Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ሠርቶ ወይንስ ሰርቆ? ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

$
0
0

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

arab ethiopia
ሰሞኑን አዲስ አበባን የሚዘዋወር ሰው በብዙ አካባቢዎች ከሚያያቸው ወያኔያዊ መፈክሮች አንዱና ጎልቶ የሚታየው “በሀገር ውስጥ ሠርቶ መለወጥ ይቻላል!” የሚለው ነው፡፡በትላልቅ የጨርቅ ጀንዲዎች ላይ ከባባድ ተምኔቶችን በመፈክርነት ጽፎ በየአደባባዩ መስቀል የወያኔ ትልቁ መገለጫ ነው – የደርግም፡፡ ግን አብዛኞቹ መፈክሮች ከምኞትና ሰውን ከማቁልጭለጭ አልፈው አያውቁም – የሁለቱም፡፡ ያን ስንት ድሃ ሊያለብስ በሚችል አቡጄዲ የተሰቀለ መፈክር ሳነብ ወዲያው ያልኩት ‹በሀገር ውስጥ ሠርቀህ መለወጥ ይቻላል›፡፡ (ሠርተው በድካማቸው ፍሬ የሚያልፍላቸው የሉም ማለት በመሠረቱ ስህተት ነው፤ ሠርተህ ሲያልፍልህ ግን በሥራህና በቁሣዊ ዕድገትህ መካከል የሚጠበቅ የጊዜ፣ የመነሻ ወረት፣ የጥረት፣ የትርፍ ‹ማሪጂን›፣ የዕውቀት፣ ለመክሰር የመዘጋጀት፣ ከሠራተኞች ጋር የሚኖር የጥቅማ ጥቅምና የመሳሰለው ግንኙነት ሊታዩ ይገባል፡፡ አለበለዚያ እንደወያኔ ሀብታም ትናንት ሥራ ጀምረህ በማግሥቱ ቀጭን ጌታ ከሆንክ ከሥራህ ቀድሞ ብልግናህ ማለቴ ብልጽግናህ ታዬ እንደማለት ነውና ይህ ንግድ ሳይን ማጅራት መምታት ነው – እኛ ባልተወለደ አንጀት እየተመታን እንዳለነው፡፡)

በላይኛው አንቀጽ የጠቀስኩትን መፈክር ሳነብ እስቃለሁ፤ ፍርፍር ብዬ ነው የምስቀው፡፡ ምክንያት አለኝ፡፡ ትልቅ ምክንያት፡፡ ለዝርዝሩ በ‹አዲስ መስመር እንገናኝ› – (ኩረጃ በኔ አልተጀመረም)፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በአሁኑ ዘመን ሠርተህ ሊያልፍልህ አይችልም፡፡ በየትኛው ሒሣብ? ኧረ እንዴት ተደርጎ? ምን ሠርተህና ማንስ አሠርቶህ? ሕግን ጠብቀህ ከሠራህ የመጀመሪያው ከሣሪ አንተ ነህ፡፡ ቀረጡ፣ ግብሩ፣ ኪራዩ ባንተ በሕጋዊው ነጋዴ ላይ ይቆለላል፡፡ ባይገርምህ ከዘር አኳያ ማውራት ስልችት አለኝ እንጂ ወያኔዎች አንድን ትግሬ ያልሆነ ምሥኪን ነጋዴ በነባሩ የመንግሥት የኪራይ ቤት ላይ – ለምሳሌ የ200 ብሩን ኪራይ በአንድ ጊዜ 10000 በማድረግ እሱ አጨብጭቦ – አብዶም ሊሆን ይችላል – ሲወጣላቸው ከ200 ባነሰ ኪራይ ‹የኛ ነው› ለሚሉት ሰው የሚያከራዩ ዓለም ከምታመርታቸው ግፈኛ ዜጎቿ መካከል ተወዳዳሪ የሌላቸው አረመኔዎች ናቸው ብዬ ብናገር ደስ ባለኝ ነበር፡፡ ሂድ አይሉህም – እንድትሄድ ግን ያደርጉሃል፡፡ በትግርኛ ‹ውፃዕ አይተበሎ፤ ከምፅወፅዕ ግበሮ› ይባላል፡፡ የተንኮልና የወንጀል ማምረቻ ዘመናዊ ፋብሪካዎች ናቸው፡፡ ግፋቸውና የሸራቸው ድርና ማግ ተጎልጉሎ አያልቅም፡፡

ስለ “ባገር‹ህ› ሠርተህ ያልፍልሃል” የማሞኛ ፈሊጥ የኔን ልናገር፡፡ ሰለቸኝ፤ ደከመኝ፣ አጣሁ – ገረጣሁ ሳልል በንጹሕ ኅሊና ራሴንና ቤተሰቤን ለማኖርና ሀገሬን በሙያየ ለማገልገል ከሙያዎች በአንዱ ተሠማርቼ መሥራት ከጀመርኩ ጥቂት አሠርት ዓመታት አለፉ፡፡ የጀመርኩበት ደሞዝ የኢት. ብር 500 ነበር – ለእናት ሀገር ጥሪና (በአሁኑ የወያኔ ዘመን የአባይ ግድብ ዓይነት መሆኑ ነው) ለጡረታ ተቆራርጦ ብር 385 ይደርሰኝ ነበር፡፡ ለተለያዩ የሠራተኞች ድንገተኛ የንብረት መጥፋትና ሞትን ጨምሮ የጤና መጓደል ችግሮች ከተከሰቱም እንደብሔራዊ ሎቶሪ የዕጣ ቀን ደመወዝ መክፈያ ቢሮ ተኮልኩለው የሚጠብቁ የደመወዝ ቀበኞች ካሉም የሚደርሰኝ ገንዘብ ከዚያም ሊያንስ ይችላል፡፡ ለማንኛውም ያንን ገንዘብ ወስጄ ወር እስከ ወር የመድረስ ግዴታ ነበረብኝ፡፡ ቀስ እያለ ቤተሰብ ስጨምር ደመወዙም እያሽኮተኮተ አንድ ሺን መጠጋቱና ማለፉም አልቀረም፡፡ ያኔ ታዲያ አልዘባነን እንጂ በቤቴ ውስጥ በተለይ በምግብና በመጠጥ በልብስም ያን ያህል እንዳሁኑ የጎላ ችግር አልነበረብኝም፡፡ በአንጻራዊ ሁኔታ ሁሉም ነገር እርካሽ ስለነበር በጣም መቀናጣት ይቅር እንጂ መሠረታዊ ፍላጎቶቼን ማሟላት የሚሳነኝ አልነበርኩም፡፡

አሁን ግን አጠቃላይ የወር ገቢዬ ወደ አምስት ሺህ ብር ገደማ ደርሶ መማል ሳያስፈልገኝ እውነቱን ለመናገር ከወር እወር እምደርሰው ብዙ ፍላጎቶቼን ለምሳሌ የእንስሳት ተዋፅዖዎችን፣ አትክልትና ፍራፍሬ ወዘተ. ለማሟላት መከጀል ብቻም ሳይሆን ለማሰብም ዕድል ሳላገኝ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የምትኖሩ ዜጎች የአራት ሺህ ብር የተጣራ ደመወዝን ገንዘባዊ ዋጋ ታውቃላችሁና ይህን ለማስረዳት ብዙ መድከም አይገባኝም፡፡

እኔ – ልብ አድርጉ – ይህን መጠን የማገኘው ሁለት ቦታ ሠርቼ ነው፡፡ እንዲህ የምላችሁ “ተጨማሪ ሥራ ሥራ” ብላችሁ ለምትመክሩኝ ነው፡፡ ምን አለፋችሁ – ኢትዮጵያ ውስጥ ካላጭበረበርክና ካልሰረቅህ በቀን 48 ሰዓት ብትሠራ ከጓያ ሽሮ አታልፍም፡፡ ሰዎች እንዴት ይኖራሉ ታዲያ? ብለህ ስትጠይቅ ብዙ ነገር ዕንቆቅልሽ ሊሆንብህ ይችላል፡፡ ጠጋ ብለህ ከመረመርክ ግን ግልጽ ነው፡፡

ብዙ ሰዎች በተለይም ወጣች የተዘባነነ ሕይወት ሲመሩ ታያለህ – የአህያ ጆሮውን ከየኪሣቸው እየመዘረጡ፣ በቆንጆ መኪናዎቻቸው እየተንፈላሰሱ፣ በየቀኑ የሚቀያየሩ ቆነጃጅትን እጎናቸው ሻጥ እያደረጉ፣ ሙዚቃቸውን ልክ እንደኬንያ ማታቱ እስከጣራ ለቅቀው ከትከሻቸው ጀምሮ በስሜት እየተወዛወዙ በከተማዋ ሲንሸራሸሩ … ማታና ውድቅት ላይም በየጭፈራና ዳንኪራ ቤቱ እየተውረገረጉ ታያቸዋለህ፤ እነዚህ ወጣቶች የሚያቀርቡልህን ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን በሌለህ ኢኮኖሚ ከአቅምህ በላይ እየተበጣጠስክ – እየተበደርክ እየተለቀትክ – ያልኖርክበትን ጊዜ ደመወዝም በሞዴል ስድስትና ከብድርና ቁጠባ እየተበደርክ የምትገዛው የነሱ ድሎት እንዳይጓደል መሆኑን ታዲያ ዕወቅ፡፡ በዚያውም ላይ አንተ ለሀገርህ ብዙ ለፍተህና ደክመህ ስታበቃ የነተበ ሸሚዝ፣ የተንሻፈፈና አቧራ የሚቅም ጫማ፣ መልኩን ከአንዴም አልፎ ሁለት ሦስቴ የቀየረ ኮት ወይም ጃኬት፣ አንገቱ በዐይጥ የተበላ የሚመስል የተቦተረፈ ካናቴራ… ለብሰህ ተቆሳቁለህ ትታያለህ – መጥፎ የማይባል ደመወዝ እያገኘህ፡፡ ሀገራችን በቅጡ ልትመረመር ይገባታል፡፡ የኑሮ ልዩነት የትም ሀገር ያለ ቢሆንም የኛ ግን ከየትኛውም ጋር አይወዳደርም፡፡

ብዙ ነገሮች ብልጭልጭ ናቸው – የምታየው እውነት ከምትሰማው እውነት ይለይብሃል፡፡ የምትኖረው ሕይወት እንደምትኖር ከሚነገርልህ ሕይወት የተለዬ ነው፡፡ የተያዘው የአፍ ጂዶ ነው፡፡

የዕለትም ይሁን የወር ገቢውን በራሱ የሚወስን ሰው ጥሩ ሊኖር ይችላል፡፡ ምክንያቱም ገበያውን ተከትሎ – ወጪና ገቢውን አጢኖ የሚሸጠውን ዕቃ ዋጋ ወይም የአገልግሎት ክፍያ በዚያው መጠን ያስተካክላልና፡፡ እንደኔ ዓይነቱ መንግሥት ወይም አሠሪየ የደነገገልኝን ወርሃዊ ምንዳ የሚያገኝ ሰው ግን ሕይወቱ በመኖርና ባለመኖር አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ወደሌላኛው ዓለም እስኪጠራ ድረስ በነፍስ በሥጋም ይዋትታል፡፡ በዚህ ሁኔታ “ሀገርህ ውስጥ ሠርተህ መለወጥ ትችላለህ” ሲሉህ ብትሰማ አቅመቢስነትህን ተረድተው በደካማ ጎንህ እየቀለዱ ሊያስቁብህ እንደሆነ ይገባሃል፡፡ ለሠላሣ ዓመታት በተመሥጋኝነት የሠራሁ ሰውዬ በስተርጅናየ ደመወዜ አልበቃኝ ብሎ ለልመና ልዳረግ ምንም ባልቀረኝ ሁኔታ ይህ የወያኔ አባባል ምን ስም ሊሰጠው እንደሚችል አይገባኝም፤ “በሀገር ውስጥ ሠርቶ መለወጥ ይቻላል፡፡”

ወጣት የዩኒቨርስቲ ተመራቂዎችንና ልዩ ልዩ የግለሰብም ይሁን የመንግሥት ተቀጣሪዎችን ኑሮ ብታዩ ይዘገንናችኋል፡፡ ያልሞትን የመሰልነው እራፊ ጨርቅ ትከሻችን ላይ ጣል አድርገን በየመንገዱ ወንከር ወንከር ስንል ስለምንታይ እንጂ ከሞትን ቆይተናል፡፡ እስኪ የእግር ኳስ ጨዋ ልናይ ስቴዲየም ስንገባ እዩን – ከዚያ በነአርሰናልና ማንችስተር ጨዋታ ጊዜ ስቴዲየም የሚገባውን የአውሮፓን ጨዋታ ተመልካች ደግሞ እዩ – አወዳድሩንና የጉስቁልናችንን ደረጃ ታዘቡ – እኛን ያፈራ መንግሥት ነው እንግዲህ በምሥኪን ጎስቋሎች ላይ በደረሰው የፈጠራ ተውኔት እየተኮፈሰ ‹አድጋችኋል› እያለ በሬሣችን ላይ እያላገጠ የሚገኘው፡፡ ጭንቅላት የሌላቸው ደግሞ መንግሥት ተብዬው ብቻ ሳይሆን ባለሀብቶችም ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች – ጨካኝ አትበሉኝና – መቅሰፍት ቢወርድባቸው ደስተኛ  ሀዘንተኛ ነኝ፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ ማሰብ አይችሉም፤ እነሱ ያላቸው የመኖር መብት ሠራተኞቻቸው ያላቸው አይመስላቸውም፡፡ እነሱ እየተንደላቀቁ ሲኖሩ ሠራተኞቻቸው በስቃይና በመከራ ይኖራሉ፡፡ እነሱ በበርሜል እየዛቁ አዝመራውን ወደቤታቸው ሲከቱ ለሠራተኞቻቸው የሚከፍሉት ደሞዝ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ እናም የእውነት አምላክ እግዚአብሔር ፍርዱን ይስጣቸው፡፡…

ስለዚህ ተቀጣሪ ሠራተኛ በመንግሥትም ሆነ በግል ተቀጥሮ መሥራትን ባይፈልግ  አይፈረድበትም፡፡ የኗሪ አኗኗሪ ሆኖ በሀገሩና በቀየው በርሀብ አለንጋ እየተገረፈ ከሚሞት በማያውቀው ሀገር ተሰድዶ ከሁለቱ ዕድሎች በአንደኛው እንደፍጥርጥሩ መሆንን ይመኛል -  መሞት ወይም መዳን፡፡ በሀገሩ የበይ ተመልካች ሆኖ ነቀዞችና ግሪሣዎች የገዛ ሀብት ንብረቱን ሲመዘብሩና እርሱን ለከፋ ድህነት ሲዳርጉ ከሚያይ ዐረብ ሀገርና አፍሪካ ሀገራት አይደለም የቀይ ባሕር ዓሣና በበረሃ እያደፈጡ የሰውነት አካልን ለመለዋወጫነት የሚዘርፉ ሽፍታዎች ሲሳይ መሆንን ይመርጣል – ተጠየቁ ቀላል ነው – እዚህም ሞት ነው – እዚያም ያው ሞት ነው፤ የሞት ደግሞ ነጭና ጥቁር የለውም፡፡ በበኩሌ ይህን የወጣቶቹን መጥፎ ምርጫ መደገፌ አይደለም፡፡ ነገር ግን እኛን በነሱ ቦታ ተክተን ስናስበው የምርጫዎች መጥበብ የማያስደርጉት ነገር እንደሌለ መረዳት አይከብደንም የሚል ግምት አለኝ፡፡ ሰው ሲጨክንብህ፤ ‹የኔ ዜጋ ነው፤ አለኝታውና ዋስ ከለላው ልሁንለት› የሚልህ ተቆርቋሪ መንግሥት በሀገርህ ስታጣ፣ የኔ መንግሥት የምትለው አንተን እንደባይተዋር ቆጥሮ የእንጀራ ልጁ ሲያደርግህና እርጎውንና ዐይቡን የኔ ለሚላቸው ወገኖች እየሰጠ ለአንተ ሞትንና እሥራትን የሚያከፋፍልህ ከሆነ ምርጫህ እግርህ ባወጣ ያቺን የሲዖል ምድር ኢትዮጵያ ለቅቀህ መሄድ ነው፡፡ ዜጎች እያደረጉ ያሉትም ይህንኑ ነው፡፡ ለአፍ አቀበት የለውምና መንግሥትና አሽቃባጭ የጥቅም ተጋሪዎቹ በያዙት ሚዲያ ቢያሽቃብጡ ሰርቆ እንጂ ሠርቶ ሊያልፍለት የሚችለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር እጅግ አነስተኛ በመሆኑ አምላከ ኢትዮጵያ ፊቱን እስኪመልስልን ድረስ ያለን ብቸኛ አማራጭ ስደትና ፍልሰት ነው – እንደኔ ይህ ባይሆን ምርጫየ ነው፡፡ እናም ይህን “ከሠራህ በሀገርህ ያልፍልሃል” የሚሉትን ፈሊጥ ራሳቸው ለራሳቸው ይዘምሩት፤ እኔ ትልቁ አብነት ነኝ፤ ሠራሁ ፣ለፋሁ፣ ግን ምን ተጠቀምሁ? ባይገርማችሁ ለስደት የተነሳሳው ደህና ሥራ ያለው ሁሉ ነው፤ ሁሉም ሕዝብ ነው ለስደት የጓጓው ማለት ይቻላል፡፡ ግን ዕድሉ ጠባብ ነው፡፡ የኔ ዓይነቱ ጎምቱ ሰው ደግሞ ከእንግዲህ በኋላ ተነስቶ ነጋዴ ልሁን ቢል አንደኛ የወያኔ አሽቃባጭ መሆን ሊኖርበት ነው፤ ሁለተኛ የንግድን ሀሁ ስለማያውቅ ‹ሀ› ብሎ መማር አለበት፤ ሦስተኛ ሁሉም ሰው ነጋዴና ሁሉም ሰው ሸቃጭ ሊሆን አይጠበቅበትም፤ በሚሠራው ሥራ ሕይወቱን በአግባቡ ሊመራ የሚያስችለው ክፍያ እንደወቅቱ የገንዘብ የመግዛት አቅም እየተሰላ ሊከፈለው ሲገባ ‹ሁልህም ነጋዴ ሁን፤ ሁልህም እጅ መንሻ ወደሚያስገኝ ሥራ ተዛወር› ብሎ ፍርደ ገምድል ብያኔ መስጠቱ አግባብ አይመስለኝም፡፡

ተንቀባርረው ስለሚኖሩ ዜጎች ትንሽ ልጨምር፡፡ እነዚህ እጅጉን “የሚያስቀና” ቁሣዊ ሕይወት የሚመሩ ዜጎች ባጭሩ እነዚህ ናቸው፡- ኅሊናቸውን ለገንዘብና ለሥልጣን የሸጡ ወያኔዎች፣ የወያኔ ጋሻ ጃግሬዎች፣ ብር እንደፈለጉ እንደሚያሣትሙ የሚወራላቸው የሥርዓቱ ምሰሦዎችና ወጋግራዎች፣ በማንኛውም ዓይነት መንግሥታዊም ይሁን ኅሊናዊ ወይም ሃይማኖታዊ ሕግ የማይገዙ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ጥገኛ ነጋዴዎች፣ ካለቀረጥና ካለግብር ዕቃ ከውጭ እያስገቡ እንደፈለጉ በሀገሪቱ ላይ የሚፈነጩ ዘበናይ አልቅቶችና መዥገሮች፣ ከቻይናና መሰል ነፍሰ በላ ሀገሮች ‹ፌክ› ዕቃዎችን እያስመረቱ በጠፍ ጨረቃ በማስገባት በሕዝብ ሀብትና ገንዘብ የሚቀልዱ፣ ትላልቅ ደመወዝ የሚያገኙ የመያድና የዓለም አቀፍ ተቋማት ሠራተኞች፣ በሥራቸው አጋጣሚ ጉቦና ሙስና ውስጥ የሚዘፈቁና ደመወዛቸውን እስከመርሳት የሚደርሱ “የሕዝብ አገልጋዮች”፣ ቤትና ዕቃ የሚያከራዩ ሰዎች፣ ከሞላ ጎደል በሁሉም የሽያጭና የገንዘብ ዝውውር ከተፍ የሚሉ በጠበቀ መረብ የተደራጁ ደላሎች፣ የባንክና ኢንሹራንስ እንዲሁም የሌሎች ሴክተሮች የአክሲዮን ማኅበራትና ካምፓኒዎች ባለቤቶች፣ ለዲያብሎስ መንግሥት ያደሩ መታቾችና አስመታቾች፣ በሃይማኖትና በዕርዳታ ሽፋን ኅብረተሰቡ ውስጥ ለተለያየ ዓላማ የተሰገሰጉ ሃሳዊ መሢሆች፣ ከፍ ባለ የሽርሙጥና ‹ሙያ› ላይ የተሠማሩ ሴተኛ አዳሪዎች(በአንድ አዳር መኪና ወይ ቤት የሚያስገዙ እሳት የላሱ ሴቶች አሉ!)፣ ገንዘብ መራሽ አየር በአየር ነጋዴዎች፣ የመንግሥትን መሬት ከባለሥልጣናቱ ጋር እየተሻረኩ በብዛትና በነጻ በመውሰድ የሚቸበችቡ ዜጎች፣ የዕቃ ግዢ ሠራተኞች፣ ዕቃና ንብረትን በጨረታ ለመሸጥ ወይም ለመግዛት የሚቋቋሙ ኮሚቴዎች አባላት፣ በሀሰት የማወራረጃ ሠነድ የመንግሥትንም ይሁን የግል ድርጅትን ገንዘብ የሚሞልጩ ዜጎች፣… እነዚህና እነዚህን መሰል ወገኖች እኛ ብንራብና ብንጮህ፣ ብንሰደድና በአውሬ ተበልተን ብንሞት ያቺ ምሥኪን ታሪካዊት የፈረንሣይ ልዕልት ዳቦ ዳቦ እያሉ ለጮኹ ገበሬዎችና ሠራተኞች ‹ቤታቸው ሄደው ለምን ኬክ አይበሉም› እንዳለችው የኞች ደደቦችም ‹በሀገር ውስጥ ሠርቶ መለወጥ ይቻላል› ቢሉ የደደብነታቸው ብዛት ብዙም እንዳናዝንባቸው ያደርገናል፡፡

አንዲት ሀገር ውስጥ ችግር መኖሩን እንዴት እናውቃለን? ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሆነንን የትም ሳንዋትት ከቅርባችን ከሚገኘው የትዝብታችን ማኅደር ውስጥ እየመዘዝን ብዙ ነጥቦችን መናገር  እንችላለን፡፡ ከዚህ በታች የምጠቅስላችሁ ሀገራዊ የጤናማነት መጓደል አመላካች ነጥቦች ራሴው የታዘብኳቸው ናቸው፡፡

ሀ. ዋጋው ቀነስ ወደሚለው ወደየትኛውም ሆስፒታልና  የመንግሥት ጤና ጣቢያ ሂዱ፡፡ ለምሳሌ ጥቁር አንበሣ ሬፈራል ሆስፒታልን ላስቃኛችሁ፡፡ ይህ ሆስፒታል ከአዲስ አበባና ከክፍለ ሀገር በሚመጡ ህሙማንና አስታማሚዎች ሁልጊዜ (24/7) እንደተጨናነቀ ነው፡፡ ግቢው ውስጥ በአንድ ጊዜ ሲተረማመስ የምታዩት ሕዝብ ያለማጋነን የአንዲት ትንሽዬ ሀገር ጠቅላላ የሕዝብ ቁጥር ሊሆን ይችላል፡፡ የበሽተኛ መብዛት እንግዲህ የአንዲትን ሀገር የጤና ደረጃ ዝቅተኛነት ስለሚጠቁም (ድንገተኛ ወረርሽኝ – ኤፒደሚክ እስካልተከሰተ ድረስ ማለት ነው) የሚወራው የሀገራችን ዕድገት አፋዊ እንጂ እውናዊ ሊሆን አይችልም፡፡

በዚያ ላይ በየሆስፒታሉ የምናያቸው ዜጎቻችን የሚታይባቸው ጉስቁልና ልብን ይሰብራል፡፡ አለባበሳቸው፣ የሰውነት ይዞታቸው(ክሳት፣ግርጣት፣የአካል መጠን…)፣ ጠረናቸው፣ ወዘተ. ከአንዲት በያመቱ 11 በመቶ እንደምታድግ ከሚነገርላት የ“መካከለኛ ገቢ ከሚያገኙ” ሀገሮች ተርታ ልትሠለፍ በወራት የሚቆጠር ጊዜ ከቀራት “ፌዴራላዊት” ሀገር የተገኙ ዜጎች አያስመስላቸውም፡፡ ጥቁር አንበሣን ያዬ ሀገር የለኝም ይላል፤ ሀኪሞቹ ብዙዎቹ ሰልችተዋል፤ ሰውን እንደውሻ ይቆጥራሉ፤ በሽተኛው ከሞተ በኋላ እንዲመጣ የሚቀጥሩት – ቀጠሮ አሳጣሪ ዘመድ ከሌለ – ብዙውን ጊዜ ከስድስት ወር በላይ ነው፡፡ አልጋ የለም – ማደንዘዣ የለም – መቀስ የለም – ወስፌ የለም… እያሉ ማጉላላት የብዙዎች ሐኪሞች የደስታና የሃሤት ምንጭ ይመስላል፡፡ ሞት ጥንቡን ስለጣለ ማንም ለማንም የሚያዝን አንጀት የለውም ፡፡ ለነገሩ “ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም” እንዲሉ መንግሥት ከመጤፍ የማይቆጥረውን ሕዝብ የበታች ሠራተኛ ቢያዋርደውና በአግባቡ ባያስተናግደው አይፈረድበትም፡፡ (ወደግል እንዳይኬድ ክፍያው ሕክምናውን ሳይጨምር ለአንድ አዳር ብቻ የሚያስከፍሉት ከባለ አሥራ አምስት ኮከብ የሱትሩም ክፍያ ቢበልጥ እንጂ አይተናነስም – ዘመኑ የዝረፍ እንዝረፍ በመሆኑ የሚቆጣጠራቸው አካልም የለም – ከፈለጉ በእግርህ ገብተህ ሬሣህን ዘመዶችህ በብዙ ሺህ ብር እንዲገዙ ሊጠየቁ ይችላሉ – በቀላል የሕክምና ስህተት፡፡ ገንዘብ ማግበስበስ እንጂ ሙያዊ ሥነ ምግባር ብሎ ነገር በሁሉም ዘርፍ አርቀን ቀብረናል)፡፡ …

ለ. ፖሊስ ጣቢያም ሂድ፡፡ ሕዝቡ አዳርና ውሎው እዚሁ ነው ወይ ትላለህ፡፡ በደረቅ ወንጀልም ይሁን በፍትሐ ብሔር እየተከሰሰና እየተካሰሰ ፖሊስ ጣቢያዎችን የሙጥኝ ብሎ የምታየውን ሕዝብ ማን ሠርቶ እንደሚቀልበው ስታስብ አንዳችም መልስ አታገኝም፡፡ ወንጀልና ወንጀለኝነት የባሕርይ ስጦታዎቻችን የሆኑ ይመስል በተለይ በአሁኑ ወቅት ተካሳሹና በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የሚውለው ወገን በጣም እየተበራከተ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ደግሞ የሀገርን ዕድገት ሳይሆን በችግር ውስጥ ያለን መሆናችንን ነው፡፡

ሐ. ፍርድ ቤቶችን እንጎብኝ፡፡ ልክ እንደሆስፒታሉ ሁሉ እነሱም በሰው ግጥም እንዳሉ ይውላሉ፡፡ ፍትህን የምታገኘው – በአብዛኛው -  በገንዘብ መሆኑ እንኳንስ  ፍትህና ርትዕ ታጥበው ገደል በገቡበት በዘንድሮው ዘመንና ጥንትም የነበረ መሆኑ አይካድም – እንዳሁኑ ግን ዐይን ያወጣ የፍትህ መዛባት ታይቶ የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ በግ የሰጠው ባለጉዳይ በሬ በሰጠው ባለጉዳይ እስኪረገጥና የፍርድ ሚዛኑ በሕጉ መሠረት ሳይሆን ዳኛውና ዐቃቤ ሕጉ በተቋደሱት ንዋይ እስኪወሰን ድረስ እዚያም ቤት ብዙ መጉላላት አለ፡፡ ይህ በተለይና ይበልጡኑ በባልና ሚስት ፍቺ ጉዳይና በንብረት ክርክር ዙሪያ የሚስተዋለው የፍርድ ቤት ጭንቅንቅ የሀገርን ጤናማነት የሚያሳይ አይደለም፡፡ በነዚህም ሥፍራዎች ሰዎች ሥራ ፈትተው ከአምራችነትና ከሠራተኝነት ይልቅ አፈኛነትንና የነገር ብልት አወጣጥን እየተማሩ ስለሚውሉ ሀገር ችግር ላይ ለመውደቋ አንዱ ምልክት ነው፡፡

መ. ከተማ አውቶቡስንና ሌሎች የትራንስፖርት መኪኖችን እንቃኝ፡፡ እነዚህ ተሸከርካሪዎች ከጧት እስከማታ ሰው አርግዘው እንደወረገብ ነፍሰጡር ተንገፍጥጠው ነው የሚታዩ፡፡ በመሠረቱ ሰው አይዘዋወር አይባልም፡፡ ነገር ግን በሥራ ሰዓት ይህ ሁሉ ሕዝብ በመኪኖች እየታጨቀ ሲዘዋወር እኔን መሰል ሥራ ፈቶች ምክንያቱን ማጠያየቃችን አይቀርም – ወትዋቹ ኅሊናችን እየጠየቀ ያስቸግረናልና፡፡ በአውቶቡስ ውስጥ መቼም ሥራ እንደማይሠራ ይታወቃል፡፡ የሰዎቹን ሁኔታ ስናይ ደግሞ ብዙዎቹ የቢሮ ሠራተኞች አይመስሉም፡፡ ምናልባት የክፍለ ሀገር ተጓጓዦችን ለሥራና ለቤተሰብ ጥየቃ ልንል እንችል ይሆናል፤ በከተሞች ያለው ዝውውር ግን ብዙም ግልጽ አይደለም – በመኪናም ይሁን በእግር ሰውን ስታዩት በገፍ ተጓዥ ሆኗል፡፡ በዚያ ላይ በየአደባባዩና በየቦታው በሥራ ሰዓት የሚታየው የሕዝብ ትርምስ በእውኑ ይህ ሁሉ ሕዝብ እህል ቀምሶ ያድር ይሆን ወይ ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡ አሳሳቢ ነው፡፡ በሌሎች ሀገሮች ስናይ – በፊልምም ቢሆን – ሕዝቡ በሥራ ሰዓት ከተማ ውስጥ አይታይም፡፡ በየሥራው ይከታል፡፡ የኛ ግን ሰኞ የለ፣ እሁድ የለ፣ ጧት የለ፣ ቀትር የለ – ሲርመሰመስ ነው የሚውል፡፡ ይህ የሚያሳየው የሥራ አጡና ምናልባትም የሥራ ፈቱ ቁጥር ሥራ ከሚሠራው ይልቅ የገነነ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ጥቂቶች ሠርተው ብዙዎችነን የማስተዳደር ሁኔታ ደግሞ ክንድን የሚያዝልና ድህነትን የሚያስፋፋ ተስፋንም የሚያሳጣ እንግዳ ክስተት ነው፡፡ ‹አደጋ አለው!› – ትላለች የዘሩ ሚስት – እውነቷን ነው፡፡ በላተኛ በዝቶ ሠራተኛ ከጠፋ አደገኛ ችግር አለ – በሂደት እርስ በርስ መበላላትም ሊመጣ ይችላል፡፡ ይህን የሕዝብ ኃይል በአድልዖ ሳይሆን በአግባቡ አስተምሮና አሰልጥኖ ለሥራና ለአገልግሎት የሚያበቃ የመንግሥት ተቋም በአፋጣኝ ያስፈልገናል፡፡ የአሁኑን መንግሥት መንግሥት ካልነው ተሳስተናል፡፡ ይህ ሸውራራ የወያኔ መንግሥት በሰማሁት መረጃ መሠረት ከ50 ቢሊዮን ዶላር ከሚበልጥ ዕርዳታና ብድር ውስጥ ከ12 ቢሊዮን የሚልቀውን መዝብሮና አስመዝብሮ ወደውጭ የላከ፣ ከቀሪው 38 ቢሊዮን ዶላር ውስጥም በሙስናና ንቅዘት የአንበሣ ድርሻውን አውድሞ በተረፈችዋ መናኛ ፍራንክ ጥቂት የአስፋልት መንገዶችንና የልማት አውታሮችን ለታይታ ያህል ዘረጋ እንጂ እምነት የሚጣልበት አይደለም፡፡ አደጋ አለው ወገኖቼ! መንግሥት ቢኖረን ወገናችን እንደጨው ዘር በመላዋ ዓለም ይበተን ነበርን?

ሠ. ሥራ አለው ከሚባለው ዜጋ የማይናቅ ቁጥር ያለው ወገን ለሥራ ያለው ተነሳሽነትና የሙያ ፍቅር አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን የሚናገሩ አሉ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ለይስሙላና ለሰዓት ፊርማ ቢሮ ይገባሉ እንጂ አጥጋቢ ሥራ እንደማይሠሩ፣ የሥራ ፍቅርና ወኔ እንደሌላቸው፣ ሥራ ገበታቸው ላይ ተገኝተዋል እንዲባሉ ብቻ ግን እንዲሁ ወለም ዘለም እያሉ ውለው እንደሚሄዱ ከጥርጣሬ በላይ ገሃድ እየሆነ መምጣቱ ይወራል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥራን በአግባቡ ያለመሥራት ወይም ሊያሠራ የሚችል አካል መጥፋት ሀገሪቱን ባለቤት አልባ እንደሆነች ያስጠረጥራል፡፡ ብዙዎች እንደሚሉት በየመሥሪያ ቤቱ ከቅርጽ ባለፈ አጥጋቢ የሥራ ሂደት እንደማይከናወን ይታመናል፡፡ የደንበኞች አገልግሎት በሚሰጥባቸው ብዙ የመንግሥት መ/ቤቶች ደግሞ ባለጉዳዮች በደቂቃዎች ለሚያልቅ አነስተኛ ነገር ብዙ ሣምንታትንና ወራትን እንደሚጉላሉ የታወቀ ነው፡፡ በብዙ ቦታዎች በእጅ ተሂዶ ምንም ጉዳይ አይፈጸምም፤ በጅ ተሄዶም ቢሆን ‹የሉም፤ ስብሰባ ላይ ናቸው…› እየተባለ መመላለስ የተለመደ ነው፡፡ አደጋ አለው!

ረ. በየቦታው ትዳር እየፈረሰ፣ ልጆች ወደ ጎዳና እየተበተኑ፣ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አእሩግ ወደበረንዳና ወደደጀሰላሞች እያቀኑ በውጤቱም ማኅበራዊ ሕይወት ክፉኛ እየተናጋ ነው፡፡ ይህ ደግሞ  በአንዲት ሀገር ውስጥ የትልቅ ችግር መስፋፋትን ያመለክታል፡፡ ቤተሰብ የማኅበረሰብ መሠረት ነው፤ ብዙ ቤተሰብ በሞራልና በሃይማኖት እየዘቀጠ ሲመጣ በሂደት ችገሩ በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ጫና ያመጣና መሪዎቹም የዚሁ የሞራልና የሃይማኖት መላሸቅ ውጤቶች ሆነው አሁን እኛና ኢትዮጵያ እየተሰቃየንበት ያለው ነገር ፋሽን እንደሆነ ይቀራል፡፡ በዚህ ረገድም አደጋ አለብን፡፡ ዘር መተካት አቅቶናል፡፡ ከአሁኑ ዘመን ይልቅ የወደፊቱ በእጅጉ አሳሳቢ ነው፡፡ ሀገሪቱን ማን ይረከባት? በጎጠኝት ምች የተመታ ወያያዊ ከፋፋይ ትውልድ ወይንስ ሰፊ ራዕይ ያለው ሁሉንም በእኩልነት የሚመለከት የዘመናዊ አስተሳሰብ ባለቤት የሆነ ትውልድ? ሁለተኞቹና ‹ቆንጆዎቹ› የት አሉ? ተወልደዋል ወይንስ ገና ምጥ ላይ ነን?

ሰ. በኑሮው ጥመትና በኢኮኖሚው ድቀት ምክንያት ዜጎች አእምሯቸውን መቆጣጠር እየተሳናቸው በተለይ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የሚታየው የዕብዶችና የወፈፌዎች ብዛት ከግምት በላይ ሆኗል፡፡ ሆስፒታሎችና አውራ ጎዳናዎች የተጨናነቁት በየሴኮንዱ በሚወፍፉ ዜጎች ነው፤ ልብ ያለው ሰው የተገኘ ግን አይመስለኝም፡፡ በመሆኑም ዕብደትን የሚያባብስ እንጂ የሚቀንስ ነገር ሲከናወን አላይም፡፡ ሀገራዊ ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ ዘንድሮ ካበደው ይልቅ በመጪው ዓመት ለማበድ እየተሰናዳ ያለው በእጅጉ ይብሳል፡፡ በየመንገዱ ብቻውን እያወራ የሚሄደው ወገናችን ብዙ ነው በማለት ብቻ አንገልጸውም – ሱፉን ግጥም አድርጎ ለብሶ እጁን ከወዲያ ወዲህ እያወናጨፈና ብቻውን እያወራ አስፋልቱን ሲያቋርጥ ስታየው በዚያ ጎበዝ ኢትዮጵያዊ ዕድል አንጀትህ ይላወሳል – ነገ አንተም እንደሱ እንደማትሆን ደግሞ እርግጠኛ መሆን አትችልም – እስካሁን ካልሆንክ፡፡ አደጋ አለው!

ሸ. በሰውነት ውስጥ ነጭ የደም ሕዋስ ሲበዛ አንዳች በሽታ እንዳለ ይገመታል – በአንዲት ሀገር ውስጥ የወታደሮች ባልተለመደ ሁኔታ መርመስመስና መራወጥ አንዳች የፀጥታ ችግር መከሰቱን እንደሚጠቁም ሁሉ ማለት ነው፡፡ በተመሳሳይ መንገድ አንዲት ሀገር ውስጥ የጫት ቃሚዎች፣ የጠጪዎችና የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ ሄዶ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከደረሰ ያች ሀገር ወዮላት! እንደሚመስለኝ በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ውስጥ የተደሰተውም ይጠጣል – ያዘነውም ይጠጣል፡፡ የከፋውም ይቅማል – የተደሰተውም ይቅማል…  ‹የዘገነም አዘነ፣ ያልዘገነም አዘነ›፡፡ እርግጥ ነው – መጽሐፉ ‹ድሃ ጭንቀቱን ይረሳ ዘንድ የወይን ጠጅ ይጠጣ› ይላል፡፡ ከዚህ አንጻር የድሆች ተረከዛቸውን ወትፈው ያገኙትን መጠጣታቸው በተወሰነ መልኩ ይገባኛል – እኔም አለሁበትና፡፡ የሀብታሞች መጠንበዝ ግን ግራ ነው እሚያጋባኝ – የሚያስጨንቁንን ለመርሳት ይሆን? ዋናው ግን በአንዲት ሀገር የጠጭዎችና የጫት ቃሚዎች እንዲሁም የሀሺሽ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየገነነ ከመጣ በዚያች ሀገር አንዳች የተስፋ መቁረጥ መንፈስ እየተበራከተ ነውና አሁንም አደጋ አለው፡፡ እርግጥ ነው – አምባገነን ገዢዎች ይህንን መሰሉን ሕዝባዊ ተስፋ መቁረጥና አልባሌ ተግባር ውስጥ ገብቶ መደበቅ ይወዱታል – እንደወያኔ ዓይነቶቹ ስግብግቦች ሳይሆኑ እንደኮሚኒስት ራሽያ ዓይነቶቹ ይህንን የጥንበዛ ፕሮግራም በገንዘብ ይደጉማሉ፤ በተዛዋሪም ያረታታሉ – ሰው በሥካር ውስጥ ተዘፍቆ ፖለቲካቸውን እንዳያስብ፡፡ ‹ያውጡብሽ እምቢ፣ ያግቡብሽ እምቢ› ዓይነቱ ወያኔ ግን በገንዘብ ፍቅር በማበዱ ምክንያት ሁሉንም አክርሮ  ሰውን መደበቂያ እንኳ በማሳጣት በገላጣ ሥፍራ ላይ በየአቅጣጫው ሕዝበ አዳምን በጅራፍ እየሸነቆጠው ነው፡፡ ይሄ ቫት እሚሉት ነገር በሁሉም ዘርፍ ገብቶ የመጠጡም የምግቡም ዋጋ በመሰቀሉ አብዛኛው ሕዝብ ታዛቢ እንጂ ተሣታፊ ሊሆን አልቻለም፡፡

ቀ. በአንድ ሀገር ውስጥ ጧት ቤተ ክርስቲያን ወይም መስጂድ ያገኘኸው ሰው ማታ ጠንቋይ ቤት ካየኸው በዚያ ሀገር ውስጥ መስተካከል የሚገባው የተበላሸ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ ላይ እንደማይዋጣ ሁሉ ለሁለት ጌቶች ለመገዛት መሞከር ችግርን በራስ ላይ መጋበዝ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር በሀገራችን በስፋት ስለሚስተዋል የዕድገታችን ምልክት ሳይሆን የመንፈሳዊ ድቀታችን ዓይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ ታላላቅ የኪነ ጥበብ፣ የንግድ፣ የፖለቲካና የአትሌቲክስ ዘርፎችን በዋናነት ጨምሮ ብዙ ሰው በዚህ ብልሹ ሕይወት ውስጥ መመላለሱን መረዳት አይከብድም – በጥንቆላ ባገኘው ገንዘብ ቤተ ክርስቲያን የሠራ ሰው አውቃለሁ – አንድ ብቻም አይደለም – በዚህ መልክ ፈጣሪን ጡጦ እንዳልጣለ ሕጻን እየቆጠሩ ሊያታልሉት የሚሞክሩ እጅግ ብዙ ሰዎች አሉ ፤ ካህናትንና ቃለ እግዚአብሔርን ዐዋቂዎችን ጨምሮ – እሱው በምሕረቱ ያስባቸው፡፡ ‹የሐሙሱ ፈረስ› በጣም ከፍተኛ የሆነ አፍራሽ ሚና እየተጫወተብን አለ – አንድ ታምራት የሚሉት ዓይነት አራተኛ ክፍልን በቅጡ ያልጨረሰ የሚባል አጭበርባሪ ጠንቋይና አንዲት ‹ማርያም ነኝ› የምትል ማይም ሴት እንዲሁም  ባህታዊ ነኝ ባይ አፈ ቅቤ ‹ሊቀ ትጉሃን› በቀላሉ የሚያታልለን/ የሚያነሆልለንና ወደተፈለገው አዘቅት የሚያሰምጠን ሕዝብ ከሆንን ለአሁኑ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም ጭምር አደጋ አለው! በዬጉራንጉሩ እየሄድን ብናይ ብዙዎቻችን ከዕውቀት ማዕድ የመራቃችን ጣጣ ያመጣብን ጠንቅ ሥር ሰድዶ እግር ከወርች የጠፈነገን መሆናችነን እንገነዘባለን፡፡ እግዚአብሔር በቶሎ ካልደረሰልን በቁማችን ጠፍተናል ወገኖቼ፡፡

ተ. በአንዲት ሀገር ውስጥ ጉቦ ወይም ሙስና እግር አውጥቶ የሚሄድ ከሆነ ወዮ ለዚያች ሀገር ሕዝብ! ሕግም ሥርዓትም ፍትህም… በግለሰቦች ፈቃድ የሚወሰኑ እንጂ አድልኦ የሌለበት ሕግን መሠረት አድርገው በአስተዋይነትና በጥበብ የሚከናወኑ አይሆኑም፡፡ በአንዲት ሀገር ውስጥ ወሳኙ የበላይ አለቃ ገንዘብ ከሆነ የሕዝቡና የመንግሥቱ ግንኙነት ልክ እንደተራ የአከራይ ተከራይ ግንኙነት ነው ማለት ነው፡፡ አንድ አከራይ ያከራየውን ሰው ሲፈልግ ‹ምነው ወንድም – ቀስ ብለህ አስነጠስ እንጂ! ለጣራና ኮርኒሱም አስብለት› ወይም ‹የኔ እህት በቀን አንድ ባልዲ ተዋዋልን እንጂ በጆግ ማን ጨምሪ አለሽ?› እንደሚባሉ ሁሉ መንግሥትና ግለሰብ ከተቀላቀሉ ልክ በመለስና በመንግሥቱ ኃ/ ማርያም እንዳየነው የሚሊዮኖች ዕጣ ፋንታ በአንድ ጫታም ወይም በአንድ ሠካራም ወይም በአንድ ሀበሾኣምና ሀሺሻም እየተወሰነ ሕዝብ ዐይኑ እያየ እንጦርጦስ ይወርዳል ማለት ነው፡፡ የ80 እና 90 ሚሊዮን ሕዝብ የመኖርና ያለመኖር ዕጣ በአንድ ግለሰብ ወይም እልፍ ሲልም በአንድ የወሮበሎች ጭፍራ የሚወሰን ከሆነ ወዮ ለዚያ ሀገር ሕዝብ! ከዚህ አንጻር በሀገራችን ትልቅ አደጋ አለ፡፡ ይህ አደጋ በቅርብ ካልተገፈፈ የኛንስ ተውት ከሞላ ጎደል ጨርሰነዋል – ተተኪ ግን አይኖረንም፡፡

ቸ. በአንድ ሀገር ውስጥ የኢምግሬሽን ቢሮ በጣም ሥራ የሚበዛበት ከሆነና የተሰዳጁ ሕዝብ ቁጥር ከበዛ በዚያ ሀገር ውስጥ ከፍተኛ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ የኛን ሀገር ሁኔታ ከዚህ ነጥብ አኳያ ብመለከተው ልዩ ታሪክ እንታዘባለን፡፡ ጥቁር አንበሣ አካባቢ የሚገኘውን የኢሚግሬሽን ቢሮ ተመልከቱ፤ እንደዝናር ጥይት በዕጥፍ ድርብ ዙሪያውን እየተጠማዘዘ የሚሰለፈው ሕዝብ ለሽርሸር ወይም ለቱሪስትነት ሳይሆን በምትቀና ሚስት ከፎቅ ለመወርወር ወድዳና ፈቅዳ የተዘጋጀች ወጣት ሴትና በዘበኝነትም ይሁን በአትክልተኝነት ሠርቼ ትንሽ ፍራንክ ልቋጥርና ቤተሰቤን ልደግፍ ብሎ የቆረጠ ጉብል  ናቸው፡፡ ዜጎች አለኝታ ሲያጡ የሚሰማቸው መሪር ስሜት ለእንደዚህ ያለ የባርነት ሕይወት ዐይናቸውን እንዳያሹ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህ ሂደት ሀገሬ ብሎ ለባንዴራው የሚዋደቅ ወጣት አይኖርም – ለጊዜው ሀገርም ሁላችንን የሚያስማማ ባንዴራም ባይኖረንም፡፡ በዚያ መንገድ ሳልፍ በእጅጉ አፍራለሁ – የኢቲቪ የሀገር ዕድገት ዲስኩር ትዝ እያለኝም በውስጤ ፈገግ ማለቴ አይቀርም፡፡ ከዋሹ አይቀር ታዲያ እንዲህ ነው፡፡ መላው ዜጋ ከሀገር ለመውጣት ሌት ከቀን ተሰልፎ በሚታይበት ሁኔታ ሀገር አድጋለች እያሉ ማንቋረሩ ማንን ለማታለል እንደሆነ ፈጽሞ አይገባኝም፡፡ የሚያደርጉትን አያውቁምና ፈጣሪ ይቅር ይበላቸው፡፡

ኀ. ከፍ ሲል በጨረፍታ ለመግለፅ እንደተሞከረው የሴተኛ አዳሪነት አለቅጥ መስፋፋት፣ የዘመድ አሠራር(ሥራ ለመቀጠር፣ ለዕድገትና ለሹመት…)፣ የሀገሪቱ ዋና ዋና የሥልጣንና የጥቅም ቦታዎች በአንድ ብሔር ሥር ተጠቃሎ መግባትና ሌሎችን ባይተዋር ማድረግ፣ ኢትዮጵያዊነት የአባት ገዳይ ይመስል ጥምድ አድርጎ መያዝና ለዚህች ታሪካዊት ሀገር ትንሣኤ የሚተጉ ዜጎችን በገቡበት እየገቡ  ማሳደድ… የዕድገት ምልክቶች ሳይሆኑ የክስረት መገለጫዎች ናቸውና በእንፉቅቅ እየመጣ ያለው የዕልቂት ዘመን ድንገት ሳይደርስብን – በተለዋጭ ቃላት ልድገመው – ቢዘገይም እንኳን መምጣቱ በጭራሽ የማይቀረው የመቅሰፍት ዘመን ሳይመጣብን እገሌ ከእገሌ ሳንል ሁላችን ወደየኅሊናችን እንመለስና እያንዣበበብን ያለውን ከፍተኛ አደጋ እንግፈፍ፤ ኋላ ጊዜ ላይኖረን ይችላልና፡፡

ነ. ከዚህ በላይ በድርበቡ የተጠቀሱ ነገሮች በሙሉ ኢትዮጵያና ልጆቿ በቋንቋ ሊገለጽ የማይችል የችግር አረንቋ ውስጥ እንደገቡ የሚያመለክቱ ናቸው፤ ስለሆነም መፍትሔ ያሻቸዋል፡፡ መፍትሔው ደግሞ አንድም ከሰው አንድም ከእግዜር ነው፡፡ የሰው እስካሁን አልተሳካም – በተለያዩ ሰውኛ ምክንያች የተነሣ፡፡ የእግዜሩ ግን ቀደም ሲል ጀምሯል – አሁንም ሳይቋረጥ በራሱ ጊዜና በራሱ ፍጥነት ቀጥሏል፤ ማንም ደግሞ አያደናቅፈውም፡፡ ለመነሻነት እነኚህን ሂደቶች ልብ በሉ፡፡ ከዚያም ቀጥሎ ምን ይሆን ይሆን? ብላችሁ ስለወደፊቱ አስቡ፡፡

ኘ. በ83ዓ.ም ሕወሓት ኢትዮጵያን የማጥፋት ትልሙን በአሜሪካን በጎ ፈቃድና ቡራኬ በሄርማን ኮኸን የፖለቲካዊ ፕትርክና ቡራኬ መንግሥት ሆኖ በይፋ ጀመረ፡፡ ከትክክለኛው የጊዜ አቆጣጠር አንጻር ከአራት ዓመታት ገደማ በኋላ በ88 ትልቅ የመሰነጣጠቅ ጥፊ ደረሰበት – የጊዜው ጠ/ሚኒስትር ታምራት ላይኔ በ”ስኳር ቅሌት” ወህኒ ወረደ፡፡ አንድ በሉ፡፡ ሦስት ዓመታትን ቆይቶ በ90ዓ.ም ያልታሰበ ዱብ ዕዳ ወርዶ ከፍተኛ ዕልቂት ያስከተለ የሻዕቢያና ወያኔ የማይጠገን ስብራት ደረሰ፡፡ ሁለት በሉ፡፡ ፈጣሪ ሌሎች ሦስት ዓመታትን ታግሦ ወያኔ ራሱ በውስጥ ደዌ እንዲመታ አደረገና የሕወሓት መንደር ምንቅርቅሩ ወጣ – በሻዕቢያም በኩል እንደዚሁ፡፡ ሦስት በሉ፡፡ አራት ዓመታትን ቆይቶ በ97ዓ.ም ወያኔን እርቃኑን ያወጣ ሀገራዊ ክስተት ተፈጠረ፡፡ አራት በሉ፡፡ ሌሎች አራት ዓመታትን ቆይቶ በ2001 እና ከዚያም በኋላ እሳቱ እማይጠፋ ትሉ እማያንቀላፋ የኑሮ ውድነት ባልታወቀ ኃይል ታወጀና በየቀኑ ሽቅብ በሚወረወር የዋጋ ንረት ሕዝብ ማልቀስና ዕንባውን ወደላይ ወደአርያም መፈንጠቅ ተያያዘ፡፡ ይህም ብሶት ከተጨማሪ ወያኔዊ የዕብሪትና የትምክህት ሥራዎች ጋር ተባብሮና ተደማምሮ ሌሎች የወያኔን ሥርዓት ማብቂያ አመላካች ምልክቶችን በግልጽም በሥውርም ያሳይ ያዘ፡፡ አምስት በሉ፡፡ ከሦስት ዓመታት በኋላ በ2004 መገባደጃ ላይ በዋልድባ ገዳምና በሕዝብ ዕንባ መዘዝ ታላላቁ የብኤል ዘቡል ወኪሎች አቶ መለስ ዜናዊና ሃይማኖትን በዓሣማ ጋጣ ላይ አጋድመው የረመረሙት “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ” ጳውሎስ የአጋንንት መንጋቸውን ደጅ ላይ ለብርድና ለንፋስ እንዳጋለጡ በፈጣሪ ልዩ ‹ሰርጂካል ኦፐሬሽን› ተመትተው እስወዲያኛው አሸለቡ – ሰማይ ምድርን ‹ዕፁብ ድንቅ› ያሰኘ ሰማያዊ በረከት፡፡ ስድስት በሉ፡፡ ፈጣሪ እንደዱሮው ሦስትና አራት ዓመታትን መጠበቅ ሳያስፈልገው በዓመቱና አሁን ደግሞ ምን እየሠራ እንደሆነ በዐይናችን በብረቱ እያየን ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን እኛ ሀገር ቤት ያለነው ምሥኪን ዜጎችም ሆንን የተቃውሞው ጎራ በየአምበሉና በየጎራው እየተቧደነ የነገር ጦር ከመስበቅ፣  በደብዳቤና በድርጅታዊ መግለጫ ‹የጦፈ ጦርነት› ከማካሄድ በዘለለ አንዳች አስተዋፅዖ አድርገን ከሆነ ገና ወደፊት የሚጣራ ይሆናል፤ የታሪክ አጣሪ ኮሚሽን  ብዙ ሥራ ሊሠራ ከፊት ለፊታችን ቆሞኣለ፡፡

አ.. የተኛም ይተኛ፤ ያንቀላፋም ያንቀላፋ፤ የደከመም ይድከም፤ የተሸነፈም ይሸነፍ፤ አብሮና ተባብሮ የሚዘርፍና የሚያዘርፍ – የሚገድልና የሚያስገድልም – ይዝረፍም ይግደልም፡፡ እኛ ደግሞ እንጮሃለን፤ የሚያነብብ ያንብ፤ የሚሰማ ይስማ፤ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ እንደጨለመ አይቀርም፤ ያኔ የጨለማው ውስጥ ብካያችን በገሃድ ይገለጥና በምን ዓይነት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ምን ዓይነት የመከራ ሕይወት እያሳለፍን እንደነበር ቀጣዩ ትውልዳችን ይማራል፤ እንዲሆን የታዘዘን ከመሆን የሚያሰናክል የለም፤ ሁሉም በጊዜው ይሆናል፡፡ ጠቢቡ ቀድሞ ተናግሮታል – ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም፡፡ የብርሃንና የጨለማ መፈራረቅም የነበረ እንጂ ዛሬ የተጀመረ አይደለም፡፡ አገኘሁ ብለህ አትኩራ፤ አጣሁ ብለህም ከመጠን ባለፈ አትፍራ፡፡ ይልቁንስ ሰው ለመሆን ጣር – ሰው ሆኖ መገኘት ትልቅ የወቅቱ ፈተና ነውና፤… ከገዳይ ይልቅ ሟች የበለጠ የፅድቅ ቦታ አለው፤ ጊዜው ቀርቧል፡፡ ለዚያ ጊዜ ወዮ እንበል!!

 

ከ. እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አብዝቶ ይባርክ፤ ለሦርያና ለኢራቅ ከተመዘዘ ሠይፍና ጦርም ይሠውረን፡፡ የጥጋበኞችን ጥጋብ ወደስክነት፣ የትዕቢተኞችን ዕብሪት ወደብስለት፣ የጠይዎችን ጥላቻ ወደፍቅር፣ የሆዳሞችን ስግብግብነት ወደእርካታ ለውጦ ያለብዙ ወጪ በሚገነባ አዲስ ስብዕና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ባለቤቶች ያድርገን – ይቻለዋልና፡፡ (የፊደል ተራ ቅደም ተከተሉን ልክ እሆን ብላችሁ ነው?)

 

ኸ. በቀናነት ለሚያስተምረኝና ጉድለቴን ለሚሞላልኝ ብቻ አድራሻየ ከምሥጋና ጋር ይሄውና፡-             ma74085@gmail.com

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>