካና ተፈታታኝ ተግዳሮቶቹን አስመልክቶ ድንቅ ትንተና አድርጎባቸዋል። እንኝህንና መሰል ተዛማጅ ርዕሰ ጉዳዮችን በየምዕራፉ ካብጠለጠላቸዉ በኁላ ነዉ፤ አብዛሔነትን አስተዳድሮ ለዜግነታዊ መንግሥት መሠረት መጣል፤ ወደሚለዉ አዉደ ሐሳብ የተሸጋገረዉ። ከፊታችን ተደቅኖ ከሚታዬዉ ከዉስብስቡ ግዙፍ ሀገራዊ የፖለቲካ ችግር አንፃር፤ ይህ ነዉ፣ እያንዳንዳችንንም ኢትዮጵያዉያን ዜጎች የሚመለከተዉና ወቅታዊዉም የመፅሃፉ ምሥጢርና የአፋሩ ቅኔ።
እስኪ መጽሐፉ ካዘላቸዉ ቁምነገሮች ጥቂቱን ቀንጨብ አድርጌ ላቃምሳችሁ። “<….ሁላችን የተሳፈርንባትን፣ እየተወዛወዘች ለመስመጥ የቀረበችዉን ጀልባ ላይ፣ እሳት ማቀጣጠሉንም ሆነ ሽንቁር መሸንቆሩን አቁመን፣ ሃገራችን ባሁኗ ሰአት የምትገኝበትን አሳሳቢ ሁኔታ ተገንዝበን፣ ወደ ልበ ልቦናችን ተመልሰን በሃገራዊ የሃላፊነት ስሜት እያንዳንዱ ድርሻዉን ለመሸከም ዝግጁነቱን ማረጋጥ ይኖርበታል። …..የተቁኣማት፣ የሕግ ልዕልና ሲቪል፤ ዜግነታዊዉ መንግሥት ምሥረታም ሆነ ማደላደል ረዥም ጉዞ ቢሆንም ቅሉ የሀገሬ ልጆች፣ የተለያዩ የብሔረስብና የእምነት አባላት፣ የተለያዩ የመደብና የሙያ ማሕበራት፣ ሴቶችና ወንዶች እጅ ለእጅ ተያይዘዉ የዜግነታዊ መንግሥት ዳገቷ ላይ ሲደርሱ ይታዩኛል። አጣልቶ የሚያፋቅር ትዳር ይስጣችሁ ተብሎ ሲመረቅ ሰምተናል፣ ያጣላንም ይበልጥ እንድንፋቀር ከሆነም አጣልቶናልና ያፋቅረን!! አንዱ በሌላኛዉ ወንድሙ ባደረሰዉ በደል ምክንያት የቑጠረዉን የቅሬታ ስሜትና የታሪክ ቁርሾ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሽሮ፣ የሚያፋቃር በተደላደሉ መሠረቶች የቆመ ብሔራዊ አንድነትም ይስጠን! የሁሉንም የሕብረተሰባችን ተካይ ነቃይ ብዛሔሰብዕ ባንድነት በሚያቅፍ አቃፊ ደጋፊዉና አጣሪው አሰባሳቢና ሃገራዊ ማንነት በሆነዉ፣ ዜግነታዊ መንግሥትና ተቑማቱ ሥር ሁላችን ያስጠልለን!! ያሰባስበን!! በዚችዉ ሃገር፣ ባንድ ሃገር ልጅነት በእኩልነት ያኑረን! ያኗኑረን!! አ..ሜ..ን! ይለናል በሐገራዊ ቡራኬዉ።
ግን በተደላደሉ መሠረቶች ላይ የቆመ ብሔራዊ አንድነት እንዴት እንፍጠር? እንዴትስ ነዉ መምጣት የሚችለዉ? ነዉ ጥያቄዉ። ምን ዓይነት አንድነት ነዉ የነበረን? አብሮ ያኖረንን አንድነት አሁን ለምን ጠላነዉ? ችለናቸዉ እንጅ አብረን የኖርነዉ ተቻችለን ስላልነበር፣ እስኪ እንሞክረዉ ደግሞ ተለያይተን የሚል እንጉርጉሮዉን እያሰማ፣ ነፍጥ አንስቶ ዱር ቤቴ ያለ ክፍል አለ። ለዘመናት በደረሰብኝ በደል ከበሽታዬም ገና ስላልተፈወስኩ፣ አንድም ከእግሬ ጫማ ሥር ወድቀዉ፣ እንደገናም ላይለምዳቸዉ ቃል ገብተዉ፣ ይቅርታ ይጠይቁኝ፣ ይህ ካልሆነ፣ ከእነርሱ ጋር አብሮ የመኖሩ ጉዳይ አይታሰቤ ነዉ በማለት የበቀል ፖለቲካ ሲያካሂድ እየተስተዋለ ነዉ። እዚህ ላይ መረሳት የሌለበት ነጥብ ግን ከፊደሉ ጋር መርዙን አብሮ የተጎነጨዉ የኤሊቱ ጥያቄ ነዉ የብሔርትኝነት ጥያቄዉን ያጎላዉ? ወይንስ የአብዛኛዉ የአሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ሆኖ አብሮነትን ተፈታትኗል? በዚህ ረገድ የተደረገ ጥናትስ አለ ወይ? በእርግጥም የሕዝብ ጥያቄ ሆኖ እስከቀረበ ድረስ ግን ያንድ ሀገር ዜጎች መሆናችንን የሚያበሥር፤ የዜግነት ሕገ መንግሥታዊ መብትን በተግባር ያጎናፀፈ መልስ ማግኘት የግድ ይኖርበታል። የጥያቄዉ ግንባር ቀደም አስተጋቢዎችም፤ ጣራ የነካ የቂም በቀል ፖለቲካቸዉን ወደ ጎን በመተዉ፣ በኢትዮጵያ ሥም ይቅር ለእግኣብሔር የምንባባልበትን መንገድ ቢቀይሱ በዕዉንም የፖለቲካ ጠበብት መሆናቸዉን አስመሰከሩ ማለት ነዉ። ያ ሳይሆን ቀርቶ ግን የመጠፋፋትን መንገድ ከመረጥን ተጎጅዎቹ ሁላችንም ነን። ያለፈ ቂምና በደልን ከአዕምሯችን ፍቀን ስለነገዉ ብቻ እንሰብ!! የፅድቅ መንገዱም ይህ ነዉና። ይህን ማድረግ ካልቻልን ግን አቀንቃኙ፤ ቂማችን ተራራ፣ መንገዳችን ግራ፤ አልተገናኘንም ከፈጣሪ ጋራ። እንዳለዉ፣ እንዴት ነዉ ከፈጣሪም፣ ከኢትዮጵያም ጋር የምንገናኘዉና አብረንስ የምንኖረው ነዉ ጥያቄዉ?
በሌላዉ ጫፍ ደግሞ የተፈፀመ የታሪክ ስህተት ኖረም አልኖረም፣ በተለባበሰ የአረም እርሻ ላይ ቆሞ፤ የጭፍን አንድነት መዝሙር እያስተጋባ፤ ዛሬም እንደ ትናንቱ የአንድነት ወይም ሞት ቀረርቶና ፉከራዉን የሚያድለቀልቅ ፅንፈኛ አቑም አራማጅ አለ። ጭራሽ ጥያቄዉን መስማትና እንዲነሳም የማይፈልግ። የእምቧይ ካብ አንድነት ሳይሆን ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ማዕበል የማያናዉፀዉ፤ በኢትዮጵያዊነት ማገርና ምሰሶ ተለብዶ የቆመ፤ ብሔራዊ አንድነት የግድ ያስፈልገናል። ይህም ሲባል፤ ምንም ይሁን ምን ያለፈ ታሪካችን ኅፀፅ አልነበረበትም ብለን አንሟገትም። ለመቀበል ገታራ አቁኣም ተያዘ እንጅ፣ አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ የሚያደርገን አኩሪ ታሪካችንንም፤ አንገት የሚያስደፋ የወል የሰቆቃ ግፋችንንም በጋራ ተቀብለነዉ ወደ አዲስ የመኖር ምዕራፍ እንሸጋገር ነዉ የምንለዉ። በእንደነዚህ ዓይነት መሠረተ ሀሳቦች መስማማት የማንችል ከሆነ፣ ምን ዓይነት አንድነት ብንመሠርት እነኝህን ጫፍና ጫፍ የተለጠጡ ገታራ ፅንፎች ወደ ኢትዮጵያዊነት አሰባሳቢ ማንነት ማዕቀፍ ሥር ማጠቃለል የምንችለዉ? ስለቂም በቀል ጉዳይ ካነሳሁ በቅርቡ የሰማሁትንና ለማመን የሚያስቸግረዉን ተምሳሌት ከቶዉኑ ለአንባቢ ሳልጠቅስ ማለፍ ግድ ይለኛል። ተወዛዋዡ ወጣት አብዮት (ካሣነሽ) ደመቀ በእሳት ቴሌቪዥን ጣቢያ በታማኝ በየነ የጥበብ ቃና ሾዉ ቀርቦ ባደረገዉ ጭዉዉት፤ በ 1993 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ሲረበሽ ብቸኛ ልጃቸዉን ፍለጋ ከቤት ወጥተዉ፣ ከፖሊሶች በተተኮሰ ጥይት እየተዝለፈለፉ በደቂቃ ዉስጥ ልጃቸዉንም ያገኙትና ለራሳቸዉ ሳይሆን ለእሱ የኖሩት እናቱ ካሣነሽ፣ በእጁ እንደደገፋቸዉ እጁ ላይ እንዳሉ ሕይወታቸዉ ታልፋለች። ከቤታቸዉ ላይመለሱ ለአንዴና ለመጨረሻ እንደወጡ ቀሩ። በመላ ሕይወቱ የማይረሳዉ ገጠመኙ ቢሆንም፤ ገዳዮቹን ለመበቀል ግን እንደማያስብ፣ የሚከተለዉ ሃይማኖቱም የቂም በቀል መንገድ በር መክፈትን እንደማይፈቅድለት ሲገልፅ፤ በቴሌቪዥኑ መስኮት የማዬዉን ሰዉ ማመን፤ የገዛ ጆሮዬንም መጠራጠር ጀመርኩ። እስኪ ማን ይሙት በዓፄ ምኒልክ ሠራዊት በተተኮሰ ጥይት በቅድመ ዘር ቆጠራ ደርሶበት የቅድም፣ የቅድም አያቱ እጁ ላይ ሕይወቱ ያለፉበት ዜጋ በመካከላችን ካለ፣ የዚህን ወጣት ታሪክ ሲሰማ የቂም በቀልን ሥርዓተ ቀብር ፈፅሞ ከራሱም፣ ከሌላዉም ጋር ታርቆ፤ አዲስ የመኖር ምዕራፍ አይጀምር ይሆን ትላላችሁ? እስኪ ልቦና ይስጠን!!
ሦስተኛዉና በጣም አደገኛዉ የትርምስ አካሄድ ደግሞ፣ ተጠቃሾቹን ሁለት ፅንፈኛ አቁም አራማጆችን የማን አባቱ ገደል ገባ እያለና በችግራቸዉ ክብሪት እየጫረ፣ ችግሩንም የፈታ እያስመስለና በችግሩም እያፌዘ፣ ዓላማዉም እራሱን ከሥልጣን ላይ አደላድሎ ማቆዬት ብቻ ይሆናል። ምክንያቱ ደግሞ በተደላደሉ መሠረቶች ላይ የቆመ ብሔራዊ አንድነት መመሥረት ከመጀመሪያዉም አጀንዳዉ አይደለምና። ወጋ ወጉ ተይዟል፣ ችግር አንቆ ይዟል እንደሚባለዉ ዓይነት ሆነ እንጅ፤ ባለጊዜዉ ቡድን በችግሩ መፍቻ የማኀበራዊ ሳይንስ መድኃኒትነት ተጠቅሞ ሳይሆን፣ ለራሱ በሚያመቸዉ መንገድ ብቻ የብሔረሰቦችን ችግር ፈትቻለሁ ባይ ነዉ። የነበረንን የአሐዳዊ የመንግሥትነት አወቃቀር አፍርሶ በሐዉርታዊ (ብሔር-በሐዉርት) ፌዴራል መንግሥት መሥርቼ፣ ሁሉም እራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር አድርጌያለሁ ይለናል። ይህ ብቻም አይደለም። ብሔረሰቦቻችን ልዩነታችን ዉበታችን እያሉ እየዘመሩ፣ በየዓመቱም የብሔረሰቦችና የሰንደቅ ዓላማ ቀን እያከበሩ እንዲፈነጥዙ በማድረግ አግኝተዉት የማያዉቁትን ድል እንዲጎናፀፉ በማብቃት ተወዳዳሪ የማይገኝልኝ ለብሔረስቦች እኩልነት የቆምኩ ብቸኛ መንግሥት እኔ ነኝ ባይ ነዉ፤ የእኔ መስታወት በሆነዉ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መስኮት ስመለከታቸዉና የግል ጥሩንባዬ በሆነዉ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጣቢያ ወደ ላይ፣ ወደ ላይ እየዘለዘሉ ልዩ ልዩ ኅብረ ቀለማት ባላቸዉ አልባሳት አሸብርቀዉና ደምቀዉ ስመለከታቸዉ፣ የቆምኩለት ዓላማ ምን ያህል ግቡን እንደመታ እርካታን ይሰጠኛል ባይ ነዉ፤ የሕዝብ ብሶት ወለደኝ የሚለዉ ጀግናዉ ኢሕዲአግ። የአሃዳዊ መንግሥት አለመኖር በመርኀ ደረጃ አያጣላንም። ፌዴራሉ የፌዝና የቧልት ፌዴራል መሆኑ ነዉ፣ የማያስማማን።
ከቀድሞዉ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ አሁንም ገና ዕልባት ያላገኘዉና አብሮ የመኖርና ያለመኖር ተግዳሮታችንም ይኽዉ የብሔር-ብሔረሰብ ፈታኝ ጥያቄ መሆኑ ለሁሉም ገሃድ ዕዉነት ነዉ። በደራሲዉ መፅሃፍ እንደተገጸዉ፣ አንድ አናሳ ቡድን በራሱ ስብስብ ሥም የተቆጣጠረዉን ሥልጣንና የሃብት ምንጭ እንዳያጣ፤ ነባሩን ችግር ይበልጥ እንዲወሳሰብ አደረገዉ እንጅ፣ መፍትሄ አልሻተለትም። መፍትሄዉን አጥቶት አይደለም። ለችግሩ በትክክል መፍትሄ ከተገኘለት አናሳዉ ቡድን ቦታ የለዉም። ሥልጣን ከሌለ ደግሞ፣ በሃያ አራት ሰዓት የናጠጠ ሐብታም የሚያደርግ የሀገር ዘረፋ ሎተሪ የለም። ተመልሶ ወደ ጫካ የማይታሰብ ነዉ። የቃታ እጆች ለስልሰዋል። ጫንቃዎች አብጠዋል። ቦርጮች ወጥተዋል። በከተማዎች ብዙዉን ጊዘ የስኩኣር መጥፋት የሚያጋጥመዉ ገበሬዉ ስኩኣር መቃም ስለለመደ ነዉ፣ እየተባለ እንደሚፌዝበት፣ ተጋዳላዮቹ ዛሬ የቢራ ደንበኞች መሆናቸዉን ግን መካድ አስቸጋሪ ነዉ። ባጭሩ ብዙ ዳገት ሳንወጣና ሳንወርድ ፍላጎቶች ከመበርከት አልፈዉ ቅጥ አጥተዋል ነዉ። ሥሜቶች ገደብ አልፈዋል። ኀሊና ተጋርዷል። ለሕዝቦች የተገባዉ የጫካዉ ቃል ኪዳን አዲስ አበባ ሲገቡ ፈርሷል። ለዲሞክራሲ ማበብ የተዘመረዉ መዝሙር የቁራ ጩኸት ሆኖ ቀርቷል። በብሶት አዋለደን ለሚሉት ሕዝብ መኖር ተረስቶ ለእራስና ለቤተስብ መኖር ተመርጧል።
ስለዚህ መፍትሔዉ፣ ሥልጣን ከእጅ እንዳያፈተልክ፣ ሕዝቡ አንድ ሆኖ ጣቶቹን ወደ እኛ እንዳይቀስር፣ እርስ በርሱ ማናከስ፤ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸዉ ዕሴቶችን ድኩማን በማድረግ፣ ብሔራዊ ሥሜቱን ማኮሰስ፣ ከመንደርና ከቀዬዉ አርቆ እንዳያስብ ማድረግ፣ አስተሳስብ አድማሱን በዘር ልጟም መሸበብ፣ እርስ በርሱ ሲባላም፣ እኛ የማታለል ሥራችንን ተቀባይነት ያለዉ በሚያስመስል መንገድ ማካሄድ፡ ለዚህ ደግሞ እኛን ገና ሳያስነጥሰን ይማራችሁ የሚሉ ካድሬዎችን በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጂያችን የአብዮታዊ ዲሞክራሲን ድጟ እንዲያስመሰክሩ በማድረግ ለሥርዓቱ ዘብ በመቆም ሥልጣን ከእጅ አፈትልኮ እንዳይወጣ የሞት የሸረት ትግል ማካሄድ ለአንዳፍታም ቸል የማይባል ዓላማችን መሆን ይኖርበታል ይላሉ ኢሕዲጋዉያን። አካፋዉን አካፋ፤ ዶማዉን ዶማ ብለን ከተነጋገርን ግን እነሱ በሃገር ሃብት የኑሮን ጣዕም እያጣጣሙ ሲኖሩ፣ ድምፅ አልባዉና እነሱን አኗኗሪው ሕዝብ ግን (ከተሜዉም ገጠሬዉም) በድምፆቹ፣ በልሳኖቹ፣ ጆሮዎቹ በሆኑት የኪነጥበብ ሰዎች እንዴት ነዉ ብሶቱን የሚያሰማው ብለን እስኪ እራሳችንን እንጠይቅ? አለ ነገር፣ አለ ነገር፣ ዘንዶሮ አለ ነገር፤ አለ ነገር፣ ከርሞም አለ ነገር፤ መቼም ታመን፣ ታመን አንገት ደፍተን አንቀር። ይላል፤ ይህ የገጠሬዉ እንጉርጉሮም ሆነ፣ የከተሜዉ እሮሮ ዉስጠ ወይራም፤ ሠም ለበስ ቅኔም አይደለም። ምን ያህል ሕይወት እንደመረረዉና ወቅት ጠብቆ የሚፈነዳ ቦምብም በጉያዉ አቅፎ እንደሚኖር ጠቑሚ የሆነ ፅድቅ ቅኔ እንጅ።
ይቺ ቂም የቑጠረች አባባል ጊዜዋ ሲደርስ እንደ የካቲት 66ቱ፣ እንደ ግንቦቱ 83ቱ፣ ሌላ ብሶት የሚወልደዉ፣ ገና ሥሙ የማይታወቅ ሊመጣ ይችልና ተሰዳጁ አሰዳጅ፣ አሳሪዉ ታሳሪ፣ ፈራጁ ተፈራጅ፣ አዛዥ ናዛዡ ባላሥልጣን ከሰዉነት ወርዶ ምስኪን ዜጋ ሆኖ ሲንገዋለል የሚታይበትን ቀን ከማቃረብ፤ አስቀድሞ ቢታወቅበት ግን ሀገርንም እራስንም ማዳን አይቻልም ትላላችሁ? ያለጥርጥር ይቻላል ነዉ መልሱ። ግን ከፀሐዩ ንጉሣችንም፣ ከአብዮታዊዉ መሪያችንም ትምሕርት ማግኘት አልተፈለገም። የመፅሃፉን ርዕስና ደራሲ ለጊዜዉ በዘነጋሁት ግን ደግሞ ካነበብኩት የማስታዉሰዉ፤ ፕሬዚደንት ኮሎኔል መንግሥቱ ባንድ ወቅት የጦር አበጋዞቻቸዉን ይሰበስቡና ስለስሜኑ የሀገራችን ሁኔታ ዉይይት ያደርጋሉ። ከጦር አዝማቾቻዉ መካከል አንደኛዉ (ጄኔራል ታሪኩ ያይኔ ይመስሉኛል) ይነሱና ጟድ ፕሬዚዴንት፤ ችግራችን ሻቢያ ወይንም ጀብሃ አይደለም፣ የትግራዩ ነፃ አዉጪ ከተመታ እነኛን ይተዋቸዉ ብቻቸዉን የትም አይደርሱም፣ ዋናዎቹ ፍልፈሎች እነኘህ ናቸዉ ይሉና ሃሳባቸዉን ያቀርባሉ። ዘወር በል አንተ የምታዉቀዉ ጉዳይ የለህም ይባሉና ቀልባቸዉ ይገፈፋል። ብዙም ሳይቆይ ሁላችን በዓይናችን በብሌኑ ያየነዉን ዕዉነት በመናገራቸዉ ብቻ፤ ቀልባቸዉ ብቻም ሳይሆን፣ ዘግይቶም ማዕረጋቸዉም ጭምር ይገፈፍና የአብዮቱ ሠይፍ አርፎባቸዉ ይችን ዓለም ተሰናብተዋል። እዉነት እንነጋገር ከተባለ፣ መቀሌን እስከተቆጣጠሩ ድረስ መንግሥት የእነሱን ሥም አንስቶና ዕዉቅና ስጥቶ ለመነጋገርና ብሔራዊ ዕርቅም ለማዉረድ ፍላጎቱም አልነበረም። ከዚህ ነጥብ ጋር የሚሄድ፣ እስኪ አንድ ስንኝ ከመዝሙረ ዳዊት ላቃምሳችሁ። ዕብን ዘመነንዋ ነደቅት ወይዕቲ ኮነት ዉስተ ርዕሰ ማእዘንት (የተናቀች ድንጋይ እርሷ የማዕዘን ጭንቅላት-ራስ ትሆናለች እንደ ማለት) ሆነና የተናቀችዋ የደደቢት ፅንስ ለዚህ በቅታ፤ የደርግን መንግሥት በዚህ መንገድ ተሰናብተን አሁን እምንገኝበት ደረጃ ደርሰናል። አሁን ጥያቄዉ በደርግ መቃብር ላይ ሥልጣኑ ያበበዉ ኢሕአዲግ ለሕዝብ የገባዉን ቃል ፈፅሟል ወይ? የሚፈለገዉ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትስ በሀገራችን ሰፍኗል ወይ? ያለጠብ መንጃ አስገዳጅነት በሕዝብ ይሁንታ የተመረጠ መንግሥትስ አለን ወይ? እነዚህ ሁሉ የሚገዙብት፤ በሕዝብ ይሁንታ የረቀቀና የፀደቀ ሕገ መንግሥት አለን ወይ? በእነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች አለመመለስ ልቡ ለሸፈተ ሕዝብና ፋኖ ተሠማራ ላለ ቡድን፣ የማስተናገጃ መልሱ አሁንም እንደ ትናንቱ እኛ በመጣንበት ኑና ሞክሩን ነዉ ሽለላው? ወይንስ……..? እስከ መቼስ ነዉ ወንድም ወንድሙን እየገደለ ጀግና የምንባባልበትን አሳፋሪ ብቻም ሳይሆን አንገት አስደፊ የሆነዉን፣ የታሪክ ምዕራፍ ለአንዴዬና ለመጨረሻ ጊዜ የምንዘጋዉ?
ለመሆኑ የአሰባሳቢ ማንነት፣ ባንድ ሀገር ልጅነት-የኢትዮጵያ ፋንታ ደራሲ ምን የሚለን አለ? ልዩነታችን ዉበታችን ነዉ ለማለት የምንደፍረዉ ወይም የደራሲዉን አገላለፅ ልዋስና …ከአብዛኄነታችን ጋር መኗኗር ችለናል ማለት የምንደፍረዉ፤ ስለመንግሥት አስተዳደር፤ የሥርዓቱ ባሕርይና ምንነት ዙሪያና ሳቢያ የተለያዩ ዕይታ አመለካከቶች መኖራቸዉንና ጉራማይሌነታቸዉን በተግባር ተቀብለን ማስተናገድ መቻላቸዉን ማረጋገጥ ስንችል ብቻ ነዉ። ለሁሉም በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ ቀዳሚዉ ብሔራዊ መግባባት ነዉ። ከሁሉም በፊት አንዱ ከሌላዉ ጋር የሚኖረዉ መስተጋብር፣ ግንኙነት፤ ተዛምዶ ነዉና ወሳኙ መቀሰም ያለበት ትምህርት ቢኖር፣ የዚህን ዓላማ ተግባር አስፈላጊነትንና ቀዳሚነትን መገንዘቡ ላይ ነዉ ቅድሚያ የምንሰጠዉም።…. ከብሔረተኛ መፈክርነት ባሻገርና በመለስ፣ ኢትዮጵያዊነት እንደ አንድ ሐገራዊ የኢድዮሎጂ ትክክለኛዉ ይዘቱ መፈታት አለበት ነዉ በሌላ መልኩ። ማለትም ከሌሎች ከእሱ ጋር ከሚፎካከሩ ኢድዮሎጂዎች አሸንፎ ወይንም የእሱን ተፃራሪዎች በአመክንዮ አምክኖ፣ አሰባሳቢ የበላይነቱን ማረጋገጥ ካልቻለ፣ ኢትዮጵያዊነት እንደ ኢድዮሎጂ የትሕተ ሀገራዊ ማንንትን ካባ ከደረቡ ቅርንጫፍ ማንነትቾች ጋር ግብግቡን ሳያሸንፍ ይቀርና ይሽመደምዳል። ይህ ግን አይታሰቤ ነዉ።…. በሀገሪቷ የዲሞክራሲ ልደት ወይም የመበታተን ዋዜማ ላይ ቆመን፣ ማንም ይግዛ ማን ገዢዉ አካል የዜጎቹ መብት ሳይገሰሥ፣ በተፍጥሮ የተጎናፀፉት ሰብዓዊ መብታችዉ ሳይገፈፍ፣ ሕገ መንግሥታቸዉን በራሳቸዉ ወኪሎች አርቅቀዉና አፀድቀዉ፤ ባጭሩ ሌሎችን የማኗኗር ሕይወት የሚገፉባት ሳትሆን፤ እነርሱ እራሳቸዉም የሕይወትን ጣዕም የሚቀምሱባት ሀገር ኢትዮጵያዊነት አሰባሳቢ ማንነት አሸንፎ እንዲወጣ፤ እንዚህን ሁሉ ተግባራት በዋስትናነት የሚመክቱ ተቑማትን በማረጋገጥ፣በተደላደሉ መሠረቶች ላይ የቆመ ብሔራዊ አንድነትን መፍጠር ይኖርብናል ነዉ የመልዕክቱ አስኹል። ደራሲዉ በመጨረሻም የመፅሃፉን ዋንኛ የመዳረሻ ግብ ሲያጠቃልለዉ፣ ለዜግነታዊ መንግሥት መሠረት የመጣል ክንዉን የሩቅ ተግባር እንጅ፣ ባንድ ጀንበር የሚከናወን የይድረስ፣ የይድረስ ተግባር አለመሆኑን አፅንኦት ይሰጠዋል። …. አሰባሳቢ የሆነ ሀገራዊ ማንነት ለመቅረፅ የምናደርገዉ ረዥም ጉዞም በሀገራችን ከምንመኘው ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ጋር ተዳብሎ የሚታይ ብቻ ሳይሆን፤ በዋንኛነት ነጥሮ መዉጣት ያለበት ብሔራዊ አጀንዳችን መሆኑንም ያሠምርበታል። ይህንን ሀገራዊ ራዕይም ወደ ተግባር ለመመንዘር፤
በሥልጣን ላይ ያለዉን መንግሥት ማስገደድ፣ ካልሆነም ማስወገድ፣
የብዙዎች ስምምነት የታከለበት ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረስ፤
የሸግግር ጊዜ ተግባራትን በመግባባት መንደፍ፤
እነኝህ ቅድመ ሁኔታዎችም ለምንፈልገዉ የለዉጥ እንቅስቃሴ ወሳኞች በመሆናቸዉ፤ ስለሌላዉ ማዉራቱን አቆመን እርስ በራሳችን ስለወደፊቱ መነጋገር ማስፈለጉን አስረግጧል፤ ዜጋዉ እርስ በርሱ ሳይተማመን ኢትዮጵያዊነት አይሰበክም ይላል። ከዚሁ ጋር አያይዞም፣ በአካል ስንነጋገር፣ የብዙ ዓመት ጟደኛቸዉ በመፅሃፉ ጀርባ ባስመዘገቡት መወድስ፣ < የልቡን እንደ ልቡ፣ ለነገ ሳይል የሚናገረዉ ጟደኛዬ> የሚለዉን የዶክተር ደረጀ ዓለማዬሁን አባባል ጋሼ የሱፍ ሲያጫዉተኝ ከዚህ ይልቅ <ለነገ ብሎ የልቡን እንደ ልቡ የሚናገረዉ ቢባል እኔን በሚገባ ይገልፀኛል። ይህንንም የምለዉ ዝምብዬ ከምድር በመነሳት ሳይሆን፣ የወደፊቱ የአብሮነታችን ጉዳይ፣ ወይም የነገዉ ዕጣ ፋንታችን ስለሚያሳስበኝ ነዉ ይላል። በቅርቡም ዋሸንግተን ላይ በተካሄደ ሕዝባዊ ስብሰባ የአማርኛው ቃና የሚጥመዉ የጊዜያችን ጥቁሩ ሰዉ የአኝዋኩ ኢትዮጵያዊ ኦባንግ ሜቶ ስለነገዉ ካሰብን፣ ለመተማመን እንነጋገር በማለት እንደደገመዉ፣ ድሉን እንድናቃርብና ኢትዮጵያዊነት አሰባሳቢ ማንነት እንዲያብብ፣ እንዲፈካና በአሸናፊነትም ተመንጥቆ እንዲወጣ ማድረግ አለብን ባይ ነዉ ጋሼ ዩሱፍ። እኔ በማንነት ፍለጋዉ ጉዟችን የአፋሩን ቅኔ፣ ቅኝት በተገለጸዉ መልክ ተረድቼዋለሁ። እናንተስ? ለማንኛዉም ገና መፅሃፉን አግኘታችሁ ላላነበባችሁ መልካም ንባብ።