Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ናሚቢያ፤ ሌላዋ የፍትሕ ጀግና! ኢትዮጵያስ? –ኪዳኔ ዓለማየሁ

$
0
0

“ዘ ጋርዲያን” (The Guardian) በተሰኘው ታዋቂ ጋዜጣ እ.አ.አ ነሐሴ 15 ቀን 2006 እንደ ተዘገበው፤ የጀርመን መንግሥትን በመወከል፤ ወ/ሮ ሔይደማሪ ዊዞረክ-ዜዩል (Mrs. Heidemarie Wieczorek-Zeul)፤ የጀርመን የልማት ሚኒስትር፤ ሐገራቸው እ.አ.አ. በ1904 በናሚቢያ ነዋሪዎች (ሔሬሮዎች) ላይ ስለ ፈጸመችው የዘር ማጥፋት ወንጀል ይቅርታ ጠይቀዋል። ለዚህም ወንጀል፤ ናሚቢያውያን (ሔሬሮዎች) ከይቅርታ መጠየቁ በተጨማሪ $4 ቢሊዮን ካሣ እንዲከፈል የጀርመን መንግሥትን መጠየቃቸው ተገልጿል። ከዚህ ቀጥሎ በቀረበው ምንጭ ላይ በመጠቆም ዝርዝር ሐተታውን መመልከት ይቻላል፤

http://www.theguardian.com/world/2004/aug/16/germany.andrewmeldrum

ከላይ በተጠቀሰው ዜና እንደ ተገለጸው፤ ጀርመኖች በፈጸሙት ወንጀል 65 000 ሔሬሮዎች (በኋላ ናሚቢያን) እንደ ተጨፈጨፉ ታውቋል። በጊዜው የነበረው የጀርመኑ የጦር መሪ፤ ጀኔራል ሎታር ቮን ትሮዛ፤ የናሚቢያን ጎሳ (ሔሬሮዎችን) ጥርግርግ አድርገው እንዲጨርሱ ትእዛዝ ማስተላለፉ ተገልጿል። የዚህ የጀርመን ጄኔራልና “የኢትዮጵያ ጨፍጫፊ” በመባል የሚታወቀው የሮዶልፎ ግራዚያኒ አስተሳሰብና ተግባሮች ተመሳሳይነት የሚያስገርም ነው። ለማንኛውም፤ የናሚቢያ መንግሥትና ናሚቢያውያን በሐገራቸው ላይ ለተፈጸመው ወንጀል በመቆርቆር ፍትሕ እንዲገኝ በመታገል ላስገኙት የመጀመሪያ ተጨባጭ ውጤት ሊደነቁ ይገባል። ምንም እንኳ፤ ለጊዜው የጀርመን መንግሥት የሚፈለግበትን ካሣ ለመክፈል ፈቃደኛ ባይሆንም በናሚቢያ ሕዝብና መንግሥት በኩል በቀጣይ የሚከናወነው ጥረት ተገቢውን የፍትሕ ውጤት እንደሚያስገኝ ይታመናል። ለማስታወስ ያህል፤ ናሚቢያ፤ በኢትዮጵያ ድጋፍ ጭምር ከቅኝ ግዛት ቀምበር የተላቀቀችው በቅርብ ጊዜ መሆኑ የታወቀ ነው።

ከናሚቢያ በተጨማሪ፤ ተመሳሳይ የፍትሕ ጀግንነት ካስገኙት ሐገሮች ውስጥ፤ እሥራኤል፤ ሊቢያ፤ ኬንያና ኢንዶኔዚያ ይገኙበታል። ከነዚህ ውስጥ በተለይ እሥራኤል ይቅርታ በመጠየቋም ሆነ በተከፈላት እጅግ ከፍ ያለ ካሣ በኩል ተምሳሌት የሆነች ሐገር ናት። ሌላዋ ለሐገሯ ክብርና ፍትሕ በመቆም ተጨባጭ ውጤት ያስገኘች ሐገር ሊቢያ ናት። በነግራዚያኒ መሪነት ሊቢያ የኢጣልያ ቅኝ ግዛት በነበረችበት ጊዜ ለተፈጸመው የ30 000 ዜጎች ጭፍጨፋ ኢጣልያ ለሊቢያ $5 ቢሊዮን ለመክፈል መስማማቷ ተረጋግጧል። ኬንያም፤ በእንግሊዝ መንግሥት፤ እንዲሁም ኢንዶኔዚያ በኔዘርላንድስ መንግሥት በቅርቡ ይቅርታ ተጠይቀው ካሣ እንዲከፈላቸው ተደርጓል። እነሱም ለሐገራቸው ክብርና ፍትሕ ታግለው መብታቸውን በማስከበራቸው ሊደነቁ ይገባል።

ትልቁ ጉዳይ፤ ኢትዮጵያ ለደረሰባት እጅግ መራርና አሰቃቂ የፋሺሽት ኢጣልያ የጦር ወንጀል ምን ጥረት እየተከናወነ መሆኑን የሚያጠይቀው ነው። እንደሚታወቀው፤ እ.አ.አ. በ1935-41 ፋሺሽት ኢጣልያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ዘመን፤ አንድ ሚልዮን ኢትዮጵያውያን ተሰውተዋል። ከነዚሁ ውስጥ፤ በሶስት ቀኖች ብቻ (የካቲት 12-14 ቀኖች 1929 ዓ/ም)፤ በአዲስ አበባ ከተማ፤ 30 000 ኢትዮጵያውያን ተጨፍጭፈዋል። በተጨማሪም፤ 2000 ቤተ ክርስቲያኖች፤ 525 000 ቤቶችና 14 ሚሊዮን እንስሶች ወድመዋል። እንዲሁም መጠነ-ሰፊ የሆነ የኢትዮጵያ ንብረት በፋሺሽቶች ተዘርፎ አሁንም በቫቲካንና በኢጣልያ መንግሥቶች ይዞታ የሚገኝ አለ።

በኢትዮጵያ ላይ፤ በመርዝ ጪስ በመጠቀም ጭምር፤ ለተፈጸመው የጦር ወንጀል፤ ኢጣልያ እስካሁን ድረስ የከፈለችው ኢምንት የሆነ፤ ቆቃ ግድብ የተሠራበት $25 ሚሊዮን ብቻ ነው። ኢንዲያውም፤ የጦር ወንጀሉ አልበቃ ብሏት፤ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው፤ በቅርቡ፤ የኢጣልያ መንግሥት ለግፈኛው የጦር ወንጀለኛ ለግራዚያኒ ልዩ መታሰቢያና መናፈሻ አስመርቃለታለች። በነገራችን ላይ፤ በምረቃው ሥነሥርዓት ላይ የቫቲካን ተወካይ ተገኝተው እንደ ነበር ቢ.ቢ.ሲ ዘግቧል።

ባቲካንም በጊዜው የነበሩት ፖፕ ፓየስ 11ኛና የፋሺሽቱ መሪ፤ ሙሶሊኒ፤ እጅና ጓንት ሆነው በኢትዮጵያ ላይ ለተፈጸመው የጦር ወንጀል፤ እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ አልጠየቀችም። አይሑዶችን ግን፤ በናዚ ጀርመኒ ስለ ደረሰባቸው ጭፍጨፋ በጊዜው የተቃውሞ ድምፅ ባለማሰማቷ ብቻ በመደጋገም ይቅርታ ጠይቃለች።

በአጠቃላይ፤ ኢትዮጵያ ለተፈጸመባት የጦር ወንጀል የሚገባት ፍትሕ፤

1ኛ/ የኢጣልያ መንግሥት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተገቢውን ካሣ እንዲከፍል ማድረግ፤ ይኸውም መከናወን ያለበት

ለኢትዮጵያ ሕዝብ በተጨባጭና ለዘለቄታው በሚጠቅም መንገድ፤ ለምሳሌ አስፈላጊ በሆኑ ፕሮጀክቶች

ሊፈጸም ይገባል።

2ኛ/ ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ልትጠይቅ ይገባል።

3ኛ/ ከኢትዮጵያ የተዘረፉት ንብረቶች ለባለቤቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲመለሱ ማድረግ ያስፈልጋል። አመላለሱ

ግን አስተማማኝ በሆነ መንገድ ለመጪው ትውልድ ሁሉ ታሪካዊ ማስረጃነቱ ተጠብቆ እንዲቆይ ማረጋገጥ

ያስፈልጋል።

4ኛ/ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመውን ወንጀል መዝግቦ ተገቢው ፍትሕ እንዲገኝ

አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ይገባዋል።

5ኛ/ ለግፈኛውና ወንጀለኛው ፋሺሽት፤ ለግራዚያኒ፤ አፊሌ ከተማ (ኢጣልያ) የተቋቋመው መታሰቢያና መናፈሻ

መወገድ ይገባዋል።

በተጨማሪ፤ ሰሞኑን የቫቲካን ከፍተኛ መልእክተኞች ቡድን ኢትዮጵያን በመጎብኘት ላይ በመሆኑ ከቫቲካን ስለሚያስፈልገው ፍትሕ ጉዳይ ለመነጋገር ጥሩ አጋጣሚ ሊያስገኝ ይችላል። የሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣኖች፤ በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሪዎችና ሌሎችም በኢትዮጵያ ለሐገር ፍትሕ የሚታገሉ ሰዎችና ድርጅቶች በዚህ አጋጣሚ ቢጠቀሙ መልካም ይሆናል።

ዓለም-አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ – የኢትዮጵያ ጉዳይ (Global Alliance for Justice – The Ethiopian Cause) www.globalallianceforethiopia.org ከላይ ለተዘረዘሩት አምስት ዓላማዎች እየተንቀሳቀስ መሆኑንና በሚቀጥለውም የየካቲት 12 የሰማእታት ክብረ-በዓል ቀን፤ ከኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር በመተባበር በዓለም ዙሪያ ከ30 ከተሞች በላይ ለሐገር ፍትሕ ጥረቱን ይቀጥላል። በዚህ አጋጣሚም፤ ከዚህ በላይ በተጠቀሰው ድር-ገጽ ውስጥ የሚገኘውን ዓለም-አቀፍ አቤቱታ አንባቢዎች እንዲፈርሙት ይጋብዛል።

ውድ ሐገራችን የሚገባትን ክብርና ፍትሕ እንድትጎናጸፍ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ተባብረን እንድንታገልና ተፈላጊውን ውጤት እንድናስገኝ ቸሩ የኢትዮጵያ አምላክ ይርዳን። አሜን።

 

Comment

 

 

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>