ወንድሙ መኰንን፣ ብሪታኒያ
የዛሬ 30 ዓመት ገደማ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሒሣብ መዝገበ አያያዝ ትምሐርት አስተምር ነበር። ዛሬም በሱው ነው እንጀራዬን በስደት ዓለም ከስቃይ ጋር እንደወጥ እያጣቀስኩ የምበላው። ታዲያ ያኔ፣ የመምሕራን ካፌቴሪያ ለምሳ በየጠረጴዛው ዙሪያ በቡድን በቡድን እየተሰበሰብን አንዳንድ ክፍል ውስጥ ያጋጠሙን ገጠመኞች እያነሳን እንስቅ ነበር። አንድ ዕውቅ የኢኮኖሚክስ መምሕር ነበሩ። እግዚአብሔር ይመስገንና፣ ዛሬም በሕይወት አሉ። ስማቸውን ግን አልጠቅስም። ታዲያ አንድ ቀን ከጎናችን ካለው ጠረጴዛ ላይ ሁነው ምሳ እየበሉ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በዕለቱ ያጋጠማቸውን አስቂኝ ክስተት ሲገልጹ፣ ጆሮዬን ጣል አድርጌ እንደዋዛ እሰማቸው ነበር። ነገሩ እንዲህ ነው። አንዳንድ ጠጠር ያሉ የኢኮኖሚክስ ጽንሰ-ሀሳቦችን አንስተው ሲያስተምሩ፣ አንድ ወጣት ተማሪ ነገሩ ከብዶት ነው መሰል፣ ሳያስበው እንቅልፍ ይዞት ለሽ ይላል። ያንን ያዩት ዕውቁ የኢኮኖሚክስ ባለሙያ፣ ድምጻቸውን በድንገት በጣም ክፍ በማድረግ፣ ጮክ ብለው ማስተማር ይጀምራሉ። እንቅልፉን ይለጥጥ የነበረው ተማሪ በርግጎ ተነስቶ ይቆማል። መምሕር ትኵር ብለው አይተውት፤ “ይቅርታ! ቀሰቀስኩኽ እንዴ? ምን ላድርግ ብለኽ ነው። እንጀራ ነው የሚያስጮኸኝ።” አልኩት ብለው ሲናገሩ ጠረጴዛቸው ዙሪያ የተኮለኮሉት በሳቅ አውካኩ። እኔ ባልስቅም፣ ነገሩን ልብ ብዪ ከጎናቸው ከነበረው ጠረጴዛ እሰማቸው ስለነበር እስካሁን አስታውሰዋለሁ። ታዲያ፣ ዛሬ ይኸንን ምን አስታወሰህ ትሉኝ ይሆናል። አምባሳደር “ብርሀኑ” ከበደ፣ ለሪፖርተር ጋዜጣ የሰጡትን ቃለ-ምልልስ አንድ ወንድሜ ከአገር ቤት አካባቢ አንብቦት እኔም እንዳነበው ስለጋበዘኝ፣ አንብቤ ስጨርስ፣ “ምስኪን! እንጀራ ሁኖባቸው ነው የሚጮኹት” ብዬ እርፍ።
አምባሳደር “ብርሀኑ” ከበደን፣ ባልተረዱት ነገር ገብተው፣ አሳዳሪ ጌቶቻቸውን ለማስደስት አንዴ ጀርመን ሬዲዮ ድረስ ደውለው፣ ሌላ ጊዜ፣ ቪኦኤ የአማርኛ ዝግጅት ድረስ ደውለው፣ የሆነውን አልሆነም እያሉ ሲቀሉ ሰምቼአቸው፣ የወንድምነቴን ያክል፣ “ይኸ ነገር አይስማማዎትም። ባይሆን፣ ለመዋሸት – ለመዋሸት፣ ወያኔ ከትግራይ ያስመጣልዎትን ታኮዎች ይጠቁሙና፣ እነሱ ይዋሽልዎት። እርስዎ ምን በወጣዎት” ብዬ መከሬአቸው ነበር። በኔ ሞት፣ ያኔ የጻፍኩትን ምክር ከላይ ያለውን ማጣቀሻ፣ ወይም የግርጌ ማስታወሻው ጠቁመው፣ ወንድማዊ ምክሬን አንብቡልኝ። እንደማይከፉ ቃል እገባልዎታለሁ። ታዲያ ወያኔ ካልሆኑ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ በዛሬ ጊዜ አሁን ማን እንዲህ ያለ ገንቢ ምክር ይለግሳል? ያአውም ለባላንጣችን ታማኝ አገልጋይ አሽከር! ያንን ምክሬን ሰምተው፣ ለብዙ ጊዜ ዝም በማለታቸው ከእንዲህ ዓይነት ቅሌት እራሳቸውን ቆጥበው ሥራቸውን ብቻ በመሥራት ላይ ነበሩ ብዬ አምኜ ነበር። ምን ያደርጋል! “ድመት መንኵሳ፣ ዓይጧን አትረሳ” ነው የሚባለው? ጠፍቶኝ እንዳይመስላችሁ! አውቄ አጣምሜው ነው።
አምባሳደር ብርሀኑ፣ ከደርግ ዘመን ጀምረው ቀጣሪዎቻቸውን በማስደስት በሥራ የታወቁ ናቸው። የቤልጀየሙ ሥራቸው እንዳለ ሁኖ፣ ለንደን ከመጡ በኋላ፣ ለወያኔ የሠሩትን ውለታ፣ በአውሮፓ ያሉት የወያኔ ጉዳይ አስፈጻሚዎች የሠሩት በሙሉ ተሰብስቦ ቢደመር የለንደኑን አያክልም። ስለዚህ እራሳቸው እንዲህ እያሉ ስለራሳቸው ይመሰክራሉ።
“ለዓለም ገበያ ለሽያጭ የቀረበውን ቦንድ በተመለከተ በውጭ የተሸጠ በጣም ጠቃሚ እንኳን ባይባል፣ የአውሮፓ አጠቃላይ ተደምሮ የዚህ የእንግሊዝ ይበልጣል፡፡ ወደ 1.4 ሚሊዮን ዶላር ቦንድ ሸጠናል፡፡” (ሪፖርተር ታኅሳስ ፩ ቀን ፳፻፯)
ጎበዝ ደላላ! አሻሻጭ! የጠባ የጠነባውን የወያኔ የዘር ፖሊቲካ፣ በአፍዝ አደንግዝ ኪስ ማውለቅ ፕሮፓጋንዳ ሕዝቡን አታሎ ገንዘ መሞሸልቅ፣ መሸጡን ደኅና አድርገው ተክነውበታል። ኧረ እኛም ምስክር ነን። በዚሁ በሪፖርተር ቃለ ምልልስ፣ የእንግሊዝን መንግሥት በማግባባቱ ሥራና የፈጸሙትን ጀብዱ እንዲህ ሲሉ ያስረዳሉ።
ትልቁ ነገር ግን በኢትዮጵያ ኢንቨስት የሚያደርጉ ኢንቨስተሮች ትልልቆች ናቸው፡፡ ለአብነት ለመጥቀስ ዲያጆ የሚባለው በኢትዮጵያ ውስጥ በ225 ሚሊዮን ዶላር ሜታ ቢራ ፋብሪካን ገዝቷል፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ 100 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት አድርጓል፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ 325 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት አለው ማለት ነው፡፡ ዩኒሊቨር የሚባለው ትልቁ የመልቲላተራል ኩባንያ በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመርያ የኢንቨስትመንት ኦፕሬሽን እየጀመረ ነው ያለው፡፡ ሦስተኛ ፒተርድ የሚባለው የቆዳ ውጤቶች አምራቾች ድርጅት ለሰባ ዓመታት ጥሬ ቆዳ ይገዛ የነበረው በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ሦስት ፋብሪካዎች ሠርቶ ከ1,500 እስከ 2,000 ሠራተኞች ቀጥሮ እያሠራ ይገኛል፡፡ ይኼም የታወቀ ብራንድ ስለሆነ የቆዳ ውጤቶቹ ብሪቲሽ ኤርዌይስ የሚጠቀምበት ትልልቅ ሱቆች ውስጥ እየገባ ነው፡፡ ሌላ በማዕድን ፍለጋ ስንሄድ ታሎ በነደጅ ፍለጋ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ካምፓኒ ነው፡፡
አሁንም ይሄ የሚያሳየው ሰውዬው በተሰለፉበት ሥራ ውጤታማ መሆናቸውን ነው። ነገር ማበላሸት የሚጀምሩት፣ ጋዜጠኛው ወደማይሸጠው የወያኔ ፖሊቲካ ሲመራቸው ነው። እኔ እሳቸውን ብሆን፣ “እዚህ ጋ ወራጅ አለ” እል ነበር።
ሪፖርተር፡ “ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ መንግሥት በቁጥጥር ሥር የዋሉት የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸውን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ በተመለከተ የእንግሊዝ መንግሥት ስሜት ምንድን ነው? ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን (በግላቸው) ለኢትዮጵያ መንግሥት የመማፀኛ ደብዳቤ መጻፋቸው ይነገራል፡” ለሚለው ጥያቄው መልስ ሲሰጡ፣ “ጉዳዩ ይህን ያህል ትልቅ ጫና የለውም፡፡ ነገር ግን ግለሰቡ የእንግሊዝ ዜጋ እንደመሆኑ መጠን በእንግሊዝ መንግሥት የሆኑ ዕርምጃዎች መወሰድ አለባቸው የሚሉ አሉ፡፡ ሰውየው ለምን ታሰረ የሚል አይደለም፡፡ በሕግ ይዳኝ የሚል ነገር ነው፡፡” ሲሉ አቃለው ተናግረዋል። አንዳርጋቸውንም ሲከሱ፣ ያላንዳች ሀፍረት እንዲህ ብለዋል።
ይኼ ሰውዬ የሽብር ተግባር ላይ ገብቷል፡፡ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከሚፈልጉ ኃይሎች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ይሠራ ነበር፡፡ ሦስተኛ ራሱም ይህንን አምኗል፡፡ ብዙ ጊዜ እጅ ከፍንጅ የተያዙና የታሰሩ ሰዎች እሱ እንደሚያሠለጥናቸውና የቡድኑ መሪ እንደሆነ፣ ከኤርትራ መንግሥት ጋር አብሮ እንደሚሠራ በግልጽ ያስቀመጠው ነገር አለ፡፡ እሱ እንደተያዘ ግንቦት ሰባት የሚባለው ድርጅት ራሱ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጦርነት ነው ያወጀው፡፡
አዪዪዪ! “አይ አለማወቅሽ፣ አገርሽ መራቁ አለ ሰውዬው!” ለመሆኑ፣ የወያኔው ወኪል፣ አሳዳሪ ጌታቸው ወያኔ ትላንትና ከሻዕቢያ ጋር አብሮ ኢትዮጵያን ሲያደማ እንደነበሩ ያውቁት ኑሯል? እንዴታ! በድንብ ነው እንጂ! የኤርትራን “ናጽነት” ዕውን ለማድረግ የስንት ኢትዮጵያዊን ደም አብረው እንዳአፈሰሱ ዘንግተውታል ማለት አይቻልም። የደርግ ዲፕሎማት በነበሩበት ጊዜ የወያኔና የሻዕቢያን አደገኛ አካሄድ የሀገር ክህደት መሆን ሲያብራሩ አልነብሩምን? ለመሆኑ ዛሬዎቹ ወያኔ ባለሥልጣናት እና ሞት የገላገለን የኢትዮጵያ ጠቅልላይ ሥቃይ አልነበሩም፣ “የተገነጠለችውን የኢትዮጵያን ጠቅላይ ግዛት እንዳገር ዕወቁልን” ብለው በአፍሪካ አንድነትና በተባበሩት መንግሥታት ኮሪዶሮች ኮሮጆ ተሸክመው ሲሯሯጡ የነበሩት? እሱ ነው ድርጊት ነው በታሪክ ዓይን የአወጣ የአገር ክህደት! በዚህ ወራዳ ድርጊታቸው የዓለም መንግሥታትን አስደምመው አልነበረም። ለመሆኑ ኢትዮጵያን ያለወደብ ያስቀራት ከሀዲ መንጋ፣ አንዳርጋቸው ነው ወይስ የወያኔ ዘረኛ ወራሪ? አምባሳደሩ፣ ምን አለ ቁስል ያለበትን ቦታ እየመረጡ ባይነካኩ? ሻዕቢያን በተመለከተ፣ ወያኔ የሞራል ብቃት የለውም ማንንም ለመወንጀል። ነገሩ፣ “የትላንትናውን የወንጀል ባልደረባዬን አትቀሙኝ” ወይንም “ባሌን አትቀሚኝ” ዓይነት ቂመኝነት ነው። ትላንት ከሻዕቢያ ጋር “በአንድ አልጋ ካልተኛን፣ በአንድ ጉድጓድ ካ…” ብለው እነፕሮፌሰር አሥራትን የመሰሉትን ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች ያስገደሉ ገንጣይ አስገንጣይ አገር ሻጮች፣ ዛሬ ደርሰው ከኤርትራ ጋር የተጎዳኘን ሁሉ “ዓይንህን ላፈር” ማለት ሌብነት እንጂ ምን ሊባል ነው? አምባሳደር እዚያ አካባቢ ወያኔን የረከሰ ፖሊቲካ ለመሸጥ ባይሞክሩ ጥሩ ነበር። ለምን ቢሉኝ፣ ሰውየው “እናቴን ያገባ ሁሉ አባቴ ነው” እንዳለው ነገም ዴሞክራሲያዊ የሆነ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ በግድም ሆነ በውድ ቢቋቋም፣ በተማሩት ሙያና በአካበቱት ልምድ ገዢዎቹን ሳይሆን ኢትዮጵያን ሊያገለግሉ ይቻላሉና፣ እንዳናምርርብዎት፣ የብዙዎቻችንን ቆሽት ከሚያድብን ንግግር ራቅ ቢሉ ነገም የመሥራት ዕድል ይኖርዎት ነበር።
ሰውዬው ከዚያም አልፎ ተርፎ፣ እነ አመንስቲ ኢንተርናሽናል፣ እነ ሕይማን ራይትስ ዎትች አልቀሩአቸውም። እንዲህም እስከማለት በቅተዋል።
“ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ድርጅቶች አሉ፡፡ እነ ሂውማን ራይትስ ዎች እና እነ አምኒስቲ ኢንተርናሽናል አሉ፡፡ እነሱ በመንግሥት ላይ የሚቀሰቅሱት ውንጀላ ይቀጥላል፡፡ ውንጀላቸው መሠረት የለውም፡፡ ዲሞክራሲ በአንድ ሌሊት የምትፈጥረው አይደለም፡፡ የእንግሊዝ ወይም የኖርዌይ ዓይነት ካልሆነ ብለህ ዲሞክራሲ አይደለም ብለህ ልትፈርጅ አትችልም፡፡”
“አወቅኩሽ ናቅኩሽ” አለ አሉ ሰውዬው። እነዚህ ግዙፍ ድርጅቶች በዓለም ዙሪያ በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነታቸውና ተአማኒነታቸው እንደ ሐውልት የተተከሉ ናቸው። እነዚህን የትም አይደርሱም፣ አሉታዊ ተጽዕኖም አያደርሱም ማለት ጅልነት ነው። እነዚህ ድርጆቶች እኮ ናቸው ደርግ በጥይት ሐሩር ሲያራውጣቸው በዓለም ጥብቅና ቁመውላቸው ሲሟገቱላቸው የነበሩት። ያኔ ሲሰደዱ፣ ወዳጆቻቸው ነበሩ። ዛሬ እነሱ አሳዳጆች ሲሆኑ፣ ከጠላት ቆጠሩአቸው? ዓለም ተለዋዋጭ ናት። እንኳን እነዚህ በ17 መርፌ የተጠቀመ ቡቲቶ ለብሰው ልሥልጣን የበቁ ወንበዴዎችና፣ የሮም መንግሥትም ወድቋል። የማይበገር የሚመሰለው የሶብየት ሕብረትም መንግሥት ፈራርሷል። አሳዳጆቹ በተራቸው እንደሚሰደዱ ጥርጥር የለንም። የጊዜ ጉዳይ ነው። ያቺ ቀን እንደገና ብቅ ስትል፣ ዓይናቸውን በጨው አጥበው፣ “ጥብቅና ቁሙልን” ሊሉ ነው እነዚህ ዓይን አውጣዎች። የአሜሪካና የእንግሊዝ መንግሥታት ወያኔ የጸረ-ሽብር ዘመቻ የቃል ኪዳን አጋራቸው ስለሆነች እነዚህን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ጩኸት ቦታ እንደማይሰጡአቸው ተናግረዋል። እንግሊዝን በተመለከተም እንዲህ ብለዋል።
“የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የመጣ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ውስጥ አንደኛ ደረጃ ይዛ ትገኛለች፡፡ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግንኙነቱ ዘርፈ ብዙ እየሆነ ነው የመጣው፡፡ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ዕርዳታ እንግሊዞች ‹‹Value for Money›› [ገንዘብን ለታሰበለት ዓላማ ማዋል] በሚል መርህ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰጠው ዕርዳታ ለትክክለኛ ዓላማው እየዋለ መሆኑንና የሕዝብን ሕይወት በመለወጥ ተግባራዊ እየሆነ መሆኑን በደንብ አስቀምጠዋል፡፡ እንደ ምሳሌም ይጠቅሱታል፡፡”
ይኸ እንግዲህ፣ “እኛ አሽከራቸው እስከሆን ድረስ ንዋዩን ያለምንም ጥያቄ ያፈሱልናል” የሚል የሚመስል ድምዳሜ ነው። ግን አምባሳደሩም ሆነ የሪፖርተር ዘጋቢ አንድ ነገር ረስተዋል። በየዓመቱ የሚወጣው የዩኤስ ስቴት ደፓርትመንት የሰብዓዊ መብት ረገጣ በኢትዮጵያ ዘገባ፣ አለማንሳታቸው አይግርምም? ዘንድሮም ተመሳሳይ ዘገባ በዪኬ መንግሥት ወጥቱአል። የአውሮፓ ሰብዓዊ መብት ኮሚሺን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሰፕቴምበር 24 ቀን 2014 የተወያየበት የወያኔ አፈና፣ የአንዳርጋቸው ጠለፋ፣ የጋዜጠኞች መታፈን፣ “የጸር-ሽብርተኝነት ሕግ”፣ የጋዜጠኝነት ሕግ፣ የመያድ ሕግን በተመለከተ፣ ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት ሳይሆን ጋጠ-ወጥ የሆነ ማፊያ ቡድን ኢትዮጵያን የሚያስተዳድር እስኪመስል ተወያይቶባታል። “እኔ አላይም” ለማለት ካልሆነ፣ እንደሰጎን አንገትን አሸዋ ውስጥ ቀርቅሮ፣ አደጋ ሲመጣ መሸሸግ መላ ሰውነትን ከሞት አያድንም። አምባሳደር “ብርሀኑ” ከበደ፣ ጸሐይ የሞቀውን፣ ዓለም ያወቀን የሰብዓዊ መብት ረገጣ በኢትዮጵያ “የለም” ብሎ ድርቅ ብሎ መሸፋፈን አይቻልምና፣ ያንን ለመከላከል መሞከር ትዝብት ላይ ይጥላል። አምባሳደር! 23 ዓመት እኮ አንድ ሌሊት አይደለም። ደግሞ ዴሞክራሲ በአንድ ሌሊት አይሠራም እያሉ የዘባነኑብናል። የሰው ልጅ መብት ረገጣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከደርግ ዘመን በላይ አሁን ብሶበታል!
ሌላው በጣም የገረመኝ አንድ ነገር፣ ሳይጠየቁ የዘበዘቡት፣ የኛ ዲያስፖራ የተባልን፣ “የጥቂቶቹ” ወያኔ ቁጥጥር ሥር አንውልም ብሎ አሻፈረኝነት ጉዳይ ነው። አምባሳደር ሆዬ “አገር ቤት የሚካሄዱትን አዎንታዊ ለውጦችን፣ ልማቶችን ማየት አለባቸው” ካሉ በኋላ እንዲህ ነበር ያሉት።
ልንታሰር ይሆናል የሚል ፍርኃት ያላቸው አሉ፡፡ ኢሕአዴግ 90 ሚሊዮን ሕዝብ የሚመራ ድርጅት ነው፡፡ እገሌ ወጣ እገሌ ገባ ብሎ ለመቆጣጠር ጊዜም የለውም፡፡ አንድም የተሳሳተ አመለካከት ነው አልያም ለራስ የሚሰጡት ግምት ነው፡፡ ሰው ከገደሉ ወይም ሌላ ወንጀል ከፈጸሙ ኢሕአዴግም ማንም አያድናቸውም፡፡ ሕግ ነው የሚመለከታቸው፡፡ ኤርፖርት ላይ እንደሚታነቁ የሚያምኑ ሰዎች አሉ፡፡ ኢሕአዴግ ግን ስለመኖራቸውም አያውቅም፡፡
ወቸ ጉድ! ከተናግሮ አናጋሪ ይሠውራችኹ! ሪፖርተር ይኽቺን ‹‹ኤርፖርት ላይ እንደሚታነቁ የሚያምኑ ሰዎች ቢኖሩም ኢሕአዴግ ግን ስለመኖራቸውም አያውቅም›› የምትለዋን ሐረግ መዝዞ ነው እንደ አርዕስት የተጠቀመባት። አይ አምባሳደር! እሶም እንደ አሳዳሪ ጌቶችዎ እንደ ጅል ይቆጥሩን ገቡ እንዴ? እኛ እኮ ከዚያ በላይ ነቄ ነን! ለመሆኑ ወያኔ ሚሊዮን ዶላር አፍስሶ፣ እንደሌባ ሸምቆ፣ ኢትዮጵያ ኤርፖርት ሳይሆን፣ ሰናዓ ኤርፖርት ድረስ መሽጎ፣ ወንድማችንን አንዳርጋቸው ጽጌን የጠለፈው አለመኖሩን ባለማወቁ ኑሯል? ጃታኔ አሊን ኬኒያ ድረስ ቅጥር ነፍሰ ገዳይ ልኮ ሲያስረሽን፣ ውጪ የምንኖረው፣ ተቃዋሚ ዲያስፖራ መዘንጋቱ ነበር። የኢትዮጵያን ኤርፖርት ተውት፣ ከኬኒያ ስንቶቹ ስደተኞች ናቸው እየተፈኑ የተወሰዱት? አቶ ሱሉብ አህመድና አቶ ዓሊ ሁሴን እኮ ከኬኒያ የተጠልፉት በዚህ ዓመት ጃኑዋሪ 26 ቀን መሆኑን ዘንግተውት ይሆን? ለመሆኑ፣ US$23,000,000 ከፍለው የበፊቱን የጋምቤላ አስተዳዳሪ የነበሩትን ኦኬሎ አክዩዪን ከጁባ የጠለፉት አፋኞች፣ ማንንስ ይምራሉ! ክቡር አምባሳደር! ለመሆኑ ስንት የደኅንነት አባል ነው፣ የራስዎ ለንደን የሚገኘው ቢሮዎ የሚያሰማራብን? እነዚህ ጆሮ ጠቢዎች፣ ምን ለመሥራት ይሆን የዘመቱብን? እንዲያው እራስዎ ጅል ሁነው አያጃጅሉን ጃል!
አንድ መርዶ ለአምባሳደር ብርሀኑ ከበደ ልንገራቸው። አንዳርጋቸው ጽጌን መጥለፋችሁ ትልቅ ስሕተት ነው። እስክንድር ነጋን፣ ርዕዮት ዓለሙን፣ አንዱዓለም አራጌን፣ ውብሸት ደሳለኝን፣ ናትህናኤል መኰንንን፣ ምትኩ ዳምጠን፣ የሺዋስ ይሁናለምን፣ ኪንፈሚካኤል ደበበን፣ ኦልባና ሌሊሳን፣ የእስልምና ጉዳይ ተከታታዮችን ወያኔ ሲያስር ለጊዜው ተናደን ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተን ነበር፣ ግን እንደአሁን አላመረርንም። ገንዘብ ልመና የመጡትንም ባለሥልጣኖቻችሁን አሳፍረን መልሰናቸው ነበር፣ ግን አልቀጠልነበትም። አንዳንድ ሆዳሞችን በየማሕበረሰባችን እያስሰረጋችሁ አስገብታችሁ፣ ቤተክርስቲያናችን ሳይቀር በሆዳደር ልማታዊ መንኰሳት ልትቀሙን ስትነሱ እሱን ለማስጣል፣ በተለይ ለንደን ውስጥ ጌቶችዎ የሚሠሩትን ወንጀል ከማጋለጥ ትንሽ ረገብ ብለን ነበር። ወንድማችንን አንዳርጋቸውን ከየመን ያንን ሁሉ ገንዘብ አፍስሳችሁ ስትጠልፉት፣ የተዳፈነውን እሳት ቆስቁሳችሁ አነደዳችሁት። ያውላችሁ ትግሉ ተቀጣጥሎላችኋል። አሁን ሆይ-ሆይ ተበሎ ይብርዳል ብላችሁ እየጠበቃችሁ ነው። እንደ ቋያ እሳት እይተንቀለቀል፣ ነበልባሉ እየጦፈ ነው። እነዚህ “ጥቂት” የሚሉአቸው ሰዎች ናቸው ሎንዶን ላይ 5th September 2014 ከአውሮፓ ሁሉ ተሰብሰበው መንገዱን ያጨናነቁት። ከሁለት ወር በኋላ፣ 7th November 2014 እነዚህ ጥቂት ናቸው፣ የብራሰልሱን Schuman Square ቀውጢ ያደረጉአት! የድሮ መሥርያ ቤትዎ ባልደረቦች፣ ወያኔ እምባሲ ውስጥ የሚሠሩት ሠራተኞች አለንገሩዎትም እንዴ ምን እንደሆነ። ሆ ብሎ ያ ሁለ ሰልፈኛ ወደ ኤምባሲው ሲተም፣ ተደናግጠው፣ ባለአምባሻውን የወያኔ ባንዲራ ከተሰቀለበት አውርደው፣ እዚያ መሬት ላይ ጥለው ነብር ሩጠው ገብተው በራቸውን ዘግተው የተቀረቀሩት! “ድኃን አትናቁ፣ ድኃ እንዴት ይናቃል፣ ትኋን እንኳን በአቅሙ፣ አልጋ ያስለቅቃል!” ሲባል አልሰሙም እንዴ!
እሳቱ ገና አልቆመመ። በዚህ ብቻ መሽ አባርቶ! እነዚህ “ጥቂት” የሚሉአቸው ሰዎች ናቸው ባለሥልጣኖቻችሁን በአሜሪካና በአውሮፓ ከተሞች ሲያሯሩጡአቸው የነበሩት። ዋሽንግተን በየሁለቱ ሳምንት ሰኞ ሰኞ የእንግሊዝ ኤምባሲ ይሸበራል፣ በኢትዮጵያ ሰላማዊ ሰልፎች! በየሁለቱ ሳምንት፣ ዓርብ ዓርብ የለንድን የውጭ ጉዳይ መሥርያ ቤትን በሰላማዊ ሰልፍ ይናወጣል። “የጎዳና ነውጥ ነው የምትሉት? “ምንም ለውጥ” አያመጡም፣ ያሉት፣ እኛ በፈጠርነው ማዕበል እኮ ነው የዩኬ መንግስት £2 ሚሊዮን ፓወንድ የወያኔ ባለሥልጣኖች የሚሰለጥኑበትን ገንዘብ የያዘባችሁ። £20 ሚሊዮን ፓወንድ የደኅንነቶች ስልጠና ፕሮግራማችሁን የተሰረዘው እኮ በድምጻችን ነው! የኛ እኮ ግፊት ነው፣ ትላልቅ ጋዜጦች፣ እንደ Independent, The Guardian, and The Daily Mail የመሳሰሉት ጋዜጦች መንግሥታቸውን በጥያቄ እንዲያጣድፉ የተገደዱት! በኛና፣ እነዚያ ምንም ለውጥ አያመጡም ያሉአቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ተሟጋቾች፣ እንደ Amnesty International, Human Rights Watch, the Frontline, Pen International, Reprieve, Redress መሆኑን የሚረዳ ጭንቅላት አለዎት? አስተዳዳሪ ጌቶችዎ ካዝና ውስጥ ያለውን የብር ምንዛሪ ደርቆባቸዋል። ለእርስዎና ውጪ ለበተናቸው የደኅንነት ወፈሰማይ የሚከፍለው ደሞዝ አይነሮውም። ያንን መርዶ የዓለም ባንክ ሰሞኑን ነግሮናል። ከዚህ በፊት እንደመከርኩዎት፣ ከስዎ በፊት እንደነበረው አምባሳደር እርስዎም አገር ፈልገው ቢኮበልሉ ከአሁኑ ይሻልዎታል። ዕድሜዎ እየገፋ ነው። እየጨለመብዎት ነው። አሁንም ጨለማው ከበደ። ካረጁ አይበጁ!