ከዚህ ቀደም በነበሩት 5 ክፍሎች የእስራኤልን ታሪክ በአጭር በመቃኘት ስለአንድ ማዕከላዊ ድርጅትና ስለተቋማት አስፈላጊነት፣ ትግሉን ዓለምአቀፋዊ ስለማድረግ፣ ስለዳያስፖራው ወሳኝ ሚና፣ የጋራ ቋንቋ ለአንድ አገር ያለውን ጥቅም በሚመለከትና በአገር ጉዳይ የሀይማኖት መሪዎችና አገልጋዮች ሊኖራቸው ስለሚገባው የመሪነትና የማስተባበር ሚና ተገልጿል። ቀጣዩ ክፍል 6 ስለማስረጃና ስለማስረጃ ተቋም አስፈላጊነት ያብራራል።
- ሁሉንም መዝግቦ መያዝ (Documentation & Archaiving)
በእስራኤላውያን የትግል ጊዜም ሆነ እስራኤልን ከመሠረቱበት እ.ኤ.አ 1948 በኋላ ሕዝብን ለማሳወቅ፣ ወንጀለኞችን ወደፍትሕ ለማቅረብ፣ ችግሩ እንዳይደገም ዓለምን ለማስጠንቀቅና ለማስገንዘብ በከፍተኛ ደረጃ የጠቀሙት በራሳቸው በእስራኤላውያን እና እስራኤላዊ ባልሆኑ ሌሎች ሰዎች በጊዜው ይደርስ ስለነበረው ግፍና ሰቆቃ በጽሑፍ፣ በፎቶግራፍ፣ በቪዲዮና በድምፅ ተመዝግበውና ተቀርጸው የተያዙ ማስረጃዎች ናቸው።
ይልቁንም እስራኤላውያን ለዚህ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ካቋቋሙ በኋላ ይህ ተቋም በሕፃናት ከተሣሉ ሥዕሎች ጀምሮ ከ25 ሺህ በላይ የተለያዩ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ በማጥናትና ለማስረጃ፣ ለምርምርና ለሙዚየም እንዲመቹ አድርጎ በማዘጋጀት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በጀርመኖች የማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የነበረችው አነ ፍራንክ (Anne Frank) የተባለች ትንሽ ልጅ ከመሞቷ በፊት በየቀኑ ስትመዘግበው የነበረው የግሏ ገጠመኝ (Diary) እና ሌሎችም ተመሳሳይ ስብስቦች ከነዚህ መካከል ተጠቃሽ ናሙናዎች ናቸው። እነዚህ ማስረጃዎች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ለ6 ሚሊዮን አይሁድ ሕይወት መጥፋት ተጠያቂ የሆኑት የናዚ ወንጀለኞች ወደፍርድ ቤት ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ በእጅጉ ጠቅመዋል። ለመማሪያ፣ ለምርምርና በሕዝብ እንዲጎበኙ በሚዚየም ተቀምጠው እስከዛሬም በጥቅም ላይ እየዋሉ ነው። እነዚህ ተቋማትና ድርጅቶች በእስራኤል ብቻ የተወሰኑም አይደሉም። በመላው ዓለም በተለያዩ ከተሞች ይህን የሚሠሩ በርካታ የአይሁድ ተቋማት፣ ላይበራሪዎች፣ ሙዚየሞች፣ የማስረጃ ክምችት (Archivals) እና የምርምር ተቋማት ዛሬም ይገኛሉ። በአሜሪካን አገር ብቻ United States Haloucast Memorial Museum በሚል በሚታወቀው ተቋም ሥር ይህን ሥራ የሚሠሩ አያሌ ድርጅቶች በበርካታ የአሜሪካ ከተሞች ውስጥ ይገኛሉ።
እነዚህን ማስረጃዎች በመንተራስ የተዘጋጁ መጻሕፍት፣ ፊልሞች፣ ትያትሮችና ትእይንቶች (Exhibitions) ቁጥራቸው አያሌ ነው። ይህ በእስራኤላውያን የደረሰውን ዓለም እንዲገነዘበው፣ እንዲማርበትና ይህን መሰል ነገር በድጋሚ በማንም እንዳይደርስ ካለው አስተዋጽኦ በላይ ለእስራኤላውያን ጥንክሮ መሥራት፣ ብልጽግና፣ አይበገሬነትና የመንፈስ ኩራት አጎናጽፏል። ከወደቁበት መነሳትና አገራቸውን መልሰው ማቋቋም ብቻ ሳይሆን እንደ እንስሳት እያዩ የገደሏቸውን ጀርመኖች ይቅርታ ለማስጠየቅና እስራኤላውያን በዓለም ፊት አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱና እንዲከበሩ እነዚህ ማስረጃዎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም።
ከዚህ ምን እንማራለን? በመጀመሪያ ማስረጃና መረጃን የሚያሰባስብ፣ የማያቋርጥ የመረጃ ዳሰሳ የሚያደርግ፣ ለሥራ እንዲመች አድርጎ የሚያከማች/የሚያደራጅ፣ ሳይበላሹ ተጠብቀው እንዲቆዩ የሚንከባከብ፣ የሚቆጣጠር፣ ማስረጃዎቹ ለሌሎች የሚደርሱበትን የሚያመቻች፣ የሚያጠናና የሚተነትን ጠንካራ ተቋም ያስፈልገናል። ይህ ተቋም ከአገዛዙ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በጠቅላላ እና በግእዝ በአማርኛና በሌሎችም የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና የተለያዩ የዓለም ቋንቋዎች ስለኢትዮጵያ የተጻፉትን ማንኛውም መጻሕፍት፣ የተዘጋጁትን የፎቶግራፍ፣ የድምፅና የቪዲዮ ሥራዎች ከአገር ውስጥም ከውጭም በስጦታ፣ በግዢ እና ኮፒ በማድረግ የሚሰበስብ መሆን ይኖርበታል። በፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ጥረት በማይክሮፊልም የተሰባሰቡት ሥራዎች ቋሚ ምስክር ናቸው። በአርቲስት ታማኝ በየነ አስተባባሪነት ይህ ተቋም በቅርቡ መቋቋሙ ደግሞ የቡድኑን አርቆ አስተዋይነት የሚያመለክትና እጅግ የሚያስደስት ነው። በሰው ኃይል፣ በእውቀት፣ በአደረጃጀትና በገንዘብ አቅም እንዲጠነክርና ሥራውን በብቃት እዲወጣ የመላው ኢትዮጵያዊ ድጋፍ ያስፈልገዋል። ይህ ተቋም ትንሽ ቀደም ብሎ ቢሆን ኖሮ በቅርቡ በአዲስ አበባ በኪሎ እየተሸጡ በነበሩት ታሪካዊ መዛግብት ላይ ሊደርስባቸው ይችል እንደነበረ መገመት ይቻላል። አሁንም በየሰው እጅ ያሉትን በስጦታና በግዢ ለመሰብሰብ ጥረት ቢያደርግ ለአገርና ለወገን ባለውለታ ይሆናል።
መረጃዎች ዕለት በዕለት እየሰበሰቡ ለዚህ ተቋም ማስተላለፍ ደግሞ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ኃላፊነት ነው። ይህ ሁለተኛው አስፈላጊ ተግባር ነው። ማንም ነፃነት ወዳድ ኢትዮጵያዊ በእጁ የገባውን መረጃና ማስረጃ ከቻለ ዋናውን ካልቻለ ኮፒ አድርጎ፣ ያጋጠመውን በጽሑፍ፣ በፎቶና በቪዲዮ መዝግቦ የማስቀረት ኃላፊነት አለበት። ሕፃናት ሳይቀር በገጠርና በከተማ በዚህ አገዛዝ ሲፈጸሙ ያዩትንና ስለአገዛዙና ስለኑሮአቸው የሚሰማቸውንና በቤተሰባቸው የደረሰውን በሥዕልና በጽሑፍ እንዲገልጹት መምህራንና ወላጆች ማበረታታት ብሎም ማስረጃውን በጥንቃቄ ቀን መዝግበው ማስቀመጥና በጊዜው ለተቋሙ ማስተላለፍ ይኖርባቸዋል።
ዛሬ በየሰው እጅ ያለው ተንቀሳቃሽ ስልክ ካሜራ አለው። ይህን ካሜራ በመጠቀም ብዙ መረጃዎች ወጥተዋል፤ አሁንም እየወጡ ነው። ነገር ግን ከዚህም በበለጠ እያንዳንዱ ዜጋ ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ በካሜራው ቀርጾ የማስቀረት ኃላፊነት ሲወስድ ከፍተኛ ሥራ ይሠራል። መሻሻል የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር የምስሎቹን ጥራት በሚመለከት ነው። ለዚህ መፍትሔው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትኩረት ሰጥተው የካሜራ ባለሙያዎችን ከመቅጠር ጀምሮ ለአንዳንድ የድርጅት አባላቶቻቸው በቂ የፎቶግራፍና የቪዲዮ ቀረጻ ስልጠና በመስጠትና ከካሜራ ጋራ በማሰማራት ከፍተኛ ሥራ ሊሠሩ ይችላሉ። አባላቶቻቸው አደጋ ላይ እንዳይወድቁ ሚስጥራዊ ጥቃቅን ካሜራዎችን እንዲጠቀሙ ማድረግ ይቻላል። እዚህ ላይ ጠንካራ የሆኑት በውጭ የሚገኙ የኢራን አክቲቪስቶች በኢራን 2009 (እ. ኤ. አ) ምርጫ የተነሣ መንግስታቸው የወሰደውን ጭካኔ የተሞላበት ርምጃ ለማጋለጥ የተጠቀሙበትን ዘዴ መጥቀስ ይጠቅማል። በዳያስፖራ የሚገኙት አክቲቪስቶች ከምርጫው በፊት በርካታ ሚስጥራዊ ካሜራዎችን ገዝተው ወደአገር ውስጥ ማስገባት ችለው ስለነበረ ከምርጫው በኋላ በምርጫው ውጤት ያፈረው የኢራን መንግሥት የወሰደው ርምጃ በዓለም የቴለቪዥን መስኮት ሊናኝና ከፍተኛ ውግዘት ሊያደርስበት በቅቷል። በገንዘብ የተሻለ አቅም ያለውና ለቴክኖሎጂ ቅርብ የሆነው ኢትዮጵያዊው ዳያስፖራ በዚህ በኩል ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርበታል።
(ይቀጥላል)
ኢትዮጵያ በቆራጥ ልጆቿ ሥራ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኖራለች!